Print this page
Sunday, 09 May 2021 00:00

"የሁለቱ መደመሮች" መጽሐፍት ዳሰሳ

Written by  አንዳርጋቸው ጽጌ
Rate this item
(0 votes)


               “--አፍሪካውያን ወደ ዘመናዊነትና ገናናነት ለማምራት አንድ አይነት አፍሪቃዊ ፍልስፍና ያስፈልገናል፣ ይህን ፍልስፍና የህልውናችን ዋስትና አድርገን በመነሳት ብቻ ነው ከገባንበት ውርደትና ወደፊት ከሚያጋጥሙን አደጋዎች መትረፍ የምንችለው--”
         
            (ክፍል - 5)
የዘመናዊነት እድሎች፣ ፈተና፣ ድልና ሽንፈት
በታሪክ እንዳየነው ለፈጣን ዘመናዊ እድገት የተመቻቹ ሃገሮች በአንድ በኩል የተለያዩ ቋንቋዎችና ማንነቶች በመጨፍልቀ አንድ ወጥ ማንነት በሂደት በመፍጠር፣ ውስጣዊ መረጋጋትና የዘመናዊነት መሰረት የጣሉ ናቸው። ብዙዎቹ የአውሮፓ ሃገሮች የዚህ ምሳሌ ናቸው። ጦርነት፣ ማስገበር፣ ፈጣንና ዘመናዊ የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ግስጋሴ ማድረግ፣ የተረጋጋ ማህበረሰብ መፍጠር፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያለ ፋታ የተከናወኑባቸው ሃገሮች ናቸው፤ የምእራብ አውሮፓ ሃገሮች።
በምስራቁ በኩልም የምናየው በፍጥነት ወደ እድገት የመጡት ሃገሮች በአብዛኛው፣ ከ90 በመቶ በላይ የሆነው ህዝባቸው የአንድ ቋንቋ፣ ባህልና እምነት ባለቤት የሆነባቸው ሃገሮች ናቸው።  እነዚህ ሃገሮች እራሳቸውን በማዘመን ማንነታቸውን ባህላቸውንና ታሪካቸውን ለመከላከል መንቀሳቀስ ሲጀምሩ የተከፋፋሉ የውስጥ ማንነቶች፣ የታሪክ ሽሚያዎችና የባህል ሽኩቻዎች እንቅፋት ያልሆኑባቸው አገሮች ናቸው። እነዚህ ሃገሮች አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኙት ሁሉንም የሃገራቸውን ህዝብ ለአንድ አላማ በተጠንቀቅ እንዲቆም፣ በአንድ ላይ በአንድ አቅጣጫ እንዲተም ማድረግ ይችላሉ።  አድርገውታልም። የታወቁት የጃፓን የአጥፍቶ ጠፊ (የካሚካዚ) ፓይለቶችና የጃፓን ወታደሮች የዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው። ተራራን በአካፋና ዶማ ንደው የሚደለድሉ፣ መከራ የማይበግራቸው የ1940 እና 1950ዎቹ የቻይናው መሪ የማኦ ዜዱንግ ወጣት ተከታዮች ሌላ ምሳሌዎች ናቸው።  
ከዚህ ውጭ አንድ ባህል አንድ ቋንቋና አንድ እምነት የሚጋሩ ሆነው ወደ ዘመናዊነት የሚያደርጉት ጉዞ ከሽፎባቸው መከራቸውን የሚያዩት በርካታ የመካከለኛው ምስራቅ ሃገሮች ናቸው። እንደ ሩቅ ምስራቅ ሃገሮች  የመካከለኛው ምስራቅ ሃገሮች በፍጥነት ወደ ልማት መግባት የተሳናቸው የቀድሞ ስልጣኔና ማንነታቸውን የሚመጥን እድገት ማስመዝገብ ያልቻሉት፣ በምእራባውያን ቀጥተኛና ቀጥተኛ ያልሆነ የቅኝ አገዛዝ ስር በመውደቃቸው ነው። ቅኝ ገዥዎች  የመሃከለኛው ምስራቅ ሃገሮችን በጋራ የሚያስተሳስራቸው እሴቶች አውደመው ችግር ውስጥ እንዲወድቁ ያደረጓቸው ሃገሮች ናቸው። ዛሬ በዘመናዊነትና በባህላዊነት (modernisation and tradition) መካከል በአረብ ሃገራት ወስጥ የሚታየው አውዳሚ ሽኩቻ የዚህ የምእራብ ሃገራት የቅኝ ተገዥነት ቅርስ ውጤት ነው።
በርካታዎቹ የአረብ ሃገራት በጃቸው ባለው የነዳጅ ሃብት ላይ የተመሰረተ፣ የቀድሞውን የአረብና የእስልምና እምነትና ስልጣኔ የሚመጥን፣ በቴክኖሎጂና በሳይንስ ምእራባውያንን ሊያስከነዳ የሚችል ከራሳቸው ማንነት ጋር የተዋሃደና ያንን ማንነት ለመከላከል ታቅዶ የተገነባ ዘመናዊ ስልጣኔ የሌላቸው የሆኑት፣ ለዘመናዊነት የሚሆነው የሞራልና የመንፈስ ስንቃቸው በቅኝ ገዥዎች የተበላ በመሆኑ ነው።
አረቦች፣ አሜሪካኖችና እንግሊዞች እንዳሻቸው የሚያደርጓቸው ናቸው። የምእራባውያን የሸቀጥ ማራገፊያ ናቸው። ከአረብ ህዝብ የሚዘረፍ ሃብት በምእራባውያን ሆቴሎች ካዚኖዎች ይጠፋል። ውድ ቤተ መንግስቶች ይገነባበታል። ለምእራብ መንግስታት መሪዎችና ባለስልጣናት ውድ ስጦታ ይበረከትበታል፡፡ በየምእራብ ሃገሮች ባንኮች ታጭቆ ይገኛል።  አንድ አይነት ለአረብ መነቃቃት መሰረት የሚሆን የአረብ ፍልስፍና ሳይኖር፣ አረቦች ከገቡበት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቀውስ እንዲሁም ከሰላም ማጣትና ከምእራባውያን አሻንጉሊትነት ነጻ መውጣት እንደማይችሉ ግልጽ ሆኗል። እኛም ከድህነት ጋር ከአረቦች የባሰ ሁኔታ ውስጥ የገባን እንደውም የፈረንጆቹ ብቻ ሳይሆን የእነዚህ አረቦች መጫወቻ መሆናችንን አንዘንጋ።  
ወደ አፍሪቃ ስንመጣ፣ የትኛውም ሃገር የአንድ ቋንቋ እምነትና ባህል ተላባሽ ሆኖ አናገኘውም። ሁሉም ሃገሮች ከኢትዮጵያ በስተቀር በአውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች የተፈጠሩ ናቸው። አፍሪካ ውስጥ  አንዱ ቋንቋ ባህልና እምነት በአካባቢው የሚገኘውን ሌላ ቋንቋ እምነትና ባህል ጨፍልቆ፣ አውሮፓውያኑ በሄዱበት መንገድ ተጉዞ፣ ሃገር መፍጠር የቻለ የለም።
በአፍሪካ  በአንድ ሃገር ውስጥ የሚገኙ በርካታ የዘውግ ማህበረሰቦች መኖርና የእርስበርስ መሳሳብ በአንድ ላይ መደረግ ለሚገባው የጋራ የዘመናዊነት እንቅስቃሴ እንቅፋት እንደሚሆን የታወቀ ነው። ከሁሉም በላይ ግን ትልቁ የአፍሪካ ሃገሮች ችግር፣ የተለያዩ ብሄረሰቦች በአንድ ሃገር መገኘታቸው አይደለም።  እያንዳንዱ ሃገር እንደ ምስራቅ ሃገራት ዘመናትን የተሻገረ፣ ከማንነቱ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ፣ ሌሎች በስልጣኔና  በጉልበት እንዳይጨፈልቁት ሊከላከለው የሚሻው፣ የጋራ የሚለው ሃገራዊ የባህልና የታሪክ እሴት የሌለው መሆኑ ነው።
ይህ ችግር በእያንዳንዱ አፍሪካ ሃገር ምእራባውያን ቅኝ ገዥዎች ትተውት ከሄዱት የራሳቸው የባህል፣ የቋንቋና የታሪክ ተጽእኖ ጋር ተዳምሮ፣ የአፍሪካን ሃገሮች እንደ ምእራብና እንደ ምስራቁ ሃገሮች በፍጥነት ዘምነን፣ ምእራቡም ሆነ ምስራቁ ሊያሳድሩ የሚችሉትን ተጽእኖ እንቁቋም የሚል የውስጥ ግፊት እንዳይኖራቸው አድርጓቸዋል። አፍሪቃውያን ሌላው ሁሉ ቀርቶ ፈጣሪ በሰጣቸው፣ ከሁሉም የሰው ዘር በፊት የነሱ ሃብት በነበረው፣ ለነጩና ቢጫው ባስተላለፉት፣ ሁሉን ቀዳሚ የሰው ልጅ የመልክ ቀለማቸው፣ የፊት ቅርጻቸውና ጸጉራቸው ሳይቀር የሚያፍሩ ፍጥረቶች እስከመሆን ደርሰዋል።
“አፍሪካውያን ወደ ዘመናዊነትና ገናናነት ለማምራት አንድ አይነት አፍሪቃዊ ፍልስፍና ያስፈልገናል፣ ይህን ፍልስፍና የህልውናችን ዋስትና አድርገን በመነሳት ብቻ ነው ከገባንበት ውርደትና ወደፊት ከሚያጋጥሙን አደጋዎች መትረፍ የምንችለው” የሚለው የአፍሪካ ምሁራን እሪታ የበረታው ለዚህ ነው።   
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ከምእራብ፣ ከምስራቅ፣ ከመካከለኛው ምስራቅና ከአፍሪካ የተለየ ሁኔታ እናገኛለን። ኢትዮጵያ በርካታ ቋንቋዎች፣ ባህሎችና እምነቶች ለረጅም ዘመን በአንድ ላይ ከሞላ ጎደል በአንድ  ሃገር ውስጥ የተገኙባት ሃገር ናት። በዚህ ሃገር ውስጥ ማለቂያ የሌላቸው የመገበር የማስገበር፣ የመውረርና የመወረር ታሪኮች ቢኖሩም፣ የትኛውም የቋንቋ የባህልና የእምነት ማህበረሰብ ሌሎቹን ጨፍልቆ የአውሮፓ መንግስታት የፈጠሩትን አይነት የአንድን ቋንቋ፣ እምነትና ባህል ያለው ህዝብና ሃገር መፍጠር የቻለ የለም። አለመሆኑንም እያየነው ነው።  በጦርነትና በወረራ ማንነታቸውን ያጡ ጠቅለው የወደሙ ማህበረሰቦች የሉም ማለት አይደለም። ይህም ሆኖ የቋንቋና የእምነት ብዝሃነታችንን አለምም እኛም እናውቀዋለን።
“ለምን በየጊዜው የመጡ ሃይለኛ ነገስታት ባላባቶች ወይም ኤሚሮች የአውሮፓ መሪዎች እንዳደረጉት አንድ ወጥ የቋንቋ የባህልና የእምነት ሃገር መፍጠር አልቻሉም” ለሚለው ጥያቄ መልሱ “በዋንኛነት የበላይነት ካገኙት ንጉሶች ወይም ባላባቶች ወይም ኤሚሮች የዘመናዊ መንግስት ምስረታ አቅም ጋር የተያያዘ ነው” የሚለው ነው። አውሮፓውያኖቹ የዘመናዊ ሃገር ምስረታ ወረራና ውጊያ ውስጥ ሲገቡ ከባላባታዊ የኢኮኖሚ፣ የአስተዳደርና የአመራረት እድገት ደረጃ እየወጡ የነበሩበት ወቅት ሲሆን የኛ ሃገር ምስረታ ከጥንት የጀመረ ፍጹም ባህላዊ በሆነ መንግስታዊ አስተዳደርና የኢኮኖሚ ስርአት ውስጥ የተከናወነ መሆኑ ነው።

Read 2772 times