Saturday, 08 May 2021 12:47

አርቲስት መስፍን ጌታቸው ሀሙስ ይዘከራል

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

   በረጅምና ተከታታይ የቴሌቪዝን ድራማዎቹ፣በፊልምና በሬዲዮ ድራማ ስራዎቹ የታወቀውና በቅርቡ በኮረና ቫይረስ ምክንያት ህይወቱ ያለፈው ከያኒ መስፍን ጌታቸው፤ የፊታችን ሀሙስ መጋቢት 5 ቀን 2013 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር እንደሚዘከርና እንደሚመሰገን የአርቲስቱ የቅርብ ጓደኞች ገለፁ፡፡ በዕለቱ የአርቲስቱን ስራ የሚዘክር አጭር ዘጋቢ ፊልም፣የህይወት ታሪኩን የሚገልፅ ፅሁፍና፣ከሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ፅሁፍ ጋር የተሰናሰለ ዘመናዊ የዳንስ ዝግጅት በተመስገን ልጆች የዳንስ ግሩፕና ሌሎችም መስፍንን የሚዘክሩ ስራዎች ለታዳሚዎች እንደሚቀርቡ ታውቋል፡፡ በቤተሰቦቹ በወዳጅ ዘመዶቹና በሙያ አጋሮቹ በተሰናዳው በዚህ የምስጋና ፕሮግራም ላይ መስፍን ለኪነ-ጥበቡና ለኪነ- ጥበብ አፍቃሪያን ያበረከተው አስተዋፅኦ በደንብ ይቃኛልም ተብሏል፡፡
አርቲስትና ደራሲ  መስፍን ጌታቸው “ዘመን” እና “ሰው ለሰው” በተሰኙ ረጃጅምና ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎቹ ፣250 ክፍል በነበረውና ሁለት ደራሲያን ጋር በሰራው “የቀን ቅኝት” ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ፣ “ዙምራ” በተሰኘውና የዘረኝነትንና የጠባብ ብሔርተኛነትን ቀድሞ በዳሰሰበት ፊልሙ፣ በቀደመው ጊዜ በቅዳሜና እሁድ የሬዲዮ መዝናኛ የሬዲዮ ድራማዎቹ፣ “ሰቀቀን” በተሰኘውና አሁን በህይወት የሌለው ጥላሁን ጉግሳ ዓለሙ ባዘጋጀው የመድረክ ተውኔቱና በሌሎችም በርካታ ስራዎቹ በኪነ-ጥበቡ ላይ አሻራውን ሲያሳርፍና ኪነ-ጥበብን ሲያጎለብት የኖረው አርቲስትና ደራሲ መስፍን ጌታቸው እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ሰፊ የቴሌቪዥን ስራ እቅዶችን አቅዶ በመተግበር ላይ እያለ በኪቪድ-19 በሽታ በቅርቡ ህይወቱን ያጣ መሆኑ ይታወሳል፡፡ በአርቲስቱ የምስጋናና የዝክር ስነ ሥርዓት ላይ በርካታ የሥነ-ፅሁፍና የኪነ ጥበቡ ዘርፍ ባለሙያዎችና አድናቂዎች፣ቤተሰቦቹ ወዳጅ ዘመዶቹና በርካቶች በመታደም እንደሚዘክሩትና እንደሚያመሰግኑትም የመርሃ ግብሩ አዘጋጆች ገልፀዋል፡፡

Read 11761 times