Saturday, 08 May 2021 12:28

ኮሚሽነር አበረ አዳሙ - ከአርበኞች ግንባር እስከ አማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነርነት - (1961-2013)

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(3 votes)

  በቀድሞው የጎጃም ክፍለ ሀገር፣ ቆላ ደጋ ዳሞት አውራጃ፣ደጋዳሞት ወረዳ መለስ ብሳና ሜዳ ቀበሌ የካቲት 13 ቀን 1961 ዓ.ም የተወለዱት የቀድሞው አርበኞች ግንባር መስራችና ታጋይ እንዲሁም የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበረ አዳሙ በድንገተኛ ህመም ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል።
 ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ባላቸው ትምህርትን የመቀበል ተፈጥሯዊ ተሰጥዖ በአራት ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በማጠናቀቅ ሀገር አቀፉን የስምንተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተና ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ወደ 9ኛ ክፍል ተዛውረዋል።
ኮሚሽነር አበረ ተወልደው ባደጉበት አካባቢ ቅርብ የሆነ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ባለመኖሩ ከትውልድ አካባቢያቸው አጎታቸው ይኖሩበት ወደ ነበረበት አምቦ ከተማ በመሄድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለው በላቀ ውጤት  አጠናቀዋል።
 በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና  ለኮሌጅ የሚያስገባ ነጥብ በማምጣታቸው ወደ አዲሰ አበባ በመምጣት የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የመግቢያ ፈተናን ወስደው በማለፋቸው በፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሚሰጠውን የመኮንነት ትምህርት አጠናቀው በምክትል መቶ አለቅነት ማዕረግ በፖሊስ ዲፕሎማ በ1986 ዓ.ም ተመርቀዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ከተመረቁ በኋላ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዞን 2፣ ወረዳ 21፣ ቂርቆስ ፖሊስ ጣቢያ ተመድበው በወንጀል መከላከል፣ ወንጀል ምርመራና በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ለአምስት ዓመታት ያህል ሰርተዋል፡፡ በኃላፊነት በነበሩበትም ሰዓት ወንጀልን በመከላከል፣ ህዝብን በማገልገል ተደጋጋሚ ሽልማትን ያገኙ ሲሆን በወቅቱ በነበረው ስርዓት የአለቆችን መመሪያ አይቀበልም በሚል ሰበብ ከሦስት ጊዜያት በላይ ለእሰር ተዳርገው ነበር፡፡
 ኮሚሽነር አበረ ጥቃትን የሚቀበል ሰብዕና የሌላቸው በመሆኑ ይህንን በደል በመጠየፍ በቀድሞው የደህንነት ኃላፊዎች ከታሰሩበት ቦታ የተደገሰላቸውን ሞት አምልጠው ለስደት ተዳርገዋል።
ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ለአገራቸው ባላቸው ቀና ምኞትና የለውጥ ፍላጎት በወቅቱ በመንግስት ይፈጸም የነበረውን  ግፍና በደል በመቃወም  ወደ ኤርትራ በረሀ ወርደው “የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር” የሚባል ድርጅት ከትግል ጓደኞቻቸው ጋር በመመስረት የወታደራዊ ክንፍ አዛዥ በመሆን ሲታገሉ ቆይተዋል።
ከዚያም ትግሉን ለማስፋትና ህወሓት መራሹን መንግሥት ከሥልጣን በፍጥነት ለማውረድ ከኤርትራ በተጨማሪ በደቡብ ሱዳን፣ በኬኒያና በዩጋንዳ ትግሉን ሲመሩ ቆይተዋል።  በኋላም ራሳችውን ከቀጥታ የትግል ተሳትፎ ለተወሰነ ጊዜ በማግለል፣ በኬንያ ሊሙሩ ከተማ በሚገኘው የአሜሪካን ዩኒቨርስቲ የነፃ ትምህርት ዕድል በማግኘታቸው በሊደርሺፕ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል። በመቀጠልም በዓለም አቀፍ ስደቶኞች ረጅ ተቋማት አማካኝነት ወደ ስዊድን ሀገር በማቅናት በስደተኝነት ይኖሩ ነበር። ከዚያም /ግንቦት 7 የነፃነትና የእኩልነት ንቅናቄን/ መስርተው ከመስራች አባልነት አንስቶ እስከ ከፍተኛ አመራርነት ድረስ ታግለው አታግለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በስዊድን ሀገር የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ፕሬዚዳንት በመሆን ማህበረሰቡን አገልግለዋል።
በስዊድን ቆይታችውም በሕግና በማህበረሰብ ሳይንስ ጥናት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በከፍተኛ ውጤት ያገኙ ሲሆን የመመረቂያ የምርምር ጽሁፋቸው በዩኒቨርስቲው ተመርጦ በመታተም ለገበያ ቀርቦላቸዋል፡፡ መጽሀፋቸውም በታዋቂው የኢንተርኔት መገበያያ መረብ በአማዞን በሽያጭ ላይ ይገኛል።
 ኮሚሽነር አበረ አዳሙ   አንጋፋና ታዋቂ ከሆነው ማልሞ ዩኒቨርስቲ  ደግሞ የማስተርስ ዲግሪያቸውን በዓለም አቀፍ ስደተኞችና የማህበረሰብ ግንኙነት በከፍተኛ ማዕረግ ወስደዋል፡፡
ከዚያም ጥሩ ገቢ የሚያሰገኝ ሥራ አግኝተውና ልጆች ወልደው፤ ከትግሉ ጎን ለጎን የግል ኑሯቸውን ማጣጣም በጀመሩበት ወቅት የዛሬ 3 ዓመት በሀገራችን አንፃራዊ ለውጥ መምጣቱን ተከትሎ፣ በተደረገላቸው ጥሪ ህዝባቸውን ለማገልገል ወደ ሀገራቸው ተመለሱ።
በሀገር ደረጃ የመጣውን ለውጥ በመቀላቀል በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽን ታሪክ የመጀመሪያው በፖሊስ ሳይንስ የተመረቀ ፖሊስ ኮሚሽነር በመሆን፣ ከየካቲት 2011 ዓ.ም እሰከ ሚያዝያ 2013 ዓ.ም ድረስ አገልግለዋል፡፡
ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ቆፍጣና ወታደር፣ ምሁር፣ ደራሲ፣ ገጣሚ  የሕግ ባለሙያና አገራቸውን አጥብቀው የሚወዱ ሰው እንደነበሩ ይነገርላቸዋል።
በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ለተደረገው ሪፎርም ጥናት በማድረግና በመምራት  ከፍተኛ አስተዋፅኦ ከማድረጋቸውም በላይ ሪፎሩሙን በቁርጠኝነት በመምራት አመርቂ ውጤቶች እንዲመዘገቡ አድርገዋል፡፡
ኮሚሽነር አበረ በቅርቡ በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ለአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ቁርጠኛ አመራር በመስጠት በአገር አቀፍ ደረጃ ለተገኘው ድል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
ባለትዳርና የሁለት ወንድ ልጆች አባት የነበሩት ኮሚሽነር አበረ አዳሙ፤ ሚያዝያ 26 ቀን 2013 ዓ.ም ባጋጠማቸው ድንገተኛ ህመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው  ከዚህ አለም በሞት ተለይተዋል። የቀብራቸው ስነስርዓት ሚያዝያ 28 ቀን 2013 ዓ.ም በባህርዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል።

Read 11764 times