Print this page
Saturday, 01 May 2021 13:23

6ኛው አገራዊ ምርጫ 2013 ጥቂት ቀናት የቀሩት አገራዊ ምርጫ ምን ተሟላ? ምን ጎደለ?

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 እስካሁን ወደ 28 ሚ. ገደማ መራጮች ተመዝግበዋል ፓርቲዎች ከቀረበላቸው የሚዲያ የአየር ሰዓት 54% ብቻ ነው የተጠቀሙት

              የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ግንቦት ወር ላይ ለማካሄደው 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ቀንን ማራዘሙ ይታወቃል። ምን ውጤት ተገኘ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከቦርዱ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ወ/ሪት ሶሊያና ሽመልስ ጋር በዚህና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግራቸዋለች።

          የመራጮች ምዝገባ ቀን ከተጠናቀቀ በኋላ እንደየ አካባቢዎቹ የሁለትና ሶስት ሳምንት ማራዘሚያ አድርጋችኋል። ከምዝገባው መራዘም በኋላ ያለው ሂደት ምን ይመስላል?
ባለፈው 18 ሚሊዮን ህዝብ መመዝገቡን ገልፀን ነበር አሁን 22 ሚ አካባቢ ደርሰናል። ነገር ግን ለተወሰኑ ቀናት (ባለፉት ሶስት ወይም አራት ቀናት ማለት ነው) የምርጫ ክልል አስፈፃሚዎቻችንን ወደ ማዕከል ጠርተን ነበር - በምርጫ ክልል ደረጃ ያሉትን፡፡ የጠራናቸው ደግሞ በስራቸው የሚገኙ የምርጫ ጣቢያ ሰራተኞችን ዳታ እንዲያመጡልን ነው፡፡ በዚያ ምክንያት  በእነዚህ ቀናት ትክክለኛ ዳታውን መሰብሰብ አልቻልንም፡፡ ሌላ ጊዜ በየሁለት ቀኑ  ነው የምንሰበሰበው ስለዚህ 22 ሚሊዮን አካባቢ የሚለው ትክክለኛው መረጃ ባይሆንም እንኳን ያንን ያህል እንደሚሆን  ይገመታል። ይሄ ቁጥር የቅርቡን የአማራንና የአዲስ አበባን ያካተተ አልመሰለኝም። ያም ሆኖ 22 ሚሊዮን ገደማ መመዝገቡ ተገምቷል ነገ ከነገ ወዲያ በተለያየ ሁኔታ ቁጥሩ ሊቀየር ይችላል፡፡
ስለዚህ በተራዘመው ጊዜ የመራጩ ቁጥር የታቀደውን ያህል ሊሆን ይችላል ብሎ መናገር ይቻላል?
እኛ በእርግጥ ይህን ያህል ቁጥር ያለው ህዝብ ይመርጣል ብለን ያስቀመጥነው ቁጥር የለም ነገር ግን ለዝግጅት 50 ሚ ህዝብ ድረስ ለመምረጥ ቢመዘገብ፣ ያንን ያህል ህዝብ ቦርዱ የማስተናገድ አቅም አለው ለማለት ነው፡፡ ይሄ ማለት በምርጫ አስፈፃሚዎች በህትመትም ሆነ በቁሳቁስ በማቅረብ በኩል ዝግጅት አለን፡፡ እኛ  በዚህ ግምት ልክ ነው የምንሰራው፤ እናም እስከ 50 ሚ የሚደርስ  መራጭ ቢመዘገብ ለማስተናገድ ሁለንተናዊ ዝግጅት አለን፡፡ አሁን ቁጥሩ እየጨመረ ነው፤ እንደምታውቀው የቀሩ ቀናትም አሉ፡፡
ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ከእነአካቴው የምርጫ ጣቢያ ያልተቋቋመባቸው አካባቢዎች አሉ። ለምሳሌ በሰሜን ሸዋ፣ምዕራብ ወለጋና ሌሎች አካባቢዎች በነዚህ አካባቢዎች መሻሻል ታይቶባቸው ምርጫ ምዝገባ የተጀመረባቸው ቦታዎች ይኖራሉ?
የተሻሻለ ነገር አለ፡፡ ባለፈው የምተርጫ ምዝገባ ቀኑን ስናራዝም አንዱ የተቀስነው ነገር ለምሳሌ በኦሮሚያ ላይ ከአራቱ ወለጋዎች መካከል ስድስት ቀበሌዎች ላይ ምርጫ ማድረግ እንደማንችል ነው የደመደምነው ቀበሌዎች ላይ ባደረግነው ጥናት። እንደሚታወቀው የምርጫ ክልል ቢሮ ከፍተናል። በወረዳ ደረጃ ቢሮዎቻችንን ከፍተን ዕጩዎቻችንን መዝግበን ነበር። ምርጫ ግን ወደ ቀበሌ ደረጃ የሚወርድ በመሆኑ እነዛ ስድስት ቀበሌዎች ላይ ያለውን ሁኔታ እስክናረጋግጥ ድረስ አቆይተነዋል። በሌሎቹ አራት ወረዳዎች ግን የቁሳቅስ ስርጭት፣ የአስፈጻሚዎች ስልጠና ባለፈው ሳምንት አከናውነን  የመራጮች ምዝገባ ልንጀምር እየተዘጋጀን ነው አሁን በቃሌ አላውቃቸውም። እነዛ ስድስት ቀበሌዎች ላይ አሁንም የመራጭ ምዝገባ አናካሂድም። በሌሎቹ ላይ ግን የመራጮች ምዝገባ ለመጀመር ቁሳቁሶችም ማዕከል ልከናል። የአስፈጻሚዎች ስልጠናም ተጠናቋል፡፡ በአጠቃላይ የተወሰነ መሻሻልና ከክልሉ መንግስትም ከፍተኛ ድጋፍ እየተደረገልን ነው። በተለይ በአካባቢው ላይ ባሉ የምርጫ ጣቢያዎች ፀጥታውን በማስከበር የመራጮች ምዝገባ ሊደረግ የሚችልበትን ሁኔታ በማመቻቸት በኩል ጥሩ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ በቤኒሻንጉል መተከል ላይ አልጀመርንም፤ ነገር ግን ካማሼ ላይ የቁሳቅስ ስርጭትና የአስፈፃሚዎች ስልጠና ጀምረናል፡፡ የመራጮች ምዝገባም ይጀመራል ማለት ነው፡፡ ይህን ስንመነለከት መሻሻል አለ፡፡ ይህ እንግዲህ ከአካባቢው በተለይ መሬት ላይ ካሉ የፀጥታ አካላት ጋር በትብብር መስራትና ይጠይቃል፡፡
የአማራ ክልሉ ማለትም የሰሜን ሸዋና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በጣም የቅርብ ጊዜ ሁነት ነው። ይህንን የማራዘም ውሳኔ በምንወስንበት ጊዜ እንኳን ግጭቱ ነበር፡፡ ስለዚህ ያንን አካባቢ ደግሞ እንመለከትና በአካባቢው የመራጮች ምዝገባ ማካሄድ እንችላለን ወይስ አንችልም የሚለውን እንገመግማለን- የአካባቢው የፀጥታ ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውን፡፡
ወቅቱ ከመቼውም የበለጠ አስቸጋሪ መሆኑ ይታወቃል የፀጥታውም የወረርሽኙም ችግር እንዳለ ሆኖ ከምርጫው ጋር በተያያዘ ልትወጡት ያልቻላችሁት ተግዳሮት ምንድን ነው?
ተግዳሮቱ አንዱ ከአንዱ ተነጥሎ የሚታይ አይደለም። በአጠቃላይ ኦፕሬሽኑ በጣም በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ሁለት ነገሮች አሉ። አንደኛ ከዚህ በፊት ከነበሩት ምርጫዎች ይሔኛው ምርጫ ይለያል፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩት የምርጫ ኦፕሬሽኖች ይፈፀሙ የነበሩት አብዛኛቹ በመንግስት የዝቅተኛው መዋቅር ነው፡፡ ለምሳሌ ቀበሌ አስ፤ ከዛ የምርጫ ጣቢያ አለ ፤ቀበሌው ቁሳቁሶቹን ይወስዳል፤ ያሰራጫል፣ አስፈፃሚዎቹም ከዚያው ናቸው። ባጠቃላይ በዝቅተኛ የመንግስት መዋቅር ይሰራ ስለነበር ከፍተኛ የገለልተኝነት ጥያቄ ነበረበት። ይህንን ጥያቄ ለማስወገድና የእውነትም ምርጫው በትክክል በገለልተኝነት መካሄድ ስላለበት፣ እንደከዚህ ቀደሞቹ ምርጫዎች በዝቅተኛ የመንግስት መዋቅር መካሄድ የለበትም። ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ፣ በዝቅተኛ የመንግስት መዋቅር ሲሰራ በነበረበት ጊዜ፣ በምርጫው ተዓማኒነት ላይ ጥያቄ ስለነበረ ማለቴ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ አይነት ወቀሳዎችና የእምነት ማጣት እንዳይኖር ሙሉ በሙሉ የምርውን ሂደት የሚሰራው ቦርዱ ነው ይሄ ለቦርዱ ትልቅ ጫና፡፡ ምክንያቱም እስከ ዛሬ በመላ አገሪቱ ቦርዱ ይጅን አይነት የኦፕሬሽን አቅም የገነባ አይደለም። ይሄ የመጀመሪያ ሙከራ እንደመሆኑ፣ የቦርዱ አቅም እየተፈተነ ያለ አንዱ ተግዳሮት ነው፡፡
ከዚህም ችግር ስንነሳ ደግሞ ሌሎች ነገሮች ለዚህ ጉዳይ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ የፀጥታው ሁኔታ ለዚህ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ የፀጥታው ሁኔታ ለዚህ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ አሁን  ያለው የአገሪቱ ሁኔታ እንቅስቃሴ ለማድረግ ያስቸግራል። በተለይ በሁለተኛው ደረጃ የምናደርገው እንቅስቀሴ ከባድ ነው፡፡ የመጀመሪያው እኛ ማዕከል እቃ ለማንቀሳቀስ ባንቸገርም፣ ክልል ላይ ደርሰን ከዚያ ወደ ምርጫ ጣቢያ ስንቀሳሰቅ አስቸጋሪ ነው። የምናገኘው ድጋፍም በተወሰነ ደረጃ የተገደበ ነው። እዚህ ላይ ደግሞ የደህንነቱን ጉዳይ ስትጨምሪበት፣ የፀጥታ አካላትም በተለያዩ አካባቢዎች ሌላው ችግር ነው፡፡ ምክንያቱም የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ብዙ የፀጥታ ችግሮች መኖራቸው እሙን ነው። እነዚህ አካላት በየአካባቢው ያለውን የፀጥታ ችግር እየቀረፉ ነው፤ እንደገና የምርጫውን አካባቢ የፀጥታ ሁኔታ የሚሰሩት። ለምሳሌ ቁሳቁስ ማንቀሳቀስ የሚከናወነው ሁልጊዜም በእጀባ ነው።  ይሄ ማለት ደግሞ ከፍተኛ የፀጥታ የሰው ሃይል ይጠይቃል ማለት ነው። ይህንን ስትመለከቺው ምርጫው በዚህ አስቸጋሪ ወቅት መደረጉ በሂደቱም ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ይኖረዋል ማለት ነው።
በተለይ በአዲስ አበባ መራጮች ለመመዝገብና የምርጫ  ካርድ ለመውሰድ ሲሄዱ በተደጋጋሚ አልቋል እየተባለ እንደሚመለሱ፣ በተለያየ ሚዲያ ቅሬታቸው ሲያቀርቡ ሰንብተዋል። ቦርዱ ይህንን ችግር ያውቀዋል? ካወቀው ለመፍታት ያደረገው ጥረት ምንድን ነው?
ትክክል ነው። ትላንትና ከትላንት ወዲያ እኛም ራሳችን ወጥተን ችግሩን ለማየት ሞክረናል። የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳም በየምርጫ ጣቢያዎቹ እየተዘዋወሩ ለማየት ሞክረዋል። በመጀመሪያ እነዚህ ቅሬታዎች የሚመጡባቸው አካባቢዎች፣ አብዛኛውን ጊዜ ብዙ ሰው የሚኖርባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ናቸው። እነዚህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ነዋሪዎች ደግሞ ከ2007ቱ ምርጫ በኋላ የተስፋፉ ናቸው። እኛ የፖፑሌሽን ፕሮጀክሽን የለንም- እንደሚታወቀው። የህዝብ ቆጠራም አልተደረገም፤ የአሰፋፈር መረጃም የለም። ስዚህ እኛ መነሻ ያደረግነው በ2007 ከነበረው ምርጫ ተነስተን፣ በዚህ ላይ ይህን ያህል ፐርሰንት ሰው ቢጨምር በሚል ገምተን ነው እየሰራን ነው።
እርግጥ የቁሳቁስ እጥረት የለብንም። የሚያጋጥመን ችግር ግን ምንድን ነው? የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ አካባቢና የከፈትናቸው ምርጫ ጣቢያዎችና የተመዝጋዎች ፍላጎት አለመመጣጠን አሳይቷል።
እኛም ንዑስ ጣቢያዎችን ወዲያው እየከፈትን ችግሩን ከስር ከስር ለመቅረፍ እየሞከርን ነው። ምክንያም አንድ  የምርጫ ጣቢያ  ከ1 ሺህ  500  በላይ ተመዝጋቢ አያስተናግድም።  የዚያ የ1 ሺህ 500  ተመዝጋቢ የራሱ ኮድ አለው። ከዚያ በላይ ከመዘገብን ለቆጠራም አስቸጋ ነው የሚሆነው። እንደውም ከዚህ በፊት በአንድ ምርጫ ጣቢያ 1 ሺህ ነበር።
ስለዚህ አንድ ምርጫ ጣቢያ 1 ሺህ 500 ተመዝጋቢዎቹን መዝግቦ ሲጨርስ፣ የምርጫ ቁሳቁሱን መልሶና የምርጫ ኮዱን ዘግቶ ያለው አረዳድ በአዲስ ኮድና ቁሳቁስ ሌላ ነው መመዝገብ የሚችለው። አንድ የምርጫ ጣቢያ መራጮችን መዝግቦ ሲጨርስና አዲስ ሲጀምር፣ ተጨማሪ አስፈጻሚዎች ያስፈልጋሉ። ተጨማሪ ቢሮዎች መከፈት አለባቸው። ይሄንን ከከተማ አስተዳደሩ ጋር እየተነጋገርንበት ነው። የጋራ መኖሪያ አካባቢዎቹ ላይ የታየው ችግር ይህንን ነው የሚመስለው። አንዳንድ ጊዜ በማህበረሰቡ ዘንድ ካርድ ሲልቅ እየሄዱ ዝም ብሎ ካርድ መጨመር የሚመስል ነገር አለ። እንደዚያ ግን አይደለም። ቅድም እንደገለጽኩልሽ 1 ሺህ 500 ተመዝግቦ ሲያልቅ ያ ተዘግቶ እንደ አዲስ ሌላ ነው የሚጀመረው፡- ይሄ ማለት ሌላ አዲስ የምርጫ ጣቢያ እንደመክፈት ማለት ነው።
እኔ ለምሳሌ ትላንት የካ አባዶ ሄጄ ያጋጠመኝ የመጀመሪያው ዙር አልቆ ተዘግቶ፣ ሁለተኛውም አልቆ ሶስተኛ ዙር እየጠበቁ ነው ያገኘሁት። ስለዚህ ትላንትና የአዲሱን ዙር መከፈት እየጠበቁ ነበር ማለት ነው። እንደምታስታውሽው፤ የምዝገባው የመጀመሪያ ቀናት ላይ ተመዝጋቢ የለም ብለን ነበር። “ ከተማው ላይ የነበረው የተመዝጋቢ ቁጥር አነስተኛ ነው፤ ተመዝገቡ እያልን “ነበር። ልክ የመጨረሻዎቹ ቀናት አካባቢ ደግሞ ምዝገባው ሊጠናቀቅ በሚል ወደ መረባረብ አመራ መሰለኝ። እንዲህ አይነት እጥረቶች በተለይ ከላይ በገለጽኩልሽ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተከስቶ ነበር። እኛ ከስር ከስር ንዑስ ጣቢያዎችን እየከፈትን ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የተመደበላቸውን የሚዲያ የአየር ሰዓት በአግባቡ እየተጠቀሙ አይደለም የሚል ግምገማ ቀርቧል፤ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
ፓርቲዎቹ  እስካሁን ካለው የሚዲያ የአየር ሰዓት 54 በመቶውን ብቻ ነው የተጠቀሙት።
በአግባቡ ላለመጠቀማቸው የሚያነሱት ምክንያት ምንድን ነው?
በዚህ ጉዳይ ላይ ከእነሱ ጋር ውይይት አድርገን ነበር። በውይይቱ ላይ የሚያነሱት  ችግር የአቅም ማነስ ነው። “እኛ የአቅም ችግር አለብን፣ የምርጫ ቅስቀሳና ይዘቶችን ፕሮዲዩስ ለማድረግና በተባለው ጊዜ ለሚዲያዎቹ ለማድረስ ከባድ ሆኖብናል። ሚዲያዎቹም ቢሆኑ ያን ያህል ትብብር አያደርጉልንም” በሚል በተወሰነ መልኩ ቅሬታ ያነሱ አሉ። እውነት ነው፤ በፓርቲዎቹ በኩል የአቅም ችግር አለ። አሁን ደግሞ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የሚሰራጩ  ፕሮዳካሽኖች መስፈርት በጣም ከፍ እያለ ነው። እናም በዚያ መስፈርት መሰረት አዘጋጅቶ ለመስራት በጣም መቸገራቸውን ገልጸዋል። ሌላው አጋጠመን ያሉት አንዳንድ ቦታዎች ላይ የቋንቋ ችግር ነው።
ለምሳሌ እኛ በምንፈልገው ቋንቋ ሚዲው እያስተላለፈልን አይደለም የሚል ቅሬታ ቀርቧል። በውይይቱ ላይ ሚዲያዎቹም ስለነበሩ የምርጫ ዴስኩ ያንን ቋንቋ አውቆ ይዘቱን የሚመዝን ሳያውቁ ማስተላለፍ እንደሚቸግራቸው ገልጸዋል። ነገር ግን ይዘቱን ማወቅ የምርጫ ዴስኮች ሃላፊነት እንደሆነና በጊዜያዊነትም ቢሆን ይህን የሚያይላቸው ሰው እየመደቡ ማስተላለፍ እንዳለባቸው ተስማምተናል። ዋናው ግን በአቅም ችግር በሚዲያ መተላለፍ ያለባቸው እየተላለፉ አይደለም የሚል ነው። አልፎ አልፎ ደግሞ እኔ የምፈልገው ሚዲያ ላይ አልተመደብኩም። እዚህኛው ላይ... ኤፍ ኤም ላይ መመደብ ነበረብኝ በሚል፣ በደቡብ ብሔረሰቦች ክልል ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ያነሷቸው አቤቱታዎች ነበሩ። ለዚህም አሰራሩና አመዳደቡ እንዴት እንደነበረና እንደተከናወነ ምላሽ ተሰጥቷል።


Read 3040 times