Tuesday, 04 May 2021 00:00

የለውጥ ውሽንፍሩን የሚያረጋጋ ሰላም “ለውጥ” ዘገየብን

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(0 votes)

 • የምርጫ ክርክሮችን ሰማችሁ? የአገራችን “ለውጥ”፣ በመቶ አመትም የሚያልቅ አይመስልም። እያንዳንዱ ፓርቲ፣ በየፊናው “የለውጥ አብዮት”       ለማወጅ ይፎክራል።
  • የአገራችን ፓርቲዎች የህብረት ዝማሬ፣ “ለውጥ” የሚል ሆኗል። የአምስት ዓመታ “የለውጥ ማዕበል” ለጊዜው አይበቃንም?
  • አገር ማለት፣ “ሕግና ሥርዓት” ማለት እንደሆነ፣ ያለ ሰላምና ያለ እርጋታም መንግስት ፋይዳ እንደሌለው በፓርቲዎች ተዘንግቷል። ብዙ ኢትዮጵያውያን     ግን፣ የተረጋጋ ኑሮ የናፈቃቸው ይመስላል።
  • “ሰላምና መረጋጋት”፣ ዛሬ ዛሬ፣ “የህዝብ ጥያቄ” ሆኗል ማለት ነው? የብዙ ሰው ምኞት ወደ ሰላም እያመዘነ ነው። ሆነም አልሆነ፣ ሰላምን የሚያበዛ
    ሕግና ሥ ርዓት ነ ው የ ሚበጀን። እናም…..
  • “ለውጥ” የተሰኘው የፓርቲዎች ዜማ፣ “ለውጥ” ያስፈልገዋል። ከጦርነትና ከጥቃት፣ ከግድያና ከስደት፣ ከውድመትና ከሁከት ማረፍ አለባት - አገሪቱ።
  • ሁከትና ነውጥ ሲበዛ፣ እልፍ ቦታ እየተቦረቦረና እየሰነጣጠቀ፣ የአገርና የኑሮ ጉዳት ከቁጥጥር ውጭ ይዝረከረካል። እየተፈረካከሱ የመተረማመስ፣        እየተናዱ የመጥፋት መዘዝ ይመጣል።
  • የስጋትና የአደጋ ዘመን ሲራዘም፣ ምን የማይናጋ ምን የማይበላሽ ነገር አለ? ከብዛቱ የተነሳ፣ እንኳን ለቁጥጥር ለቁጥርም ያስቸግራል።
  • ሰላም ሲደፈርስ፣ የኢኮኖሚ ቀውስ እየበረታ፣ የዜጎች ኑሮ ክፉኛ ይብረከረካል። የስራ አጥነትና የድህነት ምሬት ይባባሳል። ይሄም ተመልሶ፣ የሁከትና     የነውጥ ማመከኛ ይሆናል።
  • ጥቃትና ጥፋት ሲዘወተር፣ ሃሳብን ይበትናል፣ በብዥታ እያፈዘዘ ይጋርዳል። እያቃዠ ያደናብራል። እሳት የሚተፉና የሚያከስሉ፣ ሁሉንም የሚያንቋሽሹና     የሚያረክሱ ምላሾች ይረዝማሉ። ጥፋትንና ጥቃትን እንደመነሻ እየተጠቀሙ፣ በተራቸው መልሰው፣ የጥላቻና የጥፋት ሰበቦችን ይነዛሉ።
  • መርዶ ሲደጋገም፣ ስጋት ሲንሰራፋ፣ የህይወት ክብር ተንጠፍጥፎ ይጠፋል። የስነ ምግባር ጭላንጭል ይዳፈናል። ተስፋ ይጨልማል።
          
         የዘንድሮ የምርጫ ርዕሰ ጉዳዮች፣ በጣም ቀላል እና በጣም ግልጽ ጉዳዮች መሆን ነበረባቸው። ለምን ቢባል፣....
አንደኛ ነገር፣ ለተረጋጋ ኑሮ፣ የእፎይታ ጊዜ የሚሰጥ የሰላም አየር ርቆናል። በስራ አጥነትና በድህነት ችግር ላይ፣ የዋጋ ንረት ተደርቦበት፣ የብዙ ዜጎች ኑሮ ግራ የሚያጋባ ሆኗል።
ህግና ሥርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ ይባስኑ እየተሸረሸረ፣ የስጋትና የጥቃት ግርዶሽ አጥልቶብናል። የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካና የዘረኝነት አስተሳሰብ፤ ቀስ በቀስም የሃይማኖት ፖለቲካ እየታከለበት፣ እለት በእለት ጥፋትን እየፈለፈለ፣ የአገሪቱን ህልውና እየተፈታተነ ነው።
ሰላም ሲጠፋ፣ ሕግና ስርዓት ሲደፈርስ፣ የኑሮ ቅሬታ ሲበረክት፣ ተስፋ ሲደበዝዝ፣ አገሬው በዘረኝነትና በሃይማኖት ፖለቲካ ሲጠመድ፣... ከሩቅም ከቅርብም ጸበኞችን ይጋብዛል። ኢትዮጵያ ለአደጋ የሚያጋልጥ፣ የሶማሊያንና የሱዳንን አዝማሚያ መመልከት ይቻላል።
ትልቋ አገር ኢትዮጵያ፣ የጥቃቅን ጎረቤት አገራት፣ የኤርትራም ሆነ የጂቡቲ፣ የሶማሊያም ሆነ የሱዳን ተፅእኖም ሆነ አደጋ የሚያሰጋት አገር መሆን አልነበረባትም። ነገር ግን፣ ከታሪክም እንደምንማረው፣ አሁንም እንደምናየው፣ ኢትዮጵያ ስትደፈርስ፣ ዙሪያዋ ሁሉ ይረበሻል። ለመዳፈር የሚያስፈስፍና የሚሽቀዳደም ይበረክታል።
በአጭሩ፣ የሰላምና የእርጋታ፣ የኢኮኖሚና የኑሮ፣ የሕግና የስርዓት ጉዳዮች፣ ሁሉንም ጤናማ ዜጋ የሚመለከቱ ዋና ዋና የምርጫ ጉዳዮች መሆን ይገባቸው ነበር። በብዛት እየሰማን ያለነው ግን፣ የለውጥ ዜማና የነውጥ ወሬ ነው።
የለውጥ ምስቅልቅልና የተረጋጋ ሰላም፣.... ለሁሉም ጊዜ ይኑረው።
“የአብዮት ለውጥ” ለማፈንዳት የማይፎክር ፓርቲ የለም ማለት ይቻላል። አንጋፋም ሆነ አዲስ፣ ትንሹም ትልቁም ፓርቲ፣ እንደየዝንባሌው፣ በተለያየና በተቃራኒ አቅጣጫ፣ ህገ መንግስትን ለመቀየር፣ ያልወደደውን አንቀፅ ለመሰረዝ፣ የምኞቱን ያህል አንቀፆችን ለመጨመር ይምላል። እንዲህ አይነት “ለውጥ”፣ በረዥም ጊዜና ቀስበቀስ፣ ወይም ደግሞ በስርነቀል የለውጥ አብዮትና በነውጥ እንጂ፣ በአንድ ምርጫ የሚሆን ጉዳይ እንዳልሆነ ጠፍቷቸው ነው?
አዎ፤ አብዛኞቹ የአገራችን ችግሮች፣ ለብዙ ዓመታት የተከማቹ ስለሆኑ፣ ብዙ መሠረታዊ ለውጦችን እንደሚጠይቁ አይካድም። በቀላሉና በአጭር ጊዜ የሚስተካከሉ፣ መልክ የሚይዙና እፎይ የሚያስብሉ አይደሉም።
አዎ፣ አንዳንዶቹ ችግሮች፣ በተለይም የድህነትና የኋላቀርነት ሸክም፣ ለምዕተ አመታት ሲወርዱ ሲዋረዱ የመጡ በመሆናው፣ በአንዴ አራግፈን የምንገላገላቸው “የአጋጣሚ እንከኖች” አይደሉም።
ህግመንግስቱም፣ ካፒታሊዝምን በሶሻሊዝም የሚቀይጥ፣ የግለሰብ መብትን በብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ የሚበረዝ፣ ባለ ብዙ ጣጣ ህገመንግስት ነው። ግን ደግሞ በዘፈቀደ ደርዘን አንቀፆችን በመሰረዝና በመቀየር፣ አልያም አንደኛውን ሙሉ ለሙሉ አሽንቀንጥረን በመጣልና በሌላ በመተካት፣ ወደ ተዓምረኛ መፍትሔ መድረስ አንችልም።
ህግና ስርዓትን ንደን፣ በንትርክ ለመተረማመስ ካልሆነ በቀር፣ ህገመንግስትን ለማሻሻል የሚያበቃ የሃሳብ ብቃት፣ ሰፊ የተቀባይነትና የስምምነት ደረጃ ላይ የደረሰ ፓርቲ፣ እስካሁን የለም። ምን ማለት ፈልጌ ነው?
ለዘመናት የተከማቹ ችግሮችን ማስወገድና የህገመንግስት ፈተናዎችን መፍታት፣ ለአገራችን ቀላል አይደለም። በትክክለኛ አስተሳሰብና በተቃና መንገድ፣ የረዝም ጊዜ ጥበበኛና ብርቱ ጥረትን ይጠይቃል። ወደ ስልጣኔ የሚወሰድ መልካም የለውጥ ጉዞ፣ ረዥም ነው። ከዚህ አንፃር፣ “ለውጥ” የሚለው የፖለቲካ ዜማ፣ ቀን ከሌት፣ ከዓመት ዓመት ቢደጋገም፣ ላይገርም ይችላል።
ነገር ግን፣... ሁሉም ነገር ልክ አለው። ሁሉም ነገር፣ ጊዜ አለው።
ከአምስት ዓመት በላይ አገሪቱን ሲንጥና ሲያንገጫግጭ የቆየው የሰላም እጦት፣ ከእንግዲህ ብዙም አያራምድም። ቶሎ መፍትሄ ማግኘት አለበት። አገራችን፣ በጊዜ እርጋታ ካላገኘች፣ የሚነቅዙና የሚሰነጣጠቁ የአገር ምሶሶዎች፣ የሚዛነፉና የሚሰበሩ ማገሮች ይበዛሉ። ከእለት ተእለት ጥፋቶችና መርዶዎች ጋር፣ ከቀን ወደ ቀን እየሳሱ የሚበጠሱ የአገር ድርና ማጎች ይበረክታሉ።
ያለ ሕግና ሥርዓት አገር አይኖርም። ያለ ሰላም፣ የመንግስት አቅም ይመክናል።
አዎ፤ ለረዥም ጊዜ የተከማቹ ችግሮችን ለማስተካከል በሚደረጉ ጥረቶች፣ አንዳንዴ አላስፈላጊ እክሎች ይገጥሟቸዋል። ሰላምን የሚያሳጡ እንቅፋቶች ይፈጠሩባቸዋል። “መልካም ለውጥ” ማለት፣ ሁልጊዜ ከመነሻ እስከ መድረሻ ተመቻችቶ የተዘጋጀ መንገድ አይሆንም።
ሰላምን የሚያደፈርሱና እርጋታን የሚነሱ እንቅፋቶች ይከሰታሉ - ጊዜያዊ እንቅፋቶች።
ቢሆንም ግን፣ እንቅፋቶች “ጊዜያዊ” ከመሆን ካለፉ፣ ተጨማሪ እዳዎችን ይጭኑብናል። ከዓመት ዓመት በሚሸጋገሩና በሚደራረቡ “እንቅፋቶች” ሳቢያ፣ ሀገሪቱ ለረጅም ጊዜ ሰላም ካጣች፣ እርጋታ ርቋት በነውጥ ከተጠመደች፤ በቀላሉ የማይሽሩ አዳዲስ ችግሮች ውስጥ ትዘፈቃለች። ነባር ችግሮችን ለማስተካከል ተብሎ የተጀመረ “ለውጥ”፤ ሀገሪቱን ለአዳዲስ ችግር ይዳርጋታል።
በሌላ አነጋገር፣ ማንኛውም “መልካም ለውጥ”፣ ከጊዜያዊ እንቅፋቶች ባያመልጥም እንኳ፣ ሰላምን የሚያጸና እንጂ፣ ሰላምን የሚያሳጣ እንደማይሆን ማረጋገጥ፣ የፓርቲዎችና የፖለቲከኞች ሃላፊነት ነው።
ይህም ብቻ አይደለም።
ማንኛውም “መልካም ለውጥ”፣ አንዳንድ ህጎችን ከማሻሻልና ከመለወጥ ጋር መቆራኘቱ ባይቀርም እንኳ፣ ህግና ስርዓትን የሚያደረጅ እንጂ፣ ህግና ስርዓትን የሚቦረቡር፣ ወደ ስርዓተ አልበኝነት እያንሸራተተ የሚያፋጅ መሆን አይገባውም።
ህግ እየረከሰና ስርዓት እየፈረሰ፣ ጎን ለጎን እልፍ ህጎች ቢሻሻሉ፣ እልፍ የመዋቅርና የአሰራር መመሪያዎች ቢስተካከሉ ምን ይረባሉ? ህግ የመለወጥና ተቋማትን የመገንባት ጥረቶች፣ አንዳች ፋይዳ የሚኖራቸው፣ በተግባር የሚተረጎሙ ከሆነ ብቻ ነው።
ማለትም፣ ለውጦች ሁሉ ፋይዳ የሚኖራቸው፤ ህግና ስርዓትን የምናከብር እስከሆነ ድረስ ብቻ ነው። ህግና ስርዓት ከፈረስ፣ ምድረ ሲኦል እንጂ፣ መኖሪያ አገር አይኖርም። ህግና ስርዓት ገና ሳይፈርስ፣ እየሳሳ እየላላ ሲመጣ እንኳ፣ ትርጉሙ ምን ማለት እንደሆነ፣ በቀጥታና በተደጋጋሚ አይተነዋል። በግፍና እንደዘበት ህይወት ይረግፋል። ንብረት በየሰበቡና በዘፈቀደ ይወድማል። ሰላምና እርጋታ ይጠፋል። የስጋትና የጥርጣሬ መንፈስ ይሰፍናል - ለጭፍን ጥላቻና ለተጨማሪ የክፋት ዘመቻም፣ የሰበብ እድሎችን ይፈለፍላል። በጊዜ ካልተገታም፣ የለየለት እልቂትና ትርምስ ይነግሳል።
ያለ ህግና ስርዓት፣ “አገር” ብሎ ነገር አይኖርም።
ያለ ሰላምና ያለ እርጋታ ደግሞ፤ “መንግስት”፣ ለወጉ ያህል እንኳ፣ ሕግና ስርዓትን የማስከበር አቅም ያጣል።
አገር ከተተረማመሰ፣ በስንቱ ቦታ፣ ስንት ፖሊስና ወታደር ማሰማራት ይቻላል? በዳይን ከተበዳይ፣ አጥፊን ከንጹህ ለመለየት የማይቻልበት ውጥንቅጥ ከተፈጠረ በኋላ፣ እልፍ ለእልፍ ፖሊስና ወታደር ማዝመት፣ መፍትሄ አይሆንም።
ስንቱን መክሰስ፣ ስንቱን ማሰር ይችላል? ምናለፋችሁ፤ ሰላምና እርጋታ፣ ሕግና ስርኣት፣ መቼም ቢሆን፣ ቸል መባል የለባቸውም - የህልውናና የኑሮ፣ የነጻነትና የመብት ዋስትና ናቸውና።

Read 2637 times