Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 September 2012 10:48

የኳስ ህጎች’ና እኛ…

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!

እንግዲህ ኳሱ ተጀመረም አይደል … ጥያቄ አለን ‘ተጀመርልን’ ነው የሚባለው ወይስ

‘ተጀመረብን’? ግራ የሚያጋባ ነገር ሆኖብናላ! ገና ከአሁኑ ወሬው ‘ፕሬሚየር ሊግ’ እየሆነ ነው፡፡ ሌላም ጥያቄ አለን … አሁን ወደ ማንቼ ሄደ ምናምን የሚሉት ቫን ፐርሲ … አለ አይደል … ለግራዚያኒ ወታደሮች ያጨበጭቡለት የነበሩ፤ በየሚኒ ባሱ ፎቶውን ይደረድሩለት የነበሩ ሁሉ እንደ ከሀዲ ሲያበጠለጥሉት እየሰማን ነዋ! (እኛም አገር በተለይ ትልቅ የሚባሉ ክለቦች አካባቢ በ‘ሌላ ማልያ’ የሚመጡ ተጨዋቾች እንዲህ አይነት የ‘እንቁላል ሻጭነት’ እርግማን ምናምን ይደርስባቸዋል የሚባለው እውነት ነው እንዴ!)

እናላችሁ … ሰው ይሻለኛል ብሎ ወደመረጠው አካባቢ ስለሄደ ምናምን ብቻ ይሄን አይነት እንደ ከሀዲ የመቁጠር አስተሳሰብ በብዙ ነገሮች ላይ ስላለ የኳስ ህጎች በሌሎች ነገሮች ላይ ይተግበሩልን፡፡ (ከኳስ ጋር የተያያዘ ነገር ብዙ አድማጭና ‘የአየር ሰዓት’ ያገኛል ብዬ ነው…) እናላችሁ … በነበረበት ቦታ መአት አገልግሎት ሰጥቶ ‘ወደ ሌላ ካምፕ’ የሄደን ሰው … በከሃዲነት ለምናብጠለጥል … አለ አይደል … ‘የሎው ካርድ’ ምናምን የሚያሰጥ ደንብ ነገር ይውጣልንማ!

ይቺን ጨዋታ ስሙኝማ … እንትናዬዋ የሆነ ምንችክ ያለ የእኔ ቢጤ እየጨቀጨቃት ለዓይኗ እንኳን ለማየት ደብሯታል፡፡ ታዲያላችሁ … አንድ ቀን እሱዬው ሆዬ … “ቅዳሜ ተገናኝተን ብንጫወት ምን ይመስልሻል?” ምናምን ነገር ይላታል፡፡ እሷዬዋም “አይመቸኝም …” ነገር ትለዋለች፡፡ “ለምን አይመችሽም?” ብሎ ሲጠይቃት ምን ብላ መለሰችለት መሰላችሁ … “ቅዳሜ ራስ ምታት ያመኛል፣” አሪፍ አይደል! (በእርግጠኝነት፣ ወንድሟም ይሁን አጎት ባይኖራትም ‘የአጎቷ ልጅ’ ከሆነ ሰው ጋር ቢያዩዋት እንቁላል ሻጭ እንደሚያደርጋት አትጠራጠሩ፡፡ አንዳንድ እንትናዎች በተዘዋዋሪ የሚሰጣችሁ ‘ሬድ ካርድ’ ይግባችሁ እንጂ! ለ‘ሬድ ካርድ’ ሁለተኛው ‘የሎው ካርድ’ የቀራችሁ ደግሞ ከቋንጣ ፍርፍር ሻል ወዳለው ነገር ከፍ በሉማ!”) እናላችሁ በብዙ ነገሮች ላይ … አለ አይደል … “ቅዳሜ ራስ ምታት ያመኛል፣” እየተባልን ‘ሬድ ካርድ’ ብልጭ የሚደረግብን ሰዎች አለን፡፡

ስሙኝማ … እንግዲህ ጨዋታም አይደል … አንዳንድ ጊዜ እንዲሁ “ጥመም” “ጥመሚ” የሚያሰኘን ጊዜ አለላችሁ፡፡ አንድ ሰውዬ ጓደኛውን “ውጪ እየዘነበ ነው እንዴ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ጓደኝየው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው … “ታዲያ ቤት ውስጥ ሲዘንብ አይተህ ታውቃለህ?” ይኸውላችሁ … ‘ደግ አያናግርህ’ ሲል እንዲህ ነው ‘እያንጋደደ’ የሚወስደው፡፡ ይሄን ጊዜ “ኦፍ ሳይድ” ብሎ በፊሽካም ይሁን ያለ ፊሽካ የሚያስቆመን ያስፈልገናል፡፡

እኔ የምለው … ኳስ ላይ ፔናሊቲ ክልል ውስጥ ሳይነኩ “ዳይቭ” እየገቡ ዳኛ ለመሸወድ የሚሞክሩ ተጫዋቾች ልብ ብላችሁልኛል! … በሌላም ህይወት እንደዛ አይነት ‘የመሸወድ’ መአት ነገር አለላችሁ፡፡ አንዳንዶቻችን በጣም እየለመደችብን የሄደች ነገር አለች … ለምሳሌ ለምን ዕቁብ አንጥልም ነገር እንልና “እኔ እኮ እንደው እግረ መንገዳችንን በሰበቡ እንድንገናኝ ብዬ ነው እንጂ…” ምናምን ነገር እንላለን፡፡ ከዚያ ልክ ዕቁቡ ሲጀመር “የመጀመሪያ ዕጣ ለእኔ ካልተሰጠኝ…” በሚል “አለበለዛ ዕቁቡ ይፍረስ” አይነት ግርግር እንፈጥራለን፡፡

ስሙኝማ … ከዚህ በፊት የጠቀስናት የመጽሐፍ አካባቢ ጨዋታ አለች አይደል … አሳታሚ ስናፈላልግ “እኔ’ኮ ሥራዬ ታትሞ ሰው እጅ ይግባልኝ ብዬ ነው እንጂ ገንዘቡ ለምን አሥር ዓመት አይቀርም …” ምናምን ብለን መጽሐፋችን ወጥቶ ገና አሥር ፓኬት እንኳን ‘ሳይቸበቸብ’ በወጣ በአምስተኛ ቀኑ “ለምንድነው ድርሻዬን የማትሰጠኝ!” አይነት ንትርክ ውስጥ እንገባለን፡፡ እናማ … እንዲህ አይነት ለለመደብን ከፕሬሚየር ሊግ ወደ ሦስተኛ ዲቪዚዮን በአንዴ የሚያወርድ ህግ ይካተትልንማ!፡፡

ስሙኝማ … እግረ መንገዴን የሆነች ነገር ትዝ አለችኝማ … ሰዎችን እኮ የምር “ስለ ሰው፣ ስለ ሰው…” ምናምን ነገር እያለ ይመስላል፡፡ በፊት ነገሬ ብላችሁልኝ እንደሁ መንገድ ላይ ሱሪ፣ ቀሚስ፣ ጃኬት ምናምን ዘርግተው ከሚሸጡት ልጆች ለመግዛት “የሚያውቀኝ ሰው ቢያየኝስ!” እየተባለ ስንት ታክቲክና ስትራቴጂ ተነድፎ ነው፡፡ መሸትሸት ሲል ወደ ምንሊክ አደባባይ አካባቢ ሸፈንፈን እያሉ መውጣት የታክቲኩ ዋና አካል ነበር፡፡

ልጄ ዘንድሮ ደግሞ በጠራራ ፀሐይ በግፊያ ሆኖላችኋል የምንገዛው፡፡ ሁልጊዜ “አሼሼ ገዳሜ” የለማ! ለነገሩ ብዙ ጊዜ ለተመሳሳዩ ዕቃ በሱቁና መንገድ ላይ በተዘረጋው መካከል እስከ መቶና ሁለት መቶ ብር ልዩነት ታገኛላችሁ፡፡ ታዲያላችሁ … “ዕድርተኛ አይቶኝ የቡና መጣጫ ቢያደርገኝስ…” የለ፣ “የመሥሪያ ቤት ሰዎች ከች ብለውብኝ የድራፍት ወሬ ብሆንስ!...” በቃ፣ የምር አሪፍ ነገር ነው፡፡ ያለቦታው የሚገባ “ሰው ምን ይለኛል?” ነው እስከዛሬ ሲጫወትብን የኖረው፡፡ አሁን ልጄ … ዘወር ብሎ ማየት የለ፣ መሳቀቅ የለ … በጠራራ ፀሐይ ግፊያ ጀምረናል፡፡ እናማ … እንዲህ ‘ግላጭ የመንገድ ግብይት’ ለለመድነው ‘የጨዋታው ኮከብ’ ምናምን የሚል ማበረታቻ ይደረግልንማ!

ስሙኝማ … መቼም ወግ አይደል፣ የ‘ኳሱ ምንቸት’ ከገባ አይቀር ስለዚህ አገር የተጨዋቾች የዝውውር ገበያ ስትሰሙ በቃ ግር ይላችኋል፡፡ ‘የዝውውር መስኮት’ የሚለው ተለውጦ ‘የዝውውር ሁለት ተካፋች በር’ ምናምን ይባልልን፡፡ የአውቶብስ እያጡ በእግር ይኳትኑ የነበሩ የጨሱ ተጫዋቾች በነበሩባት አገር፣ “እንዴት ለኳስ ተጫዋች ሁለት ሺህ ብር ይከፈላል!” ይባልባት በነበረች አገር … ለዝውውር እስከ ግማሽ ሚሊዮን ብር ወጣ ሲባል ስትሰሙ … አለ አይደል … “እንደው ‘ጉድ የአንኮበር ቅጠል’ ማለት አይተዋችሁ ብሎን ይቅር!” ያሰኛል፡፡ በጣም የሚገርማችሁ … አንድ ተጫዋች ሦስትና አራት መቶ ሺህ ብር መግዛት የሚችሉ ክለቦች ነፍስ ያለው የራሳቸው መለማመጃ ሜዳ እንኳን የላቸውም፡፡

እናማ … ይሄ አልጋ ሲሉት ምናምን ለሆነ ፉትቦላችን ለአንድ ተጫዋች ብዙ መቶ ሺህ የማውጣት ኮሜዲ ‘የሎው ካርድ’ ያስፈልገዋል፡፡ ለሁለትና ሦስት ተጫዋች ዝውውር ተከፈለ የሚባለው እኮ መለስተኛ የታዳጊዎች ማሰልጠኛ ማቋቋም ይችላል! እናማ ... ከቫን ፐርሲ ዝውውር ይልቅ የአገራችን የተጫዋቾች ሽያጭና ግዢ ነገር እያስገረመንም፣ ግራ እያጋባንም እንደሆነ ይመዝገብልን፡፡

እዚህም ላይ ሌላም ጥያቄ አለን … ከቡድኖች የተጫዋች ግዢና ሽያጭ ጀርባ የኤጎና የ‘ዝሆኖች ፉክክር’ አለ የሚባለውን ነገር አስረዱንማ፡፡

ስሙኝማ … እንግዲህ ጨዋታም አይደል … ይቺን ስሙኝማ … ባል ሆዬ ለሚስቱ “የእኔ አበባ ድንገት አንድ ነገር ብሆን ችግር እንዳይገጥምሽ የሕይወት ኢንሹራንስ ገብቻለሁ፡፡ ድንገር ብሰናበት ሃምሳ ሺህ ፓውንድ ታገኛለሽ…” ይላታል፡፡ ሚስትየዋ ምን አለች አሉ መሰላችሁ … “በቃ ከእንግዲህ ግልግል ነው፡፡ በታመምክ ቁጥር ዶክተር መጥራት” አያስፈልግም፣” ብላው አረፈችላችሁ፡፡ ለዚች አይነቷ የአንድና ሁለት ጨዋታ ‘ሬድ ካርድ’ ብቻ ሳይሆን ዕድሜ ልክ የኢንሹራንስ ቢሮ ባለበት ህንጻ በመቶ ሜትር ቀርባ እንዳታልፍ የሚያግድ ቅጣት መጣል ነው!

ስሙኝማ…ይቺን ነገር በየሳምንቱ ማንሳት ሳይኖርብን አይቀርም፡፡ ግራ የሚገባ ነገር እኮ ነው…ለእነኚህ መንገድ ላይ እግራችሁ ስር ለሚተፉ ሰዎች “ሬድ ካርድ” የሚሰጥልን ይጥፋ! አሁን አሁንማ “ሰው ላይ ሊያርፍ ይችላል…” የለ፣ ምን የለ…ልክ “ከፍተኛ ርቀት በማስመዝገብ በሚል “ጊነስ ቡክ ኦፍ ሬከርድስ” መግባት የፈለጉ ይመስል ከዳር ዳር ይወንጭፉላችኋል፡፡ እኔ የምለው…አንዳንዱ ሰው ምላሱ ላይ “ባላ ነገር” አለው እንዴ! እናም…የ“ሪሚቲቭነት” የመጨረሻው ጥግ ስለሆነ ለእንደዚህ አይነቶቹ “ሬድ ካርድ” እየሰጡ “ለአንድ ዓመት በማንኛውም የከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ላይ እንዳትንቀሳቀስ…” የሚል እገዳ ይጣልልንማ!

እናላችሁ…ነገራችን እንዲሰማልን የኳስ ህጐች ሌላው የህይወት ዘርፍ ላይ ሁሉ ይሥራልንማ! ደህና ክረሙልኝማ!

 

 

 

Read 2057 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 10:52