Saturday, 29 May 2021 14:44

የአልጋ ላይ ፖለቲካ

Written by  አሳዬ ደርቤ
Rate this item
(2 votes)

    የውሃ ሙሌት ማከናወን አስቤ ወደ መኝታ ቤት ሳመራ እሜቴ በጀርባዋ ተኝታለች፡፡ ተገቢውን የመስመር ዝርጋታ ካከናወንኩ በኋላም ተርባይኔን ግድቧ ውስጥ አስገብቼ መሾር ሳስብ ‹‹አትንካኝ›› በማለት ተቆጣች፡፡ ቁጣዋን በመስማት ፈንታም እጄን ሰድጄ በግድቡ ዙሪያ ያለውን ቁጥቋጦ እየነጨሁ የምንጣሮ ሥራ ማከናወን ስጀምር ‹‹ውሳኔዬን ነግሬኻለሁ እኮ›› በማለት ተናገረች፡፡
‹‹ምን ብለሽ ነው የነገርሽኝ?››
‹‹ሠራተኛ በሚል ሥም ያስገባኻትን ቅምጥ ከዚህ ቤት ካላስወጣህ በቀር ልትሞላኝ አትችልም››
‹‹አስወጣታለሁ ብየሻለሁ እኮ፡፡ ምንድን ነው ስምንት ወር ሙሉ መጨቃጨቅ››
‹‹የምጨቃጨቀውማ አስወጣታለሁ እያልክ እግሬ ወጣ ሲል ስለምታወጣት ነው››
ያን ጊዜም ‹‹እረ በስማም በይ›› እያልኩ በምተሃተኛ መዳፌ ላሟሟት ስሞክር ‹‹ዞር በልልኝ ብየኻለሁ›› በማለት የወሲብ ማእቀቡን አጠናከረችው፡፡
በዚህም ንግግሯ ደንፉ እየበላሁ ‹‹ለአንቺና ለእሷ ቀርቶ ለተፋሰሱ አገራት የሚበቃ በቂ የውሃ ክምችት በውስጤ ስላለ ወሬውን ትተሽ ጠጋ በይና ልሙላሽ›› በማለት ከሃማስ ሮኬት ተርታ የሚሰለፍ የተፈጥሮ ሃብቴን ላስገባ ስል፣ እንደ እስራኤል አይረን ዶምስ ከአየር ላይ ቀልባ ከፍተኛ የሆነ የመሠረተ ልማት ውድመት ትፈጽም ጀመር፡፡
ያን ጊዜም ‹‹ፊትሽን አጣፍሬ እንደ አሜሪካ ባንዲራ ሳላቃጥልሽ በፊት ሉኣላዊነቴን በሚጋፋ መልኩ ከጭኔ መሃከል ገብቶ የሚፈተፍት እጅሽን ባፋጣኝ ታነሽ ዘንድ ትጠያቂለሽ›› በማለት አስጠነቀቅኳት፡፡
ሴትዮዋ ግን ማስጠንቀቂያዬን በመቀበል ፈንታ ከበፊቱ በላቀ መልኩ ተርባይኔን እንደ በሶ እየጨበጠች ‹‹እጄን ባላነሳስ?›› ብላ ስትጠይቀኝ ‹‹አቃጥልሻለሁ›› ማለቴን ትቼ ‹‹አወግዝሻለሁ›› በሚል መልስ ላስለቅቃት ሳስብ ‹‹ከቤቴ ያስገባኻትን ወራሪ አሁኑኑ ተጣርተህ እንድትወጣ ካልነገርካት በቀር አልለቅህም›› የሚል ትዕዛዝ አስተላለፈች፡፡
በዚህም መሠረት ሳሎን የተኛችውን ልጅ ‹‹ፊያሜታ›› ብዬ ከተጣራሁ በኋላ ‹‹ውጭልኝ›› ማለቱን ትቼ ‹‹አድኚኝ›› በማለት ጮህኩ፡፡
ፊያሜታም በብርሐን ፍጥነት ተንደርድራ በመምጣት ሕይወቴን ካተረፈችልኝ በኋላ… ተጨብጦ የቆየ ሰውነቴ ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን አጎንብሼ ስመለከት...ሰከላ አካባቢ የሚገኘው የዘር ማመንጫ ፍሬዬ በጣም ከመጎዳቱ የተነሳ የግንቦት ሃያ ፍሬ መምሰሉን ተረዳሁ፡፡
በዚህም ምክንያት ይህቺን አደገኛ ጁንታ በአሸባሪነት ፈርጄ፣ ከአልጋዋና ከመኝታ ቤቷ አሽቀንጥሬ ስጥላት፣ እሪታዋንና ለቅሶዋን የሰማ ዲታ ጎረቤታችን ከጠባቂዎቹ ጋር ሮጦ መጣ፡፡ ከዚያም የእኔን ጉዳት ችላ ብሎ በእሷ ላይ የተፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲያዳምጥ ከቆየ በኋላ ‹‹እናንተ ሰዎች›› እያለ የመኝታ ቤታችንን በር ሲያንኳኳ ‹‹ሰዎች ሳንሆን ሰው ነን›› አልኩት፡፡
በዚህን ጊዜም ባለሃብቱ ‹‹ምንም ሁን አያገባኝም፡፡ ሆኖም ግን መኝታ ቤትህ ውስጥ ያስገባኻትን ሴት ማባረርና ከሚስትህ ጋር መደራደር እስካልቻልክ ድረስ ከዚህ ቤት መውጣት አትችልም››… በማለት የቪዛ እገዳ ማድረጉን ሲናገር፣ ፊያሜታ ገላ ላይ ተደፍቼ እየሾርኩ እንዲህ የሚል መልስ ሰጠሁ፡፡
‹‹በውስጣዊ ጉዳያችን ገብተህ የምርጫ ሂደቱንና የውሃ ሙሌቱን ባታደናቅፍ ጥሩ ነው››

Read 2308 times