Print this page
Saturday, 22 May 2021 14:25

የርባገረዱ ፈላስፋ

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(1 Vote)

    "የተወልደን ህይወት ስንመለከት፤ በህይወት የመኖርን ዓላማ ዳግም ለመጠየቅና እንደ ሰው ምን ልናደርግ እንደሚገባ ለማሰብ እንገደዳለን፡፡ ዕውቀትን ፍለጋም  የህይወት ግብ አድርገን ለመመልከት እንደፋፈራለን፡፡ ዕውቀት ለምን ዓላማ? የሚል ጥያቄም አንስተን መልስ ለማግኘት እንጓጓለን፡፡--"
       
           ጠብታ
‹‹ኢትዮጵያዊው ሳይንቲስት›› (የምድራችን ጀግና)፣ ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ታትሞ ለንባብ የበቃውን የጓደኛዬ የዘነበ ወላን መጽሐፍ ያነበብኩት በቅርቡ ነው፡፡ ዘነበ ወላ ‹‹በፒራሚድ ቅርጽ ነው የጻፍኩት›› ያለውን፤ የተወልደ ብርሃን የህይወት ታሪክ የቀረበበትን መጽሐፍ ሳነብብ ብዙ ሐሳብ እያነሳሁ ጥያለሁ፡፡ መጽሐፉን ጨርሼ አስተያየት ለመጻፍ ስሞክር የገጠመኝን  ችግር ለመናገር ከሚቻለው በላይ የስሜትና የሐሳብ ሸክም መያዝ ነው፡፡ በህሊናዬ ምህዳር የሐሳብ ግርግር ተፈጠረብኝ፡፡
እንዲህ የሚርመሰመሰውን ሐሳብ እና ስሜት፤ ጩኸት እና ግርግር ‹‹ባለህበት እርጋ›› ለማለት አልቻልኩም፡፡ ከዕውቀት የሚመነጭ ሥልጣን የሌለው ሰው፤የዘነበን መፅሐ ፍ በማንበብ የሚፈጠርበትን፤ ሦስት እና አራት ክፍለ ጦር የሚሆን ሐሳብ እና ስሜት ማስተዳደር አይቻለውም፡፡
ይህች ጽሑፍ ጠብታ ሆና፤ የተወልደ ህይወት ውቂያኖስ ሆኖ ተቸግረናል፡፡ ይህን ችግር ለማስወገድ ወይም የሐሳብ ትርምሱን ለማስወገድ አንድ መላ አለ፡፡ መላው፤ ውቂያኖስን የምትውጥ አንዲት ጠብታ መፍጠር ነው፡፡ ይህችም ጠብታ ‹‹ማየት ግንኙነትን ማየት ነው›› የምትል ናት፡፡
‹‹ማየት ግንኙነትን ማየት ነው ይባላል፡፡›› እውነት ነው፡፡ ግንኙነትን ማየት የማይችል ሰው፤ የሚያየውን ነገር በደንብ ለመረዳት አይችልም፡፡ እና ዘነበ  ‹‹ኢትዮጵያዊው ሳይንቲስት›› (የምድራችን ጀግና) ብሎ የሰየመውን መጽሐፍ ሳነብ የተረዳሁት አንድ ነገር፤ ተወልደ ብርሃን የሚያየውን ነገር በነጠላው ዝም ብሎ የሚያይ ሰው አለመሆኑን ነው፡፡ እንዲያውም ዓይኑ የሚያየው ግንኙነትን ነው፡፡ ግንኙነትን የሚያይ በመሆኑም የሚያየውን ነገር በደንብ ለመረዳት ይችላል፡፡ ተወልደ ብርሃን የሚነካው ነገር ሁሉ ፍሬ የሚያፈራለት ለዚህ ይሆናል፡፡
መነሻ
ዘነበ በዚህ መጽሐፍ የሚያሳየን የአንድን ሰው ህይወት ነው፡፡ ግን ‹‹የአንድ ሰው የህይወት ታሪክ ነው›› ማለት እውነቱን ይሸፍጣል ይመስለኛል፡፡ ግን ምን ማድረግ ይቻላል፡፡ መጽሐፉ የዶ/ር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሄርን የህይወት ጉዞ የሚያሳይ መጽሐፍ መሆኑን መቀየር አይቻልም፡፡
ሆኖም የተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር የህይወት ታሪክ የሚነበብበት ይህ መጽሐፍ፤ የመላው ዓለም፣ የሦስተኛው ዓለም፣ የአፍሪካ፣ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ከግለሰብ ታሪክ ጋር የተዳቀሉበት መዝገብ ነው፡፡ እንደ ተወልደ ብርሃን ያለ ህይወት፤ የብዙ ሰዎችን ህይወት የሚነካ ህይወት በመሆኑ፤ የአንድ ግለሰብ ታሪክ አድርጎ ማየት አስቸጋሪ ነው፡፡ አንድ ሰው የሚኖርበትን ዓለም፣ የሚኖርበትን አህጉር፣ የሚኖርበትን ሐገር እና የሚኖርበትን አካባቢ ሲነካ፤ ሰውዬውን እንደ አንድ ሰው ማየት አስቸጋሪ ነው፡፡ ዘነበም ‹‹ተወልደ ብዙ ሰው ነው›› ይለዋል፡፡
ተወልደ ብርሃን እንደ ስሙ ነው፡፡ ብርሃኑ በበርካታ የህይወት መስኮች ላይ አርፎ ይታያል፡፡ ተወልደ ባረፈበት መስክ ሁሉ ብርሃን ይፈነጥቃል፡፡ ለውጥ ያመጣል። ልክ እንደ ግሪካዊቷ የአፈ ታሪክ ገፀ ባህርይ እንደ ፐርሲፎኒ፤ የነካው ወይም የረገጠው ቦታ ሁሉ በአበባ ይደምቃል፡፡
ልደት
ዘነበ ስለ ተወልደ ብርሃን ልደት ሲተርክልን እንዲህ ይላል፤
‹‹እኔ ወደዚህች ምድር በመጣሁበት ዘመን ዓለማችን በጦርነት እየታመሰች ነበር፡፡ ይህንን መዘዝ ለዓለማችን ያመጣው ግለሰብ አዶልፍ ሂትለር ይባላል፡፡ የዚህ ሰው ባልንጀራም ቤኒቶ ሙሶሊኒ፤ በአገራችን ነጻነት ላይ ክተት አወጀ፡፡ በዘመኑ የነበረው መንግስታችን ፈረሰ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም አጼ ኃይለ ሥላሴ ወደ እንግሊዝ አገር ተሰደዱ። አቅም ያለው በዱር በገደሉ ተሰዶ የሽምቅ ውጊያ እያካሄደ ነበር፡፡ አቅመ ደካማዎቹ ደግሞ በጾምና በፀሎት፤ አምላክ ወገኖቻቸውን እንዲረዳላቸው ይማጸኑ ነበር። ይህ መዓት በፕላኔታችን ላይ ሲዘንብ እልፍ አዕላፎች ለሕልፈት ተዳረጉ። የዚያኑ ያህል ደግሞ በመጪው ዘመን ኖረው የበኩላቸውን ለማድረግ ወይም የዕጣ ፈንታቸውን ለመኖር ከተወለዱት አያሌ ሕጻናት መካከል አንዱ እኔ ሆንኩኝ፡፡;
ተወልደ በአባት እና በእናቱ፤ በአክስቱና በአያቱ እጅ ያደገ፤ እንደ ልጅ በገጠር ያደገ፤ እንደ ተማሪ አስኳላ የገባ፤ እንደ እረኛ የኖረ እንደ ሐይማኖት በኦርቶዶክስ ክርስትና መደብ የበቀለ፤ በአያቱ ት/ቤት የተማረ፤ ድህነትን የታገለ፤ በዚህ ጉዞ ዓይኑን ከፍቶ የመመልከት ጸጋን የታደለ የህይወት ተማሪ ነው፡፡
ዘነበ ወላ፤ ‹‹የዶክተር ተወልደ ብርሃን ታሪክን ሳጠና አያሌ ‹ቤተ መቅደስ› የሆኑት ሰዎች በሕይወቱ ተከስተዋል፡፡ የመጀመሪያዎቹ አቦይ ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ዮሐንስ፤ እናቱ (ወለላይ) ወይዘሮ መዓዛ ተወልደ መድህን፤ አክስቱ ወይዘሮ ትበርህ ተወልደ መድህን፤ መምህር ሐብቴ ዘርኤ፤ ሚስተር ማርሻል፤ ሚስስ ማርሻል፤ መምህር ነገሬ፤ መምህር ህላዌ፣ ሚስተር ስፕሪንገር፤ ዶክተር ጌታቸው ቦሎዲያ እና ሌሎቹም በጀግንነቱ ላይ በቅደም ተከተል ጉልህ አስተዋጽዖ እንዳላቸው ተገንዝቢያለሁ፡፡… እኔ ደግሞ የእንግሊዝ ተወላጅ የሆኑትን ባለቤቱን ወይዘሮ ሱ ኤድዋርድስን እጨምራለሁ›› ይላል፡፡እነዚህ የተጠቀሱት ሰዎች ሁሉ የተወለደን ዓይን በመክፈትና የህይወት መሰላል በመሆን የረዱት ናቸው፡፡ በዘነበ አገላለጽ፤ የህይወቱ ‹‹ቤተ መቅደሶች›› ናቸው፡፡   
ርባገረድ
ተወልደ የተወለደባት ርባገረድ፤ በጦርነት፣ በአመጽ፣ በአካባቢ መራቆት የምትጠቃ የአስተዳደር በደል የሚያጠቃት ነች፡፡ በእግር ተረጋግጦ አመድ እንደሆነ የት/ቤት ሜዳ ርባገረድም እንዲሁ በፖለቲካ በአስተዳደር ችግር ወዘተ ተረጋግጣ አመዷ ቡን ያለች መንደር ነች፡፡ ከዚህ ምድር ተወልደ ብርሃን ተወለደ፡፡ የስሙ  ትርጉም ብርሃን ተወለደ ነው፡፡ ርባገረድ ቆላማ የአየር ንብረት ያላት ናት፡፡ አንዳንዴ ድርቅ የሚገርፋት ብትሆንም፤ ብዙውን ጊዜ በሚያዝያ አካባቢ ዝናብ ታገኛለች፡፡ በሰኔ መጨረሻ ዝናብ የሚጀምር ቢሆንም፤ ርባገረድ ዋናውን የክረምት ዝናብ የምታገኘው ግን በሐምሌ ወር ነው፡፡ ጤፍ፣ ማሽላ፣ በቆሎ፣ ዘንጋዳ እና ዳጉሳ  ይመረትባታል፡፡  ከጥራጥሬ አተር፣ ምስር እና ባቄላን ምድሪቱ ትሰጣለች። ድንች እና ስኳር ድንችን የመሳሰሉ የሥራ ስር ውጤቶችም ትለግሳለች፡፡
ተወልደ ርባገረድን በልጅነቱ ዓይን ሲመለከታት አንዳንድ ትላልቅ ዛፎች ያሉባት። በርካታ ቁጥቋጦ እና ትላልቅ ድንጋዮች በብዛት የሚታዩባት ናት። በሃ ድንጋይ ያለበት አካባቢ ነው፡፡ የዕጽዋዕት ሽፋን በብዛት የሚገኝበት አካባቢ ባለመሆኑ፤ የአካባቢው ድንጋያማ ገጽታ ጎልቶ ይታያል። ትናንሽ ተራራዎችም አሉ። አፈራቸው በጠቅላላ በዝናብ ታጥቦ አልቋል፡፡ በአካባቢው ባለው ሜዳ በመስኩ እየቦረቀ እና ከብት እያገደ ያደገው ተወልደ፤ ከተፈጥሮ ጋር ለመተያየት ጥሩ አጋጣሚ  ያለው ልጅ ነው፡፡
ህይወት እንደ መምህር
አንድ የሂንዱ መምህር (ሳድጉሩ ይባላሉ) ‹‹ዮጋ ማለት›› ይላሉ፤  ‹‹ዮጋ ማለት የህሊናን፣ የስሜትን የአካል ፈተናዎችን በብቃት ለማለፍ የሚያስችል ‹‹ሰውነት›› ይኖረን ዘንድ የህይወትን መሣሪያዎች የመሳል፣ የመቅረጽ እና የመሞረድ ጥረት ነው፡፡ በዚህ ሂደት የሚያደርጉትንና የሚደረግባቸውን ነገር ለመረዳት  ንቁ ይሆናሉ›› ይላሉ፡፡
ዮጊዎች በህይወት ጎዳና አድራጊ ወይም ተደራጊ እየሆኑ የሚጓዙ አይደሉም፡፡ ይህንማ ሁላችንም እናደርገዋለን፡፡ ወይ አድራጊ ነን፡፡ ወይም ተደራጊ ነን፡፡ እነሱ ግን አድራጊ ሲሆኑ በንቃት፤ ተደራጊ ሲሆኑም በንቃት ነው፡፡ ነገሩ፤ እያወቁት ወደ እንቅልፍ ዓለም የመሻገር ነገርን ይመስላል፡፡ስለዚህ ዮጊዎች በማስተዋል ስለሚጓዙ፤ ከልምዳቸው ውስጥ ትምህርት እየቀሰሙ ይጓዛሉ፡፡ ለህይወት ብቁ የሚያደርግ ትምህርትን ይቀስማሉ፡፡ የህይወትን ፊደል በማጥናት ልምድ ይቀስማሉ፡፡ ራሳቸውን ይሰራሉ፡፡ የተወልደ ህይወት እንዲህ ያለ ጠባይ አለው፡፡
ዘነበ እንደሚነግረንም፤ ተወልደን በዓለም አቀፍ መድረክ የሚመለከቱት አንዳንድ የውጭ ሀገር ሰዎች ደግሞ አካላዊ አኳኋኑን (ዘይቤውን) አይተው ህንድ ይመስላሉ ይሉታል፡፡እኔም ተወልደ ህንዳዊ ባይሆንም እንደ ፈላስፋና እንደ ህንዶች ህይወትን ሰርስሮና አደራጅቶ የመመልከት ክህሎት የታደለ ሰው መሆኑን ከንባቤ ተረድቻለሁ።
የተወልደ የህይወት ገጠመኞች ሁሉ እየተቀባበሉ የዮጊ ስልጠና የሰጡት ይመስላል። ራሷ ህይወት ገና ከማለዳው የሚሆነውን አውቃ የምታሰለጥነው እንጂ፤ በተራ የህይወት ጎዳና የምትወስደው አይመስልም፡፡ ተወልደ እንደ ሀገር የኢትዮጵያ፤ እንደ ብሔር ትግራይ፤ እንደ መንደር ርባገረድ በከፈቱት የህይወት ጎዳና በመረማመድ የሆነውን የሆነ ሰው ሳይሆን፤ በተመረጠና በራሷ በህይወት እጅ ተነቅሶ በተደራጀ የሥልጠና ካሪኩለም በማለፍ የተፈጠረ ሰው ይመስላል፡፡
ካሪኩለም ሆን ተብሎ የተመረጠና ውጤቱ አስቀድሞ ታውቆ፤ ክንውኑ ታይቶ ለአንድ ማህበራዊና ግላዊ ዓላማና ግብ የተግባርና የነቢብ ስልጠና የሚሰጥበት የመማር- ማስተማር ስርዓት (ሂደት) ነው። ጠመኔ፣ ጥቁር ሰሌዳ፣ የየትምህርት ዘርፉ መምህራን፣ አስተዳደሩ ሁሉ ይሁነኝ ተብሎ የተደራጀ ነው፡፡ በዚህ ሂደት የሚያልፍ ተማሪ የተሳለ፤ በሚሰማራበት የሥራ መስክ ብቁ የሆነና የተሟላ ህይወት ለመምራት የሚችል ሰው ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ታዲያ የተወልደ ተራ የህይወት ገጠመኞች እንደ ካሪኩለም ሆን ተብለው የተመረጡ ሁነቶች እንጂ ተራ የህይወት ክስተቶች አይመስሉም፡፡
ይህ አስተያየት አሳሳች ነገር ሳይኖረው አይቀርም፡፡ ምክንያቱም አንዳንዶቹ የሀገራችን የታሪክ ክስተቶች የሁላችንም የሕይወት ገጠመኞች ናቸው፡፡ መንገዱ የሁላችንም መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ ወሳኙ ጉዳይ መንገዱ ሳይሆን መንገደኛው መሆን አለበት፡፡
 የተወልደ ዓይን
ተወልደ በዕውቀት የተወለወለ መነጽር ያለው ሰው ነው፡፡ መነፅሩን አዘውትሮ በሳይንስ፣ በታሪክ፣ በፍልስፍና፣ በባህል፤ ወዘተ የሚወለውል ሰው በመሆኑ አጥርቶ የሚያይ ምሁር ነው፡፡ እንዲህ አይቶ የሚስበው የሐሳብ ሐረግ፤ የሚመረምረውን ስርዓተ ሐሳብ በውል መረዳቱን የሚያመለክት ነው፡፡
‹‹ማየት ግንኙነትን ማየት ነው›› ብለን ነበር፡፡ የተወልደ ፀጋ ግንኙነትን የማየት ነው፡፡ ተወልደ ብርሃን ሁሉንም ነገር በአንድ እይታ ውስጥ የሚያስገባ ልዩ ፀጋ አለው። ይህ ፀጋ የተሰራው ከትህትና እና ከፍቅር ነው፡፡ የተወልደ መነጽር ሌንስ የተሰራው ከትህትና እና ከፍቅር ነው። ተወልደ ከተዛባ አመለካከት በሚጠብቅ ምሁራዊ ሥነ ምግባር የተገራ ህሊና ያለው እና ሁሌም ለመማር ዝግጁ የሆነ ሰው ነው፡፡
የተወልደ የተለየ ነገር ቅን ልቦና፣ ግንኙነትን የማየት ጸጋ፣ ፍቅርና ርህራሔ ናቸው፡፡ የርህራሄ መምህሩ እናቱ ይሆናሉ። የማየት ጸጋ መምህሩ አባቱ ይሆናሉ። ተቃራኒን የማክበርና የመኖር ብልሃትን ወይም የሆደ ሰፊነት መምህሩ አያቱ ይሆናሉ፡፡ ከዚያ በኋላ በኢትዮጵያና በትግራይ የተከሰተው ታሪካዊ ሁነት ሁሉ እንደ ተለያዩ መምህራን እየሆኑ ተወልደን ይስሉታል። መከራው ያስተምረዋል፡ ችግሩ ይገራዋል። እነዚህ ሁሉ ሆነ ተብለው ተወልደን ለአንድ ነገር ለማብቃት ታስበው የተዘጋጁና በካሪኩለም የተደራጁ የትምህርትና የስልጠና ግብአቶች ይመስላሉ፡፡
የተወልደ ህይወት DNA
ተወልደ ብርሃን አንድ ግለሰብ ነው፡፡ ግን ግለሰብነቱ፤ ከሰው ልጆች ጋር ያለውን ህብረት እንዳያይ አያደርገውም፡፡ እንደ ነገሩ ሁኔታ የጠቅላላው የሰው ልጆች፤ የሦስተኛው ዓለም ዜጎች ወይም የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ሴል ሆኖ ይሰራል፡፡ እናም በሴል ውስጥ እንደሚገኝ DNA፤ በተወልደ ህሊና ከህይወት ልምድ፣ ከትምህርት፣ ከምርምር የተገኙ መረጃዎች ይገኛሉ፡፡ ይህን ይዞ ራሱን የህብረተሰብ (የሰው ልጆች፣ የአፍሪካ፣ የኢትዮጵያ) ሴል አድርጎ የሚገኝበትን ህብረተሰብ አገልግሏል፡፡ እያገለገለ በህይወት ጎዳና ተጉዟል፡፡ ጥሙድ እንደ በሬ፤ ጽኑ እንደ ገበሬ ሆኖ የሰው ልጆችን ሲያገለግል ኖሯል፡፡ ስለዚህ አንዱን ተወልደ ብርሃንን ተመልክተን የሰው ልጆችን ጉዳይ እናያለን። በእርሱ የህይወት ታሪክ ውስጥ የሰው ልጆችን ታሪክ ማንበብ ይቻላል፡፡
የተወልደን ህይወት ስንመለከት፤ በህይወት የመኖርን ዓላማ ዳግም ለመጠየቅና እንደ ሰው ምን ልናደርግ እንደሚገባ ለማሰብ እንገደዳለን። ዕውቀትን ፍለጋም  የህይወት ግብ አድርገን ለመመልከት እንደፋፈራለን። ዕውቀት ለምን ዓላማ? የሚል ጥያቄም አንስተን መልስ ለማግኘት እንጓጓለን። ባወቅነው ዕውቀትም ምን ማድረግ እንዳለብን እንማራለን፡፡ ዕውቀት እውነት ነው፡፡ ዕውነትን መሸከም የሚችል ሰብዕና ምን ዓይነት እንደሆነ እንረዳለን፡፡
ዕውቀትና ዕውነት ለሰው ልጅ መሆኑ የሚያነጋግር አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ደግሞ በሀገር በአህጉር የተከፋፈለ የኑሮ ስርዓት ያለው በመሆኑ፤ የተወልደም ኃላፊነት ጠበብ- ሰፋ ይላል፡፡ ተወልደ- እንደ ሀገር ኢትዮጵያዊ ስለሆነ - የኢትዮጵያ ነገር ይበልጥ ይቀርበዋል፡፡ ከሀገር ወጣ ሲል አህጉር- አፍሪካ ይመለከተዋል፡፡ እንደ አንድ ፍጥረት በፕላኔት- መሬት የሚኖሩት ሰዎች ሁሉ ጉዳይ ያሳስበዋል፡፡ በሌላ አገላለጽ በአንዱ ውስጥ ሁሉንም ያያል፡፡
ሀገሩ ኢትዮጵያና አህጉሩ አፍሪካ የከፋ ድህነት ያለባቸው ናቸው፡፡ ፕላኔት- መሬትን ከተመለከትን- ድሆቹ በደቡብ የዓለም ንፍቀ ክበብ የሚኖሩ ናቸው፡፡ ታዲያ በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ የሚኖሩት ባለጸጎች፤ በደቡባዊው ዓለም የሚኖረውን ህብረተሰብ የሚጎዳ ነገር ሲያደርጉ፤ የድሆቹን ወገን ወክሎ የሀገሩን፣ የአህጉሩንና የላቲን አሜሪካውያንን (የደቡቡን ንፍቀ ክበብ ዓለም ህዝቦችን) መብት ለማስከበር ይታገላል። ከርባገረድ እስከ ሪዮ የምናየው የተወልደ ህይወት፤ ይህን ትግል የሚያደርግበት የህይወት ጉዞ ነው፡፡
የህይወት ጠበቃ
ግን ተወልደ ሰው በመሆኑ እይታው በሰው የተወሰነ አይደለም፡፡‹‹ማየት ግንኙነትን ማየት ነው› ብለናል፡፡ ስለዚህ ከሰው ተነስቶ ወደ ሌሎች ፍጡራን መብት ይዘምታል፡ የህይወትን ምስጢር ለመረዳት ሲሞክር የታየው ግንኙነት በመሆኑ፤ ሰውን ከእጽዋት ጋር አዛምዶ ያየዋል። በዚህም፤ ሰው ራሱን የተፈጥሮ አለቃ አድርጎ የማየት ቅዠት ውስጥ እንዳይገባ ይመክራል፡፡
አርስጣጣሊስ፤ ‹‹የሁሉም ነገሮች መለኪያ ሰው ነው›› (Man is the measure of all things) ይላል፡፡ ይህ የተሳሳተ መሆኑንና በዚህም የሰው ልጅ ከምን ዓይነት ችግር እንደወደቀ ተወልደ ተመልክቷል፡፡ ሰው ወደ ውጭ የሚተነፍሰውን የተቃጠለ አየር (ካርቦንዳይ ኦክሳይድ) ዕጽዋት ወደ ውስጥ ይስቡታል፡፡ ዕጽዋት ወደ ውጭ የሚተነፍሱትን ጋዝ (ኦክስጅን) ሰው ወደ ውስጥ ይምገዋል፡፡ ስለዚህ ዕጽዋት ከሌሉ ሰው የለም። በገራገሩ፤ ሰው ከሌለ ዕጽዋት የለም ማለት ይቻላል፡፡ ሰውን ለመጥቀም ዕጽዋትን መጉዳት መጨረሻው ሰውን መጉዳት ነው፡፡
አሁን የተፈጥሮ ሚዛንን የሚያዛባ የሰው የምርት እንቅስቃሴ አደጋ መሆኑን በግልጽ ከምናይበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ሆኖም ከሚያገኙት ትርፍ ወዲያ አሻግረው ለማየት የማይፈቅዱት ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች፤ ይህን እውነት ለመቀበል አይፈልጉም፡፡ የዓለም ኃያላን መንግስታት ፍላጎት በእነዚህ የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የሚመራ በመሆኑ፤ ኃያላን መንግስታት ችግሩን ለማስወገድ የሚያስችል የዓለም አቀፍ ስምምነት እንዳይፈጠር ዓይናቸውን ጨፍነው ይሟገታሉ፡፡ ታዲያ ተወልደ ከዚህ አስፈሪና አስቸጋሪ ፍልሚያ ውስጥ ገብቶ፤ ስግብግብነት እና የኃይል ሚዛን ጨዋታ ውስጥ የገባውን ዓለም ከስህተት ለመመለስ ጥረት ሲያደርግ እንመለከተዋለን፡፡
‹‹ሰው የሁሉ ነገር መመዘኛ ነው›› የሚል የፍልስፍና አመለካከት ከፈጠረው የሥነ እውቀት ስህተት ጀምሮ፤ የንግድ ትርፍን የማሳደግ እና ከትርፉ የሚገኘውን የበላይነት ለመቀዳጀትና ለማስጠበቅ የሚደረገው እውር ትግል በሰው ልጆች ላይ የፈጠረውን አደጋ ለማስቀረት ሲሟገት እናየዋለን፡፡ ሰው፤ የተፈጥሮ አለቃ ሳይሆን፤ አንድ የተፈጥሮ አካል መሆኑን የሚያስረዳ ትሁት ፍልስፍናን ሲያስተምር እንሰማዋለን፡፡
ተወልደ የሚተቸው ይህ ትህትና የጎደለውና የተሳሳተ አመለካከት ስር ሰዷል። በሰውና በዕጽዋት- በሰውና በእንስሳት መካከል የበላይ እና የበታችነት ግንኙነት ተመስርቷል፡፡ እርግጥ ነው ሰው አቅም አለው፡፡ ኢንተለጀንት ነው፡፡ ግን ይህን ኢንተለጀንስ በአግባቡ ካልተጠቀመበት ራሱን ያጠፋል፡፡ ሰው በአዕምሮው እንዴት መጠቀም እንደሚችል ካላወቀ አዕምሮው ያጠፋዋል፡፡ እብድ ማለትም አዕምሮውን እንዴት መጠቀም እንዳለበት የጠፋበት ህመምተኛ ነው።
አንድ ሰው ከመሬት ጋር  ሲነፃፀር በጣም ትንሽ ነው፡፡ መሬትም ከፀሀይ አንጻር ስትታይ እንደ ጉድፍ ነች፡፡
በስርዓተ ጸሀይ ውስጥ ትልቅ የሆነችው ፀሐይም በኮስሞሱ ውስጥ እንደብናኝ የምትቆጠር ትሆናለች፡፡ ፀሐይ ከነአጫፋሪዎቿ ብትጠፋ ኮስሞሱ አንዳች የጎደለበት አይመስለውም፡፡ ስለዚህ ይህን ሁሉ የማገናዘብ ጸጋ ያለው የሰው ልጅ፤ እንዴት ራሱን እንደ ልዩ ፍጥረት ሊመለከት ይችላል?
ለዕጽዋት ሰው ያስፈልገዋል፡፡ ለሰውም ዕፅዋት ያስፈልገዋል፡፡ እንኳን ሰው ደቂቆቹ ትል እና ነፍሳትም ለህይወት መቀጠል ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡ ሳድጉሩ የተባሉት የሂንዱ መምህር  ‹‹በዚህች ምድር የሚኖሩት ነፍሳት ድንግት ቢጠፉ፤ ከሁለት ዓመት ተኩል እስከ አራት ዓመታት ባለው ጊዜ ህይወት ጨርሶ ይጠፋል፡፡ ደቂቅ ትላትሎች  ከህይወት ትስስር መረቡ ድንገት ቢጠፉ በምድር ያለው ህይወት በተወሰኑ ወራት ውስጥ ይጠፋል፡፡ አስገራሚው ነገር ሰው ከዚህ ስርዓት ውስጥ ቢጠፋ ተፈጥሮ ይበልጥ ትጎመራለች እንጂ አትጠፋም›› ይላሉ። አዎ ከሰው ንክኪ የተጠበቀ አካባቢ ምን ያህል በኃይል ተሞልቶ እንደሚበለፅግ የዘወትር ህይወት ትምህርታችን ነው፡፡ አፈር የሞላው የትምህርት ቤት ሜዳ ክረምት ገለል ስንልለት ምን እንደሚመስል እናውቃለን፡፡ በእኛ እግር ተደቅድቆ አመድ የመሰለው የት/ቤት ምድረ ግቢ ገለል ስንልለት አሸብርቆ እናየዋለን፡፡ የእኛን ግፍ በዝምታ ተቀብላ፤  እንደፈለግን እንድንሆን የፈቀደችልን እናት ተፈጥሮ  ዘሯን በጥበብ ከኛ ሰውራ፤ ትንሽ ፋታ ስታገኝ መልሳ በውበት፣ በኃይል ጎምርታ ለዳግም የሰው ግፍ ራሷን ታዘጋጃለች፡፡ በእውነት ሰው ትህትና ይጎድለዋል፡፡
ተወልደ በዓለም ዓቀፍ ብዝሀ ህይወት መድረክ የሚሞግተው ይህን አመለካከት ይዞ ነው፡፡ ተወልደ አወቅኩ ያለው የሰው ልጅ፤ የንግድ ትርፉን የሚመለከተው ስግብግብ የሰው ልጅ የዘረ መል ስርዓቱን በማዳቀል ሊቀለብሰው የማይችል ስህተትን በሚያስከትል ጎዳና የሚያደርገውን ጉዞ እንዲያቆም የተፈጥሮ ጠበቃ ሆኖ ይሟገታል፡፡
የዘረ መል ጥበብ ይዞ ትህትና በጎደለው ስግብግብ ህሊና የሚመራውን ምዕራባዊ ዓለም ይሞግታል፡፡ የሰው ልጆችን በአጠቃላይ፤ የደሃውን የዓለም ህዝብ በተለይ፤ የኩባንያዎች ሎሌ አድርጎ የሚያስቀር ዓለም አቀፍ ስምምነትን ለመደንገግ ከሚጣደፉ የዓለም ኩባንያ ወኪሎች ጋር የሦስተኛውን ዓለም ህዝብ ወክሎ ይታገላል፡፡
‹‹ኢትዮጵያዊው ሳይንቲስት›› (የምድራችን ጀግና) የተሰኘው የዘነበ ወላ መጽሐፍ፤ በዚያች ድህነት በነገሰባት መንደር ከሚኖር አንድ ደሀ ቤተሰብ የተወለደው ተወልደ ብርሃን ገ/እግዚአብሔር በአደገኛ የሀገራችን የታሪክ ጎዳና እየተጓዘ፤ የወደቁ ልጆችን እየሰበሰበ፤ ለሀገሩ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም  መስሎ በታየው መስክ ሁሉ እየተሰለፈ፤ በእውቀት ማጣት እና በፖለቲካ ሸፍጥ የግንግሪት በተያዘው የኢትዮጵያ የታሪክ ጎዳና እየተጓዘ፤  ለሀገሩ ያገለገለ የአንድ ታላቅ የሀገራችንን ሰው ህይወት የሚያሳይ ድንቅ መጽሐፍ ነው፡፡

Read 809 times