Saturday, 15 May 2021 14:40

መንግስት ከምርጫው ጋር ተያያዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ ቀውሶችን ለመቀነስ እንዲሰራ ተጠየቀ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 መንግስት ቀጣዩ ምርጫ ጤናማ በሆነ ድባብ እንዲካሄድና በቅድመ ምርጫም ሆነ ድህረ ምርጫ ሊፈጠሩ የሚችሉ ግጭቶችን መቀነስ የሚያስችሉ ተግባራትን እንዲከናውን የአሜሪካ መንግስት ጠየቀ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በግንቦት 29 መግለጫው፤ ምርጫው በበርካታ አስቸጋሪ ሁኔታዎች መሃል የሚካሄድ እንደመሆኑ ለግጭት መንስኤ እንዳይሆን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብሏል።
በዚህ ምርጫ የፀጥታ ሁኔታን አስተማማኝ ከማድረግ ጎን ለጎን ለፖለቲካ ፓርቲዎች የመሰብሰብ ፣ደጋፊዎቻቸውን በአደባባይ የማግኘት መብትን ጨምሮ መረጃ ማስተላለፍን የሚያቀላጥፍ የማህበራዊ መገናኛ አውታሮችን (ኢንተርኔትን) ከሚገድቡ ተግባራት መንግስት መቆጠብ አለበት ብሏል- በመግለጫው።
የፀጥታ ሃይሎችም ግጭትን ሊፈጥሩ ከሚችሉ እንቅስቃሴዎች እንዲቆጠቡ የጠየቀው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት መግለጫ፤ የአሜሪካ መንግስት ከአለማቀፍ አጋሮቹ ጋር በመሆን ምርጫውን ተከትሎ ሊፈጠሩ የሚችሉ ቀውሶችን ለመቀነስ ይረዳል ያለውን የማህበረሰብ ውይይቶችን ከወዲሁ እያካሄደ መሆኑንም አስገንዝቧል።
በትግራይ ያለው ቀውስ አፋጣኝ እልባት እንዲሰጠውና የኤርትራ ወታደሮች ክልሉን ለቀው ስለመውጣታቸው  ማረጋገጫ እንዲሰጥ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ጠይቋል- በመግለጫው።

Read 10946 times