Wednesday, 05 May 2021 00:00

የዛሬ 70 ዓመት ዓለምን ያስደመመ ጀግንነት ያሳዩ ኢትዮጵያውያን

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(1 Vote)

       • የኢትዮጵያውያን ውለታ በህዝባችን ልብ ውስጥ ለዘላለም ይኖራል” ኮሪያውያን
       • የኢትዮጵያኑ ጀግንነት ብቻ ሳይሆን ሰብአዊነትና ደግነትም አሳይተዋል
       • ኢትዮጵያ ጦር ከመላክ ባሻገር ለደቡብ ኮሪያየ400 ሺ ዶላር ድጋፍ አድርጋለች
       • በጦርነቱ ድምፃዊ ካሳ ተሰማና አትሌት ማሞ ወልዴ ተሳትፈውበታል፡፡
                  
              ከዛሬ 71 ዓመታት በፊት ነበር ሰሜን ኮሪያ ደቡብ ኮሪያን በመውረር  የጦርነት አዋጅ ያስነገረችው፡፡  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሰኔ 19 ቀን 1942 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ፤ ሰሜን ኮሪያ የጠብ ጫሪነት ተግባሯን በአስቸኳይ እንድታቆምና የጀመረችወን ትንኮሳ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አቁማ ወደ ሰላማዊ ህይወቷ እንድትመለስ  አስጠነቀቀ። ይህንን የጸጥታው ምክር ቤትን ውሳኔ ግን ሰሜን ኮሪያ ልትቀበለው አልወደደችም። የምክር ቤቱን   ውሳኔ ወደ ጎን  በማለት ወረራዋን ገፋችበት። የጸጥታው ምክር ቤትም ለዓለም ሰላም ሲባል ወረራው እንዲቀለበስ ወሰነ። በዚህም መሠረት፤ ውሳኔውን የደገፉና ለውሳኔው ተግባራዊነት ምላሽ የሰጡ  አሥራ ስድስት የዓለም ሀገራት ወታደሮቻቸውን ወደ ስፍራው ለመላክ ወሰኑ፡፡  ከነዚህ አገራት   መካከልም   ኢትዮጵያ ትገኝበታለች ። ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በሰጠችው ምለሽ  መሰረትም፤ 1122 መኮንኖችንና ወታደሮችን ያካተተው የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የቃኘው ሻለቃ ጦር፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሥር ተሰማርቶ፤ በኮሪያ ጦርነት ለመሳተፍ  ከጂቡቲ ወደብ የተንቀሳቀሰው የዛሬ 70 ዓመት ሚያዚያ 8 ቀን 1943 ዓ.ም ነበር፡፡  ከአሥር መድፈኛ ሻለቆች ተውጣጥቶ የተመሰረተው ይኸው ሰራዊት “ቃኘው ሻለቃ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶት በእንግሊዛውያን ወታደሮች ስምንት ወራት የፈጀ ስልጠና ሲወስድ ቆየ። በመጨረሻም ሚያዚያ 5 ቀን 1943 ዓ.ም ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ ባሉበት የቃኘው ሻለቃ አባላት ችሎታቸውን  ለማሳየት ወታደራዊ ሰልፍ አደረጉ፡፡
ንጉሡም፡- “እነሆ በጋራ ደኅንነት መርሕ መሠረት፤ እጅግ ቅዱስ ለሆነው ለዓለም ሰላም ዘብ ልትቆሙ፣ የዓለምን ግማሽ የሚሆን ጉዞ ትጓዛላችሁ። ሂዱና ወራሪዎችን ድል ንሱዋቸው። በኮሪያ ልሳነ ምድርም ሕግና ሥርዓትን አስከብሩ፡፡ ይሄን ሰንደቅ ዓላማ መመሪያ  አድርጋችሁ እንድትዘምቱ፣ በተሰማራችሁበት ቦታ ጀግንነት ሠርታችሁ በደረታችሁ ላይ ልዩ ምልክት አድርጋችሁ በኩራት ስትመለሱ በአደራ የሰጠናችሁን አርማ መልሳችሁ እንድታስረክቡን” በማለት ነበርሞራል ሰጥተው በክብር የሸኟቸው፡፡  የክብር ዘበኛ ቃኘው ሻለቃ ጦር፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዕዝ ሥር ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ ወደ ኮሪያ ሲንቀሳቀስ፣ በወቅቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ከነበሩት ከግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ እጅ የተቀበለውንና የጦር መመሪያ የሆነውን ሰንደቅ ዓላማና የጦሩን ዓርማ፣ የክብር ዘበኛው ጦር ዓለም አቀፍ ግዳጁን በድል አጠናቆ ሲመለስ ለንጉሠ ነገሥቱ መልሶ አስረክቧል፡፡
1122  የመጀመሪያው ዙር የቃኘው ሻለቃ አባላት   “እልም አለ ባቡሩ እልም አለ ባቡሩ፣ ወጣቱን ይዞ በሙሉ” የሚለው ዜማ በድምፃዊ ካሳ ተሰማ እየተዜመለት ተመመ፡፡   በባቡር ከአዲስ አበባ ወደ ጅቡቲ ከተጓዙ በኋላ  በመርከብ ፑዛን ወደተሰኘችው የኮሪያ የወደብ ከተማ ደረሱ፡፡  እዚያ  ሲደርሱም በአገሪቱ መሪ ፕሬዚዳንት ሲንግ ማን ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው። ከጥቂት ቀናት ቆይታ በኋላም ከአሜሪካ የጦር መሣሪያዎችና  ከኮሪያ መልክዐ ምድር ጋር የሚያስተዋውቅ ስድስት ሳምንታት የፈጀ  ሥልጠና ወስደው 85 መኮንኖችና 1037 የቃኘው ሻለቃ ወታደሮች፣ በሰባተኛው የአሜሪካ ዲቪዚዮን ሥር  ተሰለፉ።  የኢትዮጵያ ሰራዊት ሰውነቱ ቀጭንና ከሲታ፣ስለነበር  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አባል አገራት  የመከላከያ ኃይል አመራሮች፣ በሰራዊቱ ላይ  ከፍተኛ ንቀት  አድሮባቸው ነበር።  ይህን መሰል ከሲታ ጦር ውጊያውን እንዴት  መቋቋም ይችል ይሆን በሚል ሳይሰጉም አልቀሩ። ድምፃዊ ካሳ ተሰማ ክራሩን እንዳነገተ “አልም አለ ባቡሩን” እያዜመ ከጦሩ ጋር አብሮ ዘምቷል፡፡
በሁለተኛው ዙር የተጓዘው ቃኘው የጦር ግንባር ጦርነቱ በከፍተኛው የ”ቲቮ” በረዷማ ተራራ ላይ  ነበር። ሦስተኛው ቃኘው ለገሃር ማክ በሚባል ወታደራዊ መኪና ወደ ጃንሜዳ ተጉዞ ከዚያ በባቡር ወደ ጅቡቲ፤ ከዚያም በአሜሪካ መርከብ ተሳፍረው ለ22 ቀናት ተጉዘው የኮሪያ ባህር በር ፑዛን ገቡ። ጦሩ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ አባላት ነበሩት። በኮሪያው ዘመቻ ወቅት የኢትዮጵያ ሻለቃ በተለያዩ አይነት ዋና ዋና ውጊያዎች ተሳትፏል። ሰራዊቱ በሽምቅና በደፈጣ ውጊያ ተወዳዳሪ አልነበረውም። በአውደ ውጊያው የከባድ መሳሪያ ተኳሽና የሞርታር ዓላሚነትም ተመራጭ ነበር ። በግግር በረዶ ሥር ተቀብረው የቆዩ ፈንጂዎች የሚመክኑት በቃኘው ሻለቃ አባላት ነበር ። የቃኘው ሻለቃ አባላት ከአፍሪካ የሄዱ ብቸኛ ወታደሮችም ነበሩ ። በኮሪያ ምድር ከዘመቱ ምድቦች ሁሉ የተሰጣቸውን ሁሉንም ግዳጅ በድል የተወጡ ብቸኛ ወታደሮችም ነበሩ የቃኘው ሻለቃ አባላት፡፡  በቁጥር 238 ግዳጅ ተሰጥቷቸው ሁሉንም በድል ነበር የቋጩት። ኢትዮጵያ በአጠቃላይ በአምስት ዙር 6037 ወታደሮችን አዝምታለች። ከእነዚህ መካከል 122ቱ በጦርነቱ ሞተዋል። 536 ወታደሮች ቆስለዋል። የተማረከ ግን አልነበረም፡፡
በጦርነቱ ማብቂያ ከአሜሪካ ወገን ሆነው ከተዋጉት ሃያ አንድ ሀገራት መካከል ሁሉም በኮሙኒስቶች እጅ የወደቁ ምርኮኛ እስረኞች ሲኖሯቸው ኢትዮጵያ አንድም ምርኮኛ እስረኛ ያልነበራት ብቸኛ ሃገር ናት፡፡ ጦርነቱ አብቅቶ የምርኮ ልውውጥ ሲደረግ  ደቡብ ኮሪያ 8343፣ አሜሪካ 4714፣ እንግሊዝ 977፣ ቱርክ 244፣ አውስትራሊያ 26፣ ካናዳ 33፣ ፈረንሳይ 12፣ ግሪክ 3፣ ኮሎምቢያ 28፣ ታይላንድ 5፣ ኔዘርላንድ 3፣ ቤልጅየም 1፣ ፊሊፒንስ 97፣ ደቡብ አፍሪካ 9፣ ኒውዚላንድ 1 ፣ ኖርዌይ 3 ምርኮኛ ሲመለስላቸው ኢትዮጵያ ግን አንድም ሰው ያልተማረከባት ብቸኛ ሀገር ነበረች።  ይህን የኮሪያ ዘማቾችን ወደር የለሽ ጀግንነት አዝማሪዎች በስንኝ አወድሰውታል፡፡
“አይዞሽ አሞራ አይዞሽ ጭልፊት
ቃኘው ሻለቃ አልፏል ከፊት”
***
“አጨደው ከመረው ወቃው እንደ ገብስ፤
የኢትዮጵያ አርበኛ ኮሪያ ድረስ።”             
የቃኘው ሻለቃ አባላት በጦርነት የተሠውትን አባሎቻቸውን አስከሬን ለጠላት ጥለው አይሮጡም። እሳት እየዘነበባቸው የጓዶቻቸውን ክቡር አስከሬን ተሸክመው ይሮጣሉ። አንድ የኢትዮጵያ ወታደር የቆሰለ ኮሪያዊ ወታደርን እንደተሸከመ ተመትቶ ተሠውቷል።
የቃኘው ሻለቃ ጦር አባላት በኮሪያ ምድር በቆዩበት ጊዜ ሰሜን ኮሪያዎች እንደ ልዩ አይቀመሴ ፍጡር ያዪቸው ነበር። እንግሊዛዊው የጦርነት ታሪክ ጸሐፊ ጆን ኬጋን፤ “ኢትዮጵያውያን እልኸኞች ናቸው። መማረክን  አይቀበሉም። ያለ ድል ለመመለስ ፈጽሞ ፍላጎት የላቸውም። ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከፍ ብሎ ማየት የዘወትር ሕልማቸው ነው፤ ቃኘው ማለት ይህ ነው በቃ” ሲል ለማወደስ ጽፎላቸዋል።  በኮሪያ ዘመቻ ወቅት ሴቶችም ተሳታፊ በመሆን ወደ ኮሪያ አቅንተዋል፡፡  ሲስተር አስቴር አያናና ሲስተር ብርቅነሽ ከበደ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ለመጀመርያ ጊዜ በነርስነት ካሠለጠናቸው ስድስት ነርሶች መካከል ናቸው እነዚህ ሁለት ነርሶች ወደ  ኮርያ በመዝመት በጦርነቱ ለቆሰሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት  ወታደሮች ተገቢውን የሕክምና ዕርዳታ በመስጠትና በአስተርጓሚነት አገልግዋል፡፡   ኢትዮያ በኮሪያ ዘመቻ ወቅት ሰራዊቷን ወደ ጦርነቱ ከመላክ በተጨማሪ የ400 ሺ ዶላር ድጋፍ አድርጋለች፡፡
በሐምሌ ወር 1945 ዓ.ም የኮሪያ ጦርነት   ጦርነትን በማቆም ስምምነት ተጠናቀቀ። በቻይናና ሶቪየት ኅብረት በምትረዳው ሰሜን ኮሪያና በአሜሪካና በሌሎች 15 አገራት በተደገፈችው ደቡብ ኮሪያ መካከል ድንበር ተሠመረ። ከድንበሩ ወደ ሰሜንና ደቡብ ሁለት ሁለት ኪሎ ሜትር ገብቶ 250 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ድንበራቸው ከወታደር ነጻ የሆነ ቀጣና ተመሠረተ። ከጦርነቱ በኋላም የቃኘው ሻለቃ አባላት ለሶስት ዓመታት በኮሪያ ምድር በተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ኃይል ሥር የሰላም እያስከበሩ ቆይተዋል።
ኢትዮጵያም ካሰማራቻቸው የጦር ኃይሎች መካከል ከፍተኛውን የጦር ገፈት የቀመሱት የመጀመርያውና ሁለተኛው ቃኘው ሻለቃ አባላት  ነበሩ፡፡ አራተኛው ቃኘው ሻለቃ የዘመተው በሰሜንና ደቡብ ኮርያ መካከል የተኩስ አቋም ስምምነት ከተደረገ በኋላ ሲሆን ሰላም በማስከበሩ እንቅስቃሴ ላይ አተኩሮ ነበር፡፡ ወደ አገሩም የተመለሰው  አምስተኛ ቃኘው የሻምበል ጦር ኮርያ ውስጥ ቆይቶ የማረጋጋቱን ሥራ እንዲያከናውን በማድረግ ነበር። የቃኘው ሻለቃ አባላት ለመጨረሻ ጊዜ የኮሪያን  ምድር የለቀቁት በመጋቢት ወር 1948 ዓ.ም ነው።
አንደኛው ሻለቃ ለመጀመርያ ጊዜ  ከጠላት ነፃ በወጣው ‹‹ቻንቹን›› ከተማ ውስጥ ለኢትዮጵያ የኮርያ ዘማቾች መታሰቢያ ሐውልት ቆሞላቸዋል። ይህንን ሐውልት የመረቁት ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ  ነበሩ፡፡  በሐውልቱ አካባቢ ጣሪያቸው በሳር ክዳን የተሸፈኑና የኢትዮጵያን ባህላዊ  ገጽታ የሚያንፀባርቁ ጎጆዎች ተገንብተዋል፡፡ በጦርነቱ  ከፍተኛ ተጋድሎ የፈጸሙና ድል የተቀዳጁ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ለአራት የተመድ አባል አገራት መከላከያ ኃይሎች መታሰቢያ የሚሆንና በየአገሮቻቸው ስም የሚጠሩ አዳራሾችም ታንፀዋል። ከሁሉም ትልቁ አዳራሽ የኢትዮጵያ አዳራሽ  ነው፡፡
የኮሪያ ዘመቻ  70ኛ አመት የመታሰቢያ ፕሮግራም ሰሞኑን በኮሪያ ዘማቾች ፓርክ ውስጥ ተካሂዶ ነበር፡፡ በዚህ የመታሰቢያ ፕሮግራም ላይ፤ የኮሪያ ዘማቾቹ ኢትዮጵያውያን፣ ጀግኖች  የዘማቾቹ ልጆችና የልጅ ልጆቻቸው እንዲሁም ኮሪያውያን ተገኝተዋል። በመታሰቢያ መርሃ ግብሩ ላይ ምስጋናና ውደሳ ያቀረቡት ኮሪያውያኑ፤ “ኢትዮጵያውያን ለኮሪያና ለኮርያውያን ያደረጋችሁልንን ሁሉ አንረሳውም። ትውልድ ታሪካችሁን ሲያስታውሰው ይኖራል «የኢትዮጵያውያን ውለታ በሕዝባችን ልብ ውስጥ ለዘላለም ይኖራል።» የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል ለኮሪያ ዘማች ጀግኖቹም ልዩ ልዩ ድጋፎችን አድርገዋል፡፡   በኮርያ ምድር ዓለም አቀፍ ግዳጃቸውን ፈጽመው ወደ አገር ቤት ከተመለሱት የቃኘው ሻለቃ አባላት መካከል በአሁኑ ጊዜ በሕይወት የሚገኙት 100 ገደማ ቢሆኑ ነው፡፡ የደቡብ ኮርያ መንግሥትም ለእነዚህ ባለውለታዎቹ በየወሩ አበል ይከፍላቸዋል፡፡ አዲስ አበባ በሚገኘው ኮርያ ሆስፒታል ውስጥ ሙሉ የሕክምና አገልግሎት በነፃ፣ ለትዳር አጋሮቻቸው  ደግሞ 50 በመቶ ከፍለው ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ ለልጆቻቸውም ደቡብ ኮርያ ውስጥ ነፃ የትምህርት ዕድል (ስኮላርሺፕ) ሰጥቶላቸዋል፡፡ ይህንን እውነታም በ70ኛ አመት ፕሮግራሙ ላይ ያገኘኋቸው የ90 አመት የእድሜ ባለጸጋውና በ1947 ዓ.ም ወደ ኮሪያ  የዘመቱት አባት አርበኛ ስዩም ወልደጻዲቅ ነግረውኛል።
አፍንጮ በር  ናይጄሪያ ኤምባሲ አጠገብ የሚገኘውን ፓርክ፤ “የኢትዮጵያ ኮርያ ዘማቾች ብሔራዊ ፓርክ “ተብሎ የተሰየመ ሲሆን፣ በፓርኩም ውስጥ ለደቡብ ኮርያ ነፃነት ከጠላት ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ሲተናነቁ ለወደቁ 122 የቃኘው ሻለቃ ጀግኖች የመታሰቢያ ሐውልት ታንፆላቸዋል፡፡ በፓርኩ  በተገነባው ሙዚየም ውስጥ ጦርነቱን የሚገልጹ የተለያዩ ፎቶግራፎች፣በጦርነቱ ወቅት የነበሩ ታሪካዊ የጦር መሳሪያዎችና የሁሉም አገራት ምርኮኞች በየባንዲራዎቻቸው ስር በተሰለፉበት ወቅት ለብቻው ተውለብልቦ ኢትዮጵያ አንድም ምርኮኛ የሌላት ብቸኛ አገር መሆኗን  የመሰከረው ታሪካዊ ባንዲራ ይገኙበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የኮሪያ መንግስት ለባለውለታዎቹ አርበኞች ያሰራላቸውና አፍሪካ ህብረት አካባቢ የሚገኝና የሚከራይ ህንጻም አለ፡፡ የዚህ ህንጻ ገቢ ለማኅበሩ አባላት የሚከፋፈል ነው፡፡  ጃንሜዳና የቀድሞ ክብር ዘበኛ ካምፕ አካባቢ የሚገኘው አደባባይም  በቃኘው ሻለቃ ጦር ስም ተሰይሟል፡፡ እኛ ብንዘነጋቸውም ኮሪያውያኑ ባለውለታዎቻቸውን አልዘነጓቸውም፡፡  


Read 8308 times