Saturday, 29 May 2021 14:24

“የሥርቻው መጣጥፍ” እንደ ልቦለድ በጥሞና ሊመረመር ይገባል

Written by  ሳሙኤል በለጠ (ባማ)
Rate this item
(1 Vote)

          ፻. መንደርደርያ
‘Les Misérables’ ወይም ደራሲና ተርጓሚ ሳህለስላሴ ብርሃነ ማርያም መከረኞቹ ብለው በተረጎሙት ድርሳን ላይ በ1962 (እኤአ)  የሕትመት ብርሃን ሲያይ፣ ፈረንሳዊው ደራሲ ቪክቶር ሁጎ የሚከተለውን ዘመን ተሻጋሪ ሐሳብ በመጽሐፉ ላይ አስፍሮ ነበር። “በስልጣኔ መሃል ሕይወት አምካኝ ሰው ሰራሽ ገሃነም እስካለ ድረስ ሥስቱ ታላላቅ የዘመኑ መቅሰፍቶች፦ የሰው ልጅ በድህነት መዋረድ፤ የሴቶች በረሃብ መማቀቅ፤  የሕጻናት ያለ እድሜያቸው መቀሰፍ፤  እስካሉ ድረስ ድንቁርና እና ድህነት በምድር ላይ እስከተንሰራፉ ድረስ …እንደ ‘‘Les Misérables’’ ያሉ መጽሐፍት ጥቅማቸው አይሞትም።”  በዚህ ዘመን ዘለል ቃል ውስጥ ብዙ ቁም ነገር እናገኛለን፡ ጉስቁልና፣ በሽታ፣ ድህነት፣ የማይድን ሕመም በዓለም ስልጣኔ መሃል ሰቆቃና እንግልት በሕብረተሰብ ውስጥ እስካሉ ድረስ ግለታቸው የማይቀዘቅዝ አያሌ ድርሰቶች መኖራቸውን ልብ ልንል ይገባል።

በአገራችንም በድህነታችን ውስጥ ያለንን ሃብት ባልተባረከ ሃብታችን ሰበብ የገባንበትን ረመጥ የሚያሳዩ  መጽሐፎች መኖራቸው ይታወቃል። ሆነም ቀረ በሥነ ጽሑፉ ዘርፍ እጅጉን ‘ርቀውን የሄዱ አገራት መኖራቸው ሊዘነጋ አይገባም፤ ድርሰቶቻቸውም ዘመንን ተሻግረው ትላንታቸውን በዛሬያቸው እያስመሰከረላቸው ይገኛል። ታዲያ ደራሲና ተርጓሚ ማለት ምንምና ማንም ‘በሌለበት’ ምድረበዳ እንዳበበች መዓዛዋንም መልካም እንደሆነ አበባ ያለ ነው። አልፎ ሂያጅ ድንገት ሲያልፍ አበባይቱን የሚያያትና በውበቷ የሚደሰት ከሆነ መልካም ባይኖርም ግን ከአበባነቷ አትጎድልም፣ መዓዛዋንም ተፈጥሮ አትነፍጋትም። ተፈጥሮዋ ማበብ ስለሆነ! ግን አርፎ ሂያጅ በውበቷ ቢደሰት ምንኛ ነፍሱ ታደለች? ደራሲ ይጽፋል፤ የጻፈውን ድርሰት ተደራሲ አንብቦ ስሜቱን ቢጋራለት ምንኛ ደስ ይላል? ተርጓሚም የተረጎመው ትርጉም ቢመረመርለት ምንኛ ጥሩ ነው። ግን ደራሲም ተርጓሚም እንደ አበባዋ መሆን አለባቸው፤ ተነበበም  አልተነበበም በጥንካሬ መዝለቅ ፣ለነፍስ ደስ የሚያሰኝ መዐዛ ያለው ነገር ለመፍጠር ሰርክ መታተር ይጠበቅበታል። ‘Les Misérables’ ‘መከረኞቹ’ በሳህለ ስላሴ ብርሃነ ማርያም፣ ‘The stranger’ ‘ባይተዋሩ’ በሚፍታህ ዘለቀ፣ ላቅ ባለ አማርኛ ቢተረጉሙልንም፣ ከውበቷቸው፣ ከሃሳባቸው አንዳች ነገር ሳንዘግን ከገበያ መደብዘዛቸው ያስቆጫል።

አሁን ደግሞ  ‘Notes from Underground’
በፊዮዶር ዶስቶቭስኪ ተጽፎ፣ ፋሲል ይትባረክ ‘የሥርቻው መጣጥፍ’ ብሎ ተርጎሞልናል። በ98 ብር ለገበያ ቀርቧል። አሁንም ‘ሮማናት አሳታሚና አከፋፋይ’ እያከፋፈለችው ነው። በቅኝቴ ግን ያን ያህል በጥሞና የተመረመረና በቅጡ የተነበበ አልመሰለኝም፤ ምክንያቱ አንድም በመጽሐፉ ዙሪያ ውይይት ስላልተደረገ፣ሂሳዊ ዳሰሳ ስላተደረገበት ወይም የሽፋን ምስሉ ገላጭ ግን ሳቢ ባለመሆኑ፣ በሌሎች የሽፋን ምስላቸው በሚስብ ውስጣቸው ባዶ ወረቀት በሆኑ መጽሐፎች መሸፈኑ ይመስለኛል። ሌላው ትልቁ ችግር፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ስለ ፊዮዶር ዶስቶቭስኪ የሥነ ጽሑፍ ችሎታው፣ በዓለም ላይ ስላሳደረው ላቅ ያለ ተጽኖ ያን ያህል ግንዛቤው ላይኖረን ስለሚችል እንደ ምክንያት መጥቀስ ይቻላል።
ለመሆኑ ፊዮዶር ዶስቶቭስኪ ማነው?

ፊዮዶር ዶስቶቭስኪ በጥቅምት ወር 1821(እ.ኤ.አ) በሞስኮ ከተማ ተወለደ፤ የኋላ ኋላ እናቱ በምግብ መመረዝ ሰብብ ታርፋለች፤ይህ ጊዜ ለፊዮዶር ዶስቶቭስኪ ፈታኝ ወቅት ነበር፤ ሆኖም ዶስቶቭስኪ በወታደራዊ ምህንድስና ትምህርት ቤት ውስጥ ገብቶ ትምህርቱን አጠናቀቀ፤ ከጥቂት ዐመታት በኋላ አባቱ በራሱ አሽከሮች ተገደለ፡፡ ፊዮዶር ዶስቶቭስኪ ወደ ሴናት አመራ፤ ቢሆንም አሁንም በዶስቶቭስኪ ሰማይ ላይ የሚዘንበው የመከራው ዝናብ ጋብ አላለም፡፡
በ1849(እ.ኤ.አ) ሴራ ላይ ተሳትፈሃል ተብሎ የሞት ፍርድ ተፈረደበት፤ ኋላ ፍርዱ ተቀይሮ ለአራት አመታት የጉልበት ስራ እንዲሰራ ተፈረደበት፤ በሰንሰለት እግር ከወርች ታስሮ ወደ እስር ቤት ተላከ፡፡ በዚህ ስቃይ ሰበብ ዶስቶቭስኪ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ሲራመድ ያዘግም ነበር፤ ከአራት አመታት እስር በኋላ ስቃዩ አበቃ፤ ቀሪዎቹ ጊዜያቶች ለዶስቶቭስኪ ከሞላ ጎደል ብሩህ ነበሩ፤ የተለያዩ መጽሔቶች ላይ መጻጻፍ ጀመረ፤ ከእስራቱ በኋላ የራሱ ሥራ ማግኘት አልቻለም ነበር፡፡ ዶስቶቭስኪና እዳ ማግኔትና ብረት ናቸው። ‘ዘ ጋምብለር’ ን የጻፈው እዳ ለመክፈል ነው። ሕይወቱን ሙሉ በሚጥል በሽታ ሲማቅቅ የነበረው ዶስቶቭስኪ፤ ጥር 9 1881 በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ አረፈ! የቀብር ስርዓቱም በቅዱስ ፒተርስበርግ ከተማ ውስጥ በሚገኘው አሌክሳንደር ኔቬስኪ ገዳም ተፈፀመ! ዶስቶቭስኪ እንደ ፈላስፋና እንደ ደራሲ ስሙ በዓለም የገነነ ነው።

በ1860(ዓ.ም) ዶስቶቭስኪ ‘Notes from Underground’(የሥርቻው መጣጥፍ) [ን] ለሕትመት አበቃ፤ ይህ ስራው ለሥነ-ጽሑፍ እድገት ትልቅ ሚና ተጫውቷል። በዚህ ተጽኖ ሰበብ የሰው ልጅን ስቃይ መሰነድ ተጀመረ፣ ኑረት ስላጎበጣቸው ሰዎች እንጻፍ የሚሉ ደራሲዎች ተፈጠሩ። እነዚህ ትረካዎችም የሕይወትን ገጽታ በመግቢያዬም እንደጠቀስኩት ሰው እስካለ አያሌ ሰቆቃዎች ስለሚኖር፣ ሰቆቃን ከሕይወት  ፈልቅቆ መተረክ ልምድ ሆነ፤ ሰውም ‘ሕይወት ማለት ከስቃይ እየታገሉ መኖር ናት ወይም ምንም ናት’ ማለት ጀመረ፡፡ ፕሮፌሰር ምንዳርአለው ዘውዴ ‘ራስን መሰለል’ በተሰኘው መጽሐፋቸው ውስጥ አንድ ገጸ ባህሪ ስለውልናል፤ ሊኦማር ትሰኛለች፡፡ ስለ ሊኦማር አስከፊ የሕይወት ገጽታ በመጽሐፉ እንዲህ ይገለጻል። “በተራቆተው የሊኦማር ጀርባ ላይ ይታይ የነበረው ልብ የሚነካ መጅ ነበር። በጋለ ማረሻ በርከት ብለው ወደ ጎን የተሰመሩ ጠባሳ መስመሮች ይመስላል መጁ። መጅ በሊኦማር ጀርባ ላይ ድህነት ለዘመናት ሳይሰልስ ሲያኖረውና ሲያድሰው የከረመው የመከራ ማሕተም ነው።”(ገጽ-14) በሰው ሰራሽ ገሃነም ውስጥ ያለውን ስቃይ ደራሲ መጻፍ አለበት፡፡ ደራሲ ዩዶራ ዌልቲ እንዲህ ትላለች፡- “ሕይወትን እኔ ራሴ እንዳየሁዋትና እንደተረጉምኩዋት ለመጻፍ ነው የምሞክረው። በምናብ ዓለም የቱንም ያህል ርቆ ቢኬድም የተፈጠረው ሕይወት በዙሪያው ካለው እውን ሕይወት ጋር የተቆራኘ ሆኖ ነው የሚሰማኝ” ምንኛ ልቡናን የሚማርክ ቃል ነው? አዎ ደራሲ እንዲህ ነው መሆን ያለበት፤ የዶስቶቭስኪም ልቦለዶች ይህንን መርህ ሲያንጸባርቁ ይታያሉ።
“የሥርቻው መጣጥፍ” ‘አዕምሮውን’ የታመመ ሰው ኑዛዜ አንስቶ እንደገና በመንፈስ ለመወለድ የሚገባውን ቃል ይተርክልናል። በትረካው የማይዳሰስ ረቂቅ መልዕክት፣ የሚያስቆዝም፣ አልፎ አልፎ ለሕይወት መርህ የሚሆኑ  ፍልስፍናዎች ጣል ይደረጉበታል። ጉራንጉሩን የሰው ልጅ ሃሳብ ገላልጦ ያሳየናል። ለምሳሌ... “ይቅርታ ብዙ ተፈላሰፍኩ። ምን ላድርግ? ለአርባ ዓመታት ለራሴ በፈጠርኩት ሥርቻ ስለኖርኩ ነው። የልቤን አደርስ ዘንድ ፍቀዱልኝ። አዩ አርቆ አስተዋይነት መልካም ነገር ነው። የሰውን የማሰብ ችሎታ ከተግባር ላይ ያውላል። መሻትና መከጀል ግን የሕይወት ሁሉ ድምር ውጤት ነው። ሕይወት ከነጥማትና እርካታዋ። ሕይወት ቅጥ ያጣች ምስቅልቅል ብትሆንም እንኳን የምኖረው የኑሮ ጽዋ እስከ አተላው ልጨልጥ እንጂ የሕይወቴ ቁራጭ አካል የሆነውን የማሰብ ችሎታዬን ለመኮትኮት ብቻ አይደለም፤ አዕምሮ ከተማረው ውጪ ምን ያውቃል? የሰው ተፈጥሮ ግን የሐሳብም ሆነ የጭፍን ሂደት ሙሉ ሕይወት ነው። ቢሳሳትም እንኳን ሕያውነቱ አይካድም፡፡
“(ገጽ 29) መጽሐፉ አያሌ ቁም ነገሮችን ቢያነሳም በዚህ ዳሰሳ የሚያልቅ አይደለም ሃሳቡ ጥልቅ ነው። ዓላማዬም መጽሐፉን መዳሰስ ሳይሆን መልዕክት ማስተላለፍ እንደሆነ አንባቢ ልብ ሊልልኝ ይገባል።;
መሸበቢያ
እኔም እላችዃለሁ “በስልጣኔ መሃል ሕይወት አምካኝ ሰው ሰራሽ ገሃነም እስካለ ድረስ ሥስቱ ታላላቅ የዘመኑ መቅሰፍቶች፦ የሰው ልጅ በድህነት መዋረድ፤የሴቶች በረሃብ መማቀቅ፤ የሕጻናት ያለ እድሜያቸው መቀሰፍ፤ እስካሉ ድረስ ድንቁርና እና ድህነት በምድር ላይ እስከተንሰራፉ ድረስ …እንደ ‘የሥርቻው መጣጥፍ ’ ያሉ መጽሐፍት ጥቅማቸው አይሞትም።” ስለዚህ #የሥርቻው መጣጥፍ; በጥሞና ሊመረመር ይገባል።

Read 486 times