Print this page
Saturday, 08 May 2021 12:37

“በኦሮሚያ የእስረኞች አያያዥ እጅግ አሳሳቢ ነው”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

     በኦሮሚያ የእስረኞች አያያዝ እጅግ አሳሳቢና በአፋጣኝ ሊሻሻል የሚገባው መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አሳስቧል፡፡
ኮሚሽኑ በኦሮሚያ የእስረኛች አያያዝን ሁኔታ በክልሉ በተመረጡ 21 ፖሊስ ጣቢያዎች መከታተሉን ጠቁሞ፤ በሁሉም ፖሊስ ጣቢያዎች ያለው የእስረኞች አያያዝ ሠብአዊ መብትን ያላከበረና አሳሳቢ ነው ብሏል፡፡
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ  በወቅታዊ ጉዳይ የታሰሩ በሚል በርካቶች ያለ ፍርድ ሂደት ታስረው እንደሚገኙ ያመለከተው ኢሠመኮ፣ በርካቶች  “ከኦነግ ሸኔ ጋር  ግንኙነት  አላችሁ” በሚል እንደሚታሰሩና ከፍርድ ሂደት ይልቅ የፖለቲካ ውሳኔ ሰለባ እንደሚሆኑ አስታውቋል ባወጣው የምርመራ ሪፖርቱ፡፡
ፍ/ቤት የቀረቡና  የተጠረጠሩበት ጉዳይ አያስከስስም ተብለው በነፃ የተሰናበቱ ግለሰቦች “በሌላ ወንጀል ይፈለጋሉ” በሚል ታስረው እንዲቆዩ እንደሚደረግም በመግለፅም፤ ይህም ፈፅሞ ህጋዊ አሰራር እንዳልሆነ ኢሠመኮ አመልክቷል፡፡
ኮሚሽኑ ከጎበኛቸው እስረኞች መካከል የተወሰኑት በፖሊስ በተያዙበት ወቅት መደብደባቸውን  ማረጋገጡን በሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ በተወሰኑ የክልሉ አካባቢዎች ደግሞ “ባልሽ  ወይም የቤተሰብ አባልሽ የኦነግ ሸኔ አባል ነው” በማለት እናትን፣ ሚስትን፣ አባትንና የቅርብ ቤተሰቦችን ለእስር የመዳረግ ሁኔታ ማጋጠሙን አስታውቋል። ኢሰመኮ በተወሰኑ አካባቢዎች ሰዎችን ያለ አግባብ በማሰር “ኦነግ ሸኔ ነው ብለን እንከሳችኋለን” በሚል በማስፈራራት ገንዘብ የመቀበል ሁኔታዎች መኖራቸውን ከእስረኞች መገንዘቡን  አመልክቷል፡፡
ኮሚሽኑ ክትትል ካደረገባቸው ፖሊስ ጣቢያዎች መካከል ሴት እስረኛ ከ5 ወር እስከ 10 ዓመት ከሚደርሱ ህፃናት ልጆቻቸው ጋር መታሰራቸውን ማረጋገጡን እንዲሁም ከ9 እስከ 18 ዓመት የሚሆናቸው ታዳጊዎች ከአዋቂዎች ጋር ተቀላቅለው እንዲታሰሩ መደረጉን ጠቁሟል፡፡
በአብዛኛው የፖሊስ ጣቢያዎች በቂ የምግብና  መጠጥ እንዲሁም ንፅህና አቅርቦት አለመኖሩን ማረጋገጡንም ነው ኢሰመኮ ያስታወቀው፡፡


Read 11407 times
Administrator

Latest from Administrator