Saturday, 22 May 2021 13:13

ተስፋ ሰጪ የኮቪድ መድሃኒት መገኘቱ ተነገረ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ማላዊ 20 ሺህ ያህል የኮሮና ክትባቶችን በይፋ አቃጥላለች

          አውስትራሊያውያንና አሜሪካውያን ሳይንቲስቶችን ያካተተ አንድ የተመራማሪዎች ቡድን፣ በኮሮና ቫይረስ በተጠቁ አይጦች ላይ ተሞክሮ 99.9 በመቶ ውጤታማ መሆኑ የተረጋገጠና ገና በምርምር ደረጃ ላይ ቢሆንም ሰዎችን በመፈወስ ረገድም ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት ፍቱን የጸረ-ኮሮና ቫይረስ መድሃኒት ማግኘታቸውን ከሰሞኑ እንዳስታወቁ ዥንዋ ዘግቧል፡፡
የአውስትራሊያው ግሪፍዝ ዩኒቨርሲቲና ካሊፎርኒያ ከሚገኘው ሲቲ ኦፍ ሆፕ የካንሰር ምርምር ማዕከል የተውጣጡ ሳይንቲስቶች ከሰሞኑ ይፋ ያደረጉትን የምርምር ውጤት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ሳይንቲስቶቹ አግኝተነዋል ያሉት ጸረ-ቫይረስ መድሃኒት በኮሮና ቫይረስ በተጠቁ አይጦች ላይ ተሞክሮ ቫይረሱን እንዳይባዛ በማድረግና በመግደል ረገድ ውጤታማነቱ 99.9 በመቶ ፍቱን መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
ሲአርኤንኤ በተባለ ሳይንሳዊ መንገድ የሚሰራው መድሃኒቱ በተጠቂዎች አካል ውስጥ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስ ክምችት በ99.9 በመቶ ያህል እንደሚቀንስና፣ ተጠቂዎች መድሃኒቱ ከተሰጣቸው በኋላ በሳንባቸው ውስጥ ምንም የኮሮና ቫይረስ  እንደማይገኝ የምርምር ቡድኑ መሪ ፕሮፌሰር ኒጌል ማክሚላን ጆርናል ኦፍ ሞሎኪዩላር ቴራፒ በተባለው መጽሄት ባሳተሙት የምርምር ውጤት ጽሁፍ ማስታወቃቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ከዚህ ቀደም ታሚፍሉ፣ ዛናሚቪርና ሬምዲስቪርን የመሳሰሉ ጸረ-ቫይረሶች ለኮቪድ ታማሚዎች ሲሰጡ ቢቆዩም፣ በቫይረሱ የመያዝ ምልክቶችን የሚያፋጥኑና ታማሚው ቀደም ብሎ እንዲያገግም የሚያግዙ እንጂ እንደዚህኛው የምርምር ውጤት ቫይረሱን በከፍተኛ ሁኔታ የሚቀንሱና ፈዋሽ እንዳልሆኑም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ፣ ማላዊ የአገልግሎት መስጫ ጊዜያቸው አልፏል ያለቻቸውን ወደ 20 ሺህ የሚጠጉ የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ባለፈው ረቡዕ ማለዳ በመዲናዋ በሚገኘው ካሙዙ ሴንትራል ሆስፒታል ማቃጠሏን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ከውጭ አገር ዘግይተው በመግባታቸው ሳቢያ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው አልፏል ያላቸውን 19 ሺህ 610 የአስትራዜኒካ የኮሮና ክትባቶች በማቃጠል ማስወገዱን የጠቆመው ዘገባው፣ ይህም ህዝቡ በክትባቶቹ ላይ ያለው እምነት እንዲያድግ ያደርጋል ብሎ እንደሚያምኑ የአገሪቱ የጤና ሚኒስትር ቃል አቀባይ መናገራቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
ማላዊ በአፍሪካ ጊዜያቸው ያለፈባቸውን የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች በይፋ በማቃጠል ያስወገደች የመጀመሪያዋ አገር መሆኗን የጠቆመው ዘገባው፣ አገሪቱ ከአፍሪካ ህብረት ካገኘቻቸው 102,000 የአስትራዜኒካ ክትባቶች መካከል 80 በመቶ ያህሉን ለዜጎቿ መስጠቷንም አስረድቷል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ጋር በተያያዘ እንዲራዘም የተደረገውና በመጪው ሃምሌ ወር መጨረሻ ኮሮናን ለመከላከል በሚያስችል ጥብቅ ቁጥጥር እንዲካሄድ የ2020 የቶክዮ ኦሎምፒክ በድጋሚ እንዲሰረዝ የአገሪቱ ዶክተሮች ለመንግስት ጥሪ ማቅረባቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ 6 ሺህ ያህል የህክምና ዶክተሮችንና የጤና ባለሙያዎችን በአባልነት የያዘው የቶክዮ ሀኪሞች ማህበር፣ ባለፈው ማክሰኞ ለአገሪቱ መንግስት አሰባስበው ባስገቡት ፊርማ #ኮሮና አሁንም ስጋት ነው፤ ወረርሽኙ ዳግም ቢያገረሽ በቂ ህክምና ልንሰጥ የምንችለበት ሁኔታ ላይ አይደለም የምንገኘው ስለሆነም የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኦሎምፒኩ በድጋሚ እንዲራዘም በአለማቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ላይ ጫና ሊያደርጉ ይገባል; ሲሉ መጠየቃቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ማህበሩ ከአባላቱ በተጨማሪ ሌሎችም ሃሳቡን እንዲደግፉት በድረገጽ በጀመረው የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ ላይም፣ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ፊርማቸውን በማስፈር ኦሎምፒክ እንዲራዘም መጠየቃቸውን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 3357 times