Saturday, 22 May 2021 14:51

ከእግዜር ጋር ንግግር! ዝምታ (እስቲ አንዴ ፀጥታ!)

Written by  ያዕቆብ ብርሃኑ
Rate this item
(2 votes)

   … እንደ አንዳች ሞትና መቃብር ጠርዝ ላይ ያመላልሰኛል፡፡ በጩኸታሟ አዲስ አበባ መሃል አብዛኛውን የጽሞና ሀሰሳ ሰዓቴን የማሳልፈው በፈራረሱ የመቃብር ቅጥሮች ውስጥ ነው፡፡ በየሳምንቱ የማነባቸው የውጪ ጋዜጣና መጽሔቶች  ላይ እንኳን (በኮቪድ 19 ምክንያት ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ከማቆማቸው በፊት) ቀድሜ የማነበው obituary (ዜና ዕረፍት) አምዳቸውን ነበር፡፡
ጊዜው ትንሽ ቆይቷል፡፡ ከዓመት ከምናምን በፊት ከDecember 22- January 4 2019 የሚሸፍነው የthe economist መጽሔት double issue ዕትም ዜና ዕረፍት አምድ ላይ Silence as presence በሚል ርዕስ ስር ስለ መነኩሴው ቶማስ ኬቲንግ ሕልፈት የተጻፈውን አነበበኩ፡፡ ካፒታሊዝምና ፍትወት በሚያቅነዘንዘው ልቅ ዓለም እንደ ኢየሱስና እንደ ጋንዲ ባለ ከፍ ያለ ልዕለ ሰብዕና ዝምታን የሕይወት መመሪያቸው አድርገው ለ95 ዓመታት ኖረው ስላለፉት ታላቅ ሰው፤ ለ95 ዓመታት በመኖሪያ ክፍላቸው ውስጥ ከአንዲት አልጋ፣ ከመጻፊያና ማንበቢያ ጠረጼዛና ወንበር በስተቀር ምንም ስላልነበራቸው መናኝ… እንደ ጋንዲ ለንቋሳ ገጽታን የተላበሱ፣ ግን ደግሞ ትንሽ ገዘፍ ያሉ፣ ረጅም፣ ራሰ በራ፣ በሚያስተዳድሩት ገዳም የሕይወት ዘይቤያቸውን ለሚሹ ፅሞናን በጸጥታ ከማስተማሩ መልስ በገዳሙ አንድ ጥግ ተቀምጠው ሞትን በመናፈቅ (longing to death) ዘመናቸውን በሙሉ የኖሩ ግዙፍ ሰብዕና…
የእኒህ ሰው የሕይወት ዘመን ፍላጎት አንድ ብቻ ነበር፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገር… ይህንን ማድረግ የሚቻለው በጽሞና ብቻ ነው ብለው በማመናቸው ሌሎችም ከዕለት ተለት ሩጫቸው በምትተርፋቸው ጊዜ ማድረግ እንዲችሉ ሲጥሩ አሳልፈዋል፡፡ እኒህ ሰው ከበመካከለኛው ዘመን በእስፓኝ ከኖሩት st. John the cross የተዋሱትና አሻሽለው መታወቂያቸው ያደረጉት ግሩም አባባል አላቸው፡፡
‹‹God’s first language was silence.››
 - St. John the cross
‹‹everything else is bad translation.››
 - Thomas Keating
‹‹Including holy manuscripts.›› - እኔ
እኔም አልኩ… ስታወሩ ስሜታችሁን፣ ዝም ስትሉ ግን ነፍሳችሁን ማንበብ እችላለሁ፡፡ ዝም ማለት የቻለ እርሱ አሁንን ብቻ ሳይሆን ዘለዓለምን ማዘዝ ይችላል። ዝም ማለት የቻለ እርሱ ከአምላኩ ጋር እንኳን ባይሆን ከራሱ ጋር በተግባቦት ማውራት ይችላል። ግጥም ምንም አይልም። ስዕል ጥሩ ነገር ነው፡፡ ድርሰት በጣም ጥሩ ነገር ሳይሆን አይቀርም፡፡ ሙዚቃም እጅግ በጣም ጥሩ ነገር መሆን አለበት፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን ስንኩል የዝምታ ገጽታዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሁሉ በላይ ዝምታ ይበልጣል፡፡ ዝም ማለት፣ ፀጥታ (የሚረብሽ ድምጽ አለመኖር) ሁሉ ዝምታ ሊሆን አይችልም፡፡ ዝምታ (ጽሞና) ረቂቅ ነገር ነው፡፡    
የሆነን ነገር፣ መውደድህንም ቢሆን እንዴትም ብትገልጸው በተናገርከው ቅጽበት ወዲያው ትርጉሙን አዛብተኸዋል፡፡ ዋጋውን ቀንሰኸዋል፡፡ ለአለመግባባት ግዙፍ በር ከፍተሃል፡፡ ከቻልክ በጣም አስፈላጊ ካልሆነ በስተቀር ምንም አትበል፡፡ በጣም ውድ የሆነውን ነገር በዝምታና በተግባር ልትገልፀው ሞክር፡፡  እኔ እንኳን ይህችን ሹክ ልልህ ጽሁፉን ካነበብኩበት ከፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ጀምሮ ራሴን ማሳመን ተስኖኝ ይሄው ሳመነታ ነበር፡፡
ለመሆኑ የቡድሃ ብቻ የሆነ ዝምታ (Buddha’s silence) ማለት ምንድን ነው? ቡድሃ የነቃ ሰው ሆኖ ከወጣ በኋላ ስለ ሁለት ወሳኝ የሆኑ የህልውና ጥያቄዎች (Is there ultimate reality? is there any self?) ተጠይቆ ነበር፡፡ መልሱ ጥልቅ ዝምታ ብቻ ሆነ፡፡ ልክ ኢየሱስ በጲላጦስ ‹እውነት ምንድን ነው?› ተብሎ በተጠየቀ ጊዜ፣ የቡድሃ በሆነች ዝምታ ‹ላሽ› እንዳለው መሆኑ ነው፡፡ የቡድሃ ዝምታ ሌጣ ዝምታ ብቻ አይደለችም፡፡ ረቂቅ አፈክሮት እንጂ… ቡድሃ ለበርካታ ጊዜያት እጅግ በታላቅ ተመስጦ ውስጥ ሆኖ መገለጥን (Enlightenment) ከተጎናጸፈም በኋላ በዝምታው ገፋበት፡፡ እንደ ቡድሂዝም ተረኮች ከሆነ፤ ከዝምታው ጥልቀት የተነሳ ምድር ተጨነቀች፡፡ አማልክቱ ሳይቀር በፍርሃት ተንቀጠቀጡ፡፡ አማልክቱ ወደ የነቃው ሰው ቡድሃ ቀርበውም የሆነ ነገር እንዲናገር ተለማመጡት፡፡ ቡድሃም ሲመልስ እንዲህ ብሏል፡፡ ‘Those who know, they know, even without my saying, and those who do not know, they will not know by my words. Any description of light to a blind man is of no use. One who has not tasted the ambrosia of existence, of life…there is no point in talking to them about it. So I am silent.’ How can you convey something so intimate, something so personal? Words cannot.” በግርድፉ ሲተረጎም፡-   
 ‹‹የሚያውቁ እኔ ባልናገርም ያውቃሉ። የማያውቁ እኔ ብናገርም (በእኔ ቃላት) ሊያውቁ አይችሉም፡፡ ለአንድ ዓይነ ስውር ሰው ስለ ብርሃን የሚደረግ ማንኛውም ገለጻ እርባና የለውም፡፡ የሕልውናን፣ የሕይወትን ልዩ ጣዕምና መዓዛ ለማያውቁ ሰዎች የሚደረግ ማንኛውም ማብራሪያ ትርጉም አይኖረውም፡፡ እናም ዝም አልኩ፡፡ በጣም ምስጢር፣ ረቂቅ፣ የቅርባችሁ፣ የግላችሁ የሆነን ነገር እንዴት መግለጽ ይቻላችኋል? ቃላት ይሄን የማድረግ መቅን የላቸውም፡፡›› በአጭሩ ጉዳዩን በጥልቀት ያጠኑት ሰዎች እንደሚሉት፤ ቡድሃ ዝምታን ወደ ፍልስፍና ደረጃ አሳድጎታል፡፡ የማስተማሪያ መንገዱም ነበረች፡፡    
ከፈለክ ዜን ቡድሂስቶችን ሂድና ‹እንትን ማለት ምንድን ነው?› በላቸው፡፡ ሁሉም በአንድነት ‹‹ና ሻይ ጠጣ›› ይሉሃል፡፡ ግልጽ እኮ ነው ማንም በእውቀት ይኖራል እንጂ እውቀትን ሊገልጻት አይችልም፡፡ ታኦይስቶች “The Tao that can be told is not the eternal Tao. The name that can be named is not the eternal name.›› እንደሚሉት ሁሉ… ዝምታ ንግግርን የማቆም ሂደት አይደለም፡፡ እንዲያውም ዓይነተኛ የንግግር ዘዴ ነው፡፡ ዝምታ ግን ግልብ አይደለም፡፡ ጥልቅና ፅንፍ የለሽ (deep and vast) እንጂ…  
ዝምታ እውነትም ወርቅ ነው። በየሰበቡ የሚለፈልፍ ሰው፣ ያለ ኢላማ የእውር ድንብሩን እንደሚተኩስ ወታደር ይመስለኛል። እንዴዴዴ...ዝምታ ባይኖር ተናግሮ በሚያናግር መንጋ ህዝብ መሀል በፀጥታ ስቃይ ውስጥ እንኳን መኖር እንዴት ይቻላችኋል? አይ አይ ዝምታማ ከወርቅም በላይ ጥበብ ነው። ከሚናገር ይልቅ ተናጋሪውን የሚያዳምጥ ሰው የበለጠ ከጊዜ የተሻገረ ግንዛቤ ያለው ይመስለኛል።
የምንኖርበት ዘመናዊው ዓለም ፈጠራዎች ሁሉ በአብዛኛው ከፍንዳታ (Explosion) በሚገኝ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ናቸው። መኪኖቻችን፣ ጀነሬተሮችን፣ ጄቶችን፣ መንኮራኩሮችን… ተመልከቱ፡፡ ከተሞች ከፍተኛ በሆነ የድምጽ ብክለት እየተናጡ ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የዘመናዊው ዓለም ሰው ተቅበዝባዥ እየሆነ ነው፡፡ የምዕራቡ ዓለም አየር መንገዶች ድምጽ የሚከላከሉ የጀሮ ማዳመጫዎችን ለሚፈልጉ ተጓዦች ተጨማሪ ገንዘብ እያስከፈሉ አገልግሎቱን እንደሚያቀርቡ አንብቤያለሁ፡፡
ከላይ በጠቀስኩት የthe economist ከmay 4- may 10 - 2019 በሸፈነው ዕትም ethics and evolution በሚል ርዕስ ስር ባነበብኩት አንድ ጥናት መሰረት፤ ባለፉት 30,000 ዓመታት ሂደት የሰው ልጅ ጭካኔ (cruelity) እና እንስሳዊ ባህሪያት ከመሰሎቹ ዝንጀሮና ጎሬላዎች ተሽሎ የተገኘው እጅግ በጣም በጥቂቱ ነው፡፡ በዚህም መሰረት የሰለጠነው የሰው ልጅ እስከ አውሬያዊ ባህሪያቱ ይኖራል፡፡ እኔም፣ አንተም፣ አንቺም ጭምር… ከዚህ አውሬያዊነት መሻሻልን የሻተ ዝም ይላል፡፡ በየቀኑ ቢያንስ የ40 ደቂቃ የጽሞና ጊዜ ይኖረዋል፡፡ ዝም ማለት የቻለ እርሱ ራሱን ያሸንፋል፡፡ ራሱን ማሸነፍ የቻለ፣ ሌሎችን፣ ዓለምን የማሸነፍ ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡
ሼክስፒር ተናግሮ መግለፅ ላልቻለው ስሜቱ መግለጫ እንዲሆነው ‘የቀረው ዝምታ ነው’ ይላል። እባካችሁ እስቲ አንዴ ፀጥታ... ዝምምምም ... ይሄን ፅሁፍ የምታነቢ፣ የምታነብ፣ አንቺ፣ አንተ እስቲ ለአንዲት ሳድሲት፣ ለአንዲት ቅፅበት፣ ለአንዲት ደቂቃ፣ ለአንድ ኬክሮስ፣ ለአንድ ሰዓት፣ ቀን፣ ወር፣ ዓመት፣ ዘመን፣ ዘመናት፣ ቢቻለን ለዝንተዓለም ዝም እንበል! ዝምምምምም...

Read 539 times