Print this page
Saturday, 08 May 2021 13:34

ሚያዚያ 27፤ ትልቁ የድል ቀን

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

 ለሁለተኛ ጊዜ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን የቅኝ ግዛቷ ለማድረግ በተነሳች ጊዜ የከፈተችውን ወረራ፣ አባት አርበኞቻችን አምስት ዓመት ሙሉ በዱር በገደሉ ተንከራትተው፣ ደማቸውን አፍስሰው፣ አጥንታቸውን ከስክሰው  አገራችን ነፃነቷ እንደተከበረ እንዲቆይ አድርገዋል። ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለ ሥላሴና አርበኛው በድል አድራጊነት አዲስ አበባ ከተማ የገቡበት ሚያዚያ 27 የድል ቀን ለ80ኛ ጊዜ ባለፈው ረቡዕ ተከብሯል። እንኳን አደረሳችሁ - አደረሰን።
ጣሊያኖች በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን የወረሩት በከፍተኛ ደረጃ የተደራጀ እጅግ የታጠቀ ጦር ይዘው ነው። ለመንገድ ጠረጋና ሥራ ሃምሳ ሽህ ሰው አሰልፈዋል። ይህ ወራሪ ኃይል ስምንት መቶ ሽህ ጠመንጃ፣ ሃያ ስድስት ሽህ ታንክና መኪና፣ ከአንድ ቢሊዮን በላይ ጠመንጃ፣ ወደ ሰባት ሚሊዮን የሚጠጋ የመድፍ ጥይት፣ ሃያ ሶስት ሽህ መትረየስና ወደ ሶስት ሺህ የሚጠጋ መድፍ ያዘጋጀ ሲሆን በዚህ ሁሉ መሳሪያ ተጠቅሞ  ጦሩን የሚመራለት 25 ሺ መኮንኖችና ከአምስት መቶ ሽህ በላይ እግረኛ ሠራዊት አዘጋጅቶ ነበር።
ጦራቸው ወደ ውጊያ ከመግባቱ በፊት አካባቢውን ያሰልላሉ፣ አርበኞች ይደበቁበታል ተብሎ የሚጠረጠረውን ቦታ ከአየር በቦምብ ያስደበድባሉ። እግረኛ ጦራቸው ውጊያ ገጥሞ ጦርነቱ እየከበደው ከሄደ በአዲስ ጦር እንዲተካ ተደርጎ ውጊያውን ያስቀጥላሉ። አዲሱ በአዲስ ኃይልና መንፈስ ተዋግቶ ሲደክም፣ ሌላ ተለዋጭ አዲስ ኃይል እንዲገባለት ያደርጋሉ።
የጣሊያን ጦር አርበኛውን ለማጥቃት ተንቀሳቅሶ ተደጋጋሚ ሽንፈት ባጋጠመው ጊዜ፣ የአካባቢው ሕዝብ አርበኛውን ደግፏል ተብሎ ሕዝቡን ለማደህየትና አርበኛውን መጠጊያ ለማሳጣት ጣሊያኖች ለግጦሽ የተሰማራውን ከብት ሳይቀር በቦምብ ይደበድቡታል። አካባቢውን የመርዝ ጋዝ ይረጩበታል።
የጣሊያን ጦር የትጥቅ ሥጋት አልነበረበትም። መኪና በሚያስገባ አካባቢ በመኪና፣ መኪና በማይደርስበት ቦታ ደግሞ በበቅሎና በፈረስ እንዲቆሰቁስ የተመቻቸለት ነበር።
ባንጻሩ አርበኛው ቅኝ ተገዥነትን ለመቀበል ባለመፈለጉና አገሩ የቅኝ ግዛት ቀንበር ተሸክማ እንድትኖር ባለመፍቀዱ፣ እራሱን በራሱ አነሳስቶ ወደ ነፃነት ትግል  የገባ በመሆኑ፣ ከእርሱ ከራሱ ውጭ የሚያስብለት የሚፈልገውን የሚያሟላለት አልነበረውም። አንድ መሳሪያ ካለው አራት አምስት ጀሌ ይከተለዋል። በውጊያ ላይ በሚገኘው ምርኮ ከጠላት ሬሳ ላይ ከሚገፈፍ መሳሪያ ጆሌው ራሱን ያስታጥቃል። መሪው እየታወቀ ተከታዩ እየበዛ ሲመጣ፣ አካባቢውን በመከለል የእገሌ ወገን ይባልለታል። በዚያ ክልል የሚገኝ ገበሬ አርበኛውን እንደ መንግስት በማየት ከወንጀለኛ እንዲጠብቀው መጠየቅ ይጀምራል። ፍትህ፣ ርትዕ ሰጪ ያደርገዋል። በዚህ ጊዜ የአርበኛው መሪ በሥሩ ላለው ሠራዊት ሥንቅና ትጥቅ የማቅረብ ኃላፊነቱን ይሸከማል።
በአንድ ወቅት ከፍተኛ የሥንቅ ችግር የገጠማቸው ራስ አበበ አረጋይ፤ “ለራስህም ለወገንህም  ነፃነት ስትል እየገደልህ ሙት ብዬ ያሰለፍኩትን አርበኛ ሠራዊት እንዴት በችጋር ልግደለው? የሥንቅና ትጥቅ አቅርቦት የእኛ  የመሪዎቹ ፋንታ እንጂ የወታደሩ አይደለም። ወደ ጠላት ክልልም ቢሆን አገሬውን ተመሳስዬ ገብቼ ስንቅ አመጣሁ” ሲሉ የተናገሩትን መጥቀስ በወቅቱ የአርበኛው መሪዎች የነበረባቸውን ሸክም ለመገንዘብ ይረዳል። አርበኛው ተዋግቶ መሳሪያና ጥይት ይማርካል። በማረከው መሳሪያ ተዋግቶ ድሉን ያረጋግጣል። ከጠላት ነጻ ያደረገውን አካባቢም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሰፋ ይሄዳል።
ኢጣሊያ ለኢትዮጵያ “የምስራቅ አፍሪካ ኢምፓየር” የሚል ስም ከሰጠች በኋላ አገራችንን አራት ቦታ ከፋፈለቻት። አማራ፣ ሀረር፣ ኦሮሞ ሲዳሞና ሸዋ የሚሉ ክፍልፋይ ግዛቶች ተፈጠሩ። ሁሉም የየራሱ ምክር ቤት እንዲኖረው ሲደረግ፣ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ የአፍሪካ ሚኒስቴር ከሚባለው ፈቃድ ማግኘት ይጠበቅበት ነበር። ይህ ክፍፍል ዝም ብሎ የሚራመድ ሳይሆን መረማመጃ እንዲሆነው የዘርና ሃይማኖት ልዩነትን ማስፋፋት፣ እስልምናን በክርስትና ላይ ማነሳሳት፣ ኦሮሞና ሌላውን በአማራው ላይ እንዲዘምት ማድረግን ስራዬ ብሎ የያዘ እንደነበር ማሳወቅ ግድ ነው። የጣሊያኖችን ቅስቀሳ ወደ ተግባር ለመለወጥ አስቸጋሪ ሆኖ የታያቸው የጊንጪ አካባቢ ኦሮሞዎች፣ ወደ ጄኔራል ጀጋማ ኬሎ አባት ተጉዘው ምን ማድረግ እንደሚችሉ ምክር እንደጠየቁ፣ አባ ዶዮ ጥቁርና ነጭ ጤፍ ደባልቀው ሰዎቹ ጥቁር ነጩን እንዲለዩ እንደጠየቋቸው፣ ለመለየት አለመቻላቸውን ባረጋገጡ ጊዜም “ማንን ማን ይገለዋል- ማንን ማን ያጠፋዋል። ከአማራ ያልተጋባና ያልተወለደ ማነው? ልጁን ግደለው እያላችሁኝ እንደሆነ ተረድታችኋል?”  ብለው መጠየቃቸውን፣ ሰዎቹም ስህተቱን ተረድተው መመለሳቸውን ጀኔራል ጃጋማ ኬሎ በህይወት ዘመናቸው ደጋግመው ሲተርኩት እንደነበረ ማስታወስ እወዳለሁ። ዛሬ እንዲህ ብሎ የሚመክርና  የሚያስተምር ሽማግሌ ጠፍቶ ነው እርስ በርስ የምንጠፋፋው፡፡
ሚያዚያ 27 የድል ቀን በዚህ ሁሉ መከራ ታልፎ የተገኘ ፍሬ በመሆኑ፣ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ማየት የድሉን ከፍተኛነት ለመገንዘብ አስፈላጊ ይሆናል፤ ትልቅ የድል ቀን ነውና።

Read 1400 times