Saturday, 22 May 2021 12:14

አሜሪካ የኢትዮጵያን ሉአላዊነት እንድታከብር ኢትዮጵያውያኑ ለጆ ባይደን በላኩት ደብዳቤ አሳሰቡ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(3 votes)

   አሜሪካ የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና ነፃነት ልታከብር እንደሚገባና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀውን የህውኃትንና የደጋፊዎቹን አገር የማተራመስ ተግባር በዓይነ ቁራኛ እንድትከታተል፣ የኢትዮጵያ አሜሪካውያን ዜጎች ምክር ቤት ጠይቋል።
ምክር ቤቱ ትናንት ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በፃፈው ደብዳቤ፤ አሜሪካ በኢትዮጵያ የተካሄደው የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ፣ በአገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ላይ የተቃጣ ጥቃትን ለመቀልበስ የተካሄደ መሆኑንና ይህም እርምጃ የትኛውም አገር የዜጎቹን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲል የሚወሰደው እርምጃ መሆኑን ልታጤነውና ልትደግፈው ይገባል ብሏል።
ኢትዮጵያ የዲሞክራሲ አንዱ ማሳያ የሆነውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ጥረት እያደረገች መሆኑን የጠቀሰው የም/ቤቱ ደብዳቤ፤ ይህንን የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሰረት ለማፍረስና ምርጫው እንዳይካሄድ ለማደናቀፍ የሚጥሩ ኃያሎች ግን በብርቱ እየታገሏት መሆኑን አመልክቷል።
ምክር ቤቱ በዚሁ ለፕሬዚዳንቱ  በላከው ደብዳቤ፤ አሜሪካ ኢትዮጵያ ለምታደርገው አገራዊ ምርጫና ለሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ያላትን ድጋፍ እንድትሰጥና በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው የድንበር ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ እንዲሁም በሰሜን የአገሪቱ ክፍል ለሚካሄደው የመልሶ ግንባታና የሰብአዊ ድጋፍ ተግባር አሜሪካ ድጋፏን እንድታደርግ ጠይቀዋል።
 ከ115 ዓመታት በላይ የዘለቀው የአሜሪካና የኢትዮጵያ ወዳጅነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሜሪካ የበኩሏን ሚና እንድትወጣም ምክር ቤቱ ለፕሬዚዳንቱ በጻፈው ደብዳቤ ጠይቋል።

Read 11591 times