Saturday, 29 May 2021 14:37

ታሪክን የሁዋሊት

Written by  በእውቀቱ ስዩም
Rate this item
(0 votes)

     በአገሮች መካከል የሚፈጠረውን ግንኙነት የሚወስኑት ሶሰት ነገሮች ናቸው፤ ያገሮች አቅም፥ የጊዜው ሁኔታና የመሪዎች ችሎታ፡፡ ከአድዋ ድል በሁዋላ ኢትዮጵያ የረባ ንብረት ሳታፈራ፤ ዳማ ፈረሷን በታንክ ሳትቀይር ተዘናግታ ቆየች፤ ጣልያን በሞሶሎኒ መሪነት ሁለተኛውን ወረራ ፈጸመች፡፡ ያገራችን እናትና አባት አርበኞች በሚያስደንቅ ወኔ ተከላከሉ፤ ግን በጦርነቱ መሸነፍ አልቀረላቸውም። ቀዳማዊ ሃይለስላሴም ነገሩ እንዳልሰላ ሲያውቁ ሰራዊታችውን በትነው፥ ዘመድ ወዳጅ ሰብስበው ወደ አውሮፓ ተሰደዱ፤ የመንግስታት ማህበር ለሚባለው፥ የጉልቤ አገሮችን ጥቅም ለማስጠበቅ የተመሰረተው ድርጅት ፊት አቤቱታ አቀረቡ፤ ሃያላን አገሮች ሀይለኛዋን ጣልያንን ከማስቀየም ቺስታዋ ኢትዮጵያ “እንደ ፍጥርጥሯ” ትሁን ብለው ፊታቸውን አዞሩባት፤ ግርማዊነታቸው በኢንግላንድ ብርድ እየማቀቁ፥ የአዱገነትን ጣይ እየናፈቁ፤ ያባቶቻቸውን አምላክ ተአምር እየተጠበቁ በስደት ተቀመጡ፡፡
ይህ በእንዲህ እያለ አርበኞች በየፊናቸው አገራችንን ከጣልያን ያገዛዝ ቀንበር ለማውጣት ተፍጨረጨሩ፤ ምንም ጀግንነታቸው ባይጠረጠር የቄሳርን መንግስት ማስወገድ የሚሳካላቸው አልሆነም፤ ኢትዮጵያ ለቀጣይ መቶ አመታት የጣልያን ርስት ሆና አንደምትቆይ ተተነበየ፡፡
በአራት አመታት ጊዜ ውስጥ ግን ድንገት ነገሮች ተለወጡ!
ጀርመን የሁለተኛው አለም ጦርነትን አውሮፓ ላይ መርቃ ከፈተችው፤(1939) ምድረ አውሮፓ በሁለት ምድብ ተከፍሎ መፈሳፈስ ጀመረ፤ ጣልያን ሲያቀብጣት ከጀርመን ጋር ተሰለፈች፤ አለቀላት የተባለቺው ኢትዮጵያ ፈጣን ሎተሪ ወጣላት፤ በተቃራኒው ምድብ ላይ የቆመቺው ታላቂቱ ብሪታኒያ በምስራቅ አፍሪካ በቅኝ የምትገዛችው አገሮች (ግብጽ፤ ሱዳን፤ ከፊል ሱማሊያ) በሞሶሎኒ መዳፍ ከመውደቃቸው በፊት ወደ ኢትዮጵያ ለመዝመት ወሰነች፡፡ ዊንስተን ቸርቺል ግርማዊነታቸውን ከአንግሊዝና ከሱዳን ሰራዊት ጋር አሰልፎ አዘመታቸው፤ ጣልያን ፒያሳን በገነባበት አጁ ሃያ ሁለት ማዞርያን ሳይገነባ(ልን) በእንግሊዝና ጦቢያ አርበኞች ጥምረት በካልቾ ተመቶ ተባረረ፡፡
እንግሊዞች ለከፈልነው መስዋእትነት ዋጋ እንፈልጋለን አሉ፤ ኢትዮጵያውያንም ከኪሳቸው አውጥተው ነጻነታቸውን ከፈሉ ፤ እነ ቸርቺል ቀዳማዊ ሃይለስሳሴን ዙፋን ላይ አስቀምጠው አገሪቱን ተቆጣጠሩ፤ ጦሩ፤ ፖሊሱ፤ ስልኩ ፖስታው ባቡሩ በእንግሊዞች መዳፍ ገባ፡፡ ግርማዊነታቸውም” ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ” እያሉ አንጎራጎሩ፤ ግን ጮሌ ናቸውና ቀንበሩን የሚሰበሩበትን መንገድ ማብሰልሰል ጀመሩ፤ በጉዋሮ በር፤ የእንግሊዞችን የመረጃ ከበባ ጥሰው አጋዥ ፍለጋ ወጡ፤ ለአጋዥነት ወይም ለጭንቅ ደራሺነት የተመረጠቺው ደግሞ አመሪካ ነበረች፤ የኦክስፎርድ ምሩቁ ልጅ ይልማ ደሬሳ የዋየታውስ ባለስልጣኖችን ይጀነጅን ዘንድ ወደ ዋሸንግተን ተላከ፤ ጅንጀናው ሰመረ፤ አሜሪካኖቹ፤ ጣልያን ጣጥሎት የሄደውን ትራክተር ወርሰው፤ ኢትዮጵያ የምትሰጣቸውን መሬት አርሰው በጦርነት ላይ ላሉ ወታደሮቻቸው ለስንቅ የሚሆን ቢያመርቱ እንደሚያዋጣቸው አሰሉ፤ በምትኩ፤ የአንግሊዝን ቀንበር ለማላላት አገዙ፤ ለኢትዮጵያ መገበያያ ብር አተሙ፤ ገንዘብ፤ ጠመንጃ ወዘተ መለገስ ጀመሩ፤ እንዲህ እንዲህ እያለ፤” እሬትና - ማር” የሆነው የሁለቱ አገሮች የትስስር መሰረት ተጣለ፡፡



Read 2199 times