Saturday, 01 May 2021 13:21

"የሁለቱ መደመሮች" መጽሐፍት ዳሰሳ

Written by  አንዳርጋቸው ጽጌ
Rate this item
(0 votes)

    "--የአፍሪካ ምሁራን ተሰባስበው ለዚህ ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል። “የአፍሪካ ህልውና የአፍሪካ ስልጣኔና የአፍሪካ ገናናነት፣ አፍሪካዊ የፍልስፍና መሰረት ከሌለው እውን ሊሆን አይችልም። በነጮች ፍልስፍና አፍሪካን መገንባት አይቻልም።” ፍልስፍና ፍለጋ እየባዘኑ ናቸው። ይህን አፍሪካዊ ፍልስፍና ፍለጋ አይናቸውን ወደ ኢትዮጵያ እያማተሩ ነው።--"
               (ክፍል -4)
ዶ/ር ዐቢይ የኢትዮጵያን ችግር በሚገባ እንድንረዳ የሚያደርጉ፣ ጠለቅ አድርገን እንድናስብ የሚያግዙ ጉዳዮችን አንስቷል። በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ ጋር በተመሳሳይነት የእድገት ደረጃ ላይ የነበሩ እነ ጃፓን፣ ኮሪያና ቻይና የመሳሰሉ ሃገሮች እንዴት በአጭር ጊዜ ሃገራቸውን ዘመናዊ ማድረግና ማበልጸግ እንደቻሉ፣ እኛ ግን ከዘመናዊ ስልጣኔና ብልጽግና ተኳርፈን እንደቀረን በቁጭት ይነግረናል።
በ("የመደመር መንገድ” ገጽ 49-51) “የእስራኤል ህዝቦች ራሳቸውን አጠንክረው የደረጀ ሃገር ገንብተው መኖር ጀምረዋል። ለሃገር ግንባታቸው መሳካት አስተዋጽኦ ካባረከቱት ጉዳዮች መካከል፣ እንደ ህዝብ አንድ የሚያደርጓቸው እሴቶች፣ ወጎችና ልማዶችን አለመተዋቸው፣ ተመሳሳይ ስነ ልቦና እንዲኖራቸው አስተዋጽኦ አድርጓል” ይለናል።
ዐቢይ ስለ እስራኤል ሆነ ስለ እስያ ሃገሮች በፍጥነት የመልማት ምክንያቶች የሆኑትን መሰረታዊ ጉዳዮች እየጠቀሰም እነዚህን ምክንያቶች በንጽጽር ወደ እኛ ሃገር አያመጣቸውም። እነዚህ ሃገሮች ለምን ተሳካላቸው፣ እኛ ለምን አልተሳካልንም የሚለውን ጥያቄ የሚመልሰው፤ የእነዚህ ሃገር ህዝቦች መተባበር፣ በጋራ ማለምና በጋራ መስራት በመቻላቸው ነው በሚል ነው። “ለምን እኛ በጋራ ማለም፣ በጋራ መስራት አልቻልንም?" ለሚለው ጥያቄ ዞሮ ዞሮ፣ ከሃገር በቀል አመለካከቶች መጥፋት፣ ከትክክለኛ ፖሊስ እጦት፣ ፖሊሲዎችን ወደ እቅድ በመተርጎም እቅድ የማስፈጸም እውቅትና ክህሎት እጥረት፣ ከባህል ከስነልቦና፣ ከፍልስፍና የመጡ ተባብሮ ተደምሮ የመስራት የአመለካከት ችግሮች የሚሉ ምላሾች ላይ የተቸከለ ምላሽ ነው የምናገኘው።  
ዐቢይ ቴክኒካል ከሆነው መፍትሄ ወጣ ሲል የሚያቀርበው መፍትሄ “በይቅርታ ለመሻገር በፍቅር ለመደመር” እስከጣርን ድረስ ችግራችንን ለማቃለል እንችላለን የሚል ነው። ይህ መፍትሄ በስፋትና በተደጋጋሚ የሚቀርብ መፍትሄ ነው። እዚህም ላይ የመፍትሄ ምልከታዎቹ ጠንካራ የእምነት ሰው ከመሆኑ ጋርም የተሳሰሩ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ ጭሮብኛል። እምነት፤ “በይቅርታ ለመሻገር በፍቅር ለመደመር” ለጆሮ በሚጥም መንፈስን በሚያረካ ውብ ስንኝ አማካይነት የሚደረግ ጥረት፣ ሁሌም ያሸንፋል የሚል ጽናት የሚሰጥ ነው።
ፖለቲካ በይቅርታ ለመሻገር በፍቅር ለመደመር የማይፈልጉ አካላትን በመቀነስ፣ ተደምሮ ለመሄድ የሚፈልጉትን ደምሮ፣ የድምር ውጤት ማብዛት እንደሚቻል በስኬት የተጠናቀቁ ምሳሌዎች የበዙበት የህይወት ዘርፍ ነው። የወያኔና የብልጽግና ፓርቲ ግንኙነት በመቀነስ መደመርን ማግዘፍ እንደሚቻል ጥሩ ምሳሌ ነው። ወያኔ ያለበት ብልጽግና ፓርቲ ወይስ የሌለበት ብልጽግና የድምር ውጤቱ ያማረ ነው? ለሚለው ጥያቄ፤ የብልጽግና አባላት ምን መልስ እንደሚሰጡ ግልጽ ነው።
በሌሎችም የህይወት ዘርፎች አሉታዊ አስተዋጽኦ ያላቸውን አካላት በመቀነስ ለሚቀሩት አካላት ድምር ሲነርጂ መፍጠር እንደሚቻል ይታወቃል። የዐቢይ የመደመር እሳቤ፤ በመቀነስ መደመር የሚል እይታ የሌለው መሆኑ በአንዳንድ አጋጣሚዎች ከሚያመጣው በጎ የበለጠ ዋጋ አስከፋይ ሊሆን ይችላል። እስካሁንስ ሳያስከፍለን ቀርቷል ወይ የሚል ጥያቄ ያስነሳል።    
በአጠቃላይ ዐቢይ በቴክኒካል፣ ወይም በተማጽእኖ ወይም እምነታዊ በሆኑ መፍትሄዎች ይፈታሉ ብሎ ካሰባቸው ችግሮች ይልቅ ከፍልስፍና ጋር የተያያዙ ናቸው ያላቸው ችግሮች ትልቁን ቦታ ሊሰጣቸው ይገባ ነበር። መደመር፤ ቴክኒካዊ፣ ሃይማኖታዊና ተማጽኗዊ ከሆኑ ገጽታዎቹ፣ ፍልስፍናዊ ወደሆነ ገጽታ ማጋደል ባለመቻሉ የችግሮቻችንን መሰረታዊ ምክንያቶችና ቁልፍ መፍትሄዎቹን ማወቅ እንዳንችል አድርጎናል፡፡
በተለያዩ የመደመሮቹ ገጾች፣ በተለያዩ አጋጣሚዎች፣ እንደ ናይጀሪያ አይነቶቹን ሃገሮች ያነሳል። ናይጀሪያ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች፣ አንቱ በተባሉ የአለም ዩኒቨርስቲዎች በመቶ ሺዎች ልጆቿን ያስተማረች፣ አገር ናት። ናይጀሪያ የቅኝ ገዥዎች ውጤት በመሆኗ እንደኛ ሃገር በመቶዎች አመታት ወደ ኋላ የሚመለሱ የብሔር ብሔረሰቦች መካሰስ ያለባት ሃገር አይደለችም። ቅኝ ገዥዎች ከሄዱ በኋላ በተለያዩ ብሔሮች መሃከል ግጭት የተነሳባት ሃገር ብትሆንም፣ ናይጀሪያ፣ ከእነ ሃብቷና ከተማረ የሰው ሃይሏ ጋር ትንንሾቹ የእስያ ነብሮች እንኳን የደረሱበት የልማትና የእድገት ደረጃ ላይ አልደረሰችም። የምትደርስም አትመስልም። ዐቢይ ግን ናይጀሪያንም ቢሆን ያለችበትን ሁኔታ በበጎ አይን ነው የሚያየው። ለምን? ምንድን ነው በአፍሪካውያንና በእስያውያን ወይም በምእራባውያን መሃከል ያለው ልዩነት። በተፈጥሮ ሃብት፣ በሰው ሃይል፣ በሰው ምንነት ወይስ ሌላ በምን? ለምን የናይጀሪያን ዝቅተኛ የእድገት ደረጃ በቁጭት አንመለከትም?
ከላይ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች የተነሳ፣ ለትልቁና ሁሉን ገዥ ለሆነው የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ስብራት ፈውስ የሚሆን መድሃኒት ከዐቢይ ብእር አልተገኘም። “መደመር”ን  እንደተመኘው የፍልስፍና ጽንሰ ሃሳብ አድርጎ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ የአመለካከት መሰባሰቢያ ማድረግ የሚችልበትን እድልና አጋጣሚ አባክኖታል። የመደመርን ፍልስፍና ዐቢይ በ“የመደመር መንገድ” መጽሐፉ ደግሞ ደጋግሞ እንደሚያነሳው ሽንቁር እንስራ ሆኖ ነው ያገኘሁት። በመደመር መጽሐፎቹ ያላነሳቸው፣ ያልፈተሻቸው በውብ ብእሩ ያልነካቸው ችግሮቻችንና መፍትሄዎቻቸው አሉ ብዬ አላምንም። ሆኖም ግን ሁሉንም ያፈሰሳቸው በሚገባ ሽንቁሩ ባልተደፈነ የመደመር እንስራ ውስጥ በመሆኑ እንስራው ሞልቶ ጥማችንን ማርካት አልቻልንም።
መጽሐፍ የሚዳስሱ ሰዎች የአንድን መጽሐፍ ጠንካራና ደካማ ጎን አቅርበው ዳሰሳቸውን መቋጨት መብታቸው ነው። ከፈለጉም ግን ጉድለት ያሏቸውን ለይተው፣ ጉድለት ማስተካከያ ብለው የሚያስቧቸውን ሃሳቦች በዳሰሳው ማካተት መብታቸው ነው። የኔ ዳሰሳ ዝም ብሎ መጽሐፍ ለመዳሰስ ብቻ አይደለም። በተለይ ለዐቢይ መጽሐፎች የሰጠሁት ክብደት ዳሰሳ አቅርቤ ብቻ ዞር እንድል አይፈቅድልኝም። የዳሰሳውን  ዳራ በገለጽኩባቸው ቀዳሚ ገጾች ላይ እንዳመላከትኩት፤  የ”መደመርን” ድክመት ማሳየት ብቻ ሳይሆን ይህን ድክመት እንዴት ማስወገድ ይቻል እንደነበር በማመላከትም ጭምር መቋጨት ነው።  
ዶ/ር ዐቢይ በተደጋጋሚ “መደመርን” ወደ እውነተኛ ፍልስፍና መውሰድ የሚችልባቸውን እድሎች በመጽሐፉ አግኝቶ አባክኗቸዋል ብያለሁ። ቀጥሎ የምሸጋገረው ባክነዋል ካልኳቸው እድሎች ወደ ዋናው የመደመር ፍልስፍና እንዴት መሸጋገር እንችል እንደነበር ወደ ማሳየቱ ነው።
ፍልስፍና ፍለጋ
ለምን ፍልስፍና አስፈለገን? ዐቢይ ፍልስፍና ፍለጋ የገባው “ኢትዮጵያ ታማለች፤ ከህመሟ እንድትወጣ አንድ አይነት መፍትሄ ያስፈልጋታል። ይህም መፍትሄ ሃገራዊ ፍልስፍና መሆን አለበት” ብሎ በማሰቡ ነው። “የሃገር ህመሟ በድህነት፣ በእርስ በርስ ግጭት፣ በሰላም እጦት፣ በህግ የበላይነት መጥፋት፣ በሞራል በስነምግባር መበስበስ፣ በመልካም አስተዳደር እጦት፣ በመብት መገፈፍ፣ በፍትህ ማጣት በጥቅሉ በአንድ ሃገር ዜጎች ላይ ሊደርሱ በሚችሉ ስቃዮች የሚገለጹ ናቸው” ብሎ ያምናል። አይደሉም ብሎ የሚከራከረው አይኖርም።
ይህ የሃገር፣ በውርደትና በግፍ የተሞላ ወቅታዊ ሁኔታ በአእምሮው ውስጥ ቁጭትና ምሬት ፈጥሯል። ሌሎች ሃገሮችና ማህበረሰቦች እኛ ኢትዮጵያውያን ከምንሰቃይባቸው ፖለቲካዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስቃዮች ከሞላ ጎደል ነጻ ሆነው የሚኖሩ መሆናቸው ቁጭቱን አበርትቶታል። ይህ ብቻ አይደለም፤ ዛሬ ከኢትዮጵያ በላይ የተረጋጋና የበለጸገ ህይወት ያላቸው ሃገሮች፣ ቀደም ባሉት ዘመናት ስልጣኔያቸው፣ ታሪካቸውና ገናናነታቸው ከኢትዮጵያ በታች ወይም እኩል እንጂ የሚበልጡ ያልነበሩ መሆናቸው ዐቢይን ከንክኖታል።
እንግዲህ የፍልስፍና ፍለጋ ምክንያቱ ይህ ከሆነ፤ እኛም እንደ ሃገርና ህዝብ ሌሎች ሀገሮች የተቀዳጁትን ዘመናዊነት፣ ሰላም፣ መረጋጋትና የሰለጠነ ህይወት ለመቀዳጀት ከሆነ ፍላጎታችን፣ ወደ ፍልስፍናው የሚወስደን መንገድ፣ አንድና አንድ ብቻ ጥያቄ በመጠየቅ የሚጀምር መሆን ይኖርበታል። “እንዴት ነው በስልጣኔ እነዚህ ከእኛ እኩል ወይም ከኛ በታች የነበሩ ሃገሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉ ነገራቸው የሞላላቸው መሆን የቻሉት?;
ይህ ጥያቄ ሃገሮች ለምንና እንዴት በፍጥነት ወደ ዘመናዊነትና ወደ ብልጽግና እንደ ተሸጋገሩ ወደ መመርመሩ ስራ ይወስደን ነበር። የዚህ የምርመራ ውጤት አንድና አንድ ብቻ ይሆን ነበር። ይህ የምርመራ ውጤት የሚቀጥሉትን ሃቆችም ያስገነዝበን ነበር።
ዘመናዊ የሆኑ ሃገሮች በሙሉ፣ መሰረታዊ ማንነታቸውን ያልካዱ፣ የቆዩ ትውፊቶቻቸውን ባህሎቻቸውን ያልለቀቁ፣ ስልጣኔ ወይም ሃገር ማዘመን እነዚህን የኛ የሚሏቸውን ማንነቶች የፈጠሩትን፣ ታሪካቸውን፣ ባህላቸውን፣ ወጋቸውንና ትውፊቶቻቸውን ለማንበር ለማስቀጠል የመንፈስ ጽናት ያላቸው ብቻ ናቸው። መዘመን የተለየ ማንነት ባህልና ታሪክ ባላቸው ሌሎች የዘመኑ ሃይለኞች እንዳይወረሩ ወይም እንዳይጨፈለቁ ለማድረግ ነው። ሳይንስና ቴክኖሎጂ እና የቆየ ባህል የሚቃረኑ ሳይሆኑ አዲሱ የጥንቱን በማደስ በማንበር መስተጋብር ላይ ተመስርቶ የሚያድግ አድርጎ ከሚታይ እሳቤ ጋር በቅርብ የተቆራኘ ነው።
ዐቢይ በምሳሌነትና በቁጭት መቀስቀሻነት የሚያነሳቸው፣ እነ ጃፓን፣ ኮሪያና ቻይና ፈጣን የዘመናዊነት እንቅስቃሴ መሰረታቸው፤ ማንነትን ከሌሎች ሃይሎች ወረራ ለመከላከል፣ ለራስ ማንነት፣ ክብርና ኩራት ከሚሰጥ ትልቅ ትርጉም ጋር የተያያዘ ነው። ለጃፓንነት ለኮሪያዊነት ለቻይናዊነት ከሚሰጥ ብሔራዊ ክብር ጋር የተያያዘ ነው።
ጃፓን በፍጥነት ራሷን ያዘመነችው፣ ይህን ማድረግ ባትችል በዘመናዊ ኢንዱስትሪ እድገት የሚመረቱ አደገኛ የጦር መሳሪያዎች የታጠቁ ምእራባውያን፣ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ ሊወሯት፣ ባህላቸውን፣ እምነታቸውንና ማንነታቸው ሊጭኑባት፣ እንደ ልዩ ሃገርና ህዝብ የነበራትን አለም አቀፋዊ ቦታ ሊገፏት እንደሚችሉ ከመገንዘብ ነው። መሪና ተመሪ አለቃና ምንዝር መላው የጃፓን ህዝብ ከፍተኛ መስዋእትነት በመክፈል ከአሜሪካ በስተቀር ሌላውን አለም ያስከነዳ ዘመናዊ የኢንዱስትሪ ባለቤት ያደረጋት ዋናው ምክንያት ይህ ነው። ሁሉም የእስያ ሀገሮች በፍጥነት የመልማት መኮርኮሪያቸው የመጣው ለብሔራዊ ማንነታቸው ለሚሰጡት ክብርና ኩራት፣ እሱን ከየትኛውም ጥቃት በዘመናዊ እድገት ለመከላከል በማሰብ ነው።
ማዕቀፉ ሌላ ቢሆንም የ”መደመርን ሃሳብ” ዐቢይ በገለጸበት ገጽ፣ ይህን ሃቅ በደንብ የተገነዘበው መሆኑን አሳይቶናል። “የሰው ልጅ ስጋዊ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ለስሙና ለነጻነቱ ቀናኢና ሟች ነው፡፡ የሰው ልጅ የክብሩና የነጻነቱ ፍላጎት ካልተሟላለት ለምግብ ቀርቶ በህይወት ለመኖር ምንም ፍላጎት እንደማይኖረው” ነግሮናል (መደመር ገጽ 6-7)። ይህን መልእክት ያስተላለፈው በአጠቃላይ የሀገራችንን የዜጎችንም ሆነ ከሃገራችን የማንነት ፖለቲካና ከዚህ ጋር ተያይዘው የተነሱ የእኩልነትና የነጻነት ጥያቄዎችን ከምር እንድንወስድ ለማመላከት ነው። እዚህ ላይ የነጻነትና የእኩልነት ቀበኞች አድርጎ የወሰዳቸው ሃገር በቀል ሃይሎችን ነው።
ሆኖም ግን የእኩልነት፣ የነጻነትና የክብር ቀበኞቹ የውጭ ሃይሎች ሆነው ሲታዩ፣ የአንድን ሃገር ህዝብ ምን ያህል በአንድነት እንዲተባበርና ለከፍተኛ ክንዋኔ ሊያስነሳው እንደሚችል በተለይ በፍጥነት መዘመንና መበልጸግ ከቻሉት ሃገሮች ታሪክ ጋር በማያያዝ አልቀረበም። ዐቢይ በምሳሌነት የጠቀሳቸው ሃገሮች በሙሉ ለእድገትና ለዘመናዊነት እንዲነሱ ዋናው ነዳጃቸው ሃገራዊ ክብር፣ ነጻነትና እኩልነት ነው። ይህን ማሳየት ችሎ ቢሆን ኖሮ ከግለሰብ ወይም ከብሔር በላይ ተሻግረን እንደ አንድ ሃገር ህዝብ ከምግብ በላይ የምናያቸው የጋራ ጉዳዮች ምን ሊሆኑ እንደሚገባቸው ወደ መጠየቅ እናመራ  ነበር። የተነጣጠሉ ግለሰቦችና ማህበረሰቦች የነጻነትና የክብር ጥያቄ፣ ኢትዮጵያን በመሰለ ሃገር ውስጥ አጠቃላይ የሁሉንም ድቀት ሳያስከትል፣በምን መንገዱ ተፈቶ፣ ጠንካራ የበለጸገ ሃገር መፍጠር እንችላለን ወደሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ይወስደን ነበር። አልሆነም።  
ሌላው ቀርቶ ሁሉም የግራ ርእዮተ አለም እንቅስቃሴዎች መሰረት ሃገራዊ ብሔረተኛነት ነው። ይህ ሃቅ በሃገራችንም የፖለቲካ ታሪክ የተንጸባረቀ ነው። የኢትዮጵያ ምሁራንና ተማሪዎች ከግራ ርእዮተ አለም በፊት ለትግልና ለለውጥ ያነሳሳቸው ኢትዮጵያ እንደ ሃገር የምትገኝበት ታሪኳንና የቀድሞ ገናናነቷን የማይመጥን፣ ከዘመናዊነት የራቀ አዋራጅ ሁኔታ ነው። ሃገራዊ ብሔረተኛነት ነበር።
እነ ቻይና እና ራሽያ እንዲሁም ሌሎች በኮምኒስት ርእዮት በኩል ወደ ዘመናዊነትና ብልጽግና የተጓዙት ሃገሮች በራሳቸው የተለየ ሃገራዊ ሁኔታ ብሔራዊ ማንነታቸውን፣ ክብርና ኩራታቸውን እንደያዙ በመቅረታቸው የኮምኒስት ርእዮት በተዳከመበት የአለማችን ሁኔታ፣ እነዚህ ሃገሮች ከምእራባውያኑ እንዳያንሱ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ፉክክር ወስጥ ገብተው የእድገትና የብልጽግና አሴት እያሰባሰቡ ነው።
የኢትዮጵያ ታላቁን የአድዋ ድል ተከትሎ የመጣው በሃገራዊ ብሔረተኛነት ላይ የተመሰረተውና በአብዮታዊ መንገድ የተሞከረው ሃገር የማዘመን ሙከራ ሲከሽፍ ቦታውን የተካው ከሃገራዊ ብሔረተኛነት ጋር ትልቅ ጠብ ያለው የዘውግ ብሔረተኛነት መሆኑ፣ ሃገሪቱ  ሌላ ሃገር የማዘመን ነዳጅ ሊሆን የሚችል ማህበራዊ የጋራ እሴት ማግኘት እንዳትችል ሆናለች። በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ ቁልቁል ወደ ታች እንጂ በፍጥነት በልማት እንደተመነደጉትና እሷም  እንደምትቀናባቸው የእስያ ሃገሮች ማደግ አልቻለችም።    
ምእራባውያንም ቢሆኑ የየሃገራቸውን ብሔራዊ ማንንነት፣ ከአጎራባች ሃገሮች ማንነት ለመከላከል፣ አንዱ የያዘውን የዘመነ መሳሪያና ዘመናዊ የአስተዳደርና የፖለቲካ ተቋምና መዋቅር፣ ሌላው በፍጥነት እየቀዳ፣ ከጦርነትና ደም መፋሰስ ፉክክር አልፈው ነው፣ ከሁሉም ቀድመው ዘመናዊ ወደ ሆነው አለም የገቡት። ሁሉም የአውሮፓ ሃገሮች ልዩ የሚያደርጋቸውን የማንነት መለያዎች እንደያዙ ነው የሰለጠኑት። የቆዩ የዘመናት በእውነት ላይ የተመሰረቱና ያልተመሰረቱ ታሪኮቻቸውንና ትርክቶቻቸውን ለጋራ ስነልቦና መገንቢያ አድርገው ነው የተነሱት።  ከእያንዳንዱ የአውሮፓ ሃገር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የሌለውን ጥንታዊ የግሪክና የሮም ስልጣኔ አቧራ ለብሶ ከነበረበት የታሪክ ትቢያ እያነሱና እያራገፉ የጨለማውን ዘመን ማለፊያ ሻማ አድርገው ተጠቅመውበታል። ለአዲሱ ዘመን የስልጣኔ መኮርኮሪያ በማድረግ ወደፊት ገስግሰውበታል።
በቅድሚያ አንድን ማህበረሰብ ለስልጣኔ/ዘመናዊነት ወደፊት የሚገፋው፣ ተባብሮና ተጋግዞ ከፍተኛ ስነስርአት ተላብሶና መስዋእትነት እየከፈለ ወደፊት እንዲገሰግስ የሚያደርገው ከዳቦ፣ ከልብስ፣ ከመጓጓዣ፣ ከመኖሪያ ቤትና ሌሎች ዘመናዊ ቁሳቁሶች ጋር የተያያዘ ፍቅር አይደለም። እነዚህ የስልጣኔ ትሩፋት እንጂ ለመሰልጠን የሚያስፈልጉ የሞራልና የመንፈስ ስንቅ አይደሉም።
በዘመናዊነት ወደፊት ከገሰገሱት የምስራቅና የምእራብ ሃገሮች መሃል የመዘመን ፍላጎቱ የራሱን የቀድሞ ስልጣኔ፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ወግ፣ ቋንቋና የአኗኗር ዘይቤ (way of life) ማትረፍን አላማው፣ የሞራልና የመንፈስ ስንቁ አድርጎ ያልተነሳ ሃገር ማግኘት አይቻልም።
የአፍሪካም ሆነ የኢትዮጵያም ችግር ይህ ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኤክስፐርቶች ወደ ምእራብና ምስራቅ ሃገራት ልከን ብናሰለጥን፣ በሚሊዮኖች ነዋይ አፍስሰን የእነሱን የልማት ፖሊስና እቅድ ብንገለብጥ፣ በቢሊዮኖች አፍስሰን የእነሱን ዘመናዊ መሳሪያዎች አምጥተን ብንገጥም፣ አፍሪካ የበለጠ እየተዋረደች ከምትሄድበት የውርደት እስር ቤት አትወጣም። ኢትዮጵያም እንደዚሁ። ችግሩ የተፈጥሮ ሃብት አለመኖር አይደለም። ችግሩ ትምህርት ስልጠና፣ ዘመናዊ አሰራር ስልትና ቁሳቁስ ከምእራቡም ከምስራቁም የመግዛት አቅም ማጣት አይደለም። ይህ ካልሆነ ታዲያ ችግሩ ምን  ላይ ነው የሚል ጥያቄ መነሳት ይኖርበታል።
የአፍሪካ ምሁራን ተሰባስበው ለዚህ ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል። “የአፍሪካ ህልውና የአፍሪካ ስልጣኔና የአፍሪካ ገናናነት፣ አፍሪካዊ የፍልስፍና መሰረት ከሌለው እውን ሊሆን አይችልም። በነጮች ፍልስፍና አፍሪካን መገንባት አይቻልም።” ፍልስፍና ፍለጋ እየባዘኑ ናቸው። ይህን አፍሪካዊ ፍልስፍና ፍለጋ አይናቸውን ወደ ኢትዮጵያ እያማተሩ ነው።
ዶ/ር ዐቢይም ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት እዚህ ልድገመውና “ከኢትዮጵያውያን መሰረታዊ ስሪት የሚነሳ ችግሮቻችን ሊፈታ የሚችል፣ እኛው እያቃናነውና እያሟላነው የምንሄደው፣ ከአለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተገናዘበ፣ ሁላችንንም ሊያግባባና ሊያስተባብር የሚችል አንዳች ሉአላዊና ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ያስፈልገናል”  ብሎናል።
ዐቢይ ይህን ፍልስፍና ለማግኘት ብዙ ሞክሮ የተቸገረው ለምን እነ እስራኤል፣ እነ ጃፓን እነ ቻይና ኮርያና ሌሎች ሃገሮች ተሳካላቸው፣ ለምን እኛ አልተሳካልንም የሚለውን ጥያቄ መልሱን ቴክኒካል በሆነ መንገድ በመመለሱ ነው።
ቀጥሎ የሚነሳው ዘመናዊነትን ለማምጣትና ዘመናዊነትን ተከትለው የሚመጡ በሌሎች ሃገሮች የተከሰቱ በጎ ነገሮች በሃገራችን እንዲከሰቱ ለማድረግ የኛ የኢትዮጵያውያን የመንፈስ የሞራል ስንቅ መሰረት የሚሆኑ ከማንነታችንና ከሰብአዊ ክብራችን ጋር የተያያዙ፣ ከታሪካችን ከባህላችንና ከትውፊታችን የምንመዛቸው እውነተኛ የሆኑ ያልሆኑም፣ እኛ የምናምንባቸው ጉዳዮች  ምን ሊሆኑ ነው የሚለው ጥያቄ ነው። ይህን ጥያቄ ለመመለስ በቅድሚያ ከዘመናዊ እድገት ምቹነት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ሃገሮችን ተጨባጭ እውነታ በንጽጽር መልኩ ማየቱ ጠቃሚ ነው።


Read 1050 times