Saturday, 29 May 2021 14:39

ከምዕራባውያን ጋር የተፈጠረውን ቅራኔ እንዴት እንፍታው?

Written by  ሙሼ ሰሙ
Rate this item
(0 votes)

     ዛሬ ለገባንበት ቅርቃር እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ሕዝብ ከኛ ከራሳችን በላይ ኋላፊነት መውሰድ የሚገባውና ተጠያቂ የለም ባይ ነኝ። የጀግንነቱና የትልቅነቱ ትርክት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ተወደደም ተጠላ ፈተና ውስጥ የገባነው ዛሬ ድሃ ሆነን በመገኘታችን ብቻ ሳይሆን ለዝንተ ዓለም ከድሕነትና ከተመጽዋችነት መላቀቅ ባለመቻላችን ጭምር ነው።
ዛሬ ላይ “ሉአላዊነታችን ከተደፈረ”፣ ለሉአላዊነታችን መደፈር መንስኤ የሆነው ድሕነታችንንና ተመጽዋጭነታችንን፣ በእኛ በእራሳችን ድክመት የተንሰራፋ መሆኑን ማመን ባለመፈለጋችን ነው። በተለይ ደግሞ ለዘመናት የተሻለ ነገን ሊያሳዩን ሃላፊነት የሰጠናቸው፣ ሃላፊነት የወሰዱና በየደረጃው የሚገኙ መሪዎቻችን፣ ሃላፊነታቸውንና ግዴታቸውን በአግባቡ ከመወጣት ይልቅ እራሳቸውን ለማበልጸግ በዘረፋ፣ በሙስና፣ በብክነት፣ በአልጠግብ ባይነትና በከፋፋይነት ተግባር በመዘፈቃቸውና አንደ ሕዝብ ፈተናውን በጋራ እንዳንጋፈጠው ችግሮቻችንን ውጫዊ (External) ማስመሰል በመቻላቸው ነው።
ዛሬስ፣ ዛሬ ላይ ከቀደሙት ስህተታችን በመማር ራስን ወደ መቻል የሚወስደውን መንገድ በጥንቃቄና በሰከነ መንፈስ ከማቀድ፣ በቅደም ተከተል ከመመርመር፣ አቅጣጫ ከመተለምና ዘላቂ መፍትሔ ከመሻት ይልቅ ጭራሽ አበዳሪዎቻችንን፣ መጽዋቾቻችንና ቀላቢዎቻችንን” ይቀኑብናል፣ አይወዱንም፣ ስኬታማ ስለምንሆን ይሰጋሉ የሚሉ ግራ አጋቢ ክሶችን መደርደር “የላቀውና አሸናፊው” መርህና መፈክር እየሆነ ነው።
ከዚህ በላይ ፈተናችንን የሚያከረው ጉዳይ ደግሞ ከምዕራባውያን ጋር ለመደራደር ከምንሰጠው ጊዜ በላይ “ማቅ ለብሰን” “አፈር ተንተርሰን” በድህነት እንኖራለን ለሚለው ትርክት የምንሰጠው ጊዜ መጎለበቱ ነው። በዚህ መንገድ ስንዳክር ብንውል፣ አንድም ስንዝር የምንወጣው “ከፍታ” ካለመኖሩም በላይ፣ በዚህ ትርክታችን ለዘመናት ከማቀቅንበት የረሀብ፣ የሞት፣ የስደትና የድህነት አረንቋ ተመልሰን ከመደፈቅ ውጭ ሌላ አዲስ መፍትሔ እንደማይወልድልን አለመገመታችን ከንቱ “ብልጠት” እንጂ “ብልህነት” ሊሆን አይችልም።
በተለይ በገሀድ ከሚታወቅው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚቃረኑ የግለሰቦች “ስንኩልናዎች” ወደ ሰፊው መንግስትና ተቋማት ሲዛመቱ ማየቱ፣ መዘዙ ከግለሰብና ከቡድን ኪሳራ በላይ እጅግ የከፋ ሊያደርጉት እንደሚችሉ መገመት ይቻላል። ውጤቱም ሀገርን ሊያፈርስ፣ ሕዝብን ሊበትን፣ ግጭት ሊቀሰቅስና ውድመት ሊያስከትል እንደሚችል ማስገንዘብም ቀባሪውን ማርዳት ይመስለኛል።
ምን ይሻላል በከፊል:-
በመጀመርያ ከምዕራባውያን ጋር የነበረን የዘመናት መልካም ግንኙነት በዚህ ፍጥነት እንዴት ሊሻክርና ሊናድ ቻለ የሚለውን መመርመር ያሻል? ቀጥለን ከምዕራባውያን ጋር ድርድር ውስጥ ብንገባ ምን እናጣለን፣ ምንስ እናገኛለን? ምዕራባውያን ከሀገራችንና ከመሪዎቻችን ምን እየፈለጉ ነው? ከጥያቄዎቻቸው ውስጥ በሞትና በሽረት እንዲሟላ የሚፈልጉትስ የቱን ነው? የማይነኩ የምንላቸው የጋራ መርሆዎቻችን የትኞቹ ናቸው? ለእነዚህ መርሆዎችስ እስከ ምን ድረስ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን? በድርድሩ ሂደት ማረም የምንችላቸው ክሶችና ወንጀሎች የትኞቹ ናቸው? እነዚህን ለማረም የቤት ስራችንን እየሰራን ተጨማሪ ጊዜ እንዴት እንግዛ? ማዕቀቡ ከተንሰራፋ የሚፈታተኑን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተጽእኖዎችንና ቀውሶችን ለመቋቋም ምን ዓይነት ቅድመ ዝግጅትና ተከታታይ ስራ መስራት አለብን ወዘተ .. በሚሉ ፈተናዎችና ጥያቄዎች ዙርያ መድረክ በመክፈት፣ ለመደራደር ዝግጁና መልስ ያለን መሆን አለብን፡፡


Read 2286 times