Print this page
Monday, 17 May 2021 10:57

የብልፅግና ፓርቲ ራዕይ - 1 ዘላቂ፣ 1 ቀሪ፣ 1 ጊዜያዊ።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

  “የብልጽግና ርዕይ” ተብለው የቀረቡ ሶስት ዋና ዋና ነጥቦች እነሆ። ረዣዥም ዓረፍተ ነገሮች ቢሆኑም፣ ለአፍታ ታግሰን እናንብባቸው።
1ኛ ነጥብ፣ “አቅምን ተጠቅሞ ኑሮን ማደላደልና መገንባት” የሚል ሀሳብ ይዟል።
“የምናልመው የኢትዮጵያ ብልጽግና፣... ቁሳዊ፣ ሰብአዊ፣ እና የማይዳሰሱ ማህበራዊ ሀብቶቻችንን አቀናጅተን በማነፅ የምንፈጥረው አቅም፤… ያም አቅም በተራው የሚፈጥረው ጥሪትና የሚገነባው ሥርዓት፣ የህዝቦቻችንን ሁለንተናዊ መሻት በማሟላት የሚፈጥሩት ተድላንና እርካታን የያዘ፣ ሁለመናዊ ብልጽግና ነው”።
2ኛው ነጥብ፣ “አቅም ባይኖራችሁም፣ ለኑሮ አትቸገሩም” የሚል ሃሳብ አለው።
“ሁሉም ኢትዮጵያዊ፣ የኢኮኖሚ አቅሙ ፈቀደም አልፈቀደ፣ ለመኖር መሰረታዊ የሆኑት ነገሮችን ማግኘት እንዳለበት ብልጽግና ያምናል። ዜጎች ተመጣጣኝ ምግብ፣ መጠለያ፣ ንፁህ የመጠጥ ውኃ፣ መሰረታዊ የጤናና የትምህርት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን አለባቸው ብለን እናምናለን”።
3ኛው ነጥብ፣ “እምቅ አቅማችሁን እንድትጠቀሙና ሃብት እንድታፈሩ አግዛለሁ” የሚል ሃሳብ ይዟል።
“ዜጎች፣ እምቅ ችሎታቸውን በመጠቀም ሀብትን በፍትሀዊነት ለመፍጠርና ለመቋደስ የሚያስችሏቸውን የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች አገልግሎቶች፣ በያሉበት በጥራት ሊደርሳቸው ይገባል ብለን እናምናለን”።
የትኛው ያዛልቃል? የትኛው ይቀራል? የትኛው ለጊዜው ያዋጣል?
ብልጽግና ፓርቲ፣ ለምርጫ ባዘጋጀው ሰነድ፣ ራዕዩን በአምስት ቃላት አቅርቧል - “ኢትዮጵያን፣ አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ማድረግ” በማለት።
ለወትሮ፣ “ብልጽግና” የሚለው ቃል፣ “ባለፀጋ (የፀጋ ባለቤት)” መሆንን፣ ወይም የመሆን ጉዞን ያመለክታል። “የፀጋ ጌታ (በዓለ ፀጋ)” መሆንን፣ ወይም የመሆን አኗኗርን የሚገልፅ ቃል ነው - ከሃብትና ንብረት ጋር የተያያዘ። ነገር ግን፣ ፓርቲው፣ “ብልፅግና” ለሚለው ቃል ሰፊ ትርጉም ሰጥቶታል። “ብልፅግና” ማለት፣ “ቁሳዊ ሃብትን ወይም የንብረት ባለቤትነትን ብቻ” ማለቱ እንዳልሆነ፣ ልብ በሉልኝ ይላል።
በእርግጥም፣ በምሳሌያዊ አነጋገር፣ የቃላትን ትርጉም ማስፋት ይቻላል - “በእውቀት የበለፀገ አእምሮ” እንል የለ! “በሙያ የበለፀገ” ሰውም፣ “ባለሙያ (በዓለ-ሙያ)” ልንለው እንችላለን። እውቀትንና ሙያን፣ ከሃብትና ከንብረት ጋር ማመሳሰላችን ነው።
“በስነ ምግባር የታነፀ፣ ንፁህ ሰብዕና”፤ “በእውቀትና በጥበብ የተገነባ፣ መልካም ባህል” እየተባለም ይገለፃል። ባህልና ሰብዕና፣ መንፈሳዊ ነገሮች ቢሆኑም፤ ከህንፃ ጋር ስናመሳስላቸው፣ ስነምግባርንና እውቀትን ደግሞ፣ እንደ “ግንባታ ግብዓት” ይሆናሉ፣ ማለት ነው።
በዚያም ሆነ በዚያ፣ ብልጽግና ፓርቲ፣ ለራሱ ስያሜ፣.... ወይም “ብልጽግና” ለሚለው ቃል፣ ሰፋ ያለ ትርጉም ሰጥቶታል። ቁሳዊ የኑሮ ብልፅግና፣ የእውቀትና የሙያ ብልጽግና፣ የሰብዕናና የባህል ብልጽግና… በተለያዩ የፖርቲው ሰነዶች ውስጥ፣ የተለያዩ የብልጽግና ገጽታዎች ተጠቃቅሰዋል። ለምርጫ ባዘጋጀው የመወዳደሪያ ሰነድ ደግሞ እንዲህ ይላል።
“ምናልመው የኢትዮጵያ ብልጽግና፣…. ተድላና እርካታን የያዘ ሁለመናዊ ብልጽግና ነው” ይላል - የመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር።
ሁለመናዊ ብልጽግና? ተድላና እርካታ? “ይሄ ነገር፣ ከፖለቲካም በላይ የሰፋና የላቀ ጉዳይ አይሆንም ወይ?” የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። እናስበዋ!
ተድላና እርካታን የያዘ ሁለመናዊ ብልፅግና ውስጥ፣.... ምን የማይካተት ነገር ይኖራል?
ከእውቀትና ከሙያ እስከ ሃብትና ንብረት፣ ከጤንነት እስከ ሰላም፣ ከጨዋነት እስከ ቅንነት፣ ከመከባበር እስከ አድናቆት፣ ከመደጋገፍ እስከ አርያነት፣ እስከ ቢዝነስና ግብይት፣... ምን የማይነካው ነገር አለ?
ከኪነ ጥበብ እስከ ፍቅር፣ ከትምህርት ቤትና ከሃኪም ቤት እስከ ፍርድ ቤትና እስር ቤት፣ ወንጀል ከመከላከልና ከፍትህ እስከ መኪናና አውሮፕላን፣ ከግድብና ከኢንዱስትሪ እስከ ህግና ስርዓት፣ ከሳይንስ የእውቀት ግኝትና ከአዲስ የቴክኖሎጂ ፈጠራ እስከ ነፃነትና መብት፣ በአጠቃላይ ተድላንና እርካታን የያዘ ሁለንተናዊ ብልጽግና፣… ይሄ ከፖለቲካም ያለፈ፣ የስልጣኔ ትርጉም ነው - ሰፊ ትርጉም።
በእርግጥ፣ ከዚህ ሰፊ ትርጉም ጎን ለጎን፣ ዋናው “የብልጽግና” ርዕሰ ጉዳይ፣ “ቁሳዊው የኢኮኖሚና የኑሮ” ጉዳይ እየሆነ፣ በፓርቲው ሰነድ ውስጥ ቢደጋገም አይገርምም።
አዎ፣ የፓርቲው የምርጫ ማኒፊስቶ፣ በመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር በገፅ አንድ፣ ሁለመናዊ ብልጽግናን ይጠቅሳል - በሰፊው። በሌላ በኩል ደግሞ፣ በመጨረሻው ገፅ የመጨረሻው ዓረፍተ ነገርም፣ ስለ ብልጽግና ያወራል። ነገር ግን፣ ኢኮኖሚ ላይ ብቻ ያተኮረ ነው። “የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለአገራችን በመሳብ፣ አገራዊ ብልጽግናችን እውን እንደሚሆን…” እሰራለሁ ይላል - ዓረፍተነገሩ።
እንግዲህ፣ የመጀመሪያና የመጨረሻ ዓረፍተ ነገሮችን ጨምረን፣ ከመሃል ያለውንም የሰነዱ ጠቅላላ ይዘት፣ ዋና ፍሬ ነገሮችን በቅጡ ከመቃኘትታችን በፊት፣ ለዛሬ፣ ራዕዩ ላይ ብቻ ለመፈላሰፍ እንሞክራለን።
ጠቅላላው ሲመነዘር፣ ዝርዝሩ ሲጠቃለል።
ፓርቲው፣ ጠቅላላ እይታውንና አላማውን፣ የጉዞ አቅጣጫውንና መንገዱን፣ “የብልፅግና ርዕይ” በሚል ርዕስ፣ በገፅ1 ያስነብባል። ይህን የሚያፍታቱ ሃሳቦችን ደግሞ፣ በአራት ምዕራፎች አደራጅቶ፣ እስከ ገፅ35 በማቅረብ ያጠናቅቃል።
አራቱ ምዕራፎች፣ 1ኛ ፖለቲካዊ፣ 2ኛ ኢኮኖሚያዊ፣ 3ኛ ማህበራዊ፣ 4ኛ የውጭ ጉዳዮች ተብለው በፈርጅ ሊሰየሙ ይችላሉ። ደግሞስ፣ ሃሳቦች፣ በፈርጅ ተከፋፍለው ካልቀረቡ፣ እጅና እግራቸው፣ ቀንድና ጭራቸው እንዴት ይታወቃል?
በእርግጥ፣ እያንዳንዱ ፈርጅ፣ ለብቻው የተነጠለና የሌላው ባይተዋር ነው ማለት አይደለም። “በውጭ ጉዳይ” ላይ ያተኮረው 4ኛው ምዕራፍ፣ ስለ ሰላምና ፀጥታ ብቻ ሳይሆን፣ ስለ ኢንቨስትመንትና ስለ ኢኮኖሚ እድገትም ያወራል።
በኢኮኖሚ ላይ ያነጣጠረው 2ኛው ምዕራፍ ደግሞ፣ ስለ እርሻና ስለ ኢንዱስትሪ፣ ስለ መስኖና ስለ ኤሌክትሪክ ብቻ ሳይሆን፣ ስለ ውጭ ንግድና ስለ ሰላም፣ ስለ ህግና ስርዓት፣ ስለ ትምህርትና ስልጠናም ይጠቃቅሳል።
ይሄ ጥሩ ነው። ማንኛውም ሃሳብ፣ በፈርጅ የሚከፋፍልና እርስ በእርስም የሚያስተሳስር፣ ቅጥ የያዘና የተዋሃደ መሆን ይገባዋል። አለበለዚያ፣ ገና ከውጥን የቀረ፣ ጅምር የሃሳብ ሙከራ፣ ወይም የብጥስጣሽ አባባሎች የዘፈቀደ ግርግር ሆኖ ይባክናል።
ለማንኛውም፣ የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ መወዳደሪያ ሰነድ፣ በ35 ገፆች፣ በ4 ምዕራፎች፣ በ21 ንዑስ ርዕሶች፣ በ119 ተራ ቁጥሮች በተዘረዘሩ አንቀፆች ተከፋፍሎ የቀረበ ነው። ግን ደግሞ፣ ዋና ዋና የሚላቸውን ሃሳቦች በአንድ ገፅ አዋህዶ አቅርቧቸዋል።
ራዕይን በአራት መመዘኛዎች መፈተሽ።
እንግዲህ፣ “የምናልመው የኢትዮጵያ ብልጽግና….. ተድላንና እርካታን የያዘ ሁለመናዊ ብልጽግና ነው” ብሏል። ይሔ፣ ጥቅል ግቡን ያመለክታል። አላማ፣ ምኞት፣ መድረሻ፣... ልንለውም እንችላለን። purpose, objective, goal, vision…. ከሚሉ ቃላት ጋር ይዛመዳል። telos ወይም end ብለው የሚሰይሙትም አሉ - የግሪክ ፈላስፋዎችን አባባል በማስታወስ።
ግብ ማለት፣ ሌሎች ተግባራትና ነገሮች ያነጣጠሩለት፣ አንዳች ተፈላጊ ነገር ነው። የሌሎች ተግባራት መድረሻ ነው፣ ግብ። ከዚህ አንፃር ሲታይ፣ መጨረሻ ላይ የሚገኝ ነው፤ end ነው። ነገር ግን ደግሞ፣ በቅድሚያ ግባችንን አስበን ካልተነሳን፤ ለስኬት የሚያገለግሉ ተግባራትን ልናከናን አንችልም። ከዚህ አንጻር፣ ግብ፣ የሁሉም ነገር መንስኤ ነው፤ “final cause” ይለዋል አርስቶትል።
“አላማ” በቅድሚያ ከያዝክ ብቻ ነው፤ ተግባርህ ትርጉም የሚኖረው፣ ፋይዳው የሚለካው። ግን ደግሞ፣ ከበርካታ ተግባራት በኋላ ነው፤ አላማህ የሚሳካው፣ እውን የሚሆነው። በሌላ አነጋገር፣ አላማ፣ የጉዞ ቀዳሚ መነሻ የመሆኑ ያህል፣ የጉዞ መድረሻም ነው። end ነው፤ cause ነው። ሁለቱን ገፅታዎች አዳምረን፣ “final cause” እንበል?
በእርግጥ፣ “አላማ”፣ ሁሌ እውን ይሆናል ማለት አይደለም። የታሰበው ግብ፣ በእውን ሊሳካ የሚችለው፤ ከእውነታና ከተፈጥሮ የመነጨ፣ በተግባርም ሊከናወን የሚችል ከሆነ ብቻ ነው። “የምድር ጫፍ፣ ዳርቻው፣ ገደሉ አፋፍ” ድረስ ለመጓዝና አይቶ ለመመለስ የወጠነ ሰው፣ ግቡ ላይ አይደርስም፤ አላማው አይሳካም። ምናልባት፣ በምስራቅ በኩል ሄዶ፣ በምዕራብ በኩል ዓለምን ዞሮ፣ ብዙ ነገር አይቶና አውቆ ሊመለስ ችል ይሆናል፤ እድለኛ ከሆነ። ግን፣ የምድር መጨረሻው ጠረፍ፣ የገደሉ ጫፍ ላይ አይደርስም። የምድር ጫፍ ብሎ ነገር የለምና።
ልክ እንደዚያው፣ “ማራቶንን በአንድ ሰዓት የመሮጥ አላማ”፣ እውን የሚሆን አላማ አይደለም - አሁን ባለው የእውቀት ደረጃ። በሌላ በኩል፣ መኖሪያ ቤትን እንደምሳሌ እንመልከት። በእንጨትና በድንጋይ፣ በምሶሶና በማገር፣ መሰረትና ጣራ፣ ምንን ተክሎና ደርቦ፣ ምንን ፈልጦና ቆርጦ፣ ምንን አገጣጥሞና አጣብቆ….. መኖሪያ ቤት መገንባት እንደሚቻል ይታወቃል። ይህም፣ ለአላማ ስኬት ያስፈልጋል። ያለ እውቀት፣ አላማን ማሳካት አይቻልምና። በአግባቡ ተጣርቶና ተረጋግጦ በቅጡ የተበጀ እውቀት፣…. የግድ መሟላት የሚገባው የስኬት ቅድመሁኔታ ነው። formal cause ይለዋል - አርስቶትል። ጥቅል መንስኤ እንበለው?
“የምናልመው የኢትዮጵያ ብልጽግና፣ …..ተድላና እርካታን የያዘ ሁለመናዊ ብልጽግና ነው” የሚለው ሃሳብ፣ ቀዳሚ መንስኤ ነው።
ለአላማው ስኬት፣ በጥቅሉ ምን ምን መሟላት እንዳለበት አረጋግጦ ማወቅ ደግሞ፣ ሁለተኛው መንስኤ ነው - ጥቅል መንስኤ። የብልፅግና ሰነድም፣ ለአላማው ስኬት፣ ምን ምን መሟላት እንዳለበት ለማመላከት፣ ሁለት ሶስት ነገሮችን ይጠቅሳል። ከዚያም፣....
ኢትዮጵያውያን፣ “አሁን ካለው የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግር ተላቅቀው፣ እንደበለፀጉት አገሮች፣ በተድላና በእርካታ በሰላም የማይኖሩበት ምንም ምክንያት የለም” ይላል - የብልፅግና ራዕይ። አላማው እንደሚሳካ ለማስረዳት፣ የሌሎች አገራትን የብልፅግና ታሪክ በማስረጃነት ይጠቅሳል።
ይሄ ግን፣ በቂ አይደለም።
በአርማታ፣ በሲሚንቶ፣ በብረት፣ በእንጨት... መኖሪያ ቤት አልያም ግድብ መገንባት እንደሚቻል በማወቅ ብቻ፣ የቤት ባለቤት፣ የግድብ ጌታ መሆን አይቻልም። ከማወቅ ባሻገር፣ ለዚያኛው ትንሽ ፕሮጀክት 2ሺ ኩንታል ሲሚንቶ፣ ተለቅ ላለው 20ሺ ኩንታል ሲሚንቶ፣ በተጨባጭ አምርቶ ወይም ገዝቶ መገኘት ያስፈልጋል።
ግንባታ የሚከናወነው፣ “ሲሚንቶ፣ ብረት ወይም እንጨት” በተሰኙ ጥቅል ፍሬ ሃሳቦች አማካኝነት አይደለም። ይልቅስ፣ ወደ የሚጨበጥ ወደ ሚዳሰስ... ወደ ተጨባጭ ግብዓት መሸጋገርና ይዞ መገኘት የግድ ነው። መነሻ አቅም፣... ለእርሻ የሚሆን ዘር፣ ለጉዞ የሚሆን ሰንቅ መያዝ ያስፈልጋል እንደማለት ነው። ተጨባጭ መንስኤ ብለን እንሰይመው? Material cause ይለዋል - አርስቶትል።
ቀዳሚ መንስኤ (አላማ)፣ ጥቅል መንስኤ (እውቀት)፣ ተጨባጭ መንስኤ (ግብአት)፣ ... እነዚህን የግድ ማሟላት ይገባል - አላማ እንዲሳካ። ግን፣ እነዚህ ብቻ፣ በቂ አይደሉም። አላማና ምኞት፣ እውቀትና ዲዛይን፣ ድንጋይና ሲሚንቶ፣ በራሳቸው ጊዜ፣ ግድብ ወይም መኖሪያ ቤት አይሆኑልንም።
ውጤታማ ተግባርን ማከናወን፣ የስራ ጥረትን መጨመር አለብን። ውጤታማ ተግባራዊ መንስኤ፣ አድራሽ አንቀሳቃሽ መንስኤ እንደ ማለት ነው። efficient cause እንዲል አርስቶትል።
ታዲያ፣ አራቱ የስኬት መንስኤዎችን በማፍታታት ለመገንዘብ፣ በፈርጅ ከፋፍለን ማየታችን ጠቃሚ ቢሆንም፣ እርስበርስ የተዛመዱ ገፅታዎች ናቸው።
በአንድ በኩልም፣ አላማን እንደ መሪ እንደ ቀዳሚ መንስኤ፣ ተግባራዊ ስራ ደግሞ እንደ ማድረሻ መንስኤ ልንመለከታቸው እንችላለን።
በሌላ በኩልም፤ እያንዳንዱ ተግባር እንደ ቀዳሚ ሊሆንልን፣ አዳዲስ ግብአቶችን ለመፍጠር፣ አዳዲስ እውቀቶችን ለማግኘት፣ የላቀ አላማን ለመምረጥ መነሻ ሆኖ ሊያገለግለን ይችላል።
በሌላ አነጋገር፣ አላማ፣ እውቀት፣ ተጨባጭ እውነታ፣ የተግባር ወይም የስራ ጥረት... እርስ በርስ የተሳሰሩና የሚመጋገቡ፣ ከተለያየ አቅጣጫ፣ ከተለያየ አንፃር ሊመረመሩ የሚችሉ ናቸው።
አላማን መምረጥ፣ እንደ ቀዳሚ መንስኤ ከማየት አንፃር ነው፣ የብልፅግና ራዕይን ለመዳሰስ ሞከርነው።
“የምናልመው የኢትዮጵያ ብለፅግና... ተድላና እርካታን የያዘ ሁለመናዊ ብልፅግና ነው” ብሏል- የፓርቲው ቀዳሚ ዓረፍተ ነገር። ቀዳሚ መንስኤ ነው።
አላማው በምን በምን እንደሚሳካ ማወቅ፣ ከናካቴውም አላማው ሊሳካ የሚችል መሆኑን አረጋግጦ ማወቅ ያስፈልጋል ብለን የለ! አለበለዚያ ባዶ ቅዠት ይሆናልና። ብልፅግና ፓርቲ፣ ቢያንስ ቢያንስ፣ የብልፅግና አላማ ሊሳካ እንደሚችል አውቃለሁ፤ አረጋግጫለሁ ብሏል - የበለፀጉ አገራትን በምሳሌነት በመጥቀስ። ይሄ ጥቅል መንስኤ ነው - እውቀት ላይ ያተኮረ።
ነገር ግን፣ አላማው፣ በጥቅሉ በምን በምን ሊሳካ እንደሚችል ማወቅ ብቻ በቂ አይደለም። በጥቅሉና በሃሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን፣ “በእውን፣ በየትኛውን ነባር አቅም፣ በየትኛውን ተጨባጭ ግብዓት፤ በየትኛው የጉዞ ስንቅ” የሚል ጥያቄ አለ። “ምን ተይዞ ጉዞ” ይባል የለ!
“አለኝ”፣ “ይዣለሁ” ብለን ለጉዞ የምንተማመንበት “አለኝ-ታ” ይዘን የመገኘት ወይም የመፍጠር ጉዳይ ነው ጥያቄው።
ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው ምላሽ ነው፤ ሦስተኛው መንስኤ - ተጨባጭ የግብዓት መንስኤ። ብልፅግና ፓርቲ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ለስኬት የሚገለግሉ ነባር ግብአቶች፣ ለጉዞ የሚረዱ ተጨባጭ ስንቆች እንዳሉ ይጠቅሳል። ተጨማሪ አቅምና ስንቅ ለማዘጋጀት እንደሚጠቅሙም ያወሳል። ይብዛም ይነስ፣ ነባር አቅምና እስከዛሬ የተፈጠረ ሃብት ይኖራል። በእነዚህም፣ ሌላ ተጨማሪ አቅም ወይም ስንቅ መፍጠር ይቻላል ባይ ነው ፓርቲው።
“...ቁሳዊ፣ ሰብአዊና ማህበራዊ ሃብቶቻችንን አቀናጅተን በማነፅ የምንፈጥረው አቅም”...ይላል ፓርቲው። ይሄ ነው፣ እንደ ስንቅ የተገለፀው። ነባር ሃብት (ነባር አቅም)፣... እና ደግሞ ይህን በማቀናጀት የሚፈጠር አቅም... እንግዲህ፣ ይህን ይህን ደማምረን፣ “የጉዞ ስንቅ ነው፤ ተጨባጭ የግብዓት መንስኤ ነው” እንበለው።
ታዲያ፣ ስንቅና አቅም፣ ለብቻው ከተቀመጠ፣ ያለ አገልግሎት ሻግቶና መክኖ ይቀራል። ስንቅ ለጉዞ ነው። አቅምም፣ ለስራና ለተግባር፣ ለምርትና ለግንባታ ነው።
“ያም አቅም በተራው የሚፈጥረው ጥሪትና የሚገነባው ስርዓት”፣ የብልፅግና አላማን እንደሚያሳካ ይገልፃል - ፓርቲው። ነባር ስንቅንና አቅምን በመጠቀም፤ በተግባር ብልፅግናን እንፈጥራለን፣ የብልጽግና ስርዓትን እንገነባለን ባይ ነው - ፓርቲው። በሌላ አነጋገር፣ ወደ ስኬት የሚያደርስ ውጤታማ ትጋት ያስፈልጋል - (ወደ ስኬት አድራሽ መንስኤ - efficient cause እንዲሉ)። ይህን አሟላለሁ ይላል - ብልፅግና ፓርቲ።
አቅም ባይኖራችሁም አትጨነቁ የሚለው ነጥብስ? ይሄ አያዛልቅም፤ ቢቀር ነው የሚሻል።
ህልውናን የማለምለም አላማ ወይም ምኞት ብቻ የትም አያደርስም። አላማን የሚመጥን እውቀት ያስፈልጋል። አላማ፤ የግል ሃላፊነትን ያስከትላል ማለት ነው - የማወቅ ሃላፊነትን። ተፈጥሯዊ አቅምን፣ ወደ ሙያዊ አቅም ማሳደግን ይጠይቃል - አላማ። ለእርሾ ያህልም ቢሆን፣ አንዳች ቁሳዊ መነሻ አቅምን መፍጠርም፣ የእያንዳንዱ ሰው ሃላፊነት ነው። ይህም ብቻ አይደለም።
መልካም አላማውን ለማሳካት፣ ህይወትን ለማለምለም፣ የአቅሙንና የእውቀቱን ያህል፣  በጥበብና በትጋት መስራት ያስፈልጋል። ይሄም የግል ሃላፊነት ነው - ለየራሱና ከየቤተሰቡ ህልውና ሲል።
ከዚህ ውጪ፤ እህል ውሃ፣ በራሱ ጊዜ ተመርቶ፣ በራሱ ጊዜ በንጽህና ተጣርቶ፣ አይመጣልንም። ማደሪያ ቤት፣ ቅያሪ ልብስ፣…. ያለስራ፣ ከየት ይመጣል? እንደየአቅማችን ሳንሰራ? በመንግስት ድጎማ? ድጎማውስ ከየት ይመጣል? የአቅማቸውን ያህል ከሚሰሩና ከሚያመርቱ ሰዎች በመንጠቅ? እንዲህ አይነት የሶሻሊዝም ዝንባሌ፣ አያዛልቅም።
ለዚህም ነው፤ “ሁሉም ኢትዮጵያዊ፣ አቅሙ ቢፈቅድም ባይፈቅድም፣ የኑሮ መተዳደሪያ ማግኘት እንዳለበት እናምናለን” ብለን ብንናገር፣ ስህተት ላይ የምንወድቀው።
ይልቅስ፣ ሰዎች፣ እንደየአቅማቸውና እንደየእውቀታቸው፣ በትጋትና በስራ ህይወታቸውን ሲያለመልሙ፣ ለሌሎችም ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራሉ። የተቸገሩ ሰዎችን የማገዝ የልግስና አቅምም ይኖራቸዋል። ለዘለቄታው፣ ይሄ መንገድ ነው የሚያዋጣው።
ሦስተኛው ነጥብስ ምን ይላል?
“እያንዳንዱ፣ ተፈጥሯዊ አቅሙን ተጠቅሞ እንዲሰራና ሃብት እንዲያፈራ፣ በራሱ ጥረት ህይወቱን እንዲያሻሽል፣…. የትምህርት እድልን በመፍጠር አግዛለሁ” ብሏል ፓርቲው። ይሄ፣ ለጊዜው ሊያስኬድ የሚችል፣ መካከለኛ ነጥብ ነው።


Read 405 times