Saturday, 01 May 2021 13:05

ሰላምን በስዕል የገለፁ ወጣቶች ተሸለሙ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)

  “እሸት” ችልድረን ኤንድ ዩዝ ዴቨሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን “ወጣቶችና ሰላም” በሚል ርዕስ ወጣቶች ሰላምን እንዴት እንደሚረዱት በስዕል እንዲገልፁ ባዘጋጀው ውድድር ላይ ያሸነፉ ወጣቶችን ሸለመ። ድርጅቱ ባፈው ማክሰኞ ላምበረት መነሀሪያ ፊት ለፊት በሚገኘው ፓስፊክ ሆቴል ባዘጋጀው የግማሽ ቀን ወርክሾፕ ነው ከ1 እስከ 5 የወጡ ወጣቶችን የሸለመው።  ድርጅቱ እ.ኤ.አ በ2001 የተቋቋመ ሲሆን ታዳጊዎችና ወጣቶች በስነ-ተዋልዶ ጤና፣ በትምህርት በአጠቃላይ ጤናና ሁለንተናዊ እንቅስቃሴያቸው የነቁና የበቁ ሆነው አገር እንዲረከቡ በማዘጋጀት ላይ ትኩረቱን አድርጎ እንደሚንቀሳቀስ የድርጅቱ መስራችና ዋና ስራአስኪያጅ አቶ ሲሳይ ታረቀኝ ተናግረዋል።
በእለቱ 1ኛ ለወጣ 10 ሺህ ብርና ከ2 እስከ 5 ለወጡት በየደረጃው የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት ያበረከተ ሲሆን ባጠቃላይ በውድድሩ ለተሳተፉት የተሳትፎ ምስክር ወረቀት ሰጥቷል። በእለቱም በውድድሩ አሸናፊ የሆኑ ወጣቶች ስዕሎች ለእይታ የቀረቡ ሲሆን፣ የወርክሾፑን ታዳሚዎች አስደምመዋል። በዚሁ ወርክሾፕ ላይ ድርጅቱ ከኮተቤ ሜትሮፖሊታ ዩንቨርሲቲ ጋር በመተባበር ነው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ ሴት ወጣት ተማሪዎች የሰላም ግንባታ ላይ ያላቸው አስተዋጽኦ ምን ይመስላል የሚል ጥናት አጥንቶ ለታዳሚ ያቀረበ ሲሆን የጥናቱ ግኝት ሴት ተማሪዎች የጎላ ተሳትፎ እንደሌላቸው በጥናቱ መረጋገጡንና ወደፊት ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ምን መደረግ አለበት የሚለው ላይ ምክክር መደረጉንም አቶ ሲሳይ ታረቀኝ ተናግረዋል።

Read 11110 times