Tuesday, 20 April 2021 00:00

ቢ.ጂ.አይ ኢትዮጵያ 5 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት እንቦጭ አረም ማስወገጃ ማሽን በድጋፍ አበረከተ

Written by 
Rate this item
(0 votes)
ሚያዚያ 12 ቀን 2013 (ኢዜአ) ቢ.ጂ.አይ ኢትዮጵያ ጣና ሀይቅን ከጥፋት ለመታደግ በ5 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር ወጪ የተመረተ የእንቦጭ አረም ለማስወገጃ ማሽን ለጣና ሃይቅና ሌሎች ውሃማ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዛሬ በድጋፍ አበረከተ።
የቢ.ጂ.አይ ኢትዮጵያ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ገብረሥላሴ ስፍር በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ ቢ.ጂ. አይ ኢትዮጵያ በማህበራዊ አገልግሎቶች በስፋት ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል።
በማህበራዊ ዘርፍ ከሚያከናውናቸው ስራዎች መካከል የጣና ሀይቅን ለከፍተኛ ችግር የዳረገና ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የሚፈታተን እንቦጭን ለማጥፋት የሚያስችል ስራ ላይ በመሳተፍ የበኩሉን ድርሻ ማበርከት አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ማሽኑ ሀገር በቀል ከሆነው ሙላት ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ጋር በመተባበር የተሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ገብረስላሴ፤ "ማሽኑን ለማሰራት የአራት ወራት ጊዜ ፈጅቷል" ብለዋል።
ማሽኑ በራስ አቅም መሰራቱ በአዋጭነቱና የሀገር ውስጥ አምራቾችን በማበረታታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረው፤ ማሽኑ የታለመለትን አላማ እንዲያሳካ በጥንቃቄ ስራ ላይ መዋል እንዳለበት ጠቁመዋል።
ማሽኑ የተሰራበት የሙላት ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙላቱ ባሳዝነው በበኩላቸው "ቢ.ጂ.አይ ኢትዮጵያ በራስ አቅም የተሻለ ቴክኖሎጂ እንዲሰራ ከማድረጉ በላይ 120 ሺህ ዶላር የውጭ ምንዛሬ ለሀገር ውስጥ ጥቅም እንዲውል አግዟል" ብለዋል።
የጣና ሃይቅን ለመታደግ ሁሉም አካል የተቻለውን ማድረግ እንደሚጠበቅበት ያስገነዘቡት ደግሞ የጣና ሃይቅና ሌሎች ውሃማ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ዘላለም ልየው ናቸው።
Read 1737 times