Saturday, 22 May 2021 15:14

የ”ጥያቄዎቹ” - የሃሳብ ሰበዞች የምጡቅ አዕምሮ ባለቤት ሻሎም ደሳለኝ

Written by  ሳሙኤል በለጠ (ባማ)
Rate this item
(3 votes)

      “ጥያቄ አብራክ ነው፤ መፍትሄ የሚወልድ”
                            
              መቼም ይህች ዓለም ፈጽማ ”እፎይ ጨረስኩ!“ ያለችው አንድም ነገር የለም! ያልተፈጸመ ነገር ካለ ሁሌም የሚጀመር ነገር አለ፤ መጀመሪያ ምሳችን ጥያቄ ነው። በእርግጥ ጥያቄ  መልስ ዓልባ ሊሆን ይችላል። ግን አሮጌ የዘመን ብራና ታጥፎ ሌላ አዲስ የዘመን ብራና ሲዘረጋ ጥያቄው መልስ ያገኛል። ገጣሚው እንዳለው፤ አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤ ስትገቡ ሌላ በር ይጠብቃችኋል። ጥያቄ ሌላ ጥያቄ ይወልዳል። በጥያቄው መልስ መፍትሄ ይፈተልበታል፤ መፍትሄው የችግር እንቅርት በአንገቱ ማንጠልጠሉ አይቀርም፤ ችግሩ በድጋሚ ጥያቄ ያነሳል። እንዲህ እንዲህ እያለ ዘመን፤ጥያቄ እንዲሁም መፍትሄ በአንድ ተሿርበው፤ የነተበ ቀን ሌላ አዲስ ቀን እየለበሰ፤ ሰውን ሞት የሚሉት የመቃብር አፍ እየበላው፤ ትውልድ በሌላ ትውልድ እየተተካ እዚህ ደርሰናል።
ሰው ያሰበውን ሃሳብ የሚንዱ፤ሰውየውም በተናደው ሃሳቡ ብዙ ሳይቆዝም፤ ሃሳብ ለመካብ ሌላ የሃሳብ ዲንጋ የሚሰጡ መጽሐፎች በገበያ ላይ ለዓይን እንኳ ብዙም አይታዩም፤በተለይ ባለፉት ጥቂት ወራት አዲስ የፍልስፍና መጽሐፍ በገበያው አልነበረም ማለት ይቀላል። ከሰሞኑ የሕትመት ብርሃን ያየው የፍሬው ማሩፍ “ጥያቄዎቹ” የተሰኘው መጽሐፍ በገበያ ላይ መዋሉ ለተደራሲው ዘርፈ ብዙ ጥቅም ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ እኔም ገበያ ላይ ሳየው በፍጥነት ነበር የገዛሁት፡፡ መጽሐፉ በሦስት ክፍሎች በአንድ መቶ ዘጠና አንድ ገጾች ተቀንብቧል። የሽፋን ምሥሉ በሠዐሊ ዮናስ ሞገስ ሳይወሳሰብ፣ ለተደራሲ በሚማርክና ትርጉም በሚሰጥ መልኩ መሰራቱ አንብቡኝ ብሎ በዝምታ እንዲጣራ አድርጎታል፡፡ በሦስቱም ክፍሎች ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ለፈላስፎችና ለአሳቢያን (Re-Thinkers) አልፈታ ያሉ ሦስት ቁጥርጥሮችን ሰውን፣ ፈጣሪንና ሰይጣንን ከፈላስፎች፣ ከጥናቶች፣ ከሃይማኖት ድርሳናት ሃሳብ እየተዋሰ የራሱንም ሃሳብ እያከለ፤ሌላ ‘ጥያቄ’ መልሶ እያጫረብን በሚስብ መልኩ ይዳስስልናል፡፡  
“ጥያቄ?”
የዓለም ስልጣኔ የተገነባው ነፍሳቸውን ከልባቸው በጥያቄ አሟግተው፤ ከውስጠ-ሕሊናቸው ለችግር ሐቃዊ መፍትሄ ባመነጩ ሰዎች ነው። መነሻው ግን ጥያቄ ነው። ቶማስ ኤዲሰን ዓለም ለምን ጨለማ ሆነች? ብሎ በመጠየቁ አምፖል ተሰራ፤ ኤለን መስክ ለምን በኤሌክትሪክ ሃይል የሚሰራ መኪና አልተሰራም? ብሎ ሲጠይቅ፣ በኤሌክትሪክ ሃይል የሚሰራ መኪና ተሰራ፤ ጥያቄ አብራክ ነው። መፍትሄን የሚወልድ ጥያቄ እንጂ ሌላ ነገር ለችግር መፍትሄ አይሆንም፤ ነፍስ ከሥጋ ከተለየ ሥጋ እንደሚበድን፤ ጥያቄም በራሱ አዕምሮን እንደ ወርቅ በእሳት ፈትኖ ለችግር መፍትሄ ካልሆነ፤ ‘ጥያቄው’ በድን ይሆናል። ለመሆኑ የችግርና የችጋር ጥቁር አሞራ መንቆሩን ቁልቁል ዘቅዝቆ ጫጩት አቅማችንን ሊጠቀጥቀው በሠማያችን አንዣቦ፥ ስልጣኔ እንደ ምጽዐት ቀን ‘ርቆን፣ ለምንድነው የማንጠይቀው?
አመክንዮ (1)
ሥርዓተ-መንግስታቶቻችን በፊትም አሁንም ‘ሰውነትን’ ባለማስቀደማቸው በሚፈጥረው ውጥንቅጥ ሰበብ ሕዝብ በፍርሃት ጥርስ ሲላመጥ፣ሰላም ለዓይኑ እንደ ቅድቡ ሲርቀው፣ የብሔርተኝነት እሳቤ የወለዳቸውን ሕይወት ዓልቦ ሐሳቦች እንደ ጡብ እየጠፈጠፈ፤ አንሶ በሥጋት እየኖረ፣ ሕዝብ ከልዕለ-ተፈጥሮ ጋር በጥያቄ ለመቆራኘት እንዴት ይቻለዋል?
አመክንዮ (2)
የሐይማኖት አባቶች እውነት በርዷቸው፤ ከሐሰተኛ ትምህርት ጋር ተቃቅፈው፤ ሕዝብን አሜን! አሜን! እንጂ ለምን ለምን? አትበል እያሉት፣ እንዴት ነው የእምነቱ ተከታይ የሆኑት ምዕመናን ጠያቂ የሚሆኑት? ምን እውቀት አለና? ምን እምነት ይኑር? ሁሌ ሳስታውሰው የሚያስፈግገኝ አንድ ቀልድ አለ፤ ቄሱ የዲያቆኑን ሚስት ያማግጡ ኖሯል። በዚህም ሰበብ ቄስና ዲያቆን እልህ ተጋብተዋል። ታዲያ አንድ ዕለት ሥርዓተ-ቅዳሴ እየከወኑ ጽጌ ብሩ (የዲያቆኑ ሚስት) አለፍ ትላለች፤ ይህን ጊዜ....
ቄሱ :-”ጽጌ ብሩ ያዩሽ ሁሉ ደነበሩ!” ይላሉ
ዲያቆኑም:- “መምሩ ያዩትን ሁሉ አይምሩ” ብሎ ተቀበላቸው
ቄሱ በንዴት:- “ምናባህ ታመጣለህ፣ ታራለህ፣ ትደብናለህ፣ ከሥራህም ትባረራለህ..." ሲሉ፤ መቅደስ ውስጥ የነበሩት አስቀዳሽ ምዕመናን አንድ ላይ አሜን! አቤቱ ይቅር በለን! አሉ ይባላል። ለምን? ያላለ ሕዝብ እንደ ሲሲፈስ መግፋት የማይገባውን የመከራ ዲንጋይ እየገፋ አሜን! አሜን! እያለ ጣዕም ያጣ ሕይወት ይኖራል። የሐይማኖት አባቶችም ለምዕመኑ ለነፍስ የሚሆኑ፤ ጣፋጭ መንፈሳዊ ፍሬዎችን መመገብ ሲጠበቅባቸው፤ የምዕመናኑን ጥያቄ በአግባቡ ማስተናገድ ሲኖርባቸው፤ ግን አማኙን ያለማሕተብ በክር ብቻ እራቁቱን አስቀሩት፤ መገን እንጂ ሌላ ምን ይባላል? “በጥያቄዎቹ” ድርሳን ላይም በገጽ አንድ መቶ ሰማኒያ ሦስት ላይ ይህ ሃሳብ በስፋት ተዳስሷል።
አመክንዮ (3)
የዩኒቨርሲቲ መምህራን (ምሁራን) ስለ ሃሳብ ነጸነት፣ ስለ መጠየቅ ጥቅም፤ ለተማሪዎቻቸው አላስተማሯቸውም፤ ተማሪዎቹም የቱ እውነት? ከማለት ይልቅ ይህ ወገንህ አይደለም፤ የሚለው የውሸት ትርክት ከደም ሥራቸው ይቀርባቸዋል። ‘የሆነ ቦታ ላይ ያለው የትምህርት ተቋም ውስጥ ረብሻ ተነሳ’ የሚል ወሬ የጆሯችን ነፍስ ደጋግማ ሰምታለች፥ በዚህም ሰበብ ተፈጥሮ በነጻ የሰጠቻቸውን የመጠየቅና የመመራመር መብት ወደ ጎን ትተው፤ ‘ለአለማወቅ’ ቅኝ ለመገዛት ሲጓዙ እናያለን፤ በዚህ ድርሳንም በገጽ አስር ላይ “መማር እንዲህ ከሆነ ቢቀርስ” በሚል ርዕስ ሥር፣ የትምህርት ሥርዓታችን የገጠመውን ሳንካ ገልጦ፤ መፍትሄ ጠቁሞ ገጹን ወደ ሌላ ሃሳብ አጥፏል። ወደ የትም ጉዞ ከመጀመራችን በፊት የትኛው መንገድ የእውነትና የእውቀት መንገድ ነው? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። “የዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና የትምህርት ክፍል መምህር ናቸው። ለተማሪዎቻቸው የቤት ሥራ ሰጡ፤ የቤት ሥራው ክፍል ውስጥ ያለው አንድ ‘ነጠላ ወንበር’ እንደሌለ በአመክንዮ ማስረዳት ነበር፤ በማግስቱ የቤት ሥራው ሲታረም፥ ብዙ ተማሪዎች ‘ወንበሩ’ ስላለመኖሩ የሚያስረዳ ብዙ ገጽ ጽፈው መጥተዋል፤ አንድ ተማሪ ግን አንድ መስመር ነበር የጻፈው፤ መልስም የሆነው ይህ መስመር ነው። መስመሩም “የቱ ወንበር?” ይላል። ‘ጥሩ ጥያቄ ሌላ ጥያቄ ቢፈጥርም ለጥያቄው መልስ ይሆናል’ መምህራን ተማሪዎቻቸውን ‘የቱ እውነት?’ ብለው እንዲጠይቁ ካላደረጓቸው፤ የቀጣይ ትውልድን ነፍስ የሚቀጣ የእሳት አለንጋ ትተን ማለፋችን አይቀርም!
(4 ‘አለመሰልጠናችን’)
ክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል “ስልጣኔ ምንድናት?” በሚለው ድርሳናቸው፣ ስልጣኔን በሁለት ይከፍሉታል። የመጀመሪያው ‘ሰው’ ከግብረገብነቱ አንጻር ስልጣኔው ይፈከርለታል። ይህም ሲባል በትህትናው፣በርሕራሄው፣መንፈሰ ሰፊ ልብ ከያዘ ሰለጠነ እንላለን (ገጽ ሃያ) በአንጻሩ ክፉ፣ትዕቢተኛ፣ጨካኝ ሲሆን ደግሞ ያልሰለጠነ ነው እንላለን፤ ሌላው የስልጣኔ ዐይነት ግዙፉ ብለው ይጠሩታል። ይህ ሲባል “በአለባበሱ፣ በአመጋገቡ፣ በኪነ- ጥበብ፣ በኪነ ሕንጻ ማህበረሰብ ሲሰለጥን እንደ ስልጣኔ ማስረጃ ይሆናሉ” ይላሉ። አንድ ጸሐፊ በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ሞግተው ነበር፤ ክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል “ጃፓን እንደምን ሰለጠነች?” ብለው ከሚጽፉልን ይልቅ “ኢትዮጵያ ለምን አልሰለጠነችም?” ብለው ቢጽፉልን ለስልጣኔ ጉዟችን ማመላከቻ ካርታ ይሆነን ነበር ይላሉ። ልክ ናቸው ከለምን? የተነሳ ትውልድ፣ የልቡናውን መቅለዝ “በጥያቄ” ዘይት ከሞላ በዳልቻ መደብ የመጽሐፉ ሽፋን ላይ እንደተሳለው የመጨረሻ ፋኖስ ለጨለማው ዘመኑ ብርሃን መሆን ባይችል፣ ለቀጣዩ ዘመን የተስፋ ብርሃን መርጨቱ አይቀርም!
“ሰው!”
ሰው ፍጠር (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ) አወዛጋቢው ፈላስፋ ዲዮጋን በቀን ፋኖስ ይዞ ሲንከራተት ሰዎች አይተው ምን ጠፋህ? ቢሉት ሰው እየፈለግሁ ነው። ብሎ መለሰላቸው ግን ሰው ምንድነው? ሰው የሚባለው ፍጡር ቅዠት እንዳልሆነ ምን ተጨባጭ ማስረጃ አለን? የሚሉም አሳቢያን ተነስተው ነበር፤ ቢሆንም አለሁ የለሁም ብሎ መጠየቁ በራሱ “እንዳለን” ማስረጃዎች ይሆናል፥ የሚሉ አሳቢያንም አሉ፤ በእርግጥ ይህንን ውትብትብ ጥያቄ ለመመለስ ፈጣሪ መሆን ይጠበቅብናል ይመስለኛል። ቢሆንም የሰውን ምንነትና አፈጣጠር ከሐይማኖት ድርሳናት፣ አቧራ ከጠገቡ ከፍልስፍና መዛግብት አቧራውን እፍ እያልን ከሆነ ንጻሬ መተንተን እንችላለን፡፡ “ጥያቄዎቹ” ላይም ፍሬው ከገጽ 18-39 ድረስ “ሰው እንዴት እና ከምን መጣ?” የሚለውን ጥያቄ ከተፈጣሪነት ጽንሰ ሃሳብ (Creationism Theory) አንጻር ቅዱስ ቁርዐንንና ቅዱስ መጽሐፍን እያጣቀሰ፣ ከዝግመተ ለውጥ (Evolution Theory) አንጻር፣ ብሎም ከላምራክ ጽንሰ ሃሳብ አንጻር (Theory of lamarck) “ሰው እንዴት ተፈጠረ?” ለሚለው ጥያቄ የመልስ ሕብስት ጋግሮልናል። ነፍሳችን የሚጠግባትን መርጦ መመገብ የኛ ፋንታ ነው። እንደው ሃሳብ ወዳዶች ከሆንንና ረቂቅ ነገሮችን የመመርመር ፍላጎቱ ላለን ሰዎችም ስለ ነባቢት፣ልባዊት፣ሕያዊት ነፍስም ጥልቅ ትንታኔ አስቀምጦልናል (በገጽ-40-45)፡፡ ፍሬው ጥልቅ ንባብና አረዳድ አለው፤ በአጸደ-አዕምሯችን የሚመላለሱብን፣ፈራ ተባ እያልን ችላ ያልናቸውንም ሃሳቦች አልማራቸውም፤ ሞትን፣ በተለይ ራስን ስለ ማጥፋት በዚህ ጉዳይ የዓለምን በእጅጉ ተጨንቃለች፤ ብዙ ሕዝብም እንደ ቅጠል እያረገፈ ነው።  የወለፈንዲ ፍልስፍና አቀንቃኙ አልበርት ካምዩ ስለ ራስ ማጥፋት እንዲህ ይላል፡- “በመጨረሻም ሰው ራሱን ከመግደል፥ በበለጠ ለመኖር ጽናትን ሊያዳብር ይገባል።” ፍሬው ፈላስፋውና የሙዚቃ ባለሙያው ኤልያስ መልካ ስለ ራስ ማጥፋት አሉታዊነት የገጠማቸውን ግጥሞች በጥቂቱ አብራርቶልናል። (ገጽ-61)..አለፍ ሲልም የሰውን ተፈጥሮ ምንነት ይዳስሳል።  
ፍጥረት ከመፈጠሩ በፊት ያለው የወደኋላ ዘለዓለም እና የወደፊት ዘላለም በሰው የንቃተ ሕሊና ደረጃ ምን ሊባል ይችላል? ምንም ባለመባሉ ሰበብ አሁንም ድረስ ስለ የፈጣሪ ኅልዮት ብዙ ያጨቃጭቀናል። ታዲያ ፍሬው ከተለያየ አንጻር በምልከታውም በሌላም ሃሳብም ላቅ አድርጎ አንጽሮልናል። ሰይጣንም ሳይጎረብጠኝ ምንና ከየት እንደተነሳ በቅጡ አወቅሁ፡፡ “ጥያቄዎቹ” ወርቅ አዕምሮዬን በሃሳብ እፈትናለሁ የሚል ሁሉ ሊያነበውና ራሱን በሃሳብ የቱ ጋ ነኝ ብሎ ሊፈትሽበት የሚገባ መጽሐፍ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻው: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 536 times