Monday, 03 May 2021 00:00

ጎግል በ3 ወራት 17 ቢ. ዶላር ማትረፉን አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    የአለማችን አየር መንገዶች 47.7 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያጡ ይጠበቃል

          ታዋቂው የቴክኖሎጂ ኩባንያ አልፋቤት የሚያስተዳድረው ጎግል፣ ባለፉት 3 ወራት ብቻ 17 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱንና ይህም በታሪኩ ያስመዘገበው ከፍተኛው የሩብ አመት ትርፍ መሆኑን ከሰሞኑ ባወጣው  መግለጫ አስታውቋል፡፡
ጎግል በተጠቀሰው ጊዜ ያገኘው ትርፍ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ጊዜ ካገኘው ጋር ሲነጻጸር የ162 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን የዘገበው ቢቢሲ፤ ለትርፋማነቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተው፣ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በመላው አለም በተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦች ሳቢያ የጎግል ተጠቃሚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉ መሆኑንም አመልክቷል፡፡
ጉግል ባለፉት ሶስት ወራት ያገኘው አጠቃላይ ገቢ 31 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ገቢው ካለፈው ሩብ አመት በ30 በመቶ መጨመሩንም አስታውቋል፡፡
በሌላ የቢዝነስ ዜና ደግሞ፣ በያዝነው የፈረንጆች አመት 2021፣ የአለማችን አየር መንገዶች ገቢ በ47.7 ቢሊዮን ዶላር ያህል ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ አለማቀፉ የአየር ትራንስፖርት ማህበር አያታ አስታውቋል፡፡ የአመቱ የአየር መንገዶች ገቢ ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር በመጠኑ መቀነስ እንደሚኖረው ያመለከተው ተቋሙ፤ በ2020 የአለማችን አየር መንገዶች ያጡት አጠቃላይ ገቢ 126.4 ቢሊዮን እንደነበርም አስታውሷል፡፡
የአለማችን አየር መንገዶች በያዝነው አመት 2.4 ቢሊዮን ያህል ሰዎችን ያጓጉዛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጸው አያታ፤ ባለፈው አመት ያጓጓዟቸው መንገደኞች ግን 1.8 ቢሊዮን ብቻ እንደነበሩ አስታውሷል፡፡


Read 2738 times