Print this page
Saturday, 29 May 2021 14:21

“ጠይም ጨረቃ”

Written by  አፀደ ኪዳኔ (ቶማስ)
Rate this item
(9 votes)

    እያወሩ መተኛት ይችላሉ - ቄስ ባህታ። እየሄዱ መቆም፣ እየመረቁ መርገም አመላቸው ነው።  በስውር ነው ታድያ። ጠጅ እየወደዱ አንዳንዴ፣ ጠጅ ያንገሸግሻቸዋል። ሁለት ተቃራኒ ማንነት የያዙ፣ እዚህ  አማኑኤል  ምድር ላይ ማን ናቸው ከተባለ ማንም ይናገራል። አላፊ አግዳሚው ሁሉ እሳቸውን ያውቃል። ኮንዶምኒየም ፊት ለፊት ጉሊት የሚቸረችሩ ሰዎች አሉ። ሰፈሩ በሰው የተጨናነቀ ይመስላል። ሰው እንደ ጉንዳን ከቦታል። እንደ ንብ ያምማል። እንደ ኤሊ ያዘግማል። ትንንሽ ልጆች እግረኛ መንገድ ላይ ይጫወታሉ፣ ኳስ፣ አባሮሽ ... ሴቶቹ ሱዚ ይዘላሉ (ጡሊ ሁላ)። ዐይኔ ማየት የሚፈልገውን እያየ ይሄዳል። ማየት የማይፈልገውን ሰው እንዴት ነው የሚያየው? እኔ በእርግጥ መርጬ ነው የማየው! የእግር መንገድ እወዳለሁ። እራመዳለሁ... እራመዳለሁ...
... ቄስ ባህታን የማያውቅ ማን አለ? ድምፃቸው ከሰማይ ወፍ ያረግፋል የተባለላቸው... ሲቀድሱ ባልቴቶች በድምፃቸውና በቃል አጣጣላቸው ለአልጋ የሚነሆልሉላቸው፣ አልጋ ላይ ሲተኙ በደረታቸው፣ ሲነሱ በጀርባቸው... እሳቸው “ለአድባሩ ነው” ይላሉ። አድባር ምን ማለት እንደሆነ አላውቅም። ቆሌ ይርቀኛል አለዚያ ይላሉ - እሳቸው።  በቀኝ መነሳትህን ማረጋገጥ  አለብህ ባይ ናቸው። ቀኝ ግራ የሚል ጨዋታ ባይገባኝም  በተመስጦ እሰማቸዋለሁ። በዚህ ደካማ አቅማቸው፣ በዚህ የጡረታ እድሜያቸው እኔን ኮሌጅ ያስተምራሉ (በሀብታሙ ልጃቸው ቢረዱም ቅሉ)።
... ድንገት መለስ ብለው “አንተ ልጅ አለህ እንዴ?” ይላሉ። “አለሁ” የሚል መልስ ከአፌ አይወጣም። የሚወዱትን ጠጅ እገዛላቸዋለሁ። እየጠጡ ማውራት፣  መጫወት ይወዳሉ። ግሩም አባት ናቸው - ቄስ ባህታ። የልጅ ልጆቻቸውን ሰብስበው የአረቄን ጎጂነት የሚደሰኩሩ፣ የጫትን አሳባጅነት የሚለፉፍ ናቸው። ቀይ መልካቸው ላይ ትንንሽ ዐይኖች አሉ። ፊታቸው ብዙ ነገር የሚናገር ይመስላል።  እድሜ ላይ የሚተክዝ የህፃን ፊት  አይነት ነው። ሪዛቸው ተንዠርግጎ ይታያል። እድሜያቸው እንደ  እምነታቸው  ተጭኗቸው ጎብጠዋል። ቄስ ባህታ ጥሩ አባት ናቸው። የመጨረሻ ልጃቸው እንደመሆኔ ይወዱኛል። ያቀርቡኛል። ያጫውቱኛል። ይቃለዱኛል። ሰው መሆኔ የሚታየኝ ከሳቸው ጋር ስሆን ነው። እውነተኛ የአባት ፍቅር ሳያስመስሉ የሚሰጡን እሳቸው ናቸው። እናታችን  በህፃንነቴ ስለሞተች አላስታውሳታም። እሳቸውን ብቻ ይናፍቃል ልቤ፣ እሳቸውን ብቻ  ይወዳል ልቤ.... እሳቸውን ብቻ ያቅፋል ልቤ... እሳቸውን እሳቸውን ብቻ.... ወንድሞቼ ስራ ይዘው፣ ሌላው አግብቶ ከቤት ወጥተዋል... አንዱ ያንድ ድርጅት ባለቤት ነው። ሁሌ ይገርመኛል። ሲመጣ ብቻውን ነው። ሚስቱን ይዟት መጥቶ አያውቅም። ሲጋቡ እንኳን ፎቶ የላቸውም። ድግስ አልተደገሰም። ዝም ብሎ አገባሁ ብሎ ወጣ። ትልቅ ቤት እንዳለው አውቃለሁ። ግን ማንም አያውቀውም። ምስጢር ይወዳል። እንደ አኩኩሉ ድብብቆሽ ያስደስተዋል። ይሄ ልጃቸውን ቄስ ባህታ ሲገልፁት፤ “እርጉሙ ልጅ”ይሉታል።  እኔም ከሳቸው ሰምቼ እንደዚያ ነው የምጠራው።
“እርጉሙ ልጅ”
ጥቋቁር ከንፈር አለው። ሲናገር ለስለስ አድርጎ፣ በዝግታ ነው። ሰውነቱ ግዙፍ ነው። ሲሄድ ዝግ ይላል። ሰውነቱ እየከበደው ይመስለኛል። ታድያ ይሄ እርጉም ልጅ ወንድሜ ቢሆንም የማየው እንደ እሩቅ ሰው ነው።
የቄስ ባህታ የልጅ ልጆች ግቢያችንን ይሞሉታል። ግእዝ ያስተምሯቸዋል - እኔን እንዳስተማሩኝ... ዳዊት ያስደግሟቸዋል.... ልጆቹ ባይገባቸውም በዝምታ ይከታተሏቸው ነበር።
“ከርካሳ” ይላሉ።
አንድ ቀን እንዲህ ተፈጠረ :
ቴሌቪዥን የመጣ ሰሞን ነው። ቴሌቪዥን ገዝተው አሸክመው ይመጣሉ። እሳቸው በድካም አቅማቸው (ያኔ እንኳን ብዙ ደካማ አይደሉም) እየተንቀሳቀሱ ይከተላሉ። መሃል መንገድ ላይ ጠፋባቸው። ቢፈልጉ ቢፈልጉ አጡት። ይሄኔ ፊታቸው ከሚያዩት  ጠጅ ቤት ገብተው ሲጠጡ አምሽተው ቤት ይመጣሉ፡፡ ቤት ሲገቡ የገዙት ቴሌቪዥን ቁጭ ብሎ ይለፈልፋል። ይሄ የስላሴ ተዓምር ነው ብለው ፤  ሁለት መቶ ብር አስገቡ - ለስላሴ። ለካ ተሽካሚው ሰፈራቸውን ያውቀው ኖሯል፤ ሲጠፉበት ሰፈር ደርሶ ይጠያይቃል። የመንደር ሰዎች ቤቱን ያሳዩታል። ገብቶ ያስቀምጥላቸዋል። ታድያ ቄስ ባህታ ይሄን የደግነት ተግባር የስላሴ ተዓምር አድርገውት አረፉ። ልነግራቸው እፈልጋለሁ። ምናልባት እንደ እኔ አይነት ጠማማ ኩሊ ቢሆን እኮ ይዞብዎት ይጠፋል ልላቸው እፈልጋለሁ። አይሰሙኝም እንጂ።
ሁሉም ነገሮች እንደ ትላንት የሚናፈቁ ናቸው። ዛሬ የትላንት ያህል አይጥምም። የህይወትን ግርግር የሚያዩ፣ እነዚያ የሰላም ቃፊሮች እውነት በገዛ እጃቸው እየነካኩ ያስተኙታል። እሹሩሩ እያሉ  እንዲያንቀላፋ ያደርጉታል።
የምማርበት ኮሌጅ ብዙ ሰዎች ያቀፈ ነው። ሊማሩ የሚመጡትን ልጆች ሳይ አንዳች መጥፎ ስሜት ይሰማኛል። ለምን እንደሆነ ባላውቅም የሚሰማኝን ስሜት እያመነዠኩ እማራለሁ። የሚለፈልፉ አስተማሪዎች አሉ። ሌላም ብዙ ብዙ ልጆች አሉ። የምትገርመኝ አንዲት ልጅ አለች። በእርግጥ ልጅ አይደለችም። ነገረ ስራዋ ይገርመኛል። ሁናቴዋ ይደንቀኛል። አጭር ቀይ ቀሚስ አድርጋ ትመጣለች። እነዚያ ትልልቅ ዐይኖቿን ሳይ የምናገረው ይጠፋኛል። ፀጉሯን አሳጥራ  ትቆረጣለች። ከጆሮቿ እንዳይወርዱ የምትጠነቀቅ ትመስል። ትንንሽ ጆሮዎቿ ሲታዩ  የሚሰሙ አይመስሉም። አጭር ቀሚስ፣ በሸሚዝ መልበስ ታዘወትራለች። ወፋፍራም ከንፈር አላት። ስትስቅ ዓለም ሰማይ ላይ የምትደምቅ ጠይም ጨረቃ ትመስላለች። ብዙ ጊዜ ዝም ስለምትል ልቀርባት እፈልጋለሁ። የሚያስጨንቃት ነገር ካለ ብዬ አያለሁ። ሁሉን ነገር የረሳች ትመስላለች።  ዓለምን በጥበቧ የተወች የዘመን መነኩሲት ትመስላለች።    ኮሌጅ ስትመጣ ለመጀመሪያ ጊዜ አየዃት። ሲቪክ አስተማሪያችንን በጥያቄ ስታጣድፈው ተመለከትኩ። ሁሌ የማይቀይራት ቆዳ ጫማ  እንደመጥመም ብላለች። ስታናግረው ላቦቱ ተንቆረቆረ። በውበቷ ይሁን በጥያቄዋ አላውቅም። ክሳዱን አቁሞ የለበሳት ሸሚዝ ብብቷ ስር በላብ የረጠበ  ቦታ ይታያል። ለጥቁረት ያደላ ፀይም ነው። ሰልካካ አፍንጫ አለው። ሲናገር ምራቁን እየረጨ ነው። ማንም ተማሪ አጠገቡ መቀመጥ ያናድደዋል። ታድያ ጥያቄዋ ምን እንደሆነ በእርግጥ አላስታውስም። መጨቃጨቅ ትወዳለች። ማለት የሆነ ነገር መጠየቅ፣ የሆነ ነገር ትንሽ ነገር መናገር እና ዝም ማለት። ይሄ ባህሪ ከተባለ የእሷ ባህሪ ነው። አንዳንዴ ብቻዋን ፈገግ ትላለች። ደግሞ ትጨነቃለች። ፊቷን አስሬ ትዳብሳለች። እነዚያ ትልልቅ ዐይኖቿን ታጉረጠርጣለች። ዝም ብዬ አያታለሁ። ትነሳና ትቀመጣለች። ቀሚሷን ታስተካክላለች። አፍንጫዋን አስሬ ትነካካለች።  ደግሞ መልሳ ትነሳለች፤ ቀሚሷን ልታስተካክል።
ስሟን ለመጀመርያ ጊዜ ስሰማ ደንግጫለሁ። ፍቅር ትባላለች። በዝምታ ፍቅር የወደቀች፣ በመነዛነዝ ፍቅር የተለከፈች ናት። ለምን ትላለች። እንዴት ብላ ትጠይቃለች። ለመጀመሪያ ጊዜ ቀርቤ አንድ ጥያቄ ጠየኳት፤
“የያዝሽውን መጽሐፍ አንድ ጊዜ ለማየት እችላለሁ?”
ሰጠችኝ። የኦሾ መፅሐፍ ነው። ህያውነት ይላል።
“ምንድነው ህያውነት?” አልኳት።
“ህያው ማለት ያለ፣ የሚኖር፣ ዘመን ላይ ብቅ ያለ ፍጡር ማለት ነው”
“አሃ... ኦሾ አይመቸኝም” አልኳት ብዙ እንዳነበበ ሰው።
“ጥሩ”
“ማለት እምነት ላይ የሚያነሳቸው ሀሳቦች አይመቹኝም። እኔ የቄስ ልጅ ነኝ። ከሀይማኖት ጋር የተገመድኩ ነኝ። ኦሾ ደግሞ ምን ይላል--” አንድ ያነበብኩት ሀሳብ  መጣብኝ
“ምን ይላል፣  ዓለም ላይ ከሶስት መቶ በላይ ሀይማኖቶች አሉ። ሁሉም የአምላክ ስጦታ ፣ አምላክን የምንወክል ነን ብለው ያስባሉ፤ ታድያ የትኛው ነው ትክክል? አንተ የምታምነው ሀይማኖት ከነዚህ ሀይማኖቶች አንዱ ነው?’ ይላል”
“Ya...that was good idea...ማለቴ ጥሩ ኀልዮ ነው። ኦሾ የማሰብ አቅም አለው። ህይወቱ ግን እንደ ማሰብ አቅሙ የተስተካከለ አይደለም። ብዙ ብር ያባክናል። ብዙ ማለት ብዙ ብዙ ማለቴ ነው። ግን ያነባል። ብዙ መፅሐፎች አንብቧል። ስለዚህ ሀሳብ አይነጥፍበትም። ለዚህም ነው ቶሎ ቶሎ የሚፅፈው። ብዙ መፅሐፎች አሉት። እኛ ሀገር የተተረጎሙትን እንኳን ብትቆጥር ብዙ ናቸው። ይሄም ሀሳብ ጥሩ ነው። ልክ ነው ማለቴ አይደለም፤ ሀይማኖት ውስጥ ሆነህ ነፃ የማሰብ ሙብት አለኝ ብትለኝ የምሰማህ በሶስተኛው ጆሮዬ ነው። ሶስተኛ ጆሮ እኔ ጋ ይታይሃል? አታይም አይደል? አልሰማህም ማለቴ ነው። ነፃ ሆነህ ካላሰብክ ታድያ እንዴት ነው የምትመረምረው? ህግ አጣሪ ነው። ብዙ ፈላስፎች አሉ። ስለሚያስቡ ከእምነት የተፋቱ ናቸው። ግን አማኝ ፈላስፋ የለም ማለት አይደለም። ክርስትና ገና ድሮ ሲሰበክ የሚያስተምሩት የእነ ፕሌቶን፣ የእነ  አርስቶትልን ፍልስፍና አስገብተው ነው። ምክንያቱም በዚያ ጊዜ ያ ፍልስፍና ታዋቂ ነው። ገባህ አይደል የምልህ? ፍልስፍና እና ሀይማኖት ሁሌ ሊታረቁ የማይችሉ የህይወት ዘውጎች ሲሆኑ ሁሌም ግን ለመታረቅ ሸንጎ እንደሚሰበሰቡ ጨቅጫቃ ባልና ሚስቶች ናቸው። ይገናኛሉ፣ ግን ይጣረሳሉ፣ ይዋደዳሉ ግን ይገፋፋሉ። ማመን ስትጀምር ማሰብ ታቆማለህ። በቃ አምነሃላ (ብዙ ለፈለፍኩ አይደል)"
“ማመን ውስጥ መጠየቅ፣ መመርመር፣ ማሰብ የለም እያልሽኝ ነው?”
“እንደዚያ ነገር”
“የሚያምኑ የሀይማኖት አባቶችና ምዕመናን አያስቡም ማለትሽ ነው?”
“ቢያስቡማ አያምኑም ነበራ”
ዝም ብያት ሄድኩኝ። ደብተሬን ይዣለሁ። አታስብም እኮ ነው ያለችኝ እያልኩ እብሰለሰላለሁ። አለማሰብ ምን ማለት ነው? ማሰብስ? ፈላስፎች ያስባሉ ከተባለ ሀይማኖተኛ ፈላስፎች ታድያ ያስቡ አይደለም እንዴ? በእርግጥ እነሱ ማሰብ የሚሉት እግዜሩን እንደ ሰው አውርዶ መጠየቅ መመርመር ነው? እኛ ግን በእግዜር ዓለም ውስጥ ሆነን  ነው የምናስበው! ማሰብ ብዙ ዓይነት ነው። እግዜርስ ባናስብ ነው መርምሩ ያለን?  ስለዚህ ማሰብ ማለት እግዜርን መጠየቅ ብቻ አይደለም! ስለ ተፈጥሮ ማሰብ -  ስለ ሰው ማሰብ -  ስለ ባህሪ ማሰብ - ስለ ተረቶች ማሰብ - ስለ ስነፅሁፍ ማሰብ አለ። ማሰብ እግዜርን ከመደፋፈር ጋር ብቻ አዛምደው ስለሚያዩት እሳቤያቸው ተንሸዋሯል አልኩ።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ስለ እሷ አለማሰብ አልቻልኩም።
“ፍቅር .... አንቺ የሃጢያት ፍቅር ...የመጠራጠር ፅድቅ ነሽ። ማተቤን ልታስበጥሺኝ የተነሳሽ ቀንደኛ ሰይጣን ነሽ።   ካንቺ መራቅ ግን አልቻልኩም። ስለ አንቺ አለማሰብ አልቻልኩም። እውነት እውነት እልሻለሁ አፍቅሬሻለሁ።  ፍቅር ከሌለኝ ከንቱ ነኝ ብሏል ቅዱስ መፅሐፍ (#ባይጥምሽም ጠቅሼዋለሁ”) ብዬ ፃፍኩላት፣ ግን እሺ ባትልስ ብዬ አሰብኩ።  ሰይጣን ነሽ ፣ ብሎ አፍቅሬሻለሁ ማለት ምን ማለት ነው? የፃፍኩት ለእራሴ ገብቶኛል? እሷስ ስለ ቅዱስ መፅሐፍ ምን አገባት?
በድጋሚ ልፅፍላት እጄ ብዕር ጨበጠ።  ግን አልቻልኩም። በስልክ ሜሴጅ ልልክላት ፈልጌ ስልኳን አላውቀውም። ለካ እንዴት ያለሁ ከንቱ ሰው ኖሪያለሁ። በነጋታው ሳገኛት እንደለመደችው አጭር ቀሚስ ለብሳ መፅሐፍ ላይ አቀርቅራለች።
“ሰላም” አልኳት።
“ጥሩ”
ምንድነው ጥሩ? ሰላም ሲሉን ሰላም እንላለን እንጂ ጥሩ ይባላል በአባባ ሞት።
“ጌታ ክርስቶስ ይገስፅሽ” አልኩ፣ በሆዴ።
“መፅሐፉን ልየው” አልኳት።
“ምን ያደርግልሃል አንተ የቄስ ልጅ ነህ!”
“የቄስ ልጅ መፅሐፍ አያነብም”
"ሃሃሃሃሃ!"
ስትስቅ ይበልጥ ታምራለች። ጠይም ጨረቃ ነው የምትመስለው። ጨለማን በውበቷ ማፍካት ትችላለች። ጥርሶቿ ነጫጭ ባይባሉም ተስተካክለው የተሰደሩ ናቸው። ዓይኖቿ እንደ እሳት ላንቃ የሚጋረፉ  ይመስላሉ። ፊቷን ማበስ ጀመረች። ደግሞ ጭንቀቷ መጣ አልኩ። ላረጋጋት ፈለኩና...
“ፍልስፍና እኛም ድሮ አንብበናል፣ አላዋጣ ብሎን ነው የተውነው”
“ድንጋይ ነሃ!”
“ምን?”
“አልሰማኸኝም”
“ሰደብሽኝ እኮ...”
“ኦሾን ማንበብ ብልህ የሚያስብል ከሆነ፣ ዝንተ ዓለም ድንጋይ ሆኜ ልቅር”
“ድንጋይነትህን ካመንክማ ድንጋይ አይደለህም ማለት ነው”
ዝም ብያት ተነሳሁ። አስተማሪዎች መለፍለፍ ጀመሩ። ማንንም አልሰማም። ልቤ እሷ ጋር ነው ያለው። ድንጋይ የሚለውን ስድቧን አስባለሁ። እነዚያ  ወፋፍራም ከንፈሮቿን እጠማለሁ። ፍቅሯን እራባለሁ። ሁሉም ነገር ይናፍቀኛል።
በሚቀጥለው ቀን ስሄድ እያነበበች አይደለም። ደስ አለኝ። ከዚህ የፍልስፍና ዝብዝቧ ነፃ መሆኔን አየሁ።
“ሰላም”
“ጥሩ”
“ለምን ዛሬ አልጋብዝሽም። በዚያውም ስለ ፍልስፍና እናወራለን”
“ፍልስፍና ታውቃለህ እንዴ?”
“ባላውቅም ታስተምሪኛለሽ”
“እሺ እንውጣ” አለችኝ።
የኮሌጁን ፎቅ  የሚመስል ከርካሳ ቦታ ለቀን ስንወጣ፣ ውብቷን አየሁ። ጠይም ጨረቃ ናት። በውበቷ ዓለም የምታፈካ...  ጠይም ጨረቃ...
“ጠይም ጨረቃ ነው የምትመስይው” አልኳት፣ አፈር እያልኩ።
“ጠይም ጨረቃ ደግሞ ምንድነው?”
“ማለቴ እንደ ጨረቃ የዓለም ፅልመት ላይ ታበሪያለሽ... ይሄ አለም ለእኔ ፅልመት የከበባት የዘለዓለም ዋሻ ናት። ሁሉም ነገር ያስጠላል። የምማረው ሳይቀር በግድ ነው። ደካማ አባቴን ለማስደስት ምናምን..”
“መማር ካልፈልክ ለምን ለአባትህ ብለህ ትማራለህ? መማር ያለብህ ለራስህ ነው እኮ... ትምህርቱን ካልወደድከው ባትማር ይሻልሃል። ምን ያደርግልሃል? ስራ ብትይዝም አትሰራም...”
“ልክ ነሽ ፍቅር”
“ፍቅር አትበለኝ”
“ስምሽ እኮ ነው”
“ይሁና....”
 ፅጌሬዳ ሆቴል ደረስን። ሰፊ ነው።  መግቢያው ላይ  ጠባብ መንገድ አለችው። ቁጭ አልን። እኔ ቡና አዝዝኩ፤ እሷ ጃንቦ... የሴትና የወንድነት ውሉ የተቀያየረ መሰለ።  መመሳሰል አትፈልግም። በመመሳሰል ውስጥ ማስመሰል እንዳለ የታዘበች ትመስላለች።
“እና”  አለችኝ።
“እናማ እኔ የምወደው አንድ ፀሀፊ አለ... ስለ እሱ ብታወሪኝ ደስ ይለኛል። ስለ ካህሊል ጂብራን...”
“ካህሊል ጂብራን በጣም ነው የምወደው። ትክክለኛ ስሙ ጂብራን ካህሊል ጂብራን ነው። አንድ የሚወዳት ሴት አለችው። አርታኢው ናት። በብዙ ነገር አግዛዋለች። በገንዘብ ፣ በሃሳብ... በብዙ ነገር... ይወዳታል ግን አግብታለች። ልጅም አላት...የፕሌቶ ፍቅር ታውቃለህ?”
“አላውቅም ኧረ”
“የፕሌቶ ፍቅር ማለት ፕሌቶ የፈጠረው የፍቅር ግንኙነት ነው። አንዲት ሴት ከአንድ ወንድ ጋር ለመሆን የግድ ወሲብ አያስፈልግም ብሎ ያምናል። ወሲብ የሰዎችን ግንኙት የሚያበላሽ ነገር ነው። ለምሳሌ አንዲት ሴት ልትወልድ፣ ልታገባ ትችላለች። እንደዚያም ሆኖ ታፈቅራታለህ። የግድ አብሮ መኖር፣ በጋብቻ መከለል አያስፈልግም ባይ ነው። ካህሊል ጂብራን እንደዚህ አይነት ፍቅር ነው የያዘው። እንዳገባች፣ እንደወለደች እያወቀ አፈቀራት። እሷ ባትኖር ይሄ አሁን የምንደመምበትን ፅሁፍ ባልፃፈ ነበር።  እንዲህ ነው እንግዲህ ፍቅር። ሁለት ጥንዶችን ያቀራርባል። ፍቅርን በወሲብ ገበያ የሚሸጡ እነሱ ፍቅር ያልገባቸው ደንዛዞች ናቸው። ወሲብ የትም አለ። ፍቅር ግን ውስን ቦታ ነው ያለው። አሁን እኔ አግብቻለሁ )።”
“እንዴ?!” ድንግጥ አልኩ።
“ምነው?”
“አትመስይም”
“አዎ፣ አግብቻለሁ። ግን ትዳሬን አልፈልገውም። ዝም ብሎ እግር መክፈት፣ ዝም ብሎ የማይወዱትን እያስታመሙ መኖር ነው ያስከፋል። ባሌ አይወደኝም። ግን ይፈልገኛል። ለምን እንደሆነ አላውቅም... እዚህ የሚያስተምረኝ ለዚያ ነው። እሱ ድርጅት እንድሰራ።”
“እኔ እኮ...”
“እኔ እኮ ምን”
“ማለቴ ደስ ትይኝ ነበር”
"ሃሃሃሃሃሃሃ!"
ስትስቅ ታምራለች። በጣም ታምራለች።
“ሁሌም ደስ ልልህ ይችላል። መዋደድ እንችላለን። ማለቴ የግድ አብራችሁ ተኙ የሚለን ህግ የለም። ባልወድህም ልትወደኝ ትችላለህ... አንተ መወደድ ላይ እኔ አላስፈልግም። የምልህ ይገባሃል አይደል? ሰው ሰውነቱ ፍቅር ነው። ሰው ሰውነቱ መውደድ ነው። ከፍቅር ነው የተሰራነው። ክርስቶስ ከሰማይ ወርዶ ሰው የሆነው ለምን ብሎ ነው? ለፍቅር አይደል?  ፍቅር ነው የሚገዛኝ እኔ። ፍቅር ነው ዓለሜ፣ ፍፃሜዬ...እዚያ የመዋደጃ ጥርስ ውስጥ የሚገቡ እነሱ የተቀደሱ ናቸው። ፍቅር መፅደቂያ መንገድ ነው። ፍቅር ላይ ወሲብ ስትጨምርበት ነው የሚረክሰው። ነገር ዓለምህ በዚያ ቁጥጥር ውስጥ ይሆናል።  እንደ እንስሳ ትሆናለህ። ትረክሳለህ። ወርደህ ሰው ከመሆን ትወጣለህ። ፍቅር ነው የሁሉም ነገር አልፋና ኦሜጋ። እሱ ፍቅር ነው።”
“በፍቅር ታምኝያለሽ?”
“በጣም!  አምናለሁ። እሱ ነው የሚገዛኝ። የእውነት መውደድ ይስበኛል። እውነተኛ ፍቅር ይናፍቀኛል። ግን ዓለም እንደዚህ አይደለችም። ሁሉም አስመሳይ ነው። አንተ እራሱ ትዕግስትህ ይገርመኛል።  እንዴት እዚህ እንዳመጣኸኝ ይገርመኛል። እኔ ሰው አልቀርብም። የሚቀርቡኝንም ሰዎች እያስከፋሁ እርቃለሁ። ምናልባት የሆነ ነገርህ ደስ ብሎኛል። ምናልባት...”
“እና ቆይ ባልሽን ካልወደድሽው ለምን አትፈችውም?”
“ቤተሰብ አስሮ የያዘኝ እግረ ሙቅ ነው። ለገንዘቡ ይፈልጉታል።  እኔ ግን ገንዘቡ ምኔም አይደለም። ዛሬ ብተወው ደስ ይለኛል። ግን ቤተሰቤን ላለማስከፋት አብሬው እሆናለሁ። ምን ላድርግ... ነገሮች እንደዚህ ነው የሚሄዱት...”
ጃንቦ ደገመች። እኔም ቡና ደገምኩ። ደስ እያለኝ አወራን... ድንገት ፊቷን ማበስ ጀመረች። ተነሳች... ቁጭ አለች። ቀሚሷን አስተካከለች። አይኗን አፈጠጠች። አፍንጫዋን መነካካት ጀመረች። እንባ ዐይኗ ላይ ያየሁ መሰለኝ። ለማረጋገጥ ተጠጋዃት። አዎ! እንባ አቁሯል አይኗ። ድንገት ማልቀስ ጀመረች። ምን እንደሆነች ብጠይቃት ዝም አለችኝ። ድራፍቱን ጠጣች። ትንሽ የተረጋጋች መሰለችኝ።
“ምን ሆንሽ?” አልኳት ፣ ደግሜ።
“ህመም አለብኝ ታውቃለህ። እንዲህ የሚያደርገኝ ደስታ ነው። ደስታ መቋቋም አልችልም። ብዙ መድሃኒቶች እውጣለሁ። ደስታው ያስለቅሰኛል። ትንሽ ደስታ ትልቅ ነገር ነው የሚፈጥረው እኔ ላይ። አልችልም” እያለች፣ ማልቀስ ጀመረች።
“አታልቅሽ አሁን”
“ውድጄ እኮ አይደለም። ሰው ሲቀርበኝ፣ ስጠጣ እንዲህ ያደርገኛል። አንዳንዴ ሳነብም እንዲህ ያደርገኛል። አየህልኝ አይደል? ደስታም ህመም ነው። ከአቅም በላይ ሲሆን ስቃይ ነው። ሁሉም ነገር በልክ ሲሆን ያምራል። ከአዕምሯችን በላይ የሚወጣ ነገር ነው። ስቃይ ከልክ በላይ የሆነ ነገር ይመስለኛል። ፍቅርም በልክ ሲሆን ነው የሚያምረው። ጥላቻም እንደ አቅም ሲሆን ጥሩ ነው። ሁሉም እንደዚህ ነው የሚጓዙት... ኦሾ አንድ ጊዜ ምን አደረገ መሰለህ... በጣም የተከበሩ እና ትዕግስተኛ የሚባሉ መነኩሴ ቤቱ ሊያነጋግሩት ይመጣሉ። ከዚህ በፊት ሰምቷል ትዕግስተኛ መባላቸውን... እና መፅሃፍ ቅዱስ ይዘዋል። ገቡ እቤቱ። ቤቱ በመፅሃፍ የተሞላ ነው። ገረማቸው... እና እንደተቀመጡ ምን አላቸው ’ይሄ የያዝከው መፅሃፍ ተራ ተረት ነው’ እኚህ ትዕግስተኛ የተባሉት መነኩሴ ጋሉ። ‘ድሮም እኮ አንተን ለማነጋገር መምጣቴ እኔ ነኝ ጥፋተኛ’ አሉና ሊወጡ ሲሉ እንዲህ አላቸው ’አባቴ ትዕግስተኛ ነዎት ተብዬ ነበር። ይህቺን ነገር መታገስ ያልቻሉ ሌላውን በምን አቅምዎት ይታገሳሉ’ ዝም ብለውት ተቀመጡና ’አገኘኸኝ አንተ እርኩስ’ አሉት፣ ይባላል። እና ምን ልልህ ፈልጌ ነው፤ የትኛውም ነገር ልክ አለው። ከዚያ ልክ ካለፈ ንዴት ይሆናል። ስቃይ ይሆናል።”
“የሚገርም ነው!”
“ዝም የምለው ብቸኛ ስለሆንኩ ነው። በባል፣ በቤተሰብ ሽምጥ አጥር የተከለልኩ ብቸኛ ወፍ ነኝ። ሁሉም ነገር አሳዛኝ ይመስላሉ። ጊዜ ጊዜን ይተካል... መሆን የምንችለውን እንለፋለን... ግን አይሳካልንም። መኖር አድካሚ ዳገት ማለት ነው። አንዳንዴ አጫጭር ልብወለዶች እፅፋለሁ። ብዙዎቹ ብቸኝነትን የሚያቀነቅኑ፣ ሀዘንተኛ ልቦች... በእንባ የተሞሉ ናቸው። ፀለምተኛ ነሽ ይሉኛል። ፀሊም ቢሆን ነው ዓለሜ... ጨለማ ቢሆን ነው በኣቴ... ከዚያ ውጪ መውጣት አልችልም። ከዚያ ቅንፍ ስወጣ ከባህር እንደወጣ አሳ ነፍሴን የተነጠቅሁ ይመስለኛል። እስቲ ደብዳቤ ልፃፍልህ...ቢያንስ በዚያ ታውቀኝ ይሆናል”
ልከፍል ስል አይሆንም አለች። ሂሳቡን ጠቅላላ ከፍላ ወጣን። መንገዱ እረዥም ሆነብኝ። ልቤ ደከመብኝ።  ህመሟ ህመሜ ሆነ። የደስታ  ህመም ሰምቼ አላውቅም። ሰው እንዴት በደስታ ይታመማል? እንዴት ደስታ ህመም ይሆናል? ብዙ ጥያቄዎች ወደ አዕምሮዬ መጡ።
በሚቀጥለው ቀን ሳገኛት እያነበበች ነው። ስታየኝ ዘጋችው። republic ይላል። ፀሃፊው ፕሌቶ ነው። ከቦርሳዋ ውስጥ ወረቀት ወጥታ ሰጠችኝ። ዝም አልኳት። እኔ በደስታ ብዛት ተሰቃየሁ መሰለኝ፣ በደስታ ሙላት ሰከርኩ መሰለኝ ጋግርታም ሆንኩ። አስተማሪዎች ይለፈልፋሉ። እኔ የምሰማው ድምፅ የሷን ነው። እኔ የማልመው የሷን ከንፈር ነው። የሷን ፍቅር እራባለሁ። እሷን እሷን ይላል ልቤ። ደብዳቤውን ከፈትኩት...
“ለማላውቅህ እከሌ
ከማታውቀኝ ፍቅር “
 ይላል።
የማላውቅህ እከሌ (ስምህን እስካሁን አለማወቄ አይገርምም) ልብህ ወደ እኔ ተስቧል። ልታፈቅረኝ ትፈልጋለህ፣ ግን ባለትዳር በመሆኔ ትርቀኛለህ። ልትወደኝ ትፈልጋለህ ግን ባህሪዬ ግራ ያጋባህና ትሄዳለህ። መሄድ ከመምጣት ጋር የተሰናሰለ ፍቅር ነው። እምነት ነው በሁሉም ልብ ውስጥ የሚኖር የዘለ ዓለም መንፈስ። እነዚያ በጭቃ የሚጫወቱ ህፃኖች... እነዚያ በፍቅር የከነፉ ጥንዶች ልዩነታቸው አይታየኝም። ሁሉም በጅልነት ውስጥ ያሉ ልጆች ናቸው።  እውነቱን ንገሪኝ ካልከኝ ልቤ ላንተ ምንም አይነት ስሜት የለውም። ግን የቅርቤ ሰው እንድትሆን እፈልጋለሁ። የቅርብ ጓደኛ፣ የቅርብ... ሀዘኔን የማጋራህ... ትካዜዬን የምታዜምልኝ የፍቅር ወፍ እንድትሆን እፈልጋለሁ። በፍቅር  ከፈን ተገንዘን አንድ ላይ እንድንቀበር እፈልጋለሁ። ልወድህ፣ ላፈቅርህ እናፍቃለሁ...ትላንትን የመሰለ የትዝታ ዜማ እያዜምኩ በፍቅርህ ፍኖት፣ በአንተነትህ መርከብ መጓዝ እፈልጋለሁ። ላውቅህ፣ ልሳሳልህ እፈልጋለሁ። ልናፍቅህ እፈልጋለሁ። አብረን ብዙ ነገር እንድናይ እፈልጋለሁ። ላቅፍህ ፣ ሀዘንህን እንድታጋራኝ እፈልጋለሁ። ብዙ ነገር እፈልጋለሁ። ልቤ ላንተ አንዳችም ስሜት የለውም ማለቴ ቅር ያሰኝህ ይሆናል። ልቤ ለአንተ ስሜት ባይኖረው እንዴት ይሄን ሁሉ እንድትሆንልኝ እፈልግ ነበር። ግን አልፈልግህም። ደግሞ ታስፈልገኛለህ። እወድሃለሁ፣ ደግሞ እሸሽሃለሁ። እቀርብህና እርቅሃለሁ። እናፍቅህና ደግሞ ትዝ አትለኝም። ሁለት ተቃራኒ ስሜቶች አሉኝ። እንድትሆንልኝ የምፈልገውን አልፈልገውም። እስቲ አንድ ቀን ቤት ና እና እናውራ...”
ገረመኝ! እንዲህ መፃፍ ትችላለች እንዴ? እንዲህ ለእኔ ይሰማታል እንዴ?  ሁሉም ነገር ገረመኝ... ክላስ እንደጨረስን እስክትወጣ በር ላይ ጠበቅኳት። ስትወጣ አቀፍኳት። ገፈተረችኝ። ደግሜ አቀፍኳት።
“ምንድነው?”
“የፃፍሽልኝን ደብዳቤ አነበብኩት”
“አትሸወድ፤ እውነተኛ ስሜቴን አይደለም የፃፍኩልህ! ደብዳቤ መፃፍ ስለሚያስደስተኝ እንደ ልብ ወለድ ቁጠረው!”
“ምን?”
“አዎ”
“ይልቅ ቤት ብትመጣ ደስ ይለኛል ያልኩህ እውነት ነው”
“እሺ”
“መቼ ይሁን?”
“ነገ”
“እሺ”
ነገ አልደርስ አለኝ። እማራለሁ ግን ልቤ አብሮኝ የለም። ባሏን ለማየት ፈለግሁ... ቤቷ መሃል ቁጭ ብዬ ላወራት ፈለግሁ። ሁሉም ነገር ነገን የሚተልሙ ይመስላሉ። ቤት ስገባ ቄስ ባህታ “አለህ” አሉኝ።
ዝም አልኳቸው። ድሮ የሚናፍቀኝ ጨዋታቸው ሰለቸኝ። ልቤ መምታት ጀመረች። ነገሮች እየተቀያየሩ ነው። ምናልባት ወድጃታለሁ። ይሄ የፕሌቶ ፍቅር የምትለው ይመስለኛል። ለሌላ ነገር አስቢያት አላውቅም። ብቻ ከንፈሯን ብስም ደስ ይለኛል። እነዚያ ጥዑም ሀሳብ የሚያፈልቁ ከንፈሮቿን ብቀምሳቸው ደስ ይለኛል።
ስገላበጥ አነጋሁ። መቀጣጠሪያችን ፅጌሬዳ ሆቴል ነው። እዚያ ደረስኩ። አልመጣችም። ቡና አዘዝኩ። ጨረስኩት ፣ አልመጣችም። ብዙ ቆየች። ደገምኩ ቡና። ሰለስኩ፣ አልመጣችም። ከአንድ ሰዓት ቆይታ በዃላ መጣች። እንደ ድሮዋ አጭር ቀሚስ ለብሳለች። ሸሚዝ ከላይ አድርጋለች። ስስ ሸሚዝ። ጡት መያዣዋን የሚያሳይ ነው። ውበቷ ከሌላው ጊዜ በላይ አማረኝ። ጠይም ጨረቃ አልኩ በልቤ። ይህቺ እንስት ልቤን ወስዳዋለች፣ ይህቺ እንስት ቀልቤን ሰርቃኛለች። ሁለመናዬ ለእሷ መሰዋት የሚሆኑ ይመስላሉ።
ተነስተን ወደ መገናኛ ሄድን። እዚያ ነው ቤታቸው። ስገባ ትልቅ ቪላ ቤት ነው ቤቱ፤ ባለ ሶስት ፎቅ። ቁጭ አልኩኝ። ቡና አፈላችልኝ። ጥዑም ቡና። መጠጣት እንደምፈልግ ስትጠይቀኝ እምቢ አልኳት። የክላክስ ድምፅ ሰማሁ። ተነስታ ወጣች። ትንሽ እንደቆየች ከአንድ ድምፁ የማውቀው የሚመስል ሰውዬ ጋር ወደ ውስጥ ሲገቡ ሰማሁ። አየሁት! አፌ ቡጢ እንደሚውጡ ተከፈቱ። የእሱ ዐይኖች ፈጠጡ። ልነሳ ፈለግሁ፤ ጉልበቴን ግን ብርክ ያዘኝ። ላወራ ፈለግሁ፤ ምላሴ ተሳሰረብኝ።
“እርጉሙ ልጅ!”

Read 2113 times