Saturday, 08 May 2021 12:40

“የአውሮፓ ህብረት ውሳኔ ምዕራባውያኑ በአገራችን የሚያደርጉትን ያልተገደበ ጣልቃ ገብነት አመላካች ነው”

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(5 votes)

       • የህብረቱ ታዛቢ አለመላክ በምርጫው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የለም - ኢዜማ
             • ከዚህ ቀደም ህብረቱ ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርቦ አያውቅም
                  

          የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ ምርጫ ታዛቢዎች የመላክ እቅዱን መሰረዙ ምዕራባውያኑ በአገራችን ላይ እያደረጉ ያሉትን ያልተገደበ ጣልቃ ገብነት የሚያመለክት መሆኑን የፖለቲካ ልሂቃን ተናገሩ፡፡ ህብረቱ ያቀረባቸው ጥያቄዎች የአገሪቱን ሉአላዊነት የሚፃረር የቅኝ እንግዛችሁ ጥያቄ ነው ብለዋል- ምሁራኑ። ኢዜማ በበኩሉ የአውሮፓ ህብረት በታዛቢነት አለመገኘቱ በምርጫው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የለም ብሏል።
በአክሱም ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ዶ/ር ተስፋዬ ባዩ እንደሚናገሩት፤ የአውሮፓ ህብረት በዘንድሮው ምርጫ ታዛቢዎቹን በመላክ ለመሳተፍ ፍቃደኛነቱን ካሳየና ካረጋገጠ በኋላ በቀደሙት የምርጫ ሂደቶች ላይ ያልነበሩና የአገሪቱን ሉአላዊነት የሚዳፈሩ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጡ፣ ምዕራባውያኑ በአፍሪካ ብሎም በኢትዮጵያ ላይ እያሳዩ ያሉትን ገደብ አልባ ጣልቃ ገብነት አመላካች ነው ብለዋል፡፡ ህብረቱ ምርጫውን ቢታዘብም ባይታዘብም ምርጫው መካሄዱ አይቀርም ያሉት፤ ምሁሩ ከዚህ ቀደም በአገራችን የተካሄዱትና የህዝብ ተአማኒነት ያላገኙትን ምርጫዎች ሁሉ ሲታዘብ የቆየው ህብረቱ አሁን ያልተለመዱና በኢትዮጵያ መንግስት በኩል  ፈፅሞ ተቀባይነትን ሊያገኙ የማይችሉ ጥያቄዎችን ማቅረቡ የህብረቱን ወገንተኝነት በግልጽ የሚያመለክት ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የአውሮፓ ህብረት በምርጫው ላይ በታዛቢነት ላለመገኘት መወሰኑ የምርጫውን ቅቡልነት ሊጎዳው እንደማይችል ገልጿል። የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ እንደተናገሩት መጪውን አገር አቀፍ ምርጫ የተለያዩ  ዓለም አቀፍ ተቋማት በታዛቢነት ቢገኙና አስተያየታቸውን ቢሰጡ ለቀጣይ ጊዜ በምናደርገው ምርጫ ማረም የሚገባንን ለማረም የምንችልበትንና ክፍተቶቻችንን የምንሞላበትን እድል ይሰጠን ነበር። ይህ እንዲሆን ግን ለማንም የተለየ አካሄድ መከተል አይገባም፡፡ የምርጫው ዋንኛ ባለቤት ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ብቻ ናቸው። ምርጫውን በንቃት መሳተፍና ታዝቦ ማረጋገጫ መስጠትም ያለበትም ህዝቡ እንደሆነ ገልፀዋል።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፕ ቦሬል ከ20 የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽነሮች ጋር ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከጠቅላይ  ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር ተገናኝተውና ተወያይተው የቅድመ ምርጫ ጥናት ቡድን ወደ ኢትዮጵያ የላኩ ሲሆን ቡድኑም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተዘዋውሮ ለሁለት ሳምንታት ጥናት አካሂዷል፡፡ በመጨረሻም ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ሲፈፀም ታዛቢዎቹን እንደሚልክ ማረጋገጫ ሰጥቶ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ህብረቱ የኢትዮጵያ ምርጫ ተዓማኒ አካታችና ግልጽ ምርጫ እንዲሆን ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የ20 ሚሊየን ዮሮ ድጋፍ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
ከቀናት በኋላ ህብረቱ አገሪቱ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን አላሟለችም   በሚል ምክንያት ታዛቢዎቹን የመላክ ዕቅዱን  መሰረዙን አስታውቋል። ህብረቱ በኢትዮጵያ በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ታዛቢዎቹን የመላክ ዕቅዱን የሰረዘበትን ምክንያትም አስቀምጧል። ከቅድመ ሁኔታዎቹ መካከልም፡- የልኡኩ ነፃነትና የደህንነት ስጋቶች ፣ የምርጫውን ውጤት ይፋ ማድረግና  ልኡኩ የሚጠቀምባቸውን የግንኙነት ቁሳቁሶችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።  ቅድመ ሁኔታዎቹን የኢትዮጵያ መንግስት ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያትም ታዛቢዎችን ለመላክ የነበረንን ዕቅድ ሰርዘናል ሲሉ የህብረቱ ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፕ ቦሬል ገልፀዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ ህብረቱ ያቀረባቸው ቅድመ ሁኔታዎች የኢትዮጵያን መንግስት ሉአላዊነት የሚዳፈሩ ናቸው ብሏል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰጡት መግለጫ የህብረቱ  ጥያቄ የአገሪቱን ሉአላዊነት የሚፃረርና የአገሪቱን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ሆኖ በመገኘቱ ስምምነት ላይ ሳይደረስ መቅረቱን ተናግረዋል። የህብረቱ ጥያቄዎች ከዚህ ቀደም በነበሩት ምርጫዎች ላይ ያልተጠየቁና ተደርገውም የማያውቁ ናቸው ያሉት ቃል አቀባዩ፤ ከኢትዮጵያ የቴሌኮሚኒኬሽን ስርአት ውጪ የሆኑ የግንኙነት መሳሪያዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት መፈለግና የምርጫውንም ውጤት ከምርጫ ቦርድ አስቀድሞ ይፋ ለማድረግ ጥያቄ ማቅረብ ከዚህ  ቀደም ያልተደረጉና ፍፁም ተቀባይነት ሊኖራቸው የማይችሉ ጥያቄዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የቃል አቀባዩን መግለጫ ተከትሎ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የፖለቲካ ልሂቃን፤ “የህብረቱ ጥያቄ የቅኝ እንግዛችሁ ጥያቄ ነው፤ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከዚህ ቀደምም ያልነበረ ወደፊትም ሊፈፀም የማይችል የህልም እንጀራ ነው” ብለዋል፡፡
“በአገራችን ጉዳይ የሚመለከተንም ወሳኞቹም እኛው ብቻ ነን፡፡ አውሮፓውያን ሁልጊዜም በአፍሪካውያን በተለይም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ ለመግባት ጥረት ሲያደርጉ ይታያሉ፤ ይህ ግን ፈፅሞ የማይቻል ጉዳይ ነው” ብለዋል ልሂቃኑ፡፡ “ምርጫውን የሚመርጠው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፤ ውጤቱን ይፋ የሚያደርገው የምርጫ ቦርድ ብቻ ነው። ማንም አካል ከታዛቢነት የዘለለ ተግባር መፈጸም ጨርሶ አይችልም “ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ህብረቱ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ የሚታዘብ ቡድን አለመላኩ በምርጫው ሂደት ላይም ሆነ በውጤቱ ላይ የሚያመጣው ጉልህ ተፅህኖ የለም ያሉት የፖለቲካ ምሁሩ አቶ ታፈሰ ፍቃዱ፤ ውሳኔው ምርጫው በውጪው ማህበረሰብ ዘንድ ተዓማኒነት እንዳይኖረው ለማድረግ ሆን ተብሎ የተቀነባበረና ወገንተኝት የተስተዋለበት ነው ብለዋል፡፡
ህብረቱ ቀደም ሲል በአገራችን የተካሄዱ ምርጫዎችን ሲታዘብ የቆየ መሆኑን ያስታወሱት ምሁሩ በቀደምት የምርጫ ሂደቶች ያልነበሩና ያልቀረቡ አዳዲስ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጡ ህብረቱ በምርጫው ሂደት ውስጥ ለማስፈፀም ያሰበው የግሉ አጀንዳ ሊኖረው እንደሚችል ያመለከተ ነው ብለዋል፡፡  
የአውሮፓ ህብረት በአገራችን የምርጫ ሂደት ውስጥ አለመሳተፉ ከአንዳንድ የአውሮፓ አገራት ጋር ያለንን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሊያሻክረው የሚችል ቢሆንም ጉዳዩ ከአገር ሉአላዊነት የሚበልጥ አይደለም ብለዋል። አክለውም፤ የኢትዮጵያ መንግስት  በያዘው አቋም ፀንቶ ህብረቱ ምርጫውን ባለመታዘቡ በምርጫው ላይ የሚደርስ የጎላ ተፅዕኖ እንደሌለ ማሳየት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምዕራባውያኑ በአገራችን የውስጥ ጉዳይ በተደጋጋሚ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት ሊያቆሙ እንደሚገባ ምሁራኑ አሳስበዋል፡፡

Read 11711 times