Print this page
Saturday, 01 May 2021 13:01

“ሰውን ከማስከፋት በቀር፣ አይወጣኝም ደግ ነገር”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(3 votes)

  እንኳን ለብርሀነ ትንሳኤው አደረሳችሁ!
እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው...በአንድ ወቅት “አንዳንድ ቀንማ ይሻላል ውሽማ...” አይነት ነገር  ነበር፣ አይደል!  ለሪያሊቲ ሾው እኮ አሪፍ ነበር። ያው በዘመኑ ቋንቋ ‘አፕዴት’ መደረግ ስላለበት “አንዳንድ ቀን...; የሚለው ይሰረዝልን፡፡ ልክ ነዋ...“ውሽማ የሌለው፣ ዘመን ያመለጠው...” ምናምን ነገር በሚል ይተካልንማ!
ስሙኝማ...የዘፈን መልዕክቶችን ነገር ካነሳን በቆዩት ዘመናት ተዘፍነው እስካሁን ድረስ ይቺን ታክል መልዕክታቸው ሳይሳሳ የቆዩ መአት አሉ፡፡     
እንደወንዝ ድንጋይ አሳ እንደላሰው
ሙልጭልጭ እያለ አስቸገረኝ ሰው
ተብሎ ተዘፍኖ ነበር፡፡ ያን ጊዜ የሚሙለጨለጩ ሰዎች ‘አብላጫ ድምጽ’ ባልነበሩበት ጊዜ፡፡ ነገርዬው ሁሉ የእንትኑ ወደ እንትኑ ሆኖ፣ እንደ አሁኑ ሊሆን! አሁን እኮ ሙልጭልጭነት… አለ አይደል…በተቋም ደረጃ አይሰጥ እንጂ ራሳችንን በራሳችን እያሰለጠንን ‘አትራፊ’ ሙያ አይነት ነገር እየሆነ ነው፡፡ ደግሞላችሁ እኮ በሀፍረት አንገት ማስደፋቱ ቀርቷል፡፡ እንደውም የዘመኑ ዋነኛ ምከር “ገልበጥበጥ በል እንጂ!” ነው፡፡  አቋም ብሎ ነገር የለ፣ ‘ፕሪንሲፕል’ ቅብጥርስዮ ብሎ ነገር የለ... በቃ አሳ የላሰው የወንዝ ድንጋይ መሆን ነው፡፡
በቃ ዘመን ተሻጋሪ ሥራ ማለት እንዲህ አይነቱ አይደል! (እግረ መንገድ አሳ የላሰው የወንዝ ድንጋይ ሙልጭልጭ እንደሆነ አወቅን ማለት አይደል! ...ምንም እንኳን የእውቀት እጥረት ደረት የሚያስነፋበት ዘመን ውስጥ ያለን ቢመስልም፣ ለማለት ነው፡፡) የምር ግን... ይቺ ስንኝ ለዚህ ዘመን ተመጥና የተሰፋች አትመስልም?!
እናላችሁ... በተለይ ‘ቦተሊካ’ ውስጥ በአሳ የተላሰ የወንዝ ድንጋይ እየሆናችሁ ያላችሁት እውን አሳ ብቻ ልሷችሁ ነው እንዲህ የምትሆኑት! አሀ... ግራ ሲገባንስ! እንግዲህ በትንሹም፣ በትልቁም  ‘ጠርጥር፣ ጠርጥር’ የሚለን ነገር አለ አይደል... እናማ፣ ስንጠረጥር የሆነ ጥናት ነገር ቢካሄድ እኮ “በዓለም ፖለቲካ ላይ በተደረገ የህዝብ አስተያየት ምዘና መሰረት፤ በሙልጭልጭነት በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ልዩነት ዓለምን እየመሩ ያሉት...” ምናምን የሚል ሊስት ውስጥ ሳትከቱን አትቀሩም፡፡
እኛም ግራ ገባና! ...ወይ በዚህ የመገለባበጥ ክህሎታችሁ (ቂ...ቂ...ቂ...) ኦሎምፒክ ምናምን ሄዳችሁ ስማችንን አስጠሩልን፡፡ ወይ ደግሞ ‘ፖሊተካዊ መገለባበጥን በሦስተኛ ዲግሪ ደረጃ አሰልጥኖ የሚያስመርቅ’ ምናምን የሚል ትምህርት ቤት ይከፈትልንና ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች ፉክከር እንብቃ፡፡ ደግሞላችሁ... ኦፊሴላዊ እውቅናውን የሚሰጠን አካል የትኛው እንደሆነ ባናውቅም በሁሉም ነገር ላይ ማስመሰል የሚችለን ስለሌለ፣ እናንተም በማስመሰል ‘ታሰለጥኑናላችሁ፣’ እኛም በማስመሰል ‘እንሰለጥናለን’...“አራት ነጥብ” የሚባለው እንዲህ ሲሆን አይደል! (ማን ነበር ይቺን ‘አራት ነጥብ’ የምትል ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ ለአገልግሎት ያበቃት!) እናማ...እናንተ በተገለባበጣችሁ ቁጥር በስንቱ ነገር የሚጥመለመለው አንጀታችን፤ በዚህም መገለባበጥ አለበት እንዴ!
ምክር ለመስጠት የሚፈቀድልን ከሆነ... አብዝቶ መገለባበጥ የወገብ ቅጭት ሊያስከትል እንደሚችል የሆነ ሳይንሳዊ ጥናት ነገር ሳይኖር አይቀርም፡፡ እናማ... አጥሚት እየበጠበጠ የሚያመጣ እንደልብ ስለማይገኝ ቡላ እንዳማራችሁ እንዳይቀር ለማለት ያህል ነው፡፡ (እሱ ነገር “ወገብ ይጠግናል” የሚባለው ነገር... ‘ፋክት—ቤዝድ’ ነው እንዴ?!) እናማ... አሳ የላሰው የወንዝ ድንጋይ የሚያደርጋችሁ ተዉንማ! አሀ...እኛ የእናንተ መጫወቻ ብዮች ነን፣ የዳማ ጠጠሮች ነን!...ወይስ ጢባጢቤ ነን!?
እናማ... እንደ ዘንድሮ ሞራል፣ ስነምግባር የመሳሰሉ ህዝብን የሚያስተሳስሩ፣ ከአንድ ማእድ የሚያቋድሱ፣ “ጉረስልኝ በሞቴ; የሚያባብሉ ነገሮች በሳሱበት ጊዜ የጥንቶቹ ዘፈኖች አሁንም  ከእነ መልዕክቶቻቸው ‘ፏ’።
እንዳፈር ፍርስርስ ለሚለው ገላችን
እንደ ድጋይ ስብር ለሚል አጥንታችን
የእኛ መንቀባረር ከቶ ለምንድነው
የቤት መለሰኛ ጭቃ ለምንሆነው
የሚንቀባረር ፖለቲከኛ አለ? ያውም መአት! የሚንቀባረር ምሁር አለ? ያውም መአት! የሚንቀባረር ባለስልጣን አለ? ያውም መአት! የሚንቀባረር ታዋቂ ሰው አለ? ያውም መአት! የምንንቀባረር ‘እኛ’ አለን? ለቁጥር እስኪያስቸግር ድረስ መአት!
ኮሚክ እኮ ነው... ይሄ ያለንበት ዘመን እኮ በምንም ሁኔታ የሚንቀባረሩበት፣ ይቺ ሀገራችን በምንም ሁኔታ የሚንቀባረሩባት፣ ያለንበት መሬት የወረደ ሀቅ በምንም አይነት የምንንቀባረርበት አይደሉም፡፡ እናላችሁ... በእንዲህ አይነት ሁኔታ እኛ ህዝቦች ላይ ሊንቀባረሩብን የሚሞክሩ ስታዩ...ቅሽምና ወደ ‘ኤፒዴሚክ‘ ደረጃ መድረሱን ታያላችሁ። 
አይደለም ጂ ፕላስ ቱና ጂ ፕላስ ስሪ ቀርቶ፣ ጂ ፕላስ ሰርቲ ስሪ ቢደረስ፣ አእምሮ ተከራይ እንዳጣ ቤት ወና ሆኖ  በድንጋይ ላይ ድንጋይ ስለተከመረ ምን የሚያንቀባርር ነገር አለ! ይልቁንም “ሲሚንቶ ከሀገር ጠፋ!” የማያስብለውን፣ “የብረት ዋጋ ጣራ ቀድዶ ሄደ” የማያሰኘውን፣ “ታማኝ ባለሙያ ማግኘቱ አስቸጋሪ ሆነ፣” የማያስብለውን አእምሮን ከተፈለገም ‘በነጣ’ መገንባቱ የተሻለ ነበር፡፡ አንድም ሀገር መከራዋን እየበላች ያለችው እየተገነባ ያለው አእምሮ ሳይሆን ሌላ ሌላው ነገር ስለሆነ እኮ ነው፡፡
እናማ... ዘለዓለም የምትኖሩ እየመሰላችሁ፣ በባለፈረንካነት፣ በባለ ዘመናዊ ጭቃ ሹምነት፣ በባለ ድንኳን ሰበራ ተንታኝነት፣ “እኛም አንድ ሰሞን እንዲህ አርጎን ነበር...” የሚለውን ተረት የሚነግራቸው በማጣት በሚመጣ ባለጊዜነት...... መከራችንን እያበላችሁን ያላችሁት ተዉንማ! አሀ...ስንቶቻችሁን እንቻል!
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል በኋለኞቹ ዘመናት ምን የመሳሰሉ የሞራል፣ የሥነምግባርና መሰል ርዕሶችን የሚያነሱ መአት ዘፈኖችን ነበሩ፡፡ ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት ገዳዳ ፖለቲካችን ስንቱን ነገር እንዳንጋደደ የሚታያችሁ፣ አብዛኛውን ጊዜ በአጋጣሚ እንዲህ አይነት ዘፈኖችን ስትሰሙ ነው፡፡
ሥራ ውዬ ደክሞኝ ስገባ ከቤቴ
ትጠብቀኛለች ውዷ ባለቤቴ
እየተባለ የትዳርን ክቡርነትና የጥንዶችን መተሳሰብ የሚያጎሉ መልክቶች ያሏቸው ዘፈኖች የሚሰሙበት ጊዜ ነበር፡፡ የሚዘፈንበት ዘመን ነበር፡፡ አሁን ዘመን ሊለዋወጥ! ይቺን ስሙልኝማ...ጓደኛሞቹ ሲፕ እያደረጉ ወሬ ላይ ናቸው፡፡
“ምንድነው እንዲህ ፊትህን ጭፍግግ ያደረግኸው? አቦ እንጠጣበታ!”
“እባክህ ደህና አይደለሁም…”
“ምን ሆነሀል? አሞሀል እንዴ!”
“እንደዛ በለው... ማስፈራሪያ ቴክሰት አይደርሰኝ መሰለህ!”
“ማስፈራሪያ! ምን የሚል ደግሞ? ከማን?”
“ከሚስቴ ጋር መማገጥህን ካልተውክ አናትህን ነው በጥይት የማፈርስልህ፣የሚል መልዕክት በተደጋጋሚ እየደረሰኝ ነው፡፡”
“ታዲያ አርፈህ መቀመጥ ነዋ!” ይለዋል ጓደኝየው፡፡
 አጅሬው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…
“የየትኛዋ ባል እንደሆነ አላወቅሁትማ!”
እንዲህም አይነት ነገር ሊኖር ይችላል…ለማለት ያህል ነው፡፡
ደግሞላችሁ... አንድ ለመንገድ፣ እንዲህ የምትል አሪፍ ስንኝ አለች...
ወደመጣሁባት ምድር
እስከመለስባት በክብር
ሰውን ከማስደሰት በቀር
አይወጣኝም ክፉ ነገር
ይቺን ግጥም ከሰማችሁልኝ በኋላ...በተለይ የቦተሊካችንን መንደር እዩትማ! “ምን ይመስልሀል?” አትሉኝም! የሚመስለኝማ የመጨረሻዋን ሁለት ስንኝ መለወጥ ብቻ ነው.... ለሁሉም ሳይሆን አብዛኛዎቹ ለሚባሉት...
ሰውን ከማስከፋት በቀር
አይወጣኝም ደግ ነገር
ምን ይመስለኛል መሰላችሁ...ዘንድሮ ይቺ “ሰውን ከማስከፋት በቀር፣ አይወጣኝም ደግ ነገር” የምትለው ነገር በቦተሊከኞቹ አካባቢ የጋራ ባህሪይ ብትመስልም ሁላችንም ሊባል ምንም በማይቀረው ደረጃ ሳትነካካን አትቀርም፡፡
መልካም የትንሳኤ በዓል ይሁንላችሁማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1560 times