Print this page
Monday, 17 May 2021 10:55

አስፋው የምሩ (ጋሽዬ)፦ የአገር ባለውለታና የታላቅነት ተምሳሌት

Written by 
Rate this item
(13 votes)

  በማኅበረሰባችን ልማድ መሠረት በዕድሜ ታላቅ የሆኑ ሰዎችን (ወንዶችን) ‘’ጋሼ’’ ወይም “ጋሽዬ” ብሎ መጥራት የተለመደ ነው፡፡ ”ጋሼ” ብሎ ”አንተ” ከተከተለ ደግሞ የበለጠ ቀረቤታ መኖሩን ይጠቁማል፡፡ ተማሪዎቹና የአካባቢው ማኅበረሰብ አባላት አብዛኞቹ “ጋሼ” ወይም “ጋሽዬ” እያሉ ይጠሩታል፡፡ መጠሪያ ስሙ አስፋው የምሩ መሆኑን የማያውቁ ብዙ ናቸው።
በ1950ዎቹ መጀመሪያ በዛፍ ጥላ ሥር የተጀመረ የማስተማር ተግባር ከ60 ዓመታት በላይ ቀጥሎ፣ ወደ ሁለት መቶ ሃምሳ  ሺህ ለሚጠጉ ወጣቶች የትምህርት ዕድል ከፍቷል፡፡ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የዝቅተኛው ማኅበረሰብ ክፍል አባላት (እናቶች፣ሕፃናት፣የጎዳና ተዳዳሪዎች) ደግሞ የተለየ ድጋፍ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ ይህንን ያህል ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች ለዚህን ያህል ጊዜ ለማስተማርና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ድጋፍ ለማድረግ የተቻለው ያለ ምንም ቋሚ በጀት መሆኑ ደግሞ እጅግ በጣም ያስገርማል፡፡
በሦስት የተለያዩ ሥርዓተ መንግሥቶች (የንጉሥ፣ የወታደር እና የዘር ፌደራሊዝም) ውስጥ አንድ ዓይነት ዓላማ ማለትም “መሃይምነትንና ድኅነትን መቀነስ” የሚለውን ሃሳብ ይዞ ለመዝለቅ ብዙ ውጣ ውረዶችን ተቋቁሞ ማለፍ እንደሚያስፈልግ መገመት አያስቸግርም፡
“ነብይ በአገሩ…”
ተረቱ “ነብይ በአገሩ አይከብርም” የሚል ቢሆንም፣ ጋሼን በተመለከተ “አይከብርምን” በአይታወቅም” ብንተካው ለእውነታው ይቀርባል፡፡ አብዛኛው ሰው ስለ ጋሼ ማንነትና ሥራዎቹ አያውቅም፡፡ በእርግጥ ለዚህ ነገር ዋናው ምክንያት ጋሼ ራሱ ነው፡፡ ይህንን በተመለከተ በ1964 ዓ.ም በታተመች የመነን መጽሄት ላይ ከዚህ የሚከተለው ሰፍሯል፡
“አስፋው የምሩ የሚሠራውን ሥራ እወቁልኝ የማይል፤ ስለሚሰጠው አገልግሎት እንዲያመሰግኑት ፍላጎት የሌለው በመሆኑ ሥራውን መሥራት እንጂ በሠራተኝነቱ ስሙ እንዲነሳ የማይሻ ሰው ነው፡፡”
ይህ ከላይ የቀረበው ሃሳብ ጋሼን በቅርብ የሚያውቁት፤ ሁሉ በአንድ ቃልና በአንድ ልብ የሚመስክሩት እውነታ ነው።
ሌላው ምክንያት ግን የእኛም የማወቅ ፍላጎት ማነስና የማስተዋወቅ ጥረት ውስንነት ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን በኋላ በዝርዝር እንደምናየው ጋሽየ በአገራችን ከፍተኛ ክብርና ዕውቅና ያለውን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሸልማት ድርጅት “የ 1962 ዓ.ም የትምህርት ዘርፍ’ ተሽላሚ ነበር። ከእኛ በተሻለ የሚያውቁት የዓለም ሕጻናት ደግሞ “የዓለም ሕጻናት ጀግና” ብለው መርጠዉታል፡፡ ይሀንን ሽልማት ኔልሰን ማንዴላና ታዋቂዋ የህጻናትና የልጃገረዶች መብት ተሟጋች ማላይላ ያገኙት ከጋሽዬ በኋላ ነው።
እንደ አስፋው የምሩ (ጋሽዬ) አይነት ብዙም የማይታውቁ ሰዎች እንዴት ለአገርና ለወገን የሚጠቅም ተግባር ማከናወን እንደቻሉ አስፋው የምሩን (ጋሽዬን) በተምሳሌትነት አቅርቦ ማየት ይቻላል፡፡ ጋሼ የሕይወቱን ጥሪ የመለሰበትን መንገድ፣ ያጋጠሙትን ውጣ ውረዶችና የተከተላቸውን የሕይወት መርህዎች መቃኘት ብዙ ያተርፋል፡፡
የሕዝብ ፍቅርና ክብር
ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ላበረከተው ማህበራዊ አገልግሎት ከሕዝቡ ያገኘው የፍቅር ምላሽ ለእሱ ታላቁ ሽልማቱ ነው፡፡ ሁሉም “ጋሼ” የሚለውን እንደታላቅ የፍቅርና የክብር መገለጫና የማዕረግ ስም ይጠቀሙበታል። ተማሪዎቹ “የዕውቀት አባታችን፣” ወላጅ አልባ ሕፃናት “የመንፈስ አባታችን”፣ ዝቅተኛ የማህበረሰብ አባላት “የድሆች አባት” እያሉ ይጠሩታል፡፡ የጎዳና ልጆች  ‘ጋሼ’ እያሉ የእጃቸውን መዳፍ ደረታቸው ላይ በማሳረፍ፣ በልባቸው ውስጥ እንዳለ ያሳዩታል። ታላቅ የጋሼ ሽልማቶች እነዚህ ናቸው፡፡
የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሽልማት
የሽልማቱ መጽሄቱ ላይ የሰፈረው ጽሁፍ እንዲህ ይነበባል፡-
“……እኝህ በአገልግሎት ስሜት የተነሱ ትጉህ ኢትዮጵያ ይህንን ኃላፊነት በፈቃዳቸው ተሸክመው ሥራውን በሚመሩበት ጊዜ፤ ያላንዳች ጥቅም ሰውነታቸውንና ዕውቀታቸውን በሙሉ ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች መስዋዕት አድርገው መድከማቸውን የማስተማር፣ አገልግሎት ኮሚቴና ባላደራዎችም ተመልክተውታል፡፡
“…….ይህንን የመሰለ አገልግሎት እፈጽማለሁ ብሎ ለሚነሳ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ይህ ምሳሌ ኃይልና ብርታትን የሚሰጥ መሆኑን ስለተገነዘበ፤ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የ1962 ዓ.ም የማስተማር አገልግሎት ሽልማት የወርቅ ኒሻንና የምስክር ወረቀት፣ ከ፲ ሺህ የኢትዮጵያ ብር ጋር ለአቶ አስፋው የምሩ እንዲሰጣቸው ወስኗል፡፡
የዓለም ሕፃናት ሽልማት
ይህ ሽልማት በዓለም ላይ ለሕፃናት መብት ታላላቅ ተግባር ላከናወኑ ጀግኖች የሚሰጥ ሽልማት ነው፡፡ ለሽልማቱ የቀሩበት ዕጩዎች የሕይወት ታሪክና የረዷቸው ሕፃናት ታሪክ በፊልም ተቀርጾ ለዓለም ሕፃናት ይቀርብላቸዋል። በዓለም ላይ የሚገኙ ከ40000-50000 የሚቆጠሩ መምህራን ፕሮግራሙን ያስተባብራሉ፡፡
እድሜአቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑት ልጆች በቀጥታ ድምጽ በመስጠት ከቀረቡት 3 ዕጩዎች ሕፃናቱ ልባቸውን የነካውን ሰው ጅግና ብለው ይመርጣሉ፡፡ ምርጫው የሚካሄደው በህፃናቱ ነው፡፡ ሕፃናቱ “ጀግናቸው” አድርገው የመረጡት ሰው የዓመቱ የሕፃናት ጀግና ተበሉ ዓለም አቀፍ እውቅና እና ሽልማት ያገኛል። በዚህ ዓለም አቀፍ ምርጫ የተሳተፉ ልጆች  ከፍተኛው ቁጥር 7.1 ሚሊዮን ነው።
እ.ኤ.አ በ2001 /1993 ዓ.ም/ የዓለም ሕፃናት የመረጡት የእኛውን ጋሼ ነበር። ጋሼ ሽልማቱን በማሸነፍ የዓለም ሎሬት የሚል ማዕረግ ያገኘ ሲሆን  እሱ ግን ማረግና ክብሩን ትቶ “ጋሼ” መባሉን መርጦ የተለመደ ስራውን ቀጠለ።
የሽልማት ሥነስርዓት በስዊድን አገር የሚደረግ ሲሆን ሽልማቱንም የሚሰጡት የስዊድኗ ንግሥት ናቸው፡፡
ማንዴላና ማላይላ
ሽልማቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕፃናትና አስመልክቶ ከሚሰጡ ሽልማቶች በጣም ከፍተኛው ሲሆን ይህንን ሽልማት ኔልሰን ማንዴላ እ.ኤ.አ. በ2005 ዓ.ም አግኝተዋል። እ.ኤ.አ በ2014 ዓ.ም  ደግሞ  የተማሪዎችና የወጣቶች መብት ታጋይ ማላይላ ተሸልማለች ከጋሼ በኋላ ማለት ነው፡፡ ጋሼም የኖቤል ሽልማት እጩ እንዲሆን የቀረበለትን ጥያቄ ሳይቀበል ቀርቷል፡፡

የዓለም አቀፍ ወዳጆች ማኅበር ሽልማት
ጋሼ በጣም ለተቸገሩ ህፃናት መብት እና ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ላበረከተው አስተዋጽኦ ተሸላሚዎች ናቸው፡፡ ከዚህ የዓለም አቀፍ ድርጅት የዕውቅና ሽልማት ተሰጥቶታል፡፡ ሰርተፍኬቱ ላይ እንዲህ ይላል፡-
አስፋው በ10,000 የሚቆጠሩት ችግረኛ ተማሪዎችን በት/ቤቱ ያስተማረ ሊሆን ከነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ የመማር እድሉን ማግኘት የማይችሉ ልጃገረዶች ናቸው፡፡ አስፋው የተቸገሩ ልጆችን ለመርዳትና ወደ ተሻለ ሕይወት ለማምጣት ያደረገው ጥረት ለረዥም ጊዜና አንዳንዴም በጣም አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የተከናወነ ነው፡፡  
“…ዓለም አቀፍ ወዳጆች ማኅበር አስፋው የምሩ ለወላጆች/ሕፃናት መብት ላደረገው ከፍተኛ አስተዋጽኦ  ይህንን የዕውቅና ሽልማት አበርክቶልታል፡፡ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችም የተሰጡት ለሕፃናትና ለእናቶች ያደረገው ማኅበራዊ ድጋፍና ለወጣቶች ላበረከተው የረዥም ጊዜ የትምህርት አገልግሎት ነው፡፡
ስንብት
(ጋሽየ ድምጹን ሳያሰማ ክስልሳ ዓመታት በላይ ለወጣቶች፣ ለእናቶች፣ ለህጽናትና ‘ለጎዳና ልጆች’ ተስፋና ፍቅርን ሲሰጥ እንደኖረ፣ አገርና ሕዝብም ታላቅ ሰው እንዳጡ ሳይታወቃችው፣ ሚያዚያ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ላይመለስ ተሰናበተ። ለእኔ አገራችን ካፈራቻችው ታላላቅ ሰዎች አንዱ ነህ። ፈጣሪ ለነፍሰህ ሙሉ እረፍትን ይስጣት። ለኛም ያንተን መንገድ የምነከተልበተን ጥበብና ልቦና ይስጠን!!)



Read 2543 times
Administrator

Latest from Administrator