Saturday, 22 May 2021 13:35

ግልፅ ደብዳቤ ለኩሩውና ውዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ

Written by  ከፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ
Rate this item
(3 votes)

       ይህን ደብዳቤ ልፅፍላችሁ የተገደድኩት የሃገራችን ሁኔታ ስለ አሳዘነኝና ስለ አሰጋኝ ዝም ብዬ ለማየት ህሊናዬ ስለ አልፈቀደልኝ ነው። የሃገራችንን የውስጥ ሁኔታ ስመለከተው በዘር-ተኮር ጥላቻና በፖለቲካ ላይ በተንተራሰ የደም መፍሰስና መፈናቀል የታወከ ነው። እንደምታውቁት ቀደም ሲል ከጋምቤላ አኝዋክ ወገኖቻችን ጀምሮ፣ በጉራ ፈርዳ፣ በጅጅጋ፣ በሃረር፣ በበደኖ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በመተከል፣ በጉጂና በኮንሶ፣ በቅርቡም በሸዋ ሮቢት፣ በአጣዬና በከሚሴ እንዲሁም በወለጋ ብዙ ንፁሃን ወገኖቻችን በፅንፈኞች ተገድለዋል። ተፈናቅለዋልም። ንብረታቸውንም አጥተው በገዛ ሀገራቸው ስደተኞች ሆነዋል። ለሰው ልጆች ህይወት ቅንጣት የምታህል  ክብርና ርህራሄ የሌላቸው አውሬዎች፣ ለኢምንት ፖለቲካ ጥቅም ብለው በአማራ ወገኖቻችን ላይ የፈፀሙትና አሁንም በያቅጣጫው እየፈፀሙ ያሉት የግፍ ግድያና ፍንቀላ ከማሳዘኑም በላይ እጅግ የሚያስቆጣ ነው።    
  የውጪ ጠላቶቻችንን ጉዳይ ስመረምረው ደግሞ እኛ ከውስጥ ስንተራመስና ስንፋጅ እነሱ በቅጥረኞቻቸው አማካኝነት  በእሳታችን ላይ ቤንዚን ከማርከፍከፋቸውም በላይ ኢትዮጵያን ለመውረር የጦርነት ጥሩምባ እየነፉና ነጋሪት እየጎሰሙ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ለነጭ አልገዛም፣ በአእምሮዬ፣ በሰብዕናዬና በክብሬ ከማንም አላንስም፤ የራሴ ጥንታዊ አኩሪ ባህል፣ ሃይማኖታዊ ተቋማትና ፊደላት ያለኝ፣  መንግሥታዊ ሉዓላዊነቴን ለሺህ ዘመናት የጠበቅኩ ሀገር ነኝ፤ ስለምትላቸው እነሱ በበላይነት እብሪት ደረታቸው አብጦ፣ #እኮ እንዴት ተደርጎ ከእኛ እኩል ልትሆኚ፤; ብለው እሷን ለማጥፋት ያሴራሉ። ደሞም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ራሷን እንዳትችል፣ እሷ የተዋረደች ተመፅዋች እነሱ ክቡራን መፅዋች ሆነው ለዘላለም ሊቀጥሉ ይሻሉ። ስለዚህ ነፃነቴን ጠብቄና አንድነቴን አስከብሬ፣ ኢኮኖሚዬን አሳድጌ ህዝቤን  ከድህነት አላቅቃለሁ ካለች ክፉኛ ያስቆጣቸዋል፤ ያንገበግባቸዋልም። ደግሞም ለመላው ያፍሪካ ህዝቦች አርአያ ሆና በጥቅማችን ትመጣብናለች ብለው በስጋት ይርዳሉ። ስለዚህ፣ አንደኛ ለሃገሩ ሉአላዊነት የሚታገለውንና ሃገሩን ከድህነት ቀንበር ለማላቀቅ ከመጣሩም በላይ የሃገሬን ሃብት በውጭ መንግሥታት አላስበዘብዝም ያለውን ባለ ራዕይ መሪ፣ ሃገራቸውን በካዱ ቅጥረኞች ለማስገደል ወደ ኋላ አይሉም። ከተቻላቸው ባለ ራዕይን መሪ አስወግደው፣ በእሱ ፈንታ ለእነሱ ፍፁም አገልጋይ ባሪያ የሚሆን አሻንጉሊት ተክተው፣ ሃገሪቱን እንደልባቸው እየፎነኑባት ሊበዘብዟት ይጥራሉ። አሻፈረኝ፣ አሻንጉሊት አንሆንም፤ ሃገራችንን አናስበዘብዝም ያሉ የአፍሪካ፣ የላቲን አሜሪካና የእስያ መሪዎችን የአሜሪካው የስለላ ድርጅት ሲአይኤ አስገድሎ፣ የአሜሪካንን ትዕዛዝ እሺ ጌታዬ በሚሉ ቡችሎች ተክተውባቸዋል።                             
የአፍሪካን ብቻ ብናጋልጥ፡ የኮንጎው ፓትሪስ ሉሙባ፣ የጋናው ክዋሜ እንኩሩማህ፣ የቻዱ ጉኩኒ ኩዌዴ  ዐይነተኛ ምሳሌዎች ናችው። ኔልሰን ማንዴላ የውትድርና ትምህርቱን ኢትዮጵያ ውስጥ አጠናቆ፣ የኢትዮጵያን ፓስፖርት ይዞ፣ ደቡብ አፍሪካ ገብቶ ዘረኞቹን ነጮች ሊዋጋ ሲዘጋጅ ለዘረኞቹ ጠቁሞ ያስያዘው የአሜሪካው ሲአይኤ ነው። ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊንም ሃብቴን ለህዝቤ ጥቅም አውላለሁ እንጂ በአውሮፓውያንና አሜሪካውያን አላስበዘብዝም ስላለ በሲአይኤ ቀስቃሽነት አሜሪካ፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ ሊቢያን በጦር ወርረው ጋዳፊን በቅጥረኞች አስገድለው፣ ሃገሪቱን አተራምሰው፣ ቤንዚኑንን እንደ ልባቸው ለመዛቅ ችለዋል። ጋዳፊ ሆፈፌ ቢጤ ቢሆንም የሃገሩን ሉዐላዊነት ጠብቆ፣ የሃገሩን ሃብት ለህዝቡ አከፋፍሎ፣ ኢምፔሪያሊዝምን ተጋትሮ፣ አረቦችንና አፍሪካንም ጭምር በራሱ መንገድ አንድ ለማድረግ ጥሮ ነበር።
ወደ እነ ፓትሪስ ሉሙምባ፣ ክዋሜ እንክሩማህና ሌሎችም ስንመለስ፣ እነሱን በአሻንጉሊት ቅጥረኞች የገደለና መንግሥታቸውን የገለበጠ፣ ከላይ እንዳልኩት ያው ሲአይኤ ነው። የኮንጎውን ፓትሪስ ሉሙምባን ያሥገደሉት ሲአይኤ እና የቀድሞዋ የኮንጎ ቅኝ ገዢዋ ቤልጂየም ተመሳጥረው ነው።  ዋናውን የሞት ቅጣት ፓትሪስ ሉሙምባ ላይ የፈረደው ግን የአሜሪካው ፕሬዚደንት አይዝንሃወር ነበር።  እ.ኤ.አ በ1960 ዓ.ም ጠቅላይ ሚንስትር ሆኖ ተመርጦ ጥቂት ወራት እንደሠራ፣ ይህ ሰው የሶሻሊዝም ዝንባሌ አለው በማለት ገድለውት ቾምቤ በሚባል አሻንጉሊት ተኩት። ቾምቤም ሰጥ ለጥ ብሎ ለምዕራባውያን እየተገዛ የሃገሪቱን ማዕድናት አስበዘበዘ። በተለይ አልማዙን በገፍ አስጋዘው። በዚህ የተነሳ የሉሙምባ እና የቾምቤ ደጋፊዎች የእርስበርስ ጦርነት ከፍተው ተላለቁ። ከእዛ በኋላ ሞቡቱ የሚባል መሃይም  ጅላንጎ ወንበሩ ላይ አስቀምጠው ኮንጎን ጋጧት። ሞቡቱም የድርሻውን ገንዘብ ወደ ቤልጅየም፣ ፈረንሳይና ስዊትዘርላንድ አሸሸ። ሻቶ የተባሉትን የቀድሞ የፈረንሳይ ልዑላን ቤተ መንግሥቶች እየገዛ ኦናቸውን እያስቀመጣቸው ቆይቶ ገንዘቡንም ሳይበላው ሻቶዎቹንም ሳይኖርባቸው ሞተ። ኮንጎም ለሁለት ተከፍላ የዛሬ 61 ዓመት የተጀመረው የእርስበርስ ጦርነት አሁንም  ያተራምሳታል። ያ ሁሉ ማዕድን እያለው ህዝቡ ምንም ሳያገኝ በድህነት ይማቅቃል።
ቀጥሎ በሲአይኤ  የተጠቃው የጋናው ዶክተር ክዋሜ ንክሩማህ ነው። ይህ ሰው ጋናን ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ለማላቀቅ ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱት የነፃነት ተዋጊዎች አንዱ ነው። እንዲሁም በአፍሪካ አንድነት በማመኑ ከአፄ ኃይለሥላሤ፣ ከግብፁ ገማል አብደልናስር፣ ከናይጀሪያው ሰር አቡበከር ታፌዋ ባሌዋ እና ሌሎችም አዲስ ከቅኝ ግዛት ቀንበር የወጡ ሃገሮች መሪዎች ጋራ  ሆኖ ፓን አፍሪካንኢዝምን በግንባር-ቀደምነት ያቀነቅን ነበር። እንዲሁም ኢምፔሪያሊዝምን እየተዋጋ የጋናን ሃብት ለጋና ሊያውል ይጥር ነበር።  ይህ አቋሙ ያልጣማቸው ምዕራባውያንና ሲአይኤ፣ እሱ ለሥራ ጉዳይ በውጪ ሃገር ሳለ መንግሥቱን ፈንቅለውበት ለአንድ ተላላኪ አሻንጉሊት አሳልፈው ሰጡበት። በዚህ ዐይነት ንክሩማ ለጋና ያቀደላት ሁሉ የእድገት መሰረት ፈርሶ ከንቱ ቀረ።
እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ  ከፖርቱጋል ቅኝ ግዛት ነፃ ለመውጣት በሞዛምቢክ ጫካዎች ውስጥ ሶስት ግንባሮች ይታገሉ ነበር። በ1975 የኤምፒኤልኤው መሪ ኦገስቲኖ ኔቶ የሞዛምቢክን ዋና ከተማ ሉዋንዳን ያዘ። ሲአይ ኤ ግን ኦገስቲኖ ኔቶ ከአሜሪካ ይልቅ ወደ ሶቭየት ያደላል በማለት ኤፍኤንኤልን  እና ዩኒታ የተባሉትን አፍቃሬ-ምዕራቦችን ደገፈ። እውነቱ ግን ሶስቱም ነፃ አውጪዎች ከሶቭየት ኅብረት እርዳታ ያገኙ ነበር። ሆኖም ሃገሪቷን ለማተራመስ 30000 ጠመንጃዎች በኮንጎ ኪንሻሳ በኩል ከማስረጋቸው በተጨማሪ ቅጥረኞች መልምለው፣ ከዩኒታ ጋራ ገጥመው፣ ሞዛምቢክን ለዓመታት ደም በደም አደረጓት። ቤንዚንዋንና ሌሎቹንም የተፈጥሮ ሃብቷን እንዳትጠቀምባቸው እንቅፋት ሆኑባት።  
እ.ኤ.አ በ1982 ዓ.ም ደግሞ ሲአይኤ እና ዲፓርትመንት ኦፍ ስቴትስ፣ በቻድ ጉዳይ ጣልቃ ገብተው፣ ሂስኒ ሃብሬ የሚባል ሰው-በሌ አነሳስተው፣ ጉኩኒ ኩዌዴ የተባለውን በህዝብ የተመረጠን ለአሜሪካ የማይታዘዝን ፕሬዚዳንት ገለበጡ። ይህም ሂስኒ ሃብሬ የተሰኘ  አረመኔ ሰው በ8 ዓመታት የስልጣን ዘመኑ ብቻ 200 ሺ ሰዎችን ጨረሰ።  የሃገሪቱ ህዝብም በሃገሩ በሰላም ሊኖር ተሳነው።
ወደ ኢትዮጵያችን ስንመለስ፣ ንጉሡ አፄ ኃይለ ሥላሤ  በብልጠት፣ ኢትዮጵያ ከምዕራብም ከምስራቅም የማትወግን ገለልተኛ ሃገር ነች ብለው አወጁ። በዚህ ምክንያት ለአሜሪካኖቹ የማይመቹ ስለሆኑ እሳቸውን ከዙፋናቸው ለማውረድ አመቺ ጊዜ ሲጠብቁ ኖረው፣ በተማሪዎች ተጀምሮ ወደ ወታደሮችና ህዝብ በዘመተው አብዮት እ.ኤ.አ በ 1974 ዓ.ም ንጉሡ ከዙፋናቸው ተከነበሉ። ከእዛ በኋላ ወታደራዊው ደርግ ሶሻሊዝምን አውጆ ወደ ሶቭየት ካምፕ ዘው አለ። የዚህ አንዱ መንስኤው፣ በግርግሩ ተጠቅማ ሶማልያ ኢትዮጵያን ስለወረረች ንጉሡ ቀደም ሲሉ ከአሜሪካ ሊገዙ ከፍለውበት የነበረውን የጦር መሣሪያ ፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር ለኢትዮጵያ አልክም በማለቱ ነበር። ከዚያ ሶቭየት ኅብረትና ኩባ ኢትዮጵያን ከሶማልያዊው ዚያድ ባሬ ወረራ ለመታደግ  የጦር መሣሪያ ማስታጠቅ ብቻ ሳይሆን በጦርነቱ ላይ ተሳትፈው የተቻላቸውን ያህል አግዘው ነበር። ሕወሓት/ወያኔ በመጀመሪያ #የኔ አርአያ የአልባንያ ሶሻሊዝም፣ ማለትም ወደ ኋላ የቀረ ዐይነት ሶሻሊዝም  ነው; ብላ አውጃ ነበር። በመጨረሻ ግን ሶቭየት ኅብረትን ጨምሮ አልባንያና ሌሎቹም የአውሮፓ የኮሚኒስት ሃገራት ስለተንኮታኮቱ፣ #እኔ ኮሚኒስት አይደለሁም; ብላ የአሜሪካንና የአውሮፓ አገልጋይ ሆነች። በአሜሪካን አገልጋይነትዋም #አልቃይዳንና አልሸባብን ከአፍሪካ ቀንድ አጠፋላችኋለሁ; እያለች ዶክተር ዐቢይ አህመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እስከሆኑበት ጊዜ ድረስ የአሜሪካንን ዶላር በአካፋ ስትዝቅ ኖረች። ወያኔ እና ቁንጮዋ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአሜሪካንና የምዕራብ ታዛዥ በመሆናቸው፣ እነዚህ ሁለቱ እነሱን አስገልብጦ ለመጣል ምንም ምክንያት አልነበራቸውም። በተቃራኒው የእነሱን ጥቅም እስካስከበሩና ለእነሱ ታዛዥነታቸውን እስካረጋገጡላቸው ድረስ የኢትዮጵያን ህዝብ ረግጠው ቢገዙትና ቢመዘብሩት ደንታ አልነበራቸውም። በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት በባርነት ቀንበር አስገዟት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ግን ቆፍጠን ብለው “ይህ ከእንግዲህ እንዲህ ሊቀጥል አይችልም” አሏቸው  “እኛ ነፃነት የለመድን ለማንም ተንበርክከን የማናውቅ ነፃ ህዝብ ነን። ከማንም ትዕዛዝ አንቀበልም። የማንም ቡችላ አንሆንም። እርስበርስ እየተፋጀን የተፈጥሮ ሃብታችንን ባለመጠቀማችን እንጂ ድሃ አይደለንም። ሁሌ እናንተ መፅዋች፣ እኛ ተመፅዋች ሆነን አንኗኗርም። ጥቂት ዓመታት ስጡን። እንበለፅጋለን። ያለ ማንም ተፅዕኖ ከማንም ሳንለምን በገዛ ገንዘባችንና ውሃችን ግድባችንን ገድበን፣ የስልጣኔ ማማችንን ከፍ አድርገን እንሰቅለዋለን። የተፈጥሮ ሃብታችንንም ለህዝባችን  መሻሻል እናውለዋለን እንጂ ለማንም አሳልፈን አንሰጥም። ምርጫችንንም ያለ እናንተ ታዛቢነት በሰላም እናጠናቅቃለን። እናንተ ምርጫ ስታደርጉ እኛን መች ለታዛቢነት    ትጋብዙናላችሁ?  እርግጥ እስከዛሬ እውነተኛና ያልተጭበረበረ ህዝባዊ ምርጫ አድርገን አናውቅም።  ግድ የላችሁም፤ ከእንግዲህ ወዲህ የምናደርገው ምርጫ ፍፁም ዲሞክራሲያዊ ይሆናል። ከተሸነፍን ያለ ምንም ጣጣ ለአሸናፊው ወንበሩን እንለቃለን፤” አሉዋቸው።  
እንዲህ ዐይነቱ ሃሳብና ንግግር የአፍሪካን አሻንጉሊት መሪዎች ማዘዝ ለለመዱት ነጮች ከቶውንም አይመቻቸውም። እንዲህ ዐይነቱን ነፃ መሪ ከስልጣን ካላወረዱት ወይም ካላጠፉት አይተኙም። ቀድሞ ለጥ ሰጥ ብለው የሚታዘዟቸው ወያኔዎች አሁን ተደምስሰው ስለጠፉባቸው አሜሪካኖቹና አውሮፓውያኖቹ ቆጭቷቸዋል። ስለዚህ ነው የኢትዮጵያን መንግሥት #ምርጫውን ትታችሁ ከእነሱና ከሌሎቹ  ደም አፍሳሽ ታጣቂዎች ጋር ተደራደሩ፤ ጊዜያዊ መንግሥትም በቶሎ አቋቁሙ; የሚሉት።
ነፃነት ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ! ንቃ! ሀገርህን ጠብቅ!  እነሱ አሁን የሚያሴሩት ተደራደሩ እያሉ፣ ምርጫውን በማስተጓጎል፣ ቢችሉ ወያኔ ሃርነት ትግራይን እንደ ምንም ወደ ሥልጣን በማምጣት፣ ወደ ቀድሞው ባርነት ሊመልሱህ ነው።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለምዕራባውያን የማይታዘዝ መሪን ልክ በኮንጎው መሪ በፓትሪስ ሉሙምባ፣ በክዋሜ እንክሩማ እና ጋዳፊ ላይ ያደረጉትን ሁሉ ቢችሉ ለማድረግ ማለማቸው አይቀርም። የሲአይኤ አባላት አንድ መሪና መንግሥት ላይ አንድ ደባ ሲያሴሩ በአጎራባች ሃገራት ውስጥ ይመሽጋሉ። ለምሳሌ ኬንያ ውስጥ ሆነው ያለ ኬንያ መንግሥት እውቅና ወይም ኬንያ እያወቀች  በኢትዮጵያ መንግሥት መሪ በዶክተር ዐቢይ ላይ አንዳች ሴራ ቢያቀነባብሩ አይደንቅም። አያድርግባቸውና እሳቸው ከስልጣን ቢወርዱ ወይም አንድ ነገር ቢሆኑ፣ በዚህ ቀውጢ ሰአት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከሰተው ቀውስና እልቂት ማባሪያ የላቸውም። በእንዲህ አይነቱ ግርግር ውስጥ እነ ግብፅ፣ ሱዳንና ሌሎች አረቦች ተንጋግተው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ደግሞ ሳይታለም የተፈታ ነው። እነሱ ሃገራችንን ከወረሩ ደግሞ ሉአላዊነታችንና ድንበራችን ተደፍረው፣ ህዝባችን ተጨፍጭፎ፣ ሃገራችን ፈርሳ፣ የተረፍነው እንደ ሶርያውያን ሀገር-አልባ ስደተኞች መሆናችን  አያጠራጥርም።  
ክቡሩ እና ውዱ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ፡-
ከላይ የተጠቀሰው ሁኔታ ሃገራችን ውስጥ እንዳይከሰት የውስጥ ችግራችንን ለጊዜው አፍነን፣ ተቻችለን፣ ቢሆንልንም ይቅር ተባብለን፣ (በመንግሥት ላይ ያለን ቅሬታ እንደተጠበቀ ሆኖ) ተባብረንና ተረባርበን ሃገራችንን ከውስጥ እና ከውጪ ጠላት ማዳን አለብን። ሃገር ከሌለ ምንም ነገር የለም። ዝንጀሮ መጀመሪያ የመቀመጫዬን እንዳለችው ነው።  በ4500 ዓመታት የፖለቲካ ታሪካችን ውስጥ እስከዛሬ ድረስ አንዴም እውነተኛ በህዝብ ፍቃድ የተመረጠ መንግሥት ኖሮን አያውቅም። አብዛኛውን ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣን የተያዘው በንጉሣዊ ውርስና በጉልበት ነበር። የንጉሣዊው ውርስ ካከተመ 47 ዓመታት አልፎታል። ከዚያ በኋላ እስከ አሁን ያለው ጉልበታዊው ነው። ጉልበተኛ በየተራ እየመጣ አምባ ሲገንበት ጭቁኑና ግፉው የኢትዮጵያ ህዝብ በድህነት እየማቀቀ፣ በሃዘን ትዕዝብት ሲመለከት ኖሯል። በጉልበት ስልጣን ላይ የወጣ ያው ብዙ ደም ፈስሶ በጉልበት ነው የሚወርደው። ይህ ስልጣንን በጉልበት የመንጠቅ አዙሪት ወይም እሽክርክሪት ከእንግዲህ በኋላ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ  መቆም አለበት።  ዶክተር ዐቢይ የዛሬ ሶስት ዓመት ስልጣን በያዙ ጊዜ፣ #እኛ እንደ ቀድሞዎቹ መሪዎች ህዝብ ሳይመርጠን አምባገነን ሆነን ወንበር ላይ አንዘፈዘፍም። እውነተኛ ዲሞክራሲ ላይ ተመርኩዘን በሃሳብ ልዕልና ከተፎካካሪዎቻችን ጋር ተወዳድረን ከተሸነፍን ለአንዲትም ደቂቃ ሳናመነታ ወንበሩን ላሸናፊው እንለቃለን፤; ሲሉ በአደባባይ ቃል ገብተው ነበር። ከእዛም በኋላ ይህን ቃል ደጋግመው ተናግረውታል። እኔ ቃላቸውን ያጥፋሉ ብዬ አላስብም። የሰብዕናቸውን ክብርም አልጠራጠርም።  ስለዚህ እሳቸው እንዲሸነፉ የምትፈልጉ ሰዎች በምርጫ ካርዳችሁ ተጠቅማችሁ ለምትወዱት ፓርቲ ድምፃችሁን ሰጥታችሁ ከስልጣን አውርዷቸው። እርሳቸው በስልጣን ላይ እንዲቆዩ የምትሹቱ ደግሞ በምርጫ ካርዳችሁ እሳቸውንና ፓርቲያቸውን ምረጡአቸው። ከዚህ ውጪ ያለው ግን  ትርምስንና ነውጥን እንጂ ዲሞክራሲን፣ ሰላምን፣ ፀጥታንና የኢኮኖሚ እድገትን አያመጣም። ከሃገር ጋር የተያያዘ ኩርፊያና ቂም ለሃገር ምንም አይፈይድም። ለተወደዳችሁት፣ ለተከበራችሁትና ለኩሩዎቹ የሃገሬ የኢትዮጵያ ሰዎች የማስተላልፍላችሁ ጥብቅ መልዕክትና አደራ ይሄ ነው። መልእክቴንና አደራዬን ስላነበባችሁልኝና በተግባርም ስለምታውሉአቸው ምስጋናዬ ወደር የለውም።

Read 4300 times