Saturday, 15 May 2021 15:03

በኬሮድ የጎዳና ሩጫ 360ሺ ብር ለሽልማት ተዘጋጅቷል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

       ከሳምንት በኋላ በወልቂጤ ከተማ ኬሮድ አትሌቲክስ የልማት ማህበር የ15 ኪ ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ የሚያካሂድ ሲሆን ለአሸናፊዎች እና እስከ ስድስተኛ ደረጃ ለሚያገኙ አትሌቶች በጠቅላላው 360ሺ ብር የገንዘብ ሽልማት መዘጋጀቱም ታውቋል። የጎዳና ላይ ሩጫውን ግንቦት 8 ቀን ላይ ለማካሄድ እቅድ የተያዘ ቢሆንም በርካታ ተሳታፊዎች  ከፆሙ በኋላ እንዲካሄድ በመጠየቃቸው  ወደ ግንቦት 15 ዝግጅቱን መዘዋወሩን አዘጋጆቹ በአክብሮት ገልፀዋል፡፡
አሰልጣኝ ተሰማ አብሽሮ ከውድድሩ መስራቾች ጋር ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ ላይ እንዳመለከተው በጉራጌ ዞን ለመጀመርያ ጊዜ በሚደረገው የጎዳና ሩጫ ፀጥታና ጥበቃው አስተማማኝ እንዲሆን የኮቪድ ፕሮቶኮልንም እንዲያሟላ ዝግጅታቸው ጨርሰዋል፡፡ በጎዳና ላይ ሩጫው ታላላቅ አትሌቶች እንዲካፈሉ የሚፈልገው ኬሮድ በመጀመርያው ውድድር በግል ለሚሮጡ፤ ለአዳዲስ አትሌቶች በልዩ ማበረታቻ የተሳትፎ እድል ሰጥቷል፡፡ በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ለሚገኙ ክለቦች እያንዳንዳቸው 5 ወንድ እና 5 ሴት አትሌቶችን እንዲያወዳድሩም በደብዳቤ ጠይቋል፡፡ በተለያዩ ክለቦችና  የአትሌት ማኔጅመንቶች የሚወዳደሩ ስመጥር አትሌቶች በውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት አሳይተዋል፡፡
ኬሮድ አትሌቲክስ የልማት ማህበር ለ15 ኪሜ የጎዳና ላይ ሩጫው ባዘጋጀው   የሽልማት ገንዘብ ዓለም አቀፍ ደረጃ  አሰራር መከተሉን ገልጿል፡፡ በሁለቱም ፆታዎች ለሚያሸንፉት 75,000 ብር  የሚሸለሙ ሲሆን ለሁለተኛ 50,000 ብር፤ ለሶስተኛ 25,000ብር፤ ለአራተኛ 15,000ብር፤ ለአምስተኛ 10,000ብር ና ለስድተኛ ደረጃ 5,000ብር  ይበረከታል፡፡
ታዋቂው የማራቶን አትሌት አየለ አብሽሮ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ በሰጠው አስተያየት እስከታች ወርደው በመስራት  ለአገር ጥሩ የሚሰሩ ተተኪ አትሌቶችን ለማግኘት ውድድሩን አዘጋጅተዋል፡፡  የኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫን ላይ በመመስረት ቀድሞ እና ንቁ ተሳትፎ ያደረጉ ሲሆን እነሱም አትሌት አሰልጣኝ ተሰማ አብሽሮ፤ አትሌት ሙክታር እድሪስ፤ አትሌት ሰለሞን ባረጋ፤ አትሌት አየለ አብሽሮ፤ አትሌት አንዱአምላክ በልሁ፤ አትሌት ጥላሁን ሀይሌ፤ አትሌት ኮከብ ተስፋ ሌሎችም ናቸው፡፡ ውድድሮች ተተኪ አትሌቶችን እንደሚያነሳሱ በማመን ተሰባስበው የጎዳና ላይ ሩጫውን መመስረታቸው አትሌቶቹን ያስመሰግናቸዋል፡፡
በሳምንቱ አጋማሽ ላይ የኬሮድ አትሌቲክስ ልማት ማህበር በኔክሰስ ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለፀው ውድድሩ የሚካሄድበትን የሩጫ መስመር በዓለም አቀፉ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ማህበር (AIMS) ሁለት ጊዜ ተለክቶ ማረጋገጫ ተሰጥቶታል፡፡ የውድድሩ መነሻ ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ፊትለፊት ሲሆን መድረሻው በጉራጌ ባህል ማዕከል ደጃፍ ላይ ይሆናል፡፡ ውድድሩ የከተማውን ህዝብ እንግዳ ተቀባይነት እንደሚያንፀባርቅ፤ ለወጣት አትሌቶች የውድድር እድል በመፍጠር ለተሻለ ስኬት እንደሚያበቃ ታምኖበታል፡፡ ከወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበበር በተደረገ ጥናት የጉራጌ ዞንና አካባቢው ዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን አትሌቶች ለማፍራት ተመራጭ እየሆነ መጥቷል፡፡  የአየር ንብረቱ ልክ እንደእንጦጦ ተስማሚ፤ በአረንጓዴ ተፈጥሮ የተሞላ መልክዓምድር የሚገኝበትና ለአመጋገብም የተመቸ መሆኑም ታውቋል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ በወልቂጤ ከተማ የሚካሄደውን የጎዳና ላይ ሩጫን ኬሮድ አትሌቲክስ ከወልቂጤ ዮንቨርስቲና ከጉራጌ ባህል ማዕከል በጋራ ያዘጋጀው በዞኑ ስፖርቱ እንዲያድግ ከፍተኛ ፍላጎት በመፈጠሩ ነው። በተለይ ከ100ሺ በላይ አባላት ያሉት የጉራጌ ልማት ማህበር በየዓመቱ በክልሉ ለሚካሄዱ የስፖርት እንቅስቃሴዎች ድጋፍ የሚሰጥ ሲሆን በቅርቡ ለቻይናውያን ማረፊያ ተብሎ የተገነባና 6ሄክታር ላይ ያረፈ ካምፕ ለአትሌቶች እንዲጠቀሙበት አስረክቧል፡፡  ኬሮድ 15 ኪ ሜ የጎዳና ላይ ሩጫን  ስፖንሰር በማድረግ ፍቅር ውሃ፤ ቢጂአይ ኢትዮጵያና ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ተሳትፈዋል፡፡
በቀጣይ ኬሮድ አትሌቲክስ የልማት ማህበር በቡታጅራ እና በአዲስ አበባ ከተሞች ተመሳሳይ ውድድሮችንም እንደሚያዘጋጅም ታውቋል፡፡


Read 946 times