Print this page
Thursday, 20 May 2021 00:00

ሽግግር ምርጫና ምሁራን

Written by  ደስታ መብራቱ
Rate this item
(7 votes)

 ከጥቂት ሳምንታት በፊት፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ‘6ኛው ሃገራዊ ምርጫ እና የምሁራን ሚና’ በሚል ርዕስ ያንድ ቀን ውይይት አዘጋጅቶ ነበር። ይህ መድረክ፣ የጋራ ምክር ቤቱ በወቅቱ የሃገራችን ፈተናዎች ላይ ካዘጋጃቸው ተከታታይ መድረኮች አንዱ ነው። ለዚህም፣ የምክር ቤቱ አመራር ሊመሰገን ይገባል። በአዘጋጆቹ እንደተነገረኝ ከሆነ፣ የውይይቱ ግብዣ ለሚመለከታቸው የምሁራን ተቋማት ሁሉ እንዲደርስ ተደርጓል። ነገር ግን፣ የመወያያ ጽሁፍ እንዲያቀርቡ ከተጋበዙት ውጭ፣ በጣት የሚቆጠሩ ምሁራኖች ብቻ ናቸው በውይይት መድረኩ የተገኙት፡፡ ዛሬ ሃገራችን ካለችበት አጣብቂኝ አኳያ፣ የሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ መድረክ በሆነ ተቋም ለተደረገ የውይይት ጥሪ  አዎንታዊ  ምላሽ አለመስጠት እጅግ ግራ የሚያጋባ ከመሆኑም በላይ አሳሳቢም ነው። በመሆኑም፣ በዚህ አጭር ጽሁፍ፣ የሃገሪቱ ምሁራን ከፊት ለፊታችን ባለው የሽግግር ሂደት ሊኖራቸው የሚገባውን ሚና እና የምሁራንን ግብዓት በማጎልበት ረገድ የመንግሥትን ድርሻ ለማመላከት እሞክራለሁ።
እንደሚታወቀው፣ ምሁር ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን በርካታ ጸሐፊዎች በልዩ ልዩ መልኩ ተርጉመውታል። በዚህ ጽሁፍ ማእቀፍ፣ ምሁር የሚለው ቃል በተፈጥሮ ለሁሉም ሰው የተቸረውን የማሰብ ተሰጥኦ (intellect) በዕውቀት አዳብሮ አንድን ምህዳር (system) በጥልቀት የማስተዋል (observe)፣ የመመርመር (research) እና የመፍትሄ አቅጣጫ  (solution) የማመላከት ክህሎት ላለው ሰው የሚሰጥ መጠሪያ ነው። ከዚህ አኳያ፣ ከየትኛውም ዩኒቨርሲቲ በዲግሪ መመረቅም ሆነ ለዓመታት በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መቆየት የተማረ ያስብል እንደሆነ እንጂ የምሁርነት ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም። ከዚህ በተጨማሪም፣ የትኛውም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሳይገቡ ምጡቅ የሆነ ምሁራዊ ሥራ መስራትም ይቻላል። ለዚህም ማረጋገጫ ሩቅ ሳንሄድ፣ ከአራተኛ ክፍል ትምህርቱን አቋርጦ ለዘመናት ሲዘከር የሚኖር ሥራውን ትቶልን ያለፈውን ጋሼ ጳውሎስ ኞኞን ማንሳቱ በቂ ነው። ከዚህ በተቃራኒው፣ የዶክተርና የፕሮፌሰርነት ካባን ተጎናጽፈው ሊጠቀስ የሚችል ዘመን ተሻጋሪ ሥራ ሳይሰሩ የሚያልፉም ይኖራሉ። በማናቸውም የሽግግር ወቅት፣ ምሁራን ያንድን ሃገር መሰረታዊ ችግሮች በመመርመር፣ ከችግሮቹ መውጫ የመፍትሄ አቅጣጫ ማመላከት የሚያስችሉ ዕውቀቶችን የማመንጨት ታላቅ ሙያዊ ሃላፊነት ይኖርባቸዋል። ለሃገር ልማትና እድገት የሚያስቡ መንግስታትም፣ በራሳቸው እምነት ዙሪያ የሚሽከረከሩ ልሂቃን የሚሉትን ብቻ ከመስማት ባሻገር በዕውቀት የታነጸ ትንተና ላይ በመመርኮዝ፣ የመፍትሄ ሃሳብ የሚያመነጩ ምሁራንን ማድመጥ ይጠበቅባቸዋል። እንዲህ ዓይነት የምሁራንና የመንግሥታት መናበብና ትብብር፣ ለማናቸውም አይነታዊ ለውጥና ሽግግር ዋነኛ መሰረት ነው።
ከምህዳራዊ አስተሳሰብ አኳያ፣ ለውጥና ሽግግር ካለፈው፣ ወደ አለው፣ እና ወደሚመጣው መተላለፍ የሚገባውን ምህዳራዊ ተግባር (systemic function) ለማስቀጠል አስፈላጊ የሆነ እና በሁሉም ምህዳር ውስጥ የሚከሰት ሂደት ነው። በዚህ መርህ መሰረት፣ ማንኛውም ዓይነታዊ የሽግግር ሂደት፣ ከነበረው ውስጥ ጎጂውን አስወግዶ፣ በጠቃሚው ላይ ገንብቶ  አዲሱን የማዋለድ (creative destruction) ሂደት በመሆኑ የራሱ የሆኑ የጭንቀትና የምጥ ወቅቶች (moments of perturbation) ይኖሩታል። ሃገራችን ኢትዮጵያ ባሁኑ ወቅት በእንደዚህ ዓይነት ምጥ ውስጥ ትገኛለች። በዕውቀት ላይ የተመረኮዘ የምሁራን ግብዓት፣ ይህንን የምጥና የጭንቀት ወቅት በመቀነሱም ሆነ የአዲስ መጪውን ጤናማነት በመወሰን ረገድ ታላቅ ድርሻ ይኖረዋል። ለዘመናት የሃገራችን ፖለቲካ ልዩ ባህርይ የሆነው የተወራከበ ንግግር (discourse of dissonance) ሃገሪቱን በማያቋርጥ የጥፋት አዙሪት (vicious cycle) ውስጥ እየከተታት ይገኛል። ይህም በበርካታ አካባቢዎች የርስ በርስ ግጭቶችን፣ የሰላማዊ ዜጎች ሞትና መፈናቀልን እያስከተለ ነው።  ከዚህ የጥፋት አዙሪት ወደ ህዳሴ ዑደት (virtuous cycle) ለመሸጋገር የተወራከበው ንግግር በመደማመጥ ንግግር (discourse of resonance) ሊተካ ይገባዋል።  በዚህ ሽግግር ውስጥ፣ ለፖለቲካ ልሂቃኑ ንግግር በዕውቀት ላይ የተመረኮዘ የማጣጣም (harmonization) ግብዓት ሊሰጡ የሚችሉት ከላይ የተጠቀሱት ዓይነት ምሁራን ናቸው። ዛሬ ሃገራችን ኢትዮጵያ ከምትገኝበት ወሳኝ የሽግግር ወቅት አኳያ የአብዛኛው ምሁራኖቻችን ዝምታ አሳሳቢ የሚሆነውም ለዚህ ነው።
ምሁራኖቻችን ይህንን ሃላፊነታቸውን በሚገባ ለመወጣት፣ በተለምዶ ከተጓዝንባቸውና ለችግሮች ይበልጥ መባባስ አስተዋጽኦ ካደረጉ የምርምርና ትንተና ዘይቤዎች ራሳቸውን ማንጻት ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ ውስጥ የመጀመሪያው እርምጃ፣ ባንድ አቅጣጫ በተቀነበበ ትንተና ላይ በመመርኮዝ አቅላይ (simplistic) የመፍትሄ ሃሳብ ከማመንጨት መቆጠብ ነው። ውስብስብ ለሆኑ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ከባቢያዊ ምህዳሮች አቅላይ መፍትሄዎችን መስጠት ችግሩን ይበልጥ የሚያወሳስበው በመሆኑ ከዚህ መቆጠብና ውስብስብነቱን በጥልቅ ገጽታው ለመረዳት መሞከር በጣም አስፈላጊ ነው። ለዚህም እንዲረዳ፣ ችግሮችን በተናጠል ሁነቶችና ዑደቶች ላይ ብቻ ተመርኩዞ ከመተንተን መቆጠብና መዋቅራዊ ምንጮቻቸውንና ከበስተጀርባ ያሉትን አዕምሮአዊ ውቅሮች በጥልቀት መመርመር ያስፈልጋል። ይህንንም ለማሳካት ከየሙያ ሳጥናችን በመውጣት ዘርፈ-ተወራራሽ (transdisciplinary) የሆነ አጠናን ክህሎታችንን ማዳበር ይጠበቅብናል። ከዚህ በተጨማሪ፣ የመፍትሄ ሃሳቦቻችን ከአስታማሚነት ይልቅ በአሻጋሪነት፣ ከችግር ተንታኝነት ይልቅ ሃገራዊ ፋይዳ ባለው መፍትሄ አመንጪነት ሊቃኙ ይገባል። ይህንን ለማሳካትም፣ ከሌሎች ሃገሮች የሚገኙ ተመክሮዎችን ከሃገራዊ እውነታና ጠቃሚ ከሆኑ የሃገር በቀል ዕውቀቶችና ልምዶች ጋር ማዳቀል ያስፈልጋል።
በሌላ በኩል፣ ምሁራኖቻችን ከላይ የተጠቀሱትን ተግባሮቻቸውን በተገቢው መንገድ እንዲወጡ ለማድረግ አስፈላጊው ተቋማዊ ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል። ከሁሉም በፊት፣ መንግሥት ባለፉት ሥርዓቶች ውስጥ እንደታየው፣ ማናቸውንም የምሁራንን እንቅስቃሴ በጥርጣሬ ከዚያም ከፍ ሲል በጠላትነት ከመመልከት አባዜ እራሱን ማላቀቅ ይኖርበታል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ሃገሪቱ ፈጣንና  ውጤታማ በሆነ የሽግግር ሂደት ውስጥ እንድታልፍ ከተፈለገ፣ ነጻ አስተሳሰብ ያላቸው ምሁራን የሚያቀርቧቸውን ሃሳቦችና ሙያዊ ምክሮች በጥልቀት ፈትሾ፣ ጠቃሚውን በተግባር ላይ ማዋል ይጠበቅበታል። ይህንንም ለማሳካት፣ በፖለቲካ ድርጅቶችና መድረኮች የምሁራንን የተናጠል ተሳትፎ (co-optation) ከማጎልበት ባሻገር ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ከመንግሥት ተጽእኖ ነፃ በሆነ አደረጃጀት፣ በወሳኝ የሃገሪቱ የወደፊት አቅጣጫዎች፣ ምልከታቸውን እንዲሰጡ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይኖርበታል። ከዚህ በተጨማሪም፣ በተለያየ መስክ ተደራጅተው የሚገኙ የሙያ ማህበራት (professional societies) ከየመስካቸው አኳያ ለሃገሪቱ ሁለንተናዊ እድገትና ልማት ሊያበረክቱ የሚችሉትን ከፍተኛ አስተዋጽኦ መረዳትና ይህንን እምቅ ሃይል ለመጠቀም የሚያስችሉ ሁኔታዎችን መፍጠር ተገቢ ነው።  
በ2008 በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች የተጀመረው የወጣቶች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሃገራዊ ግዝፈት አግኝቶ፣ የ2010 ዓመተ ምህረቱን ተስፋ ሰጪ ለውጥ ይዞ መምጣቱ ይታወቃል። ይህ የለውጥ ሂደት ባለፉት ሶስት ዓመታት በርካታ የተስፋና የስጋት ሂደቶችን አስተናግዶ፣ አሁን ሌላ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል። ባለፉት ሶስት ዓመታት፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓቢይ አህመድ የሚመራው የለውጥ ቡድን በርካታ ተስፋ ሰጪ የማሻሻያ እርምጃዎች የመውሰዱን ያህል፣ ማድረግ የሚገባውን ባለማድረግ ወይንም ማድረግ የማይገባውን በማድረግ ሲወቀስ ይሰማል። የለውጥ ቡድኑ እንደ ማንኛውም የፖለቲካ ቡድን ሊኖርበት የሚችለው ጉድለትና ድክመት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከአሮጌው የአገዛዝ ሥርዓት የተወረሱ መዋቅራዊ ሸክሞች ጫና (forces of inertia) ፈታኝ እንደሆኑበት በርካታ ምልክቶች አሉ። ይህ፣ አሮጌው ላለመሞት አዲሱ ለመወለድና ለመውተርተር በሚያደርጉት ግብግብ መሃል የሚከሰት ጭንቅና ፈተና በማንኛቸውም ዓይነታዊ የሽግግር ወቅት የሚከሰት ተፈጥሮአዊ ሂደት ነው። እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ለዘመናት በአገዛዝ ሥርዓት ውስጥ ለቆዩ ሃገራት፣ ወደ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር የሚደረግ ሽግግርን ዕውን ለማድረግ በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጥማሉ። ይህ ሊታለፍ የሚችለው የሽግግር ሂደቱን በየደረጃው ሊያጎለብቱ የሚችሉ እርምጃዎችን (incremental steps) በመውሰድ ነው። ለዚህም ነው፣ የሚመጣው ምርጫ መካሄድ፣ አሉት ከሚባሉት ድክመቶቹና ጉድለቶቹ ጋር፣ ለሽግግሩ መጀመር ታላቅ ፋይዳ የሚኖረው።
ይህንን የሃገሪቱን መፃኢ ዕድል በክፍተኛ ሁኔታ ሊወስን የሚችለውን ሽግግር በጥሩ መሰረት ላይ ለማኖር፣ ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በአጠቃላይ፣ በተለይም ደግሞ በሥልጣን ላይ ካለው የብልፅግና ፓርቲ ታሪካዊ የመሪነት ተግባር ይጠበቃል። ከዚህም የመጀመሪያው ተግባር፣ መጪውን ምርጫ የሃገሪቱ አቅምና ተጨባጭ ሁኔታው በፈቀደ መጠን ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ማድረግ ነው። የዚህም ዋነኛ መገለጫው፣ የፌደራልም ሆነ የክልል ምክር ቤቶች የተለያዩ ሃሳቦችና የፖለቲካ አቋሞች የሚወከሉባቸው ሆነው መገኘታቸው ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ በምርጫው ማግስት ሁሉንም የፖለቲካ ድርጅቶችና የማህበረሰብ ተወካዮች የሚያሳትፍ የብሔራዊ መግባባት ውይይት ማደራጀትን ቀዳሚ ተግባር ማድረግ ነው። እንዲህ ዓይነት ውይይት፣ አካታች በሆነ ሂደት የሃገሪቱን መሰረታዊ መዋቅራዊ ችግሮች ለይቶ የመፍትሔ አቅጣጫዎቹም ላይ የጋራ መግባባት እንዲደረስ ከማገዙም በላይ፣ በልዩ ልዩ ምክንያት በምርጫው ያልተሳተፉ ወገኖችም ድምጻቸው እንዲሰማ ያስችላል። በሶስተኛ ደረጃ፣ በምርጫው ማንም ያሸንፍ ማን፣ ከምርጫ በኋላ የሚፈጠረውን መንግስታዊ የሥልጣን አደረጃጀት ከአሸናፊ ፓርቲ ጠቅላይነት (winner takes it all) መንፈስ በተለየ የሁሉንም ህዝብ ድምጽ በሚያስከብር መልኩ ማዋቀሩ ታላቅ አስተዋይነትና ብልህነት ይሆናል። እነኚህ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ዐበይት እርምጃዎች፣ የሃገሪቱን አንድነት ከማጠናከራቸውም በላይ ወደ ተሟላ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገውን ሽግግር በሁነኛ መሰረት ላይ ለመጀመር ያስችላሉ። የወቅቱ የፖለቲካ መሪዎች ይህንን ማድረግ ከቻሉም፣ በኢትዮጵያ የሀገረ መንግሥት ምስረታ ታሪክ ውስጥ በፋና ወጊነት ሲዘከሩ ይኖራሉ።  
በመጨረሻም፣ ታዋቂውና ተወዳጁ የኢኮኖሚክስ ምሁር ዶክተር እሸቱ ጮሌ በ1984 ዓም ባደረገው ታሪካዊ ንግግር፤ እኛ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ የለውጥ አጋጣሚዎች የማግኘታችንን ያህል፣ እነኚህን የለውጥ አጋጣሚዎች ሳንጠቀምባቸው መቅረታችንን አስታውሶ፣ የ1983ቱን የለውጥ ዕድል እንዳናባክን አሳስቦን ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ፣ ያም የለውጥ አጋጣሚ ከመባከን አልፎ በርካታ ጠባሳዎችን ጥሎልን አልፏል። እንደ እኔ እምነት፣ የሃገሪቱ የለውጥ ዕድሎች መባከን አንዱ አቢይ ምክንያት፣ ሁሉም መንግሥታቶቻችን ነፃ አስተሳሰብ ካላቸው ምሁራን ጋር የነበራቸውና ያላቸው መፋታት (disconnect) ነው። ለዚህም በርካታ የታሪክ ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል። ዛሬም ሌላ ታላቅ የሽግግር ዕድል ከፊታችን ተደቅኗል። ይህንንም ዕድል ላለማባከን፣ መጪው መንግሥት የምሁራንን በዕውቀት ላይ የተመረኮዘ ሃሳብና ግብዓት በአግባቡ ለመረዳትና ለመጠቀም በሩን ክፍት ማድረግ አለበት። ምሁራኖቻችንም፣ ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን በሚጠይቀው የዕውቀት ብቃትና ሥነ ምግባር ታንጸው ሃገራቸው የምትጠብቅባቸውን ምሁራዊ ግብዓት ለመስጠት መነሳሳት ይኖርባቸዋል።
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ስታለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፈሰር ሲሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትም ያስተምራሉ።


Read 5417 times