Sunday, 30 May 2021 00:00

“ራዕይ የህፃናት መርጃ ድርጅት የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ላለባቸው ልጆች ተስፋ ሰንቋል”

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(2 votes)

   ወ/ሮ ፅጌ ጥበቡ የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ


           ከጓደኞቻቸው ጋር በቀን 1 ዶላር እየቆጠቡ ወደ አገር ቤት በመላክ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ልጆች ለመደገፍ ሲታትሩ ቆይተዋል። የዛሬዋ እንግዳችን ወ/ሮ ፅጌ ጥበቡ አሁን በግል የሚያደርጉትን ጥረት ወደ ተቋም አሳድገው በአሜሪካ የተመዘገበ “ራዕይ የህፃናት መርጃ ድርጅት (Raey Child Aid) የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት መስርተዋል፡፡ የሚረዷቸውንም ልጆች ቁጥር ከ17 ወደ 124 ከፍ አድርገዋል፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ለዚሁ ስራ ወደ አገር ቤት የመጡትን ወ/ሮ ፅጌ ጥበቡን በድርጅቱ አመሰራረት፣ በወደፊት ዕቅዳቸውና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግራቸዋለች።


                ራዕይ የህፃናት መርጃ ድርጀት መቼና እንዴት ነው የተመሰረተው?
ድርጅቱ ከመመስረቱ በፊት ሃሳብ ነበረ። ሀሳቡ የተጠነሰሰው እ.ኤ.አ በ2014 ዓ.ም ነው፡፡ ህጋዊ ድርጅት ሆኖ የተቋቋመው ደግሞ በ2016 ዓ.ም ነው፤ የተመሰረተውም በአሜሪካ ነው፡፡ ይህ ድርጅት ከቋቋሙ በፊት ከጓደኞቼ ጋር በግል ተነሳሽነት፣ ገንዘብ እያዋጣን እየላክን፣ በራስ አገዝ ሴቶች ድርጅት (ራሴድ) በኩል የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውን የተወሰኑ ልጆች መርዳት ጀመርን። ራስ አገዝ ሴቶች ድርጅት (ራሴድ) ከድህነት ወለል በታች ያሉ ሴቶችን በማገዝና የኢኮኖሚ አቅማቸውን በመገንባት ሥራ ላይ የሚሰራ ድርጅት ነው።
እኛ ውጪ ሆነን ገንዘብ በእነሱ በኩል ለተረጂዎች የምንልክበትና ጥምረት የፈጠርንበት ምክንያት እኔ ወደ አሜሪካ ከመሄዴ በፊት ለሰባት ዓመታት በራሴድ ውስጥ  እሰራ ስለነበር ነው፡፡ እዛም ከሄድኩ በኋላ በራሴድ ውስጥ የተፈጠረብኝ በጎ የማድረግ  ስሜትና ፍላጎት እዛም ከሄድኩ በኋላ እንዲቀጥል ውስጤ ስለገፋፋኝ ነው፣ ለነዚህ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ድጋፍ ለመስጠት የተነሳሳሁት፡ ገና ሀ ብለን ድጋፍ ስንጀምር ከጓደኞቼ ጋር ስድስት ሆነን በቀን አንድ ዶላር እየቆጠብን፣ እያንዳንዳችን በዓመት 365 ዶላር እያጠራቀምን በመላክ ነው ስራ የጀመርነው፡፡ ያው ገንዘብ ሲወጣና ሲገባ ተጠያቂነት ስለሚያስፈልግ የምንሰበስበውን ገንዘብ ወደ ባንክ እናስገባለን ከራሴድ ጋር በተፈራረምነው የመግባቢያ ሰነድ አማካኝነት ራሴድ ብሩን ያወጣና ለልጆቹ በሚያስፈልጋቸው መልኩ ይተላለፍ ነበር፡፡
የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸውን ልጆች መርጣችሁ ለመርዳት ያነሳሳችሁ ምንድን ነው?
በዚህ ጉዳይ ላይ ያሉ ልጆችን ለመርዳት ስንፈልግ ስራውን የጀመርነው ራሴድ ቢሮ አቅራቢያ ባለው ስብስቴ ነጋሲ ት/ቤት ውስጥ ያሉ የችግሩ ተጠቂዎችን በመደገፍ ነው፤ ምክንያታችን ደግሞ በበፊቱ (በኢህዴግ) መንግስት የእነዚህን ልጆች ችግር ማዕከል ያደረገ አካትቶ የሚባል ፕሮግራም ነበር፡፡ እነዚህን ልጆች ምን ነበር የሚያደርጉት? ከ1ኛ እስከ 3ኛ ክፍል ያስተምሩና መልሰው አንደኛ ክፍል ነበር የሚያስገቧቸው፡፡ ምክንያቱም ልጆቹ ልዩ ፍላጎታቸውን ያገናዘበ የሚማሩበት ቁሳቁስም ሆነ ድጋፍ ስላልነበራቸው፣ እነዚህ ልጆች ቢያንስ የሚያስፈልጋቸው ነገር ቢሟሉላቸው በቀለም ትምህርት ውጤታማ ባይሆኑ እንኳን ሙያ በማስተማር ራሳቸውን ማስቻል ይቻላል በሚል በስብስቴ ነጋሲ ት/ቤት ውስጥ ያሉ 17 ልጆች በመደገፍ ስራ ጀመርን፡፡
አጀማመራችሁ እንዴት ነበር? ለልጆቹ ምን በማድረግ ጀመራችሁ?
ሁለት አይነት ነገር አለ። አንደኛ አንድ ሥራ ሲጀመር ታቅዶ፣ታልሞ፣ የዳሰሳ ጥናት ተሰርቶና ፕሮጀክቱ ዲፋይን ተደርጎ ነው። ሁለተኛው ዘዴ የታሰበውን ነገር ቀጥታ በተግባር በመሞከር እንደ ፓይለት ፕሮጀክት ነው የጀመርነው። መጀመሪያ ያደረግነው ከውጪ አገር የሚመጡ በልዩ ፍላጎት ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች ልጆቹ ያሉበትን ሁኔታ እንዲገመግሙልን ነው ያደረግነው፡፡ በዚህ ረገድ ወ/ሮ ሙሉ የተባለች በልዩ ፍላጎት ላይ ማስተርሷን የሰራች ባለሙያ ለእረፍት ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ፣ ልጆቹ ያሉበትን ሁኔታ እንድትገመግም አድርገን ውጤቱን ከሷ ከሰማን በኋላ ነው ሙሉ በሙሉ ወደ ስራው የገባነው፡፡
ከግምገማው ምን ውጤት ተገኘ?
ባለሙያዋ ከግምገማዋና ልጆቿ ካሉበት ነባራዊ ሁኔታ ተነስታ የነገረችን ነገር፣ “እነዚህ ልጆች ከቀለም ትምህርቱ ይልቅ ይበልጥ የሚጠቅማቸው የሙያ ትምህርት ቢማሩ ነው፤ የቀለም ትምህርቱ ላይ ገፍተው ውጤታማ ይሆናሉ ለማለት ይከብዳል” የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም የእነዚህ ልጆች ዕድሜ ከ10-28 ዓመት ነው። እኛ ድጋፉን የጀመርነው ከልጅነታቸው ጀምሮ ቢሆን ኖሮ በቀለም ትምህርቱም ውጤት ሊያመጡ ይችሉ ነበር፡፡ ስለዚህ እነዚህ ልጆች የሙያ ስልጠናና ትምህርት ላይ ነው ስራ የጀመርነው። ወደ ሙያ ስልጠና ከመግባታችን በፊት ለእነዚህ ልጆች በቂ ምግብም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ምክንያቱም ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰብ የመጡ ናቸው። የሚማሩትም የመንግስት ት/ቤት ስለሆነ ት/ቤት እንዲመጡ ለነዚህ ልጆች ምግብ ማቅረብ ነበረብንና ቁርስ ማብላት ጀመርን። ይህን ጊዜ ብዙ ተማሪዎች መምጣት ጀመሩ፡፡ ከዚያ የት/ቤት የደንብ ልብስ፣ ስዕል የሚስሉባቸውን ቀለማትና መሰል ነገሮችን ማቅረብ ጀመርን፡፡ ከዚያ ቅድም በጠቀስኩልሽ የልዩ ፍላጎት ባለሙያዎችና በመምህራኑ ትብብር ጥናት አስጠንተን የሽመና ማሽን ደግሞ አስገባን። ብቻ ለአንድ ዓመት ያህል ልጆቹን ስናለማምድ፣ ባለሙያ ስናመጣ፣ ብዙ ወጪ ብናወጣም፣ አሁን ላይ ፈጣሪ ይመስገን አንገቴ ላይ የምታይውን የመሰለ ሸማ ሰርተው እስከ ማቅረብ ደርሰዋል፤ ውጤታማ ሆነናል። እኛ ይህን መንገድ ቀይሰናል፤ ሁሉንም መድረስ ግን አንችልም፤ በዚያው ልክ በመላው ኢትዮጵያ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆች ቁጥር በርካታ እንደሆነ እንገምታለን፡፡ ስለዚህ መንግስት በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ ት/ቤቶች ላሉ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ልጆች “አካትቶ” በሚባለው ፕሮግራም የሙያ ስልጠና እንዲኖር ማድረግ አለበት ብለን እናምናለን የእኛም ራዕይ ይህን ማየት ነው፡፡ ልጆቹ እንደ ፍላጎታቸው የሙያ ትምህርት ከወዲሁ ካገኙ፣ እንደ ማንኛውም ሰው ሰርተው የራሳቸውን ገቢ አግኝተው፣ ራሳቸውን ችለው መኖር ይችላሉ፡፡
ይህን ቃለ ምልልስ የምናደርገው ጦር ሀይሎች አካባቢ በሚገኘው “ትንቢተ ኤርሚያስ” በተሰኘው የህዝብ ት/ቤት ውስጥ በተዘጋጀው የምስጋናና የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ላይ ነው። እስኪ ፕሮግራሙ ስለተዘጋጀበት አላማ ይንገሩን?
እውነት ነው፤ በፊት ስብስቴ ነጋሲ በተባለ ት/ቤት በ17 ልጆች ነበር ስራ የጀመርነው፡፡ አሁን ላይ ድጋፋችንን ወደ 4 ት/ቤቶች አሳድገን፣ የምንደግፋቸውን ልጆች ቁጥርም 124 አድርሰናል። ገና ከዚያም በላይ አናሳድጋለን፤ ራዕያችን ሰፊ ነው፡፡ ይሄ ፕሮግራም የምስጋናና እውቅና መስጠት መርሃ ግብር ነው። እነዚህን ልጆች ዛሬ 25 የሸማ ስካርፎችን፣ የእጅ ጌጣጌጦችን የወረቀትና የስዕል ሥራዎችን ለእይታ አቅርበዋል። በኮምፒዩተር ስልጠናም ውጤታማ የሆኑ አሉ፡፡ ይህ ሁሉ ውጤትና ፍሬ በልጆቹ ላይ የታየው ያለድካም አይደለም። ልጆቹ ሽመና እንዲችሉ ኮምፒዩተር አጠቃላይ  እንዲያውቁና የእጅ፣ የአንገት ጌጣጌጥ፣ የወረቀት ቅርጽና ስዕል ስለው ዛሬ ለእይታ እንዲያበቁ ስልጠና በመስጠት፣ ለልጆቹ ፍቅርና እንክብካቤ በማድረግና በትዕግስት በማሰልጠን፣ ለስልጠናው የሚሆኑ ግበአቶችን በማሟላት በአይነትም በገንዘብም ድጋፍ ያደረጉ ግለሰቦችንና ተቋማትን፣ እንዲሁም በምንሰራባቸው ት/ቤቶች ያሉ ቅን መምህራንና ሰራተኞች በአጠቃላይ ለዚህ ውጤታማ ስራ የተባበሩትን ለማመስግን የተሰናዳ መርሃ ግብር ነው፡፡
ከአንድ ዶላር መቆጠብ ተነስታችሁ አሁን ተቋም አድርጋችሁታል። የአባላታችሁስ ቁጥር ምን ያህል ደረሰ?
በ2014 እና በ2015 ዓ.ም ስድስት ነበርን፤ የምናዋጣውም በቀን አንድ ዶላር፣ በወር 30 ዶላር፣ በዓመት ደግሞ 365 ዶላር ነበር። በ2016 ዓ.ም “ራዕይ የህጻናት መርጃ ድርጅት” (Raey Child AId) ብለን ተቋም አድርገን ስናስመዘግበው አወቃቀሩም ራሱን የቻለ ቁመና ያዘ፡፡ ፕሬዝዳንት፣ ም/ፕሬዝዳንት፣ የቦርድ አባላት፣ የገንዘብ ያዥና የግንኙነት ሰራተኞች ተሰየሙለት። የቦርድ አባላቱ 8 ሲሆኑ ሌሎች ከ26 በላይ የሆኑ አባላት በየወሩ አምስት ዶላር የሚከፍሉ ደጋፊዎች አሉን፡፡ ሌላው ይህን ስራ ስንጀምር የመጀመሪያውን ማሽን የገዛልን “T –linked” የተሰኘ አይቲ ኩባንያ ነው፡፡ የዚህ ኩባንያ ባለቤት አቶ ተረፈ በየአመቱ እንደየሁኔታው 1 ሺህ፣1ሺህ 200፣ 1 ሺህ 500 ዶላር እየለገሱን ይገኛሉ፡፡ ሌሎችም እኛን ለማገዝ ፍላጎት ያላቸው አሉ፡፡ በአጠቃላይ አሜሪካ ያሉ ኢትዮጵያውያን በጣም ደግና ሩህሩህ ናቸው፡፡ ዋናው የሚፈልጉት ነገር እነሱ የሚሰጡት ገንዘብ ትክክለኛ ተረጂዎች ዘንድ ደርሶ ማየት ነው። ይህን ማየት የሚፈልጉበት ምክንያት ግልጽ ነው። በእርዳታ ድርጅቶች ላይ የሚነገር ብዙ ጉድለት ስላለ ነው። ስለዚህ የሚሰጡት ገንዘብ ትክክለኛ ቦታው ከደረሰ ደስ እያላቸው ነው የሚለግሱት፡፡
እናንተ ገንዘቡ ትክክለኛው ቦታ ለመድረሱ ማሳያ መንገዳችሁ ምንድን ነው?
እኛ ግልጽ የሆነ ፕላትፎርም ነው የዘረጋነው፤ ገንዘብ በእጃችን አንነካም፤ ሰው ሲፈልግ ዌብሳይታችን አለ፤ በቀጥታ ወደ ባንኩ ያስገባል፡፡ ራሴድ ደግሞ በተፈራረምነው የመግባቢያ ሰነድ አማካኝነት የዓመቱን በጀት ሰርተው ይልኩልናል፡፡ ያንን በጀት ቦርዳችን ያጸድቃል። ገንዘቡን በባንክ ወደ ራሴድ እናስተላልፋለን፡፡ ራሴድ ደግሞ እንዴት አድርጎ ገንዘቡን እንደተጠቀመው ቼክ ኤንድ ባላንስ እናደርጋለን፡፡ ለምሳሌ ራሴድ አንድ ወንበር መግዛት ቢኖርበት ሶስት ፕሮፎርማ መሰብሰብ አለበት፤ ኦዲት ይደረጋል። ሰለዚህ አንዲት ሽርፍራፊ ሳንቲም በመሃል የትም አትሄድም፡፡ በዚህ መልኩ ነው ግልጽነትና ተጠያቂነት የምናረጋግጠው፡፡
አሁን ህጋዊ ሰውነት ያለው ደርጅት በአሜሪካ ፈጥራችኋል። በራሴድ በኩል የምታስተላልፉትን ገንዘብ በራሳችሁ ድርጅት ማዕከል ከፍታችሁ የመስራት ሀሳብ የላችሁም?
እውነት ነው፤ በፊት እዛም ተቋም ስለሌለንና ገንዘብ በየግላችን ከኪሳችን ስናወጣ ስለነበር በራሴድ በኩል ነበር ድጋፍ የምንልከው፡፡ በ2016 ድርጅቱን ካቋቋምነው በኋላ የገንዘብ አቅማችን ውስን ስለነበር ራዕይና ራሴድ ተፈራርመን በመግባቢያ ሰነዱ አማካኝነት ስንሰራ ቆይተናል። በቀጣይ አመት ግን የራሳችንን ማዕክል አዲስ አበባ እንከፍታለን የሚል እቅድ አለን፡፡ ማዕከሉ የአሜሪካው የኢትዮጵያ ቅርኝጫፍ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ምክንያቱም እዚህም አገር ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ልጆች ከቤተሰባቸው ወስደን ማኖር አይደለም አላማችን። በለመዱት የኑሮና የህይወት ከባቢ ውስጥ ሆነው አቅማችን በሰፋና በአደገ ቁጥር በመንግሰት ት/ቤት ያሉ ልዩ ድጋፍ የሚሹ ልጆች መደገፍ፣ ማስተማር፣ ማሰልጠን ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ነው፡፡ እኛም ከአሜሪካ እየመጣን ስልጠናና የህይወት ክህሎት ማሳደጊያ እንሰጣለን፡፡ የኮምፒዩተር ስልጠናም ሳይቀር እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ ይህን ገንዘብና እውቀት የምናፈሰው ልጆቹ ራሳቸውን እንደሚችሉ ስላረጋገጥን ነው። እናንተም ሰርተው ለዛሬ እይታ ያቀረቡትን አይታችሁ እንደሚችሉ አይታችኋል፤ ግን መታገዝ፣መደገፍና ትኩረት ማግኘት አለባቸው፡፡
በአራቱ ት/ቤቶች ላሉ 124 ልጆች ይህን ሁሉ ስራ ስትሰሩ ዓመታዊ በጀታችሁ ምን ያህል ነው?
ዓመታዊ በጀት ይሄ ነው  የሚባል አይደለም፤ ገንዘቡ የተለያየ ነው፡፡ እኔ በቅርቡ ከአሜሪካ ከመምጣቴ በፊት 384 ሺህ የኢትዮጵያ ብር አስተላልፌ ነው የመጣሁት፡፡ እንዳልኩሽ በግላችን ተነስተን ድርጅት እስክናቋቁም ድረስ ሰባት ዓመት ሰርተናል፤ ስንጀምር 500 ዶላር ከዚያም 1ሺህ ዶላር እየላክን ነው እዚህ የደረስነው። እንደምናገኘውና እንደ ለጋሾቻችን ሁኔታ የምንልከው ገንዘብ ይለያያል፡፡ በእርግጥ ሁሉም የቦርድ አባላት ገንዘብ የማዋጣት ግዴታ አለባቸው፤ ሁላችንም እናዋጣለን። በዚህ ሰባት ዓመታት ውስጥ አንድም የሚከፈለው የራዕይ የቦርድ አባል ፕሬዚዳንትም ሆነ ም/ፕሬዝዳንት የለም፡ ሁሉም እያዋጣ ለመንፈስ እርካታውና ለበጎነቱ ነው የሚሰራው። ሁሉም አገሩን ወገኑን የሚወድና የሚያስታውስ ነው ዲያስፖራው አንዳንዴ መንግስት እንዲሰራልን የምንፈልገውን ራሳችን የመስራት አቅም እስካለን ድረስ ሰርተን መደገፍ እንፈልጋለን፡፡ ምክንያም ሁሉም ነገር በመንግስት ብቻ ተሰርቶ ችግር ይደፈናል፤ ተብሎ አይታሰብም። ሁሉም በየፊናው የአቅሙንና የፍላጎቱን ድጋፍ ቢያደርግ የሀገራችን ችግር ይፈታል ብለን እናምናለን፡፡
ከትምህርት ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?
ከትምህርት ሚኒስቴር ሰዎች ጋር ተገናኝተናል፡፡ በጣም ደስ የሚል ምላሽ ነው የሰጡን፡፡ ወደፊትም ይህን ፕሮግራም በትምህርት ፕሮግራሙ ውስጥ ለማካተት ቃል ገብተውልናል፡፡ ይሄ ደግሞ ይበልጥ ያበረታታናል፡፡ እኛም እነዚህን ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ልጆች እናቶቻቸውን ከመሳቀቅ አውጥተን ልጆቻቸው እንደ ማንኛውም ልጅ አቅምና ችሎታ እንዳላቸው ስናይ፣ የእናቶችና የወላጆች ደስታ ዛሬ እናንተም በዚህ ተገኝታችሁ ተመልክታችኋል፡፡ እኛ ራዕያችን በመላው አገሪቱ ባሉ ሁለም ት/ቤቶች ልዩ ፍላጎቶች ያላቸው ልጆች ትኩረት ተሰጥቷቸው፣ የሙያና የህይወት ክህሎት ስልጠና አግኝተው ራሳቸውን እንዲችሉ ማድረግ ነው ይህን ጉዞ በጥሩ ሁኔታ ጀምረነዋል፤ ብዙ ውጤት እናመጣለን ብለን እናምናለን። ሁላችንም በየአቅማችን ሀገራችንን መንግስታችንንና ወገናችንን በመደገፍ ክፍቶቻችንን ሙሉ በሙሉ መድፈን ባንችል እንኳን ማጥበብ  እንችላለን እላለሁ።

Read 2366 times