Saturday, 15 May 2021 15:19

የጋዜጠኛ አርአያ ተስፋማርያም አዲሱ መፅሐፍ ምን ይዟል?

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(2 votes)

      “በጭራሽ ፖለቲካ ውስጥ መግባት አልፈልግም”

          ጋዜጠኛ አርአያ ተስፋማሪያም “ኢትዮጵ” ጋዜጣ ላይ ከሚሰራበት ጊዜ ጀምሮ ህወሃት/ኢህደዴግ ይሰራቸዋል ያላቸውን ሴራዎችና ሸፍጦች ሲያጋልጥ ቆይቷል። በዚህም የግድያ ሙከራና ጥልቀት ያለው ድልድይ ውስጥ እስከመወርወርና በተዓምር እስከመትረፍ ያሳለፈውን ፈተና ሲናገር ቆይቷል። አሁንም “መታወቅ አለባቸው” ያላቸውን ሌሎች ምስጢሮች “ከሕወኃት ጓዳ” በተሰኘ መፅሀፉ ይዞ ብቅ ሊል ነው። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ  በቅርቡ የትግራይ ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስኪያጅ ሆኖ ከተሾመው ጋዜጠኛ አርአያ ተስፋማሪያም ጋር በአዲሱ መፅሀፉ ዙሪያ፣ በወቅታዊ ጉዳዮችና በአገር አቀፍ ምርጫው ዙሪያ ተከታዩን አጭር ቆይታ አድርጋለች።

           ለረጅም አመታት “የህወኃትን”  ፈፅሟቸዋል ተባሉ ወንጀሎችን በተለያዩ ሚዲያዎች ስታጋልጥ ቆይተሃል። “ከህወኃት ጓዳ” በተሰኘው አዲሱ መፅሐፍህ ምን አዲስ  ነገር ትነግረናለህ?
አሁንም ስለ ህወሃት ያልተነገሩ ብዙ ጉዳዮችና ምስጢሮች አሉ። ከነዛ መካከል ህውሃቶች የራሳቸውን የቅርብ ሰዎች ሳይቀር እንዴት እንዳጠፏቸው፣ የሙስና ቅሌቶችን፣ በፍትህ ላይ ምን አይነት ጣልቃ ገብነት አድርገው ፍትህን ያጣምሙ እንደነበር፣ ሰው ገድለዋል ተብለው ያለአግባብ የተገደሉ ሰዎች ጉዳይ ፣ የእስር ቤት ስቃዮች ወዘተ...ሌሎችም ብዙ  ነገሮች ተካትተውበታል። ይሄ ተሰንዶ ለታሪክና ለትውልድ መቀመጥ ስላለበት በመፅሐፉ ታትሟል።
መፅሐፉ ከወጣ በኋላ ከአንባቢው ማህበረሰብ ምን አይነት ግብረ መልስ (Feed back) ትጠብቃለህ?
ምን መሰለሽ... ይህንን መፅሐፍ ስፅፍ ጥቅም ለማግኘት አይደለም። ጥቅምም አይገኝበትም፤ ከኪሳራ በስተቀር። ነገር ግን ሰው አንብቦ ፍርዱን ለራሱ ነው የሚተወው። ሁለተኛው ነገር አሁን በትልቅ ስልጣን ላይ የሚገኙ አንድ ሰው ቢሯቸው አስጠርተው ምን ብለውኛል መሰለሽ... “አንተ ስትናገራቸውና ስትገልፃቸው የነበሩት ህወኃት ሲፈጽማቸው የነበሩት ነገሮች ለእኛ የማንቂያ ደውሎች ናቸው። እኔም ሆንኩ ሌሎች እንዲህ አይነት  ነገር እንዳንፈፅም፣ ከፈጸምን ደግሞ ምን አይነት ችግር ውስጥ እንደምንገባና ቤተሰባችንንም ምን አይነት አደጋ ውስጥ እንደምንጥል የማንቂያ ደውል ሰጥተኸናል” በማለት ያላቸውን ስሜት ገልጸውልኛል። እንግዲህ መፅሐፉ ማስተማሪያም ማስጠንቀቂያም ነው፤ ሌሎቹ እንደዚያ አይነት ነገር እንዳፈይጽሙ። ስለዚህ ግብረ መልሱ ብዙ ሰው ተምረንበታል የሚል ይመስለኛል።
እንደሚታወቀው ህወኃትን ስትታገል የነበረው ገና ነገሮች በማይደፈሩበት ወቅት ጀምሮ ነው። ትግልህ ህወኃት በአሸባሪነት እስከሚፈረጅበት ጊዜ ቀጥሏል። አሁን ላይ ሆነህ ስለ ህወኃት ስታስብ ምን ይሰማሃል? ትግልህንስ እንዴት ትገልፀዋለህ?
እኔ በሙያዬ ማድረግ የሚገባኝን ነገር ለሀገሬ ለህዝቤ አድርጌያለሁ ብዬ አምናለሁ። በዚህም እረካበታለሁ። እነዚህ ሰዎች ከመጀመሪያው ጀምሮ ለራሳቸው ታማኞች ያልሆኑ፣ ለማንም ሊሆኑ እንደማይችሉ፣ የብዙ ሰው ደም በእጃቸው ላይ ስለመኖሩና ስለሚሰሩት ሴራ  በሚታወቀው ደረጃ ስታገላቸው ኖሬአለሁ። አሁን ላይ እነዚህ ሰዎች ከስልጣንም ከህይወትም ተወግደዋል። የቀሩትም ቢሆን የጦርነት ሳይሆን የሽፍትነት ስራ ነው እየሰሩ ያሉት። በዚህም በሽብርተኝነት ተፈርጀዋል። እነዚህ ሰዎች በፊትም የትግራይ ህዝብ ጠላት ናቸው፤ አሁንም በየከተማው እየገቡ ሰዎችን እየገደሉ፣ በሬና በግ እየዘረፉና ሰው እያፈኑ ነው የሚገኙት። ይህንን ሚደርጉት ደግሞ ብዙ ቦታ ሳይሆን የተወሰነ ቦታ ነው። ተንቤን፣ ኢቲንጮና ተከዜ አካባቢ ሰዎችን እያፈኑ ይወስዳሉ። ይሄን በውስን ቦታ ነው የሚያደርጉት። በብዙ ቦታ ግን ተደምስሰዋል።
በዚህ ሁሉ ነገር የምችለውን ያህል ያቅሜን አበርክቻለሁ። ከዚህ በኋላ እነዚህ የትግራይም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች ብዙ ርቀት አይሄዱምና ከዚህ በኋላ ህዝቡን ወደ ማገዝ፣ ስነ-ልቦናውን ወደ መገንባትና ወደቀደመ የተረጋጋ ኑሮው የመመለስ ስራ ላይ እናተኩራለን ማለት ነው።
ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ህወኃት የሰሜን እዝ መከላከያ ላይ ጥቃት አደረሰ ከተባለበትና ውጊያ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁንም በትግራይ ህዝብ ላይ በርካታ በደሎች፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችና የንብረት ውድመቶች  እየደረሱበት እንደሆነ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችም ሆኑ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሲገልጹ ቆይተዋል። ይህንን የህይወት፣ የንብረትና የስነ-ልቦና  መስዋዕትነት ህዝቡ መክፈሉ እዲቆም በግልህ ምን እንቅስቃሴ እያደረግህ ነው?
በመጀመሪያ ደረጃ የትግራይ ህዝብ ሲሰማ የኖረው አንድ ነገር ነው። ለ30 ዓመት አንድ ነገር ብቻ ነው ሲጋትና ሲሞላ የነበረው። ሌላው ቀርቶ እነሱ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ የተለወጠ ነገር አልነበረም። እና አሁን እኔም ሆንኩ አብረውኝ ካሉት ሰዎች ጋር እያደረግን ያለነው ያለፈውን በማሳየት፣ መጪውንም በመንገርና አሁን ያለውንም በማስረዳት ህወኃት ሲናገርና ሲሰራ የነበረው ትክክል እንዳልነበረ ወይም የተሳሳተ ፕሮፓጋንዳ በመስጠት ያታልላቸው እንደነበረ፣ “እኛ ከሌለን የትግራይ ህዝብ ይጠፋል” እያለና እያስፈራራ፣ ልጆቻቸውን እስከ አራት ትውልድ እንደጨረሰ በመንገርና በማስረዳት ህዝቡ እውነታውን አውቆ ወደተረጋጋ ህይወቱ እንዲመለስ የተቻለንን ጥረት እያደረግን ነው። ይህን ማድረግ የምንችለው ደግሞ በሚዲያ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ሌላው ደስ የሚል ነገር የምነግርሽ፣ ለትግራይ ህዝብ የሚሆን ሁለት የዲያሊሲስ ማሽን የማላውቃቸው ሰዎች ይልኩልኛል። እነዚህን ሰዎች አላውቃቸውም፤ በቲቪ ነበር የሚያውቁኝ። ትግራይ የዲያሊሲስ ማሽን እንደሌለ በሚዲያ ተናግሬ ነበር። እነዚህ ሰዎች በቅርቡ ማሽኖቹን ይልኩልናል። ይሄም በኩላሊት እጥበት ማሽን እጦት ለሚሰቃየው የትግራይ ህዝብ በጥቂቱም ቢሆን እፎይታን ይሰጣል ብዬ፣ ስለማምን በዚህ በጣም ደስ ይለኛል። በሌላ በኩል፤ የኩላሊትም ሆኑ ሌሎች አጠቃላይ መድሃኒቶች ከውጪ አገር በእርዳታ እንዲገቡም ጥሪ እያደረግን ነው። በጦርነቱ ወላጆቻቸውን ያጡ በርካታ ህፃናት ስላሉ ትምህርት፣ የሚያስተምሯቸውን ደጋፊ ወገኖች እየፈለግንም እንገኛለን።
በእርግጥ እኛ ገንዘብ ማሰባሰብም  ሆነ ሌላ ነገር ውስጥ እጃችንን አናስገባም፤ ግን በቀጥታ ሰዎቹ እንዲረዱ ነው የምናደርገው። ከውጪም መድሃኒትን ጨምሮ ሌሎች ቁሳቁሶች ሲመጡ ልንረከብ እንችላለን። ግን ይህን ስናደርግ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ሆነን ነው።  በዚህና መሰል ሁኔታዎች ህዝቡን ለመደገፍና ለማረጋጋት እየተንቀሳቀስን ነው የምንገኘው።
በተለያየ አጋጣሚ ትግራይንና ህዝቡን ከጦርነቱ በኋላ የጎበኙ አካላት የትግራይ ህዝብ በኩርፊያ፣ በቅያሜ እና በአገሩ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንዳለ መታዘባቸውን ሲገልጹ ይደመጣል። አንተ ምን ትላለህ?
በጣም በጣም ተስፋ የማድረግ መንፈስን ሲላበስ አይቻለሁ። ለምሳሌ ከኢሮብ ጫፍ ድረስ ይደውሉልኛል። እንግዲህ ኢሮብን ካወቅሽው ኤርትራ ድንበር ጫፍ ላይ ያለ ነው። ከመቀሌም በየቀኑ መልዕክት  ይመጣል። ስልክ ቁጥር ሁሉ አስቀምጠናል።
እስካሁን አንድም ስድብና ተቃውሞ የለም። ሁሉም” አሁን ነው ሚዲያ ማየት የጀመርነው” ነው የሚለው አሁን ላይ ሲሰሙት የነበረው ነገርና እየሆነ ያለው ነገር ልዩነት እየገባው ነው -ህዝቡ። በፊት “ትግራይ ልትጠፋ ነው፣ ተወረሃል” እያሉ ሲነግሩት ስለነበር በኩርፊያ ውስጥ መሆኑ አይገርምም። ሴኮቱሬ ጌታቸው  ብቻ ነው “መብረቃዊ ጥቃት አደረስንባቸው” ብሎ የተናገረው እንጂ፣ ህውሃት በሚዲያ ለህዝቡ ሲነግረው የነበረው፣ የትግራይ ህዝብ እንደተወረረና ጦር እንደተመዘዘበት ነው። አማራጭ ሚዲያና እውነታ ባላገኘበት ሁኔታ ህዝቡ ቢያኮርፍ አይገርምም። አሁንም ግን፣ ከምርኮኞቹ ጭምር ያገኘነውና ያየነው ተስፋ ደስ የሚል ነው። አሁንም ስራ ይፈልጋል። እናም ተስፋ ሳንቆርጥ ማስተማሩንና ግንዘቤ መፍጠሩን በርትተን እንቀጥላለን።
የትግራይ ቴሌቪዥን መቀሌ በነበረበት ጊዜ ጋዜጠኞቹ ህወኃትን ነበር ሲያገለግሉ የነበረው በሚል ወደ አዲስ አበባ መጥቷል። አንተም ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነህ ተሹመሃል። እስኪ በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ስጠኝ?
ቴሌቪዥኑ አዲስ አበባ የመጣው ለሪፎርም ነው፤ ተመልሶ ሊሄድ ይችላል። አሁን ግን በዚህ ቴሌቪዥን ውስጥ ሊተባበሩ የሚፈልጉ አሉ። በአፍራሽ መንገድም የሚንቀሳቀሱ አሉ። የሚገርምሽ ይሄ ቴሌቪዝን እኮ በመንግስት በጀት ነው የሚንቀሳቀሰው። እነሱ ግን ዞረው መንግስትን ነው ሲወጉ የቆዩት። ደግሞኮ በጣም በተጋነነ መልኩ እስከ 80 ሺ ብር ነው ደሞዛቸው። ነገር ግን እያደረጉ የነበረው መንግስትን ከጀርባ መውጋት ነው።
የእነጌታቸው ረዳን ቪዲዮ እኮ እነሱ ናቸው እየቀረፁ የሚያስተላልፉት። ይሄንንም ደርሰንበታል። እነዚህ ሰዎች ጦርነት እንደሚጀምሩ እርግጠኛ ሆነው እንደነበር የምታውቂው የትግራይ ቲቪና የድምጸ ወያኔ ሙሉ የስቱዲዮ እቃዎችና ካሜራዎች ተጭነው ነው የተወሰዱት። ማይክ እንኳን አላስቀሩም። ስለዚህ ጌታቸው ረዳ እየተቀረፀ ያለው ከዚህ በተወሰደ HD ካሜራ ነው። የሚቀርፀው ደግሞ ተሻለ የሚባል ሰው ነው። ተሻለ የአባቱን ስም አሁን አላስታወስኩትም። ነገር ግን ይህ ሰው ከዚህ በፊት የፋና ም/ስራ አስኪያጅ የነበረ ነው። ሌላው ትግራይ ውስጥ ኢንተርኔት ያለው በስራ አስኪያጁ ቢሮ፣ ትግራይ ቲቪና በከንቲባው ቢሮ ውስጥ ብቻ ነው። ሌላ ቦታ የለም፤ ሌላ ቦታ እየተለቀቀ ያለው አሁን ነው። ባለፈው እሁድ ወደ 50 የሚጠጉ ጋዜጠኞች እዚህ መጥተው አዳማ ኮርስ እየተሰጣቸው ነው። ነገር ግን አንድም ሰው ጥሩ ነገር ሰርቶ አያውቅም። በትግራይ ጦርነቱ ከተካሄደበት ቀን ጀምሮ በመንግስት ላይ አፍራሽ ነገር ሲያደርጉና ሲሰሩ ነው የነበረው። መንግስት ጥፋተኛእንደሆነና ህዝቡ እንደተወረረ አድርገው ነበር የሚያወሩት እንጂ አንድም ቀን ህወኃት ያጠፋውን ጥፋትና በደል ተናግረው አያውቁም።
ጋዜጠኞቹ ይህን ሲያደርጉ የነበረው ጫና ተደርጎባቸው ይሆን ወይስ ሆነ ብለው ነው?
ሆነ ብለው ነው። እንደውም መንግስትን ማገዝና መተባበር የሚፈልጉ ጋዜጠኞች  በአማርኛውም በትግርኛውም ክፍል አሉ። ጥቂት ቢሆኑም ማለቴ ነው። እነዚህ ልጆች እውነት የሆነ ነገር ሰርተው ሲያመጡ አያስተላልፉላቸውም ነበር። አሁን ከጊዜያዊ አስተዳዳሪነታቸው የተነሱትን ዶ/ር አቶ ሙሉ ነጋን ስንጠይቃቸው “ኢንተርቪው በምሰጥ ጊዜ ጦርነቱን ህወሃት እንደጀመረው ፣እንዴት እንደጀመረውና አጠቃላይ ሂደቱን ስናገር፣ ቆርጠው ነው የሚያስተላልፉት” ብለው ነግረውናል። ዶ/ር ሙሉ በፋሲካ ሳምንት በዋለው ቅዳሜ የተናገሩትን አስተላልፈነዋል። ጋዜጠኞቹ የጦርነቱን መንስኤና በመከላከያ ሰሜን ዕዝ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት  በተመለከተ የተናገርኩትን ነገር አንድም ቀን አስተላልፈው አያውቁም ነው ያሉት ዶ/ር ሙሉ። በጋራም ስንነጋገር ጋዜጠኞቹ በግልጽ “መዘገብ አንፈልግም” ብለዋል።
በአገሪቱ ላይ የሚታየው ግጭት መፈናቀልና እልቂት መቼ ነው የሚቆመው ትላለህ? በምርጫው ላይ ያለህ ተስፋ ምን ይመስላል? ምርጫስ አትወዳደርም?
እኔ ምርጫ አልወዳደርም። ፖለቲካ ውስጥም መግባት አልፈልግም። በአጭሩ በጭራሽ ሀሳቡ የለኝም። በአገሪቱ ላይ ለው መከራ ያልፋል፤ እግዚአብሔርም ያግዘናል። ሰላሙን እሱ ያምጣልን፤ ሊነጋ ሲል ይጨልማል የሚባለው ሂደት ላይ ያለን ይመስለኛል። ለሀገሪቱ ክፉ የሚያስቡትም ሰዎች ወደ ልቦናቸው ተመልሰው ማሰብና ማጤን አለባቸው። ምርጫውም በሰላም አልፎ አገሪቱ ወደተረጋጋ ሰላማዊ ሁኔታ ትመጣለች የሚል ተስፋ ነው ያለኝ።Read 3834 times