Saturday, 15 May 2021 14:27

የፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ መልዕክትና የማህበራቱ ምላሽ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ማቲያስ፣ በቪዲዮ አስተላለፈውታል በተባለ መግለጫ፤ #በትግራይ ክልል የዘር ማጥፋት ወንጀል; መፈጸሙን የገለጹ ሲሆን በጉዳዩ ዙሪያ በተደጋጋሚ የሰጡት አስተያየት ለህዝብ እንዳይደርስ መታገዱን ተናግረዋል፡፡
ፓትርያርኩ በዚህ የ14 ደቂቃ የቪዲዮ መግለጫቸው፤ጦርነቱን ተከትሎ በትግራይ ህዝብ ላይ የከፋ ሰብአዊ ጉዳትና ቀውስ መድረሱን አመልክተዋል።
#በትግራይ ክልል እየተሰራ ያለው አረማዊ ስራ እንዲቆም ብዙ ጊዜ ተናግሬለሁ፤ግን ለህዝብ እንዲተላለፍ አልተፈቀደም; ያሉት ፓትርያርኩ፤ በተደጋጋሚ ድምጼ እንዳይሰማ ታፍኛለሁ ብለዋል።
“በኢትዮጵያ በተለይ በትግራይ እየተካሄደ ያለው የአረማዊነት ስራ የህዝብ እልቂትን ያስከተለ ነው ያሉት አቡነ ማቲያስ፤ #ወጣቶች እየተገደሉ ወደ ገደል እየተጣሉ ነው፤ እስካሁንም የግፍ ግድያ እየተካሄደ ነው፤ህዝብ ክፉኛ እያለቀ ነው፣ ሴቶች በግፍ እየተደፈሩ ነው፣ በዚህም በትግራይ ሴቶች ላይ ዘላለማዊ ቁስልና ጠባሳ ነው እየተጣለ ያለው” ብለዋል።
የትግራይ ህዝብ በሁለንተናዊ ሰቆቃ ውስጥ መሆኑን፤ ንብረቱንና ሃብቱን መዘረፉን፣ ለረሃብ እንዲጋለጥ መደረጉን፣ ገበሬዎች እርሻ እንዳያርሱ መከልከላቸውን፣ በአብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ላይ መተኮሱንና ጉዳት መድረሱን፣ መነኮሳት መገደላቸውንና መሳደዳቸውን ፓትርያርኩ ይገልጻሉ - በቪዲዮ መልዕክታቸው፡፡
ፓትርያርኩ 14 ደቂቃ ከ46 ሰኮንድ በሚፈጅ በዚህ ቪዲዮ፤ በአጠቃላይ በትግራይ  እየተፈጸመ ያለው #የዘር ማጥፋት; መሆኑን አመልክተው፤ይሄ ድርጊት የሚቆምበትን መንገድ ሁሉም ሊያፈላልግ ይገባል ብለዋል። “በተለይ የሴቶች መደፈር እጅግ ነውረኛ፣ የቆሸሸ የግፍ ግፍ ስራ ነው” ያሉት ፓትርያርኩ፤ #ይህን ያደረጉ ምን አይነት ፍጥረቶች ቢሆኑ ነው?; ሲሉ ጠይቀዋል።
መከራው ያልደረሰበት የትግራይ አካባቢ እንደሌለ የሚናገሩት ፓትርያርኩ፤#ይህ ሁሉ ሲፈጸም ሌላው ህብረተሰብ ጉዳዩን በቸልታ መመልከቱን; በመጠቆም፣ ግፉን እንዴት መቃወም አቃተን ይላሉ፡፡ ይህን ጉዳይ የዓለም ህዝብ አውቆት አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ የጠየቁት አቡነ ማቲያስ፤ የዓለም አብያተ ክርስቲያናትና መንግስታት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡ ተማጽነዋል።
በሌላ በኩል፤ ከሰሞኑ የተሰራጨው ይህ የፓትርያርኩ የቪዲዮ መልዕክት፣ የግላቸው መሆኑንና  ቅዱስ ሲኖዶስን እንደማይወክል ተገልጧል፡፡
የፓትርያርኩ መልዕክት የግላቸው መሆኑንና በግላቸው ሃሳባቸውን መግለፃቸው ተፈጥሮአዊ መብታቸው መሆኑን ያስታወቀው ማህበረ ቅዱሳን በበኩሉ፤ #የእርሳቸውን ንግግር ፖለቲካዊ ፍላጎትን ለማሳካት እንደ  ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ ሲኖዶሱን ለመከፋፈልና ለማዳከም ብሎም ተቋማዊ አንድነትን ለማናጋት የሚደረገው ርብርብ በእጅጉ የሚያሳዝን ሆኖ አግኝቸዋለሁ; ብሏል- በመግለጫው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ስር የሚገኘው “መንፈሳውያን ወጣቶችና ጎልማሶች ማህበራት ህብረት” ባወጣው መግለጫ፤ የፓትርያርኩ መልዕክት አወዛጋቢ ሊሆን አይገባውም ብሏል። #የትግራይ ጉዳይ ሁላችንም ያነባንበትና ያዘንንበት ነው፤ እሳቸውም የገለጹት ይሄንኑ ነው; ያለው ማህበሩ፤ #ይህ የፓትርያርኩ መልዕክት ትክክል እንዳልሆነ እንዲታሰብ ለምን ተፈለገ?; ሲል ጠይቋል።
ቤተ ክርስቲያኒቱ ብዙ ፈተናዎች እየተጋፈጠች መሆኑን በመዘርዘርም፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ወገኖችና ማህበራት ሁሉ በአንድነት እንዲቆሙ ማህበሩ በመግለጫው ጥሪውን አቅርቧል።

Read 1432 times