Print this page
Saturday, 08 May 2021 14:11

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    ክፍል 1 የአቶ ሌንጮ ለታ የመገንጠል መብት ንድፈ ሐሳባዊ ብዥታ



            “አንቀፅ 39ን አነሳህ አላነሳህ ገፊ ምክንያት ካለ ለመገንጠል የፈለገ መገንጠሉ አይቀርም። ሕዝብ እኮ ያስባል ፣ ያሰላስላል። እኩልነትን የማይቀበል ሀይል እስካለ ድረስ ወደድንም ጠላንም በወረቀት ተፃፈ አልተፃፈ መገንጠል ስራ ላይ ይውላል።”
(አቶ ሌንጮ ለታ፤ ፍልስምና 6 ገፅ 15)
አቶ ሌንጮ ለታ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ያሳዩት የአቋም ለውጥ በተወሰነ ደረጃ የሚደገፍ ነው። ነገር ግን የለውጡ መጠንና ንድፈ ሐሳባዊ ሚዛን  በብዥታዎች የተሞላ ነው ማለት ይቻላል። ማለትም ለውጡ ፅንሰ ሐሳባዊ ግልፅነት(Conceptual Clarity) ይጎድለዋል። ዝርዝር ውስጥ ከገባሁ ፅሁፌ ምናልባትም እስከ አምስት ክፍል ሊዘልቅ ይችላል፣ ነገር ግን እንዳይሰላቻችሁ እያሳጠርኩ በሁለት ወይም ቢበዛ በሦስት ክፍሎች ምልከታዬን አጋራችኋለሁ። (ማጣቀሻ መጽሐፍትን በመጨረሻው ፅሁፌ አስቀምጥላችኋለሁ።) ለአሁኑ አጀማመሬ ይህን ይመስላል፦
1. በእኔ ምልከታ፤ የአቶ ሌንጮ ዕይታ ከመገንጠል ንድፈ ሐሳቦች (Theories of secession) አኳያ ብዥታ ያጠላበት ነው። በአንድ በኩል አንቀፅ 39 ሕገ መንግስቱ ኖረ አልኖረ ጭቆና እስካለ ድረስ መገንጠል አይቀሬ ነው ይሉናል። ነገር ግን በአቶ መለስ ዋና አጋፋሪነት በአንቀፅ 39 ላይ የተካተተው የመገንጠል መብትና አቶ ሌንጮ ያስቀመጡት የመገንጠል ዓይነቶች ከመገንጠል ንድፈ ሐሳብ አኳያ ለየቅል ናቸው። የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት አንቀፅ 39 ንዑስ አንቀፅ 1 የሚለው እንደዚህ ነው፦
“ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ ነው፡፡”
እዚህ ጋ “መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ ነው" የሚለውን አስምሩልኝ። ይህ መብት ለመገንጠል ምናልባት ሂደታዊ ቅድመ ሁኔታዎችን (Procedural requirements) ከማስቀመጥ ባለፈ የመገንጠል ጥያቄን ለማንሳት የሚያስቀምጠው ቅድመ ሁኔታ የለም። ይህ ቅድመ ሁኔታ-አልባ የመገንጠል ጥያቄ የሚመደበው በ”Primary Rights Theory” ውስጥ ነው። ዕውቁ የመገንጠል ንድፈ ሐሳብ አጥኚ “Allen Buchanan” ይህን ቀዳሚ የመገንጠል መብትን ‘A no-fault political divorce’ በማለት ይገልፀዋል። በመቀጠልም በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት መሠረት፤ የመገንጠል መብቱ የተሰጠው ለማን ነው? የሚለውን ጥያቄንም መመለስ ግድ ነው። ማለትም የመብቱ ባለቤት (The Right holder) ማነው? ምላሹ በግልፅ ተቀምጧል። የአንቀፅ 39 ርዕስንና ንዑስ አንቀፅ 5ን መመልከት በቂ ነው፣ መብቱ የተሰጠው ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ነው። በንዑስ አንቀፅ 5 ላይ ደግሞ ለሶስቱም የመብቱ ባለቤቶች የተሰጠው ትርጉም አንድና ወጥ ትርጉም ነው። ከዚህም ባለፈ የየክልሎቹ አከላል ለዚሁ ተመቻችቶ የተሸነሸነ ይመስላል። በ”Primary Right Theory” ሥር የመገንጠል መብቱ ለብሔር ሲሰጥ ንዑስ ንድፈ ሐሳቡ “Ascriptive Group Theory” ተብሎ ይጠራል። በሌላ አንፃር የመገንጠል መብቱ በብሔር ላይ ተወስኖ ሳይሆን ለምሣሌ በመልክዓ ምድር ተሰባጥረው ለሚኖሩ ሕዝቦች ሲፈቀድ ንዑስ ንድፈ ሐሳቡ “Associative Group Theory” ተብሎ ይጠራል።
Now, theoretical categorization of Article 39 is possible. በአጭሩ አንቀፅ 39 የሚመደበው በ”Primary Right theory” ውስጥ በ”Ascriptive Group Theory” ንዑስ ንድፈ ሐሳብ ሥር ነው። ቀደም ሲል በሌሎች ፅሁፎቼ እንደገለፅኩት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የመገንጠል መብትን በዚህ መልኩ አጡዘውት ሕገ መንግስታቸው ውስጥ የከተቱት ሀገራት ሁለት ብቻ ናቸው። የኛዋ ኢትዮጵያና ከካሪቢያን በስተምሥራቅ የምትገኝ ሴንት ኪትስ እና ኔቪስ የምትባል ሚጢጢዋ ባለሁለት ደሴቶች ሀገር (53,000 ሕዝብ ብቻ ነው የሚኖርባት) ናቸው። በነገራችን ላይ “Ascriptive Group Theory” ላይ የተመሠረተ የመገንጠል መብት በዓለም አቀፍ ሕጎችም ሆነ በመገንጠል ንድፈ ሐሳብ አጥኚዎች ዘንድ ቅቡልነት የሌለው ከይሲው የመገንጠል መብት ነው። ይህ ፅንፍ የረገጠው የመገንጠል መብት የሀገርን የወደፊት ሉዓላዊ ሕልውናን ከተገማችነት የሚያፋታ (ዶ/ር ኤርሲዶ እንደሚለው)፣ ሁሌም ዜጎች የሀገራቸውን ነገ በጥርጣሬና በስጋት እንዲስሉ የሚያስገድድ ነው። እዚህ ጋ ሀገራት ሕገ መንግስታቸውን መቅረፅ ያለባቸው ወቅታዊውን ሁኔታ እየተመረኮዙ ነው የሚለውን የአቶ ፋሲል ናሆምን (ደራሲው የእሳቸውንም ቃለ መጠይቅ በመፅሐፉ አካትቷል) አመለካከት መቶ በመቶ መቀበል ያዳግታል። እንደሱ ከሆነ የሕገ መንግስቱ መሻሻልም በጣም ወቅታዊ መሆን አለበት። ለምሣሌ አሁን ባለው ሕገ መንግስት አንቀፅ 39ን ማሻሻል የሚታሰብ አይደለም። ማሻሻያውን ከአስሩ ክልሎች ዘጠኙ ደግፈው ለምሣሌ የሐረሪ ክልል ከተቃወመ ውሳኔው ፉርሽ ይሆናል (Veto power)። በእኔ ዕይታ፤ ለወቅታዊ ችግር ማሻሻያ ለማድረግ እጅግ አዳጋች የሆነውን ግትር ሕገ መንግስት መንደፍ ለቀጣዩ ትውልድ የማይፈታ እንቆቅልሽ እንደማስረከብ ይቆጠራል። ለዚህም ነው አሜሪካኖቹ ሕገ መንግስታቸው ወቅታዊ ሁኔታዎችን ማስተናገድ እንዳለበት ቢያምኑም ለ”Amendment” እና “Flexibility” ክፍት የሚያደርጉት። እነ አቶ ፋሲል ሕገ መንግስቱ ውስጥ አንቀፅ 39 እንዳይሻሻል አድርገው በነሐስ ቁልፍ ከቆለፉበት በኋላ “ወቅቱ አስገድዶን ነው” የሚል ሰበብ የሚያቀርቡት! ዓለም ሁሉ ገፍትሮት ወደ ዳር ያሽቀነጠረውን “Ascriptive Group Theory”ን በብቸኝነት በዓለም አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ውስጥ የከተቱ የወቅቱ ሕገ መንግስት አርቃቂዎች በሰሩት ፀጉረ-ልውጥ ሥራ ሊያፍሩ ዘንድ ይገባል። “The drafters design the constitution, the next generation pays for it.” ያለው ማን ነበር?
እንግዲህ የአንቀፅ 39 ንድፈ ሐሳባዊ ዳራው ከላይ ያስቀመጥኩትን ይመስላል። አሁን ወደ አቶ ሌንጮ የመገንጠል ዕሳቤ ንድፈ ሐሳባዊ መሠረት ምንነት ልወስዳችሁ ነው። መግቢያው ላይ እንደጠቆምኩት፤ አንቀፅ 39 ላይ የተቀመጠው የመገንጠል ንድፈ ሐሳባዊ ምድብና የአቶ ሌንጮ የመገንጠል አተያይ መሳ ለመሳ ናቸው። የአቶ ሌንጮ ለታ የመገንጠል ዕሳቤ ከአንቀፅ 39 በተለየ ቅድመ ሁኔታን በግልፅ ያስቀመጠ ነው። ይህን ቅድመ ሁኔታ እሳቸው መነሻ ላይ “ገፊ ምክንያት” ብለው ካስቀመጡ በኋላ በመቀጠል ገፊው ምክንያት ምን እንደሆነ ያስቀመጡት “እኩልነትን የማይቀበል ኃይል እስካለ ድረስ” በማለት ነው። በሌላ አባባል ጭቆና ባለበት የመገንጠል መብት ሊከበር ዘንድ ይገባል እንደማለት ነው። ይኼኛው አተያይ በ”Remedial Right Theory” ንድፈ ሐሳብ ውስጥ የሚመደብ ነው። ይህም ብቻ አይደለም፣ አቶ ሌንጮ ምንም እንኳን በቃለ መጠይቃቸው እንደ ወትሮው ለኦሮሞ መብት ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያም ሀገረ መንግስት እታገላለሁ ቢሉም ከGroup Theory አንፃር አሁንም እንደ ቀድሞው “Ascriptive” ናቸው። ለዚህም አቋቁመውት የነበረውን የፓርቲ ስም... #የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር;.. መጥቀስ በቂ ነው። ማለትም አሁንም የሚታገሉት ለራሳቸው ብሔር መብት ነው። በ”Remedial Right Theory” ንድፈ ሐሳብ መሠረት፤ ያለ ገደብ በማናቸውም ሁኔታ የተሰጠ የመገንጠል መብት የለም። ጭቆና ሲኖር ብቻ ነው መገንጠል የሚቻለው። ይህን ንድፈ ሐሳብ የሚደግፉ አያሌ ዓለም አቀፍ ምሁራን አሉ (መብቱ በሕገ መንግስቱ ውስጥ ይካተት ወይስ ሌላ መፍትሔ ይፈለግለት? የሚለው ክርክር እንደተጠበቀ ሆኖ) የዓለም አቀፍ ሕጎችም በተወሰነ መልኩ ለዚህኛው ንድፈ ሐሳብ ዕውቅናን ይሰጣሉ።
የአቶ ሌንጮ ለታ ገለፃ ትልቁ ችግር፤ ለየቅል የሆኑትን የመገንጠል መብት ዓይነቶችን በአንድ ቋት ውስጥ አስቀምጠው በጅምላ ማብራራታቸው ላይ ነው። ይህ ንድፈ ሐሳባዊ ጭፍለቃ፣ በመብቱ ትግበራ ወቅት ችግር ፈጣሪ ነው። ስለዚህም አቶ ሌንጮ በዝምታ ወደ “Remedial Right Theory” ካምፕ ከመዛወራቸው በፊት አንቀፅ 39 ላይ (Primary Right Theory) ያላቸውን አቋም ይፋ በማድረግ ብዥታችንን ማጥራት አለባቸው። ለምሣሌ አቶ ሌንጮ ጭቆና በሚኖርበት ወቅት መገንጠል እውን መሆን እንደሚችል ገልፀውልናል። ነገር ግን የመገንጠል ጥያቄ በጭቆና ሰበብ ብቻ ላይነሳ ይችላል። ከጭቆና ክስተት ውጪ የመገንጠል ጥያቄ የሚነሳበት አያሌ ሥነ ልቦናዊ ምክንያቶች አሉ (የሀገራችን የብሔር ፖለቲካ ከሶሻል ሥነ ልቦና አኳያ ትኩረት አግኝቶ ጥናቶች እንዳልተደረጉ መጥቀስ ግድ ይላል።) ከነዚህም ውስጥ አንዱ በዕውቁ ፈላስፋ ሄግል የተተነተነው የዕውቅና (Recognition) ንድፈ ሐሳብ ነው። ብሔሮች ዲሞክራሲያዊ መብታቸው እየተከበረላቸው፣ ምንም ዓይነት ውጫዊ ገፊ ምክንያትም ሳይኖር ኢኮኖሚው ከፈቀደላቸው ሀገር የመሆን ስሜት ውስጣቸው ሊቀሰቀስ ይችላል...በአጭር ቃል የመገንጠልን ጥያቄ የሚያነሳው ብሔር በ”ሀገርነት” መታወቅን “Status”ን ከፍ ማድረጊያ ስልት አድርጎ ሊወስደው ይችላል (በተለይም በልሂቃኑ የሚቀሰቀሰው የ”Political status” ውዝግብ ለአደገኛ ጦርነት የሚያበቃ ድብቅና ድምፅ-አልባ ገፊ ምክንያት ነው።) ሁለተኛው ጭቆና ሳይኖር የመገንጠል ጥያቄ እንዲነሳ በገፊ ምክንያትነት የሚጠቀሰው የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ የስስታምነት ባሕሪይ ነው። ይህ በሶሽዮሎጂ ዲስፒሊን በ”Rational Choice Theory” ሥር የሚጠና የመገንጠል ሰበብ ነው። ለምሣሌ ብዙ የተፈጥሮ ሀብትን በክልሉ አቅፎ የያዘ ብሔር ምንም ጭቆና በሌለበት ሁኔታ የተፈጥሮ ሀብቱን በብቸኝነት ለመጠቀም ካለው የስስታምነት ባሕሪይ (Human Greediness) ተንደርድሮ የመገንጠል ጥያቄን ሊያቀርብ ይችላል።
ከላይ የጠቀስኳቸው ሁለቱ ሥነ ልቦናዊ ገፊ ምክንያቶች ከውስጥ ወደ ውጭ የሚፈተለኩ ናቸው። ከውጭ ወደ ብሔሩ የሚሰነዘሩ አይደሉም። አንቀፅ 39 እነዚህን መብቶች ያከብራል...መገንጠሉ የተፈቀደው “በማናቸውም መልኩ ያለገደብ” ስለሆነ። የአቶ ሌንጮ የ”Remedial Right Theory” ግን ፈፅሞ እንደዚህ ዓይነቱን መገንጠል አይፈቅድም። ስለዚህም ብሔሮች ከጭቆና ውጭ ባሉ ከውስጥ ወደ ውጭ በሚፈነዱ ገፊ ምክንያቶች የተነሳ የመገንጠል መብት ጥያቄን በሚያነሱበት ወቅት የአቶ ሌንጮ ምላሽ ምን ይሆን? ለምሣሌ የኦሮሚያ ክልል ምንም ገፊ የጭቆና ምክንያት በሌለበት በ”Recognition” እና በ”Rational Choice Theory” መነሻነት የመገንጠል ጥያቄን ቢያነሳ የአቶ ሌንጮ አቋም ምን ይሆን? ምናልባት አቶ ሌንጮ አሁን የተነተኑትን የ”Remedial Right Theory”ን መርህ የሚያከብሩ ከሆነ መገንጠሉን ይቃወማሉ፣ ሕዝባዊ አመፁንም የሚቀሰቅሱት መገንጠሉን በመቃወም መሆን አለበት። በተቃራኒው አቶ ሌንጮ “ክልሉ ሀገር መሆን ከፈለገ መብቱ ነው” ካሉ ወደ “Primary Right Theory” ካምፕ ገቡ ማለት ነው። ያኔ “ገፊ ምክንያት” የሚለውን ትንታኔአቸውን ውኃ በላው ማለት ነው። ስለዚህም በእኔ ዕይታ፤ አቶ ሌንጮ ለታ በገለፃቸው ውስጥ የመገንጠል ንድፈ ሐሳብ ብዥታ አጥልቶባቸዋል። የ”Conceptual clarity” እክልም ይስተዋልባቸዋል። ይህን ለማስተካከል እኔ ወዳነሳሁት ዝርዝር ውስጥ ሳይገቡ በአንድና ሁለት ዐ/ነገር ብቻ ግልፅ ማድረግ ይችላሉ። ለምሣሌ “እኔ ሌንጮ አንቀፅ 39 ውስጥ የተቀመጠውን የ”Primary Right Theory” እቃወማለሁ፣ ጭቆና በሌለበት የመገንጠል ጥያቄ ያለገደብ መነሳት የለበትም፣ ይልቁን የምደግፈው የ”Remedial Right Theory”ን ነው” ቢሉን ኖሮ ብዥታው በጠራልን ነበር!
በቀጣዩ ፅሁፌ... አቶ ሌንጮ ያነሱት “ገፊ ምክንያት መለኪያው ምን ይሆን?” “አንቀፅ 39ን አነሳህ አላነሳህ” የሚለው አባባላቸው የቱን ያህል ልክ ነው? አቶ ሌንጮ በጣም አቅላይ (Reductionist) ሆነው በእግረ መንገድ ያስቀመጧቸው ሐሳቦች የዘርፉን ምሁራን በሁለት ጎራ ከፍሎአቸው የሚያነታርኳቸው ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው።



Read 3918 times
Administrator

Latest from Administrator