Saturday, 22 May 2021 12:20

የአሜሪካ ሴኔት የውሳኔ ሃሳብና የኢትዮጵያውያን ተቃውሞ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(7 votes)

       • የሴኔቱ ውሳኔ አሜሪካ በተደጋጋሚ ስትናገረው ከነበረው ጉዳይ ውጪ ምንም አዲስ ነገር የለውም።
       • ውሳኔው ህውኃትን ወደ ስልጣን ለመመለስ የሚደረግ ጥረት አካል ነው።
       • ትናንትና ለኤምባሲዎች የተቃውሞ ደብዳቤ ለማስገባት ተይዞ የነበረው ፕሮግራም ተሰርዟል።
                 
           የአሜሪካ ሴኔት በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ውስጥ እየተካሄደ ነው ያለውን ግጭት አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ ባካሄደው ዝግ ስብሰባ የውሳኔ ሃሳብ አሳልፏል። ውሳኔው አሜሪካ በትግራይ የተካሄደውን ህግ የማስከበር ዘመቻ ተከትሎ፣ ለወራት ስትናገረው ከነበረው ውጪ ምንም አዲስ ነገር የሌለውና ህውሐትን ወደ ቀድሞው ስልጣኑ ለመመለስ እየተደረገ ያለ መፍጨርጨር መሆኑን የፖለቲካ ምሁራን ተናገሩ።
እ.ኤ.አ መጋቢት 9 ቀን 2021 ዓ.ም ለሴኔቱ መቅረቡ በተነገረው የውሳኔ ሃሳብ፡- በትግራይ ክልል የሚካሄደው ግጭት እንዲቆም፣ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ያልተገደበ የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦት እንዲፈቀድ የሚጠይቅ ነው ተብሏል።
ሴኔቱ ከትናንት በስቲያ ባፀደቀው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ቀደም ሲል በቀረቡት የውሳኔ ምክረ ሃሳቦች ላይ ማሻሻያ አድርጓል።
ሴኔቱ ባሳለፈው ውሳኔ ላይ በትግራይ ክልል ከተከሰተው ግጭት በኋላ የፌደራሉ መንግስት ከውጭ አካላት የሚቀርብለትን የእናደራድራችሁ ጥያቄ በተደጋጋሚ ሳይቀበል ቀርቷል ብሏል። በግጭቱም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸውንና የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች ስለመውጣታቸውም ጠቅሷል።
የምክር ቤቱ ውሳኔ 10 ነጥቦችን የያዘ ሲሆን የመጀመሪያው በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው ግጭት በአስቸኳይ ይቁም የሚል ነው። የኤርትራ ጦር በአስቸኳይ ከኢትዮጵያ እንዲወጣና በመላው ትግራይ የኤሌክትሪክ፣ ስልክ፣ የባንክና የኢንተርኔት አገልግሎት በአፋጣኝና ሙሉ በሙሉ እንዲመለሱ፣ የሚሉት ይገኙበታል። ሴኔቱ በዚሁ የውሳኔ ሃሳቡ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን ለማሻሻል ተጨባጭ እርምጃዎችን  እንዲወስድ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈፀሙትን ተጠያቂ እንዲደርግና በቁጥጥር ስር የሚውሉ የህውኃት አባላት በዓለም አቀፍ ህግጋት መሰረት እንዲያዙ ይጠይቃል።
ከዚህ በተጨማሪም በፖለቲካ አመለካከታቸው የታሰሩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ደጋፊዎች፣ ማህበራዊ አንቂዎች እንዲሁም ሃሳብን በነጻነት የመግለፅ መብታቸውን ተጠቅመው የታሰሩ ጋዜጠኞች፣ በብሔራቸው፣ በሚያራምዱት ርዕዮተ ዓለምና የፖለቲካ ወገንተኝነታቸው ሳይለዩ ከእስር እንዲለቀቁም ሴኔቱ ጠይቋል።
በመላው አገሪቱ ተዓማኒነት ያለውና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍልን ያሳተፈ ብሔራዊ ውይይት እንዲካሄድ ጥሪ ያቀረበው ሴኔቱ፤ የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የገንዘብ ሚኒስትር፣ ዩኤስ አይዲ አስተዳዳሪ ከሌሎች የአሜሪካ ፌደራል መ/ቤቶች ጋር በመቀናጀት የኢትዮጵያ መንግስት የኤርትራ መንግስትና ህወሐት ተገናኝተው በመነጋገር ግጭት እንዲያቆም፣ የኤርትራ ጦር እንዲወጣና የሰብአዊ ቀውስ መፍትሄ እንዲሰጠው ጠይቀዋል።
በመጨረሻም ሴኔቱ የአሜሪካ መንግስት ከአለም አቀፍ አጋር አገራትና የተመድ የፀጥታ ምክር ቤትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የቅርብ ትስስር ፈጥረው በአገሪቱ ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ እንዲያበጁ አሳስቧል።
የአሜሪካ ሴኔት ያሳለፈውን የውሳኔ ሃሳብ አስመልክቶ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው  የፖለቲካ ምሁሩ ዶ/ር ደሳለኝ ታዬ ፤ ይህ ውሳኔ በፌደራል መንግስቱና በህወሐት መካከል የተካሄደው ግጭት ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ በአሜሪካ መንግስት ሲንፀባረቅ የቆየ አቋም እንደነበር አስታውሰው ምንም አዲስ ነገር የሌለበት፣ አሜሪካ ስታካሂድ የቆየችውን ህወሐትን ወደ ቀደመ ስልጣኑ የመመለስ ትግል አንዱ አካል ነው ብለዋል።
አሜሪካ በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ ላይ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ጫና ለማሳደርና የአገሪቱን ሉአላዊነት ለመዳፈር ሙከራ ስታደርግ መቆየቷን የጠቀሱት ዶ/ር ደሳለኝ አንድ አገር በአንዲት ሉአላዊት አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ በዚህ መጠን እኔ አውቅላችኋለሁ ማለቱ አገሪቱ ከጀርባዋ ድብቅ ዓላማና አጀንዳ ያላት መሆኑን አመላካች ነው ብለዋል።   የአሜሪካ ከወትሮ በተለየ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ገብታ ያለገደብ መፈትፈቷ ህውኃት እጇ ምን ያህል ረዥም መሆኑን የሚያመለክት ነው ብለዋል- ምሁሩ። “አሜሪካ ዛሬ  እንደ ልቧ የሚታዘዛት መሪ ማጣቷ አንገብግቧታል፤ አሁን መላው ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚቆሙበትና አሜሪካም ሆነች ሌሎች ሃያላን አገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንዲታቀቡ የሚጠይቁበትና እጃችሁን አንሱ የሚሉበት ወሳኝ ሰዓት ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
ይህንኑ የአሜሪካ ሴኔት ውሳኔና ሌሎች ሃያላን አገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት እያደረጉ ያሉትን ጫና የሚቃወምና  ኢትዮጵያውያ በጋራ ሆነው  “እጃችሁን አንሱ” የሚሉበት መርሃ ግብር በትናንትናው ዕለት ተካሂዷል። የዚሁ መርሃ ግብር አካል የነበረውና አሜሪካንን ጨምሮ እንግሊዝና ሌሎች አገራትም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንዲታቀቡ የሚጠይቀውን ደብዳቤ ለየኤምባሲዎቹ የማስገባቱ መርሃ ግብር በትናንትናው ዕለት ሳይካሄድ ቀርቷል። ለዚህም ምክንያቱ ኤምባሲዎቹ ከዚሁ የኢትዮጵያውያኑ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በትናንትናው ዕለት ዝግ መሆናቸውን በመግለፃቸው ነው ተብሏል።
የተቃውሞ ደብዳቤውን ለየኤምባሲዎቹ የማስገባቱ መርሃ ግብር ቢሰረዝም፣ ትናንት መላው ኢትዮጵያውያን አሜሪካንም ሆነች ሌሎች ሃያላን አገራት በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ያሉትን ሉአላዊነትን የሚዳፈር ተግባርና የውስጥ ጣልቃ ገብነትን እንዲያቆሙ የሚጠይቅ ተቃውሞ ተካሂዷል። የህግ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፤ የሴኔቱ የውሳኔ ሃሳብ የህግ ተፈጻሚነት የላቸውም፤ ምክረ ሃሳቦቹ የሴኔቱ አባላት በአንድ ጉዳይ ላይ የጋራ አቋማቸውን የሚያንፀባርቅበት ነው ተብሏል።

Read 12909 times