Saturday, 29 May 2021 12:18

በአፍሪካ የኮቪድ ሙስና ከወረርሽኙ በላይ አሳሳቢ ሆኗል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

        ዙማ የተከሰሱበትን የ5 ቢ. ዶላር ሙስና አልፈጸምኩም አሉ


            የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ወደ 4.8 ሚሊዮን በደረሰባትና የሟቾች ቁጥርም ወደ 129 ሺህ በተጠጋባት አፍሪካ በሚገኙ በርካታ አገራት ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋታቸውንና በአንዳንድ አገራት ሙስናው ከወረርሽኙ በላይ አሳሳቢ ሆኗል መባሉን አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
በብዙ የአፍሪካ አገራት ወረርሽኙን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚመደብን በጀትና የእርዳታ ገንዘብ ከመዝረፍ አንስቶ የተለያዩ ከፍተኛ ወንጀሎች መስፋፋታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ መሰል ሙስናዎች ከተስፋፉባቸው አገራት መካከልም ደቡብ አፍሪካ፣ ማላዊ፣ ኬንያና ኡጋንዳ እንደሚገኙበት ጠቁሟል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ እጅግ ከፍተኛ ሙስና የተስፋፋበት ቀዳሚዋ አገር እንደሆነች በሚነገርላት ደቡብ አፍሪካ፤ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2020 ብቻ 418 ሙስናዎች መፈጸማቸው ሪፖርት መደረጉን ኮራፕሽን ዎች የተባለ የጸረ ሙስና ተቋም ይፋ ማድረጉን አመልክቷል፡፡
በማላዊ ባለፈው ወር ለኮቪድ የተመደበን 1.3 ሚሊዮን ዶላር መዝብረዋል የተባሉ 64 የስራ ሃላፊዎችና የመንግስት ባለስልጣናት መታሰራቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ በኬንያ የመንግስት ባለስልጣናትና የመድሃኒት ቁሳቁስ አምራች ኩባንያ ባለሃብቶች በመመሳጠር ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ መዝረፋቸው እንደተደረሰበት አመልክቷል፡፡
በናይጀሪያ የጤና ሚኒስቴር የእቃ ግዢ ክፍል ከነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር ለሃሰተኛ የፊት ጭንብል ግዢ 96 ሺህ ዶላር ያህል ያላግባብ ማባከኑ እንደተደረሰበት የጠቆመው ዘገባው፣ በኡጋንዳ አራት የመንግስት ባለስልጣናት በከፍተኛ ሙስና ተጠርጥረው መታሰራቸውንም አስታውሷል፡፡
በሌላ የአፍሪካ የሙስና ዜና ደግሞ፣ ከፍተኛ የሙስናና የተለያዩ የማጭበርበር ወንጀሎችን ፈጽመዋል ተብለው 18 ክሶች የተመሰረተባቸው የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ መሪ ጃኮብ ዙማ፣ ባለፈው ረቡዕ በከፍተኛ ሙስና ክስ ፍርድ ቤት ቀርበው ወንጀሉን አልፈጸምኩም ሲሉ መከራከራቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
አገሪቱን እ.ኤ.አ ከ2009 እስከ 2018 በፕሬዚዳንትነት የመሩት ዙማ ከተመሰረቱባቸው ከፍተኛ የወንጀል ክሶች መካከል ከአንድ የጦር መሳሪያዎች አምራች ኩባንያ ጋር ከ20 አመታት በፊት በጥቅም በመተሳሰር የፈጸሙት 5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የግዢ ስምምነት እንደሚገኝበት ያስታወሰው ዘገባው፣ ዙማ ግን ረቡዕ ዕለት በፒተርማርቲዝበርግ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተገኝተው በሰጡት ምላሽ ወንጀሉን አልፈጸምኩም ሲሉ መከራከራቸውን ገልጧል፡፡
የ79 አመቱ ዙማ የፍርድ ሂደት ለመጪው ሃምሌ 19 መቀጠሩን የጠቆመው ዘገባው፣ ግለሰቡ በተከሰሱባቸው ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ 25 አመታት በሚደርስ እስር ሊቀጡ እንደሚችሉ መነገሩንም አመልክቷል፡፡

Read 1763 times