Saturday, 08 May 2021 12:35

“ህውኃት” እና “ሸኔ” በአሸባሪነት መሰየም በህግ ባለሙያዎችና ፖለቲከኞች እይታ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

  “ህውኃት” እና “ሸኔ” በአሸባሪነት መፈረጃቸው ተገቢነት ያለው እንዲያውም የዘገየ ውሳኔ ነው ሲሉ የህግ ባለሙያዎች የገለጹ ሲሆን ፖለቲከኞች በበኩላቸው የተለያየ አቋም አንፀባርቀዋል።
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ከትናንት በስቲያ ባካሄደው ስብሰባው፣ የቀድሞውን ዋና ገዥ ፓርቲ “ህውሃት” እና “ሸኔ”ን በ2012 በፀደቀው አዲሱ የፀረ ሽብር አዋጅ  መሰረት የሽብር ድርጅቶች ሲል ፈርጇል።
ይኼን ተከትሎም ከሚያዚያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ከእነዚህ ድርጅቶች ጋር የተገናኘ፣ ድጋፍ ያደረገና አላማቸውን ለማስፈጸም የተንቀሳቀሰ ሁሉ በሽብርተኝነት ተጠያቂ ይደረጋል ተብሏል።
የድርጅቶቹን በሽብርተኝነት መፈረጅ በተመለከተ አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የህግ ባለሙያና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ተሻለ ሁነኛው፤ በአዋጁ የተቀመጡ ዝርዝር የሽብርተኛ ድርጊቶችን በሙሉ ሁለቱ አካላት ሲፈጽሙ እንደነበር በቂ ማስረጃ እንዳለ ይገልፃሉ።
“ህውኃት” እና “ሸኔ” በዋናነት ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማ አድርገው የፖለቲካ አላማቸውን ለማስፈጸም መንቀሳቀሳቸው በገሀድ ሲታይ የከረመ ነው የሚሉት የህግ ባለሙያው፤ ይህም ከፍተኛውን የሽብርተኛነት ተግባር መስፈርት የሚያሟላ ወንጀል ነው ብለዋል።
“መንግስት ዘገየ ካልተባለ በስተቀር ድርጊቱን ፈጻሚዎቹን በሽብርተኝነት መፈረጅ ተገቢ ነው፤ በድርጅቶቹና አባሎቻቸው ላይ የሽብር ክሶችን ለማደራጀት የሚያስችሉ በቂ ማስረጃዎች አሉ” ብለዋል- የህግ ባለሙያው።
ሌላኛው የህግ ባለሙያና ጠበቃ አቶ ወንድሙ ኢብሣ በበኩላቸው፤ ድርጅቶቹ በሽብርተኝነት መፈረጃቸው ተገቢ መሆኑንና ሽብርተኛ ተብለው ለመሰየምም በአዲሱ የጸረ ሽብር አዋጅ መሰረት በቂ ማስረጃ የተገኘባቸው መሆኑን አስረድተዋል።
ሁለቱ በሽብርተኝነት የተፈረጁት ድርጅቶች የፖለቲካ አላማቸውን ለማስፈጸም ንፁሃንን እንደ ማስያዣ የሚጠቀሙ መሆናቸውን በመጥቀስም፣ ሽብርተኛ ለሚለው ፍረጃ በቂ ማስረጃ አለ ይላሉ።
ድርጅቶቹ ሽብርተኛ ተብለው መሰየማቸውም የወንጀል ድርጊቱን ለመቀነስ በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን ነው የህግ ባለሙያዎቹ የሚገልጹት። የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀ መንበር ፕ/ር መረራ ጉዲና ግን የእነዚህ ድርጅቶች በሽብርተኝነት መፈረጅ በፀጥታ ጉዳዮች ላይ መሰረታዊ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት እንደሌላቸው ይናገራሉ።
መንግስት ከዚህ  ቀደምም በተመሳሳይ አጥፊ ያላቸውን ድርጅቶች በሽብርተኝነት መፈረጁን፣ ነገር ግን ያመጣው ለውጥ እንዳልነበር የሚያስታውሱት ፕ/ር መረራ፤ ይህም ውሳኔ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለየ ይሆናል ብዬ አላምንም ብለዋል።
“በተለይ “ሸኔ” በሚል ስም  ራሱን የሚጠራ ድርጅት በሌለበት “ሸኔ” ብሎ መሰየም በኦሮሞ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችን ዒላማ ያደረገ ይመስለኛል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም “ኦነግ” ተፈርጆ የኦፌኮም አባላት በኦነግ ስም ሲታሰሩ እንደነበር ያወሱት ፕ/ር መረራ፤ አሁንም የሚቀጥለው ተመሳሳይ ድርጊት ነው ባይ ናቸው።
የህግ ባለሙያው አቶ ወንድሙ ግን የእነዚህ ድርጅቶች በሽብር መፈረጅ በአላማም ሆነ በሚያመጣው ውጤት ከዚህ ቀደም ከነበረው ፍረጃ በእጅጉ የተለየ ነው ሲሉ ይከራከራሉ።
የቀድሞው ተቃዋሚዎችን ዒላማ ያደረገ ሲሆን የአሁኑ ግን ንፁሃንን ከጥቃት ለመከላከል  ያለመ ፍረጃ ነው ሲሉም የህግ ባለሙያው ያስረዳሉ።

Read 11452 times