Monday, 10 May 2021 00:00

የተዓብዮ ፖለቲካና ህዝበኝነት፤ የአገር ጥፋት

Written by  ደስታ መብራቱ
Rate this item
(4 votes)

   በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ተጠቃሽ ከሆነው የ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ፖለቲካ አንስቶ ለዓመታት ሲባባስ የቆየው የፖለቲካ ምስቅልቅል በአሁኑ ሰዓት የሃገርን ሉዓላዊነትና ቀጣይነት መፈታተን ደረጃ ላይ ደርሷል። በዚህም የተነሳ፣ ለበርካታ ዓመታት በታጣቂ ቡድኖች ተወስኖ የቆየው ግጭትና ጦርነት በየአካባቢው ወደሚከሰቱ የሰላማዊ ዜጎች ጥቃት፣ ሞትና መፈናቀል በመሸጋገር ላይ ነው። ሃገራችን ኢትዮጵያ ከምትገኝበት ልዩ የጂኦ ፖለቲካዊ ቀጠና ጋር በተያያዘ፣ የሃገሪቱ የፖለቲካና  ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለበርካታ ውጫዊ ጣልቃ ገብነት የተጋለጠና ወደፊትም የሚጋለጥ መሆኑ አያጠራጥርም። ይህንን ውጫዊ ትንኮሳና ተጽእኖ በአስፈላጊው ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ዝግጅት የማክሸፉ አስፈላጊነት አያጠራጥርም። ነገር ግን፣ የዚህ ውጫዊ ኃይል ሽንፈትም ሆነ አሸናፊነት በዋነኝነት የሚወሰነው በሃገራዊው ፖለቲካ አረዳዳችንና አያያዛችን መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው። ይህንን ለማድረግም፣ ዛሬ ላለንበት አስቸጋሪ ሃገራዊ የፖለቲካ ፈተና ያበቁንን መሰረታዊ የህመም ምንጮች መረዳትና አስፈላጊውን የእርምት እርምጃዎች ሳይረፍድ መውሰድ ያስፈልጋል።  
ከታሪክ እንደምንረዳው፣ ባላባታዊ የሴራ ፖለቲካ ለረዥም ዘመናት በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ ለነበረው ንጉሣዊ የአገዛዝ ሥርዓት አንዱና ዋነኛው መገለጫ ነበር። በመሆኑም፣ አብዛኞቹ ቀደምት የሥልጣን ሽግግሮች በሴራና ግጭት የታጀቡ ናቸው። ከዚህ የተወረሰ በሚመስል መልኩ፣ ዘመናዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካም ከዚሁ የሴራ ፖለቲካ የነጻ አይደለም። በአሁኑ ወቅት በሃገራችን የተከሰተው አሳሳቢ ሁኔታ ግን፣ ከዚህ ባላባታዊ የሴራ ፖለቲካ በዘለለ ሌሎች ሁለት አደገኛ የፖለቲካ ባህርያት ያለው መሆኑን መረዳትና ከእነኚህ ጋር ተያይዘው የሚረጩ ጎጂ ሃሳቦችን  ማምከን እጅግ አስፈላጊ ነው። እነኚህም፣ የተዓብዮ ፖለቲካ (hubristic politics) እና ህዝበኝነት (populism) ናቸው። የእነኚህ ጎጂ አስተሳሰቦች በቅርቡ ዘመን ፖለቲካችን ውስጥ ገኖ መገኘት ሃገሪቱን በማያቋርጥ የጥፋት ዑደት ውስጥ እንድትዘፈቅ አድርጓታል።   
አብዛኛው የሃገራችን ፖለቲካ፣ የሃገሪቱን ዕውነታ ባንድ አቅጣጫ በተቀነበበ እይታ በመተንተን ሃገራዊው እውነትና መፍትሄው በእኔ እጅ ውስጥ ብቻ ነው ያለው ብሎ ከማመን ይጀምራል። ለህዝብ የመጨረሻ ዳኝነት እስከተገዛ ድረስ፣ ይህ በራሱ የጥፋት ምንጭ አይሆንም። የተዓብዮ ፖለቲካ ግን በዚህ ሳያበቃ፣ ‘የራስን ዕውነት’ በሌሎች ላይ በጉልበት ወደ መጫንና ከዚህ የተለየ አመለካከትና አማራጭ አስተሳሰብ ያላቸውን ወገኖች በኃይል ወደ መጨፍለቅ ያመራል። ይህም፣ የተለያየ አመለካከት ባላቸው የፖለቲካ ቡድኖች መካከል ለሚፈጠር ግጭትና የትጥቅ ትግል ይዳርጋል። እንዲህ ዓይነት የተዓብዮ ፖለቲካ ሁለት መሰረታዊ ምንጮች ይኖሩታል። የመጀመሪያው፣ ከወታደራዊ አቅም ጋር ተያይዞ የሚከሰተው ወታደራዊ ተዓብዮ ነው። ይህም ብዙዎቹን የአፍሪካ ሃገሮች ለፈተና ለዳረጓቸው የነጻ አውጪ ድርጅቶችና ወታደራዊ አምባገነን መንግሥታት መከሰት መሰረት ሆኖ ቆይቷል። ሁለተኛው የተዓብዮ ፖለቲካ ምንጭ፣ በአንድ ወይንም በሌላ ርዕዮተ ዓለም የተቃኘ ተቋማዊ ተረክን በሚያቀነቅኑ የፖለቲካ ልሂቃን የሚራመደው የልሂቃን ተዓብዮ ፖለቲካ ነው። ወታደራዊ ተዓብዮና የልሂቃን ተዓብዮ በተደጋጋፊነት በሚከሰቱበት ጊዜ ከፍተኛ የሃገር ጥፋት እንደሚያስከትሉ በተደጋጋሚ ታይቷል። በ1960ዎቹ በሃገራችን በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው የወታደራዊው ደርግ  ተዓብዮና በ’ተራማጅ ኃይሎች’ ዙሪያ የተሰባሰቡ ልሂቃን ተዓብዮ ያስከተለው ከፍተኛ ጥፋት የዚህ አንዱ ማሳያ ነው። የሚያስገርመው ነገር፣ የተዓብዮ ፖለቲካ መጨረሻው ሃገራዊ ጥፋት ማስከተል ብቻ ሳይሆን እንዲህ አይነቱን ፖለቲካ አራማጅ የሆኑ ድርጅቶችንም ይዞ መጥፋቱ ነው።
ሁለተኛው ከፍተኛ አደጋ የሚመነጨው በአንዳንድ የፖለቲካ ቡድኖች ከሚራመደው የህዝበኝነት ፖለቲካ ነው። እዚህ ላይ፣ በርካታ ፖለቲከኞች፣ በመካከላቸው ያለውን መሰረታዊ ልዩነት ሳይረዱ፣ ህዝበኝነትን ከህዝባዊነት ጋር ሲያምታቱት ይስተዋላሉ። የህዝበኝነት ፖለቲካ በአብዛኛው የሚመነጨው ባንድ የታሪክ አጋጣሚ የተከሰቱና ከማንነት ጋር የተያያዙ የመበደልና የመጠቃት ሁነቶችንና ሂደቶችን ቁንጽልና ስሜታዊ በሆነ መንገድ ከመተንተን ነው። ይህም ባብዛኛው የሚገለጸው፣ የዚያን ማህበረሰብ ስሜት ሊኮረኩሩ የሚችሉ ተቋማዊ ተረኮችን በማበልጸግና በራስ አምላኪነት (narcissistic) ስሜት የተቃኙ መሪዎችን በመፍጠር ነው። የዚሁ ሂደት ሌላኛው አካልም አንድን የማህበረሰብ ክፍል በጠላትነት መፈረጅና ያንን ማህበረሰብ የጥቃት ኢላማ ማድረግ ነው። ሌላው መገለጫው፣ የአንድን ማህበረሰብ ታላቅነት በመስበክ ሌሎች ማህበረሰቦች በበታችነትና ተገዢነት ስሜት እንዲንበረከኩ ጫና መፍጠር ነው። እንዲህ ዓይነቱ የህዝበኝነት አመለካከት በበርካታ ሃገሮች ውስጥ በነበሩና አሁንም ባሉ አክራሪ ብሔረተኛ ቡድኖች ውስጥ የሚከሰትና ዓለማችንንም ለከፍተኛ ጥፋትና ውድመት የዳረገ ነው። እዚህ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነጥብ፣ ከማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋት ጋር በተያያዘ፣ ህዝበኝነት የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን አዲስ ፈተና እየሆነ መምጣቱን ነው። ይህ ፈተና፣ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ገና ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሻገር ለሚታትሩት ብቻ ሳይሆን የደረጀ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ገንብተናል ለሚሉት ሃገሮችም ታላቅ ፈተና በመሆን ላይ ይገኛል። በዚህም የተነሳ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከፍተኛ የህዝበኝነት ስሜት ያላቸው መሪዎች አሜሪካንን ጨምሮ በተለያዩ የበለጸጉ ሃገሮች ወደ ሥልጣን ሲመጡ ታይተዋል።
እነኚህ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት የተዓብዮ ፖለቲካና ህዝበኝነት በራሳቸው ከፍተኛ ፈተና የሚደቅኑ ሲሆኑ፣ ሁለቱ ተጣምረው በሚከሰቱበት ጊዜ አንድን ሃገር ወደ ከፍተኛ ጥፋትና ውድመት እንደሚከቱ በታሪክ ተደጋግሞ ታይቷል።  ለዚህም፣ የአይሁድን ዘር በዋነኛ ጠላትነት በፈረጀው የአሪያን ዘር ታላቅነትና በወታደራዊ ኃያልነት የተቀነቀነው የጀርመን ተዓብዮ ፖለቲካ ያስከተለው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ትቶት የሄደውን ከፍተኛ ጥፋትና ውድመት መጥቀስ ይቻላል። ወደ ሃገራችን የቅርብ ጊዜ ሁኔታ ስንመጣም፣ የአማራውን ህዝብ በጠላትነት ፈርጆ የተነሳው የትግራይ ብሔረተኛነት ከህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ወታደራዊ ተዓብዮ ጋር ተጣምሮ ያስከተለውን ከፍተኛ ሃገራዊ ጥፋት መመልከቱ በቂ ነው። አሳዛኙ ነገር፣ ከ1960ዎቹ ውድቀቶቻችንም ሆነ ከቅርቡ ጊዜ ሃገራዊ ጥፋት ሳንማር፣ ዛሬም በፖለቲካዊ ተዓብዮና በህዝበኝነት የታጠሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ቡድኖች በርክተው መታየታቸው ነው። ይህም ሁኔታ፣ ለበርካታ ዓመታት የተለያዩ የፖለቲካ አመለካከት ባላቸው ታጣቂ ቡድኖች መካከል ተወስኖ የቆየው ወታደራዊ ግጭት፣ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ ህጻናትን፣ ሴቶችንና አዛውንቶችን ወደ ማጥቃት ተሸጋግሯል። የእንደዚህ አይነቱ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ዋነኛ ግቡ በሥልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ በህዝባዊ ተቃውሞ ማውረድ ወይንም ወደ ድርድር ማምጣት እንደሆነ ሲነገር ይሰማል። ነገር ግን፣ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሃገር ውስጥ ይህ አይነቱ አካሄድ የፖለቲካ ግብግቡን ማንም ሊቆጣጠረው ወደ ማይችል የእርስ በእርስ ጦርነት ሊያሸጋግር እንደሚችል ሁሉም ወገን ሊረዳው ይገባል። ይህ ደግሞ፣ ሁሉንም ለህዝብ ቆመናል የሚሉ የፖለቲካ ቡድኖችን፣ እንወክለዋለን የሚሉትን ህዝብና ሃገርን ወደ ከፍተኛ ጥፋትና ውድመት ይከታል።   
ከእንዲህ ዓይነቱ ሃገራዊ ጥፋት ለመዳንና ለማንኛውም ዜጋ በህይወት የመኖርና የሰብዓዊ መብት መከበር፣ መንግሥት የሚከተሉትን አበይት ተግባሮች ማከናወን ይኖርበታል። የመጀመሪያው፣ በራሳቸው ጠባብ የሥልጣን ፍላጎት የታወሩትንና የባዕዳን መጠቀሚያ የሆኑትን በተረኮቻቸው ከተሳሳቱት ወገኖች በመለየት በፖለቲካ ነጋዴዎቹ ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ይሆናል። በሁለተኛ ደረጃ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሎች መካከል ለሚፈጠሩ ግጭቶች መባባስና ለሰላማዊ ዜጎች ስጋት ምክንያት በመሆን ላይ የሚገኙትን ልዩ ኃይሎችንና ኢ-መደባዊ አደረጃጀቶችን፣ ሃገራዊ ደህንነትንና የህዝቦችን መብት በሚያስከብር መልኩ እንዲዋቀሩ ማድረግ ይሆናል። በተለይም፣ እነኚህን ልዩ ኃይሎች በመጠቀም የክልል መንግሥታት በክልል ወሰኖች አካባቢ አዲስ የፖለቲካ ዕውነታ ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት በአስቸኳይ እንዲቆም ማድረግ ያስፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ፣ በማናቸውም ክልል ውስጥ ለሚከሰት የሰላማዊ ዜጎች ህይወት መጥፋትና መፈናቀል ሊኖር የሚገባውን የክልልም ሆነ የአካባቢ አስተዳደር ተጠያቂነትን አጠናክሮ ማስፈን ይገባል። ከሁሉም በላይ፣ የሃገራዊ አንድነትና ሉዓላዊነት መጠበቅ ዋነኛው ዋስትና የሆነውን የሃገር የመከላከያ ኃይላችንን ከማናቸውም የፖለቲካ ተጽአኖ ነጻ እንዲሆን ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት አጠናክሮ በመቀጠል ለማናቸውም የተዓብዮና ህዝበኝነት ፈተና እንዳይጋለጥ መከላከል ይገባል። ምክንያቱም፣ የመከላከያ ኃይላችን የሀገራዊ ሉዓላዊነታችን የመጨረሻው ዋስትናችን ነውና።
በሌላ በኩል፣ በሃገሪቱ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከላይ የተጠቀሱትን መንግስታዊ ተግባራት ከመደገፍ ባሻገር፣ በማናቸውም የሃገሪቱ አካባቢ በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚከሰቱ ጥቃቶችን ያለ አንዳች ወገናዊነትና ህዝበኝነት፣ የማንኛውንም ዜጋ በህይወት የመኖር ሰብዓዊ መብት መከበርን መሰረት በማድረግ ሊያወግዙትና ሊታገሉት ይገባል። ከዚህ በተጨማሪም፣ ከመጪው ምርጫ ጋር ተያይዞ የሚያካሂዷቸውን ቅስቀሳዎች ቀደም ሲል ከተጠቀሱት የተዓብዮ ፖለቲካና ህዝበኝነት ህጸጾች የነጻ እንዲሆን መጣር ይኖርባቸዋል። ይህም፣ የሌላውን ወገን ‘እውነት’ ለማድመጥ መዘጋጀት፣ የጋራ በሆኑ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ መተባበር፣ በሃገራዊ ስልጡንነት የታነጸ የፖለቲካ ፉክክር ማድረግና የህዝብን የመጨረሻ ዳኝነት ማክበር ይጠይቃል። ወደ ሚዲያው ስንመጣ፤ መደበኛው ሚዲያም ሆነ የህዝብ ወገን ነን የሚሉ የማህበራዊ ሚዲያው ተዋንያኖች በሃገሪቱ ውስጥ ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሽግግር እንዲረጋገጥ ታላቅ ድርሻና ኃላፊነት እንዳለባቸው መረዳት ይገባቸዋል። ይህንንም ለማሳካት፣ በፖለቲካዊ ተዓብዮና ህዝበኝነት የተለወሱ አስተሳሰቦችን ከማሰራጨት መቆጠብና በዕውቀትና መረጃ ላይ የተመሰረቱ ሃሳቦችን ለማንሸራሸር መጣር ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ በየአካባቢው የሚደርሱ ጥቃቶችን በየብሔረሰቡ እየሸነሸኑ ከማቅረብ ተቆጥበው በሰላማዊ ዜጎች ወይንም ሰዎች ላይ የደረሰ ጥቃት እንደሆነ በማቅረብ በህዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚጥሩ አክራሪና ህዝበኛ ፖለቲከኞች ተጨማሪ አቀጣጣይ ነዳጅ እንዳያገኙ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
በመጨረሻም፣ መላው የሃገሪቱ ህዝብ ለዘመናት ያካበተው የመተሳሰብና አብሮ የመኖር እሴቶቹ ለሃገሪቱ አንድነትና ሉዓላዊነት መጠበቅ መሰረት መሆኑን በመገንዘብ፣ እነኚህ የጋራ ሃገራዊ እሴቶቻችን እንዳይሸረሸሩ ጥረት ሊያደርግ ይገባል። በተጨማሪም፣ የየአካባቢው ማህበረሰብና እምነት መሪዎች፣ ለህዝብ የቆሙ በመምሰል አንዱን ህዝብ ከሌላው ለማጋጨት የሚሞክሩ ማናቸውንም ኃይሎች በግልጽ ሊያወግዟቸውና ሊኮንኗቸው ይገባል። በተለይም ወጣቱ ትውልድ፣ ለለውጥ ያለውን የጋለ ስሜትና ፍላጎት በመኮርኮር ማቆሚያ ለሌለው እልቂት የሚያነሳሱትን የፖለቲካ ቡድኖች ሴራ በመረዳት የወደፊት ህይወቱንና ተስፋውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ጥያቄዎቹን በሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ መንገድ ማራመድ ይጠበቅበታል። ከ1960ዎቹ የእኛ ትውልድ የፖለቲካ ህይወት የምንማረው አንድ መራር ዕውነት ቢኖር፣ በተዓብዮና ህዝበኝነት የተቃኘ ፖለቲካ ከፍተኛ የሃገርና የትውልድ ጥፋት እንደሚያስከትል ነው። ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን እርምጃዎች ስንወስድ ብቻ ነው ለሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን ሃገርና ሁለንተናዊ ደህንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ ሊኖረን የምንችለው።                              
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ስታለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፈሰር ሲሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትም ያስተምራሉ።


Read 8830 times