Saturday, 24 April 2021 14:23

“የታፋኙ ማስታወሻ”

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

    የአንዳርጋቸው ጽጌ ሰኔና ሰኞ
                    
              ከወራት በፊት ለህትመት የበቃውን የአንዳርጋቸው ጽጌን “የታፋኙ ማስታወሻ” ለማንበብ የፈራሁበትን ምክንያት አውቀዋለሁ፤... ግን ደግሞ እያወቅሁም ራሴን ማሸነፍ አቃተኝ፤  ልቤ መገረፍ ፈርታ፣ ስቃይ ሽሽታ እምቢ አለችኝ፤ ... ነገሩ ሁለቴ  አልገረፍም ማለቷ መሰለኝ። እውነቷን ነው፣... አንዳርጋቸው የተያዘ ሰሞን ዓይኔን እንቅልፍ ከልክላ ራስዋ ሌት ተቀን ተጠብሳለችና አልፈረድኩባትም....ብዙ ሌሊቶች መተኛት ተስኖኝ ነበር።
አንባቢ ወዳጄን ጠየቅሁት “ደረጀ አትችለውም!...” አለኝ፤ እርግፍ አድርጌ ተውኩት። ደሞ በየመሀሉ ይቆጨኛል፣ ያስፈራኛል! በኋላ በመሀሉ ሌላ ስቃይ ያለበት መጽሐፍ አነበብኩ። ከዚያ በዚሁ ደም በነካው ልቤ ገባሁበት፡- በርግጥም ደራሲው ለሀገራችን የጦስ  በግ/ፍየል ዓይነት ሆኗል።
የመጀመሪያዎቹ ቀናት ስቃዩ፣ የሰንዐው ይሁዳ፣ ስራው ለጊዜው ቁና ቁና ቢያስተነፍሰኝም፣ ቀስ በቀስ እስራቱ እየላላ፣ እሱም ወደ ጨዋታውና ወደ ፖለቲካው ሲገባ ደስ አለኝ።
አንዳርጋቸው መጻፍ ችላል፣.... ደፋርና እውነተኛ ነው፣ ህሊናው ውስጥ ይኖራል። እውነት ለመናገር እንደሱ ዓይነት ለሌሎች የሚኖሩ ሰዎች፣ እጅግ ጥቂት ናቸው። በአብዛኛው- በየትኛውም አጋጣሚ ካገኙት ቁና ላይ ለራሳቸው የሚዘግኑ ሰዎች ይበዛሉ።
የቀደመው መጽሐፉን በሚገባ አንብቤ እዚሁ ጋዜጣ ላይ ዳሰሳ መስራቴን አስታውሳለሁ። ታዲያ በመጽሐፉ እንደ ፊልም የሚታዩት ምስሎች ዛሬም በአይነ ህሊናዬ ምድጃ ላይ ተጥደዋል። በተለይ የመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ፤  እንግሊዝ፣ ከለንደን ወጣ ብላ በምትገኝ “ውሊብ” ቢራ ቤት ውስጥ ይጠቀሙ የነበሩት አረጋውያን አይረሱኝም። ከሁሉ በላይ የኢህአፓው ከፍተኛ አመራር የነበረውን ተስፋዬ ደበሳይ በመኪና ባትሪ ያሳየኝን አልረሳውም፤ የገለጸበትን መንገድ አልጠግበውም። ስለ ተስፋዬ ደበሳይ ለማወቅ ያለኝ ጉጉት ትልቅ ቢሆንም፣ አንዳርጋቸው በጥቂቱ ግን፣ በስጋና ደም ያህል ሀውልት አንጾብኛል።
ወደ አሁኑ ልመለስ። “የታፋኙ ማስታወሻ” ልብ አንጠልጣይ መፅሐፍ ነው። ደግነቱ አልፎ ሰለምናነብበው ያን ያህል ምላጭ ገላችንን አይተለትለውም። አይናችንን እሾህ አያበጥረውም፤ግን ደግሞ ከአንዳርጋቸው ጽጌ ጀርባ የቀደሙ ሰቆቃዎችን የሚነግሩንን ፍራሾች ስናጤን ያምመናል። ፍራሹን ያጨቀየ ደምና ላብ ያለ ጥርጥር፣ ለህዝብ ነጻነትና ፍትህ የታገሉ ንጹሃን መሆኑን ስናስብ ቁጭት ያንገበግበናል።
ሙሉ ልብስ ለብሶ ሰንዓ የመን ላይ ስሞ አሳልፎ ከሰጠው የመናዊ ጀምሮ ያሉት ወታደሮችና ደህንነቶች ከፊታችን ይከሰታሉ። ይሁንና እኛ እዚህ ሆነን “ተያዘ” ስንባል የሆነውን ያህል አለመሆኑ ገራሚ ነው። እኔ እንቅልፍ  የከለከለኝ ስጋውን ይተለትሉታል፣ ያሰቃዩታል፣ በንግግር ያበሳጩታል የሚል ስጋት ነበር። ግን ደግሞ በመጽሐፉ እንደነገረን፤ጉዳዩ የፖለቲካ ስለሆነ ሌላ ስልት መጠቀም የፈለጉ ይመስላል። ሁሉም በየተራ ተቀጥቅጦ፤ ወደ ትጥቅ ትግል ዘወር ብሎ ለማየት፣ ሰቀቀን ውስጥ በገባበት ሰአት፣ ኤርትራን ከምታህል ጠላት ጋር አብሮ ጦር የመዘዘው “ግንቦት 7” ፤የወያኔ ኢህአዴግ ራስ ምታት ነበር። ቀልባቸው ግንቦት 7ትን በየትኛውም መንገድ ማጥቃት እንጂ እጃቸው ላይ ያለውን አንዳርጋቸው የሚባል ግለሰብ በማበሳጨት ነጥብ መጣል አልነበረም። ራሱ እንደሚለው፤ ምዕራባውያንን ማባበል የሌለ ምስል መፍጠር፣ ዲሞክራት መምሰል ስትራቴጂያቸው ይመስላል።
መጽሐፉን ሳነበው ያየኋቸው ነገሮች በእጅጉ ቢመስጡኝም፣ ከሁሉ በላይ ህሊናውን አድንቄያለሁ። በጣም በጎ ህሊና፣ ስስ ስሜት፣ ሃቀኝነት ቁልጭ ብለው ይታያሉ።
አንዳርጋቸው ቂመኛ አይደለም። ስለዚህም መፅሐፉ ውስጥ ያሳየነን 23 የእስር ዘመን ገጠመኝ ተዋናዮች ሲነግረን፤ ጥላቻና ቁጣ የለበትም። 23ቱም የትግራይ ተወላጆች ሆነው፣ ከነዚያ ውስጥ ያያቸውን ደግ ሰዎች አልረሳም። ትኩረቱና መደነቁ ሁሉ ወደ በጎው ነገር ያደላ ነው። ከሰንዓ ከመጣ ጀምሮ ሹፌር፣ የምግብ አብሳይ፣ ጥበቃ፣ የደህንነት ሰዎች ወዘተ.. ሁሉም ትግርኛ ተናጋሪዎች ቢሆኑም፣ ከነሱም መካከል መልካም የሆኑትን ሲያሳይ፣ በቡድን ማሰብ ምን ያህል የከሸፈ አስተሳሰብ መሆኑን አረጋግጦልናል። የሰውነት ሚዛንና ህሊና ምን ያህል ፖለቲካዊ ጥመትን አምልጦ እንደሚወጣ ያስተምረናል፡-
ከ23ቱ ሰዎች ስሟን ያወቀው በህክምና የምታገለግለዋን ነርስ ለተብርሃንን ነበር። ይህቺ ሴት ታጋይ የነበረች ናት። ጥይት ተኩሳ፣ በርሃ ተዋግታ የመጣች ነች። ግን ልቧ የእናት ልብ ነው። አንዳርጋቸው ገጽ 83 ላይ ስለዚህች ሴት እንዲህ አስፍሯል።
“እስረኛ አናት ላይ እግራቸውን ከፍተው ሽንት የሚሸኑ የወያኔ ሴት አሳሪዎች እንዳሉ ሰምተናል። ትልቅ ክፋትና ትልቅ ደግነት ሲፋጠጡ ሁሉም ክፋት በደግነት ይሸነፋል። ለተ ብርሃንም ለብቻዋ የሺ አሳሪዎችን ክፋት መቅበር የሚያስችል ደግነት ተላብሳለች። እንደ ለተብርሃን አይነቶቹ ናቸው ሁሌም በሰው ልጆች ላይ ተስፋ እንዳንቆርጥ የሚያደርጉት።”
እውነት ነው፤ የአንድ ቡድን ሰዎች ሊመሳሰሉ ቢችሉም ቡድኑ ግን አንድ ልብ፣ አንድ ሀሳብ፣ አንድ እምነት አለው ማለት አይደለም። ወያኔ ክፉ ነው ብንል እንኳን ወያኔ ውስጥ ደግ ሰዎች ይኖራሉ እያለን ነው። ግን ይህንን በጎነት ለማየት የውስጥ አይን ያስፈልጋል። ብዙዎቻችን የምናተኩረው ግድፈትና ክፋት ላይ ስለሆነ ብዙ ጊዜ በመንጋ መፈረጅ ይቀናናል።
አንዳርጋቸው ካሳየን ሰዎች ሌላኛው የትግራይ ተወላጅ ጠባቂ፣ እርሱ “አጭሩና ደጉ” በሚል ቅጽል የሚጠቅሰው ሰው፤ ይህንኑ በብሔር ማጠቃለያ የመስጠት የተሳሳተ አባዜያችንን ስህተትነት የሚያሳይ ነው፤ ጎን ለጎን “ረዥሙና ክፉው”፤ የሚያናድደን ጠባቂ አለ።
አጭሩ ደጉ ጠባቂ የሚለው ግን ሲታመም ለአለቃው ነግሮ የተሻለ ሀኪም ያስመጣ፣ የቀልዱን ኳስ ማየት እፈልጋለሁ ሲል የጋበዘውና ሌላም ብዙ ቸርነት ያደረገለት ነው። ሌላ ወጣት የአርሰናል ደጋፊም ነበረ። እዚህ ጋ ሰው ከብሔሩ ከሀገሩም አልፎ “ሰው” ወደሚለው ክብር እንደሚደርስ አሳይቶበታል።
ብዙ ቦታ ያደረሱበትን ስቃይ ሲያወራ ቁጭቱንና ምሬቱን አያሞቅም። ይልቅስ ትንሽ በጎነት ሲያይ ውስጡ ይላወሳል። ይህቺ ነገር ከጥበብ ጋር የተያያዘች ቀናነት ትመስለኛለች። ሰውየው ፖለቲካ ጥላውን ቢያጠላበትም የሥነ-ጽሑፍ ደሙ ትኩሳት የሚፍለቀለቅ ነው። የአለማችን የጥበብ ሰዎች ውስጥ ያሉት ቀጫጭን የስሜት ክሮች ውስጡ ተጠላልፈዋል። አንዳንዴ ነፍስን የሚያሰጠውም ይህ ጥቂቶች ጋ ያለ ፍቅርና ስስነት ይመስለኛል። አሌክሳንደር ፑሽኪንም ለፍልሚያ ወጥቶ ለጥይት የዳረገው፣ ጭካኔውን በጭካኔ የሚመልስበት አንጀት ስለሌለው መሰለኝ። ሲበዛ አንባቢ የነበረው የአሜሪካው መስራች አባት ሃሚልተንም፣ ሀገሩን ሰርቶ በግፍ እንዲወድቅ ያደረገው ተመሳሳይ ደም ሳይሆን አይቀርም!
የአንዳርጋቸው ጽጌ ገለጻ የሟቹን ደራሲ መስፍን ሀብተማርያምን አይነት ሰው ነው። በጣም ርህራሄና ስስት የተሞላ! ጋሺ መስፍን ሁሌ ትዝ የሚለኝ በዚህ ነው። ሰፍሳፋ የሚባል አይነት ሰው ነበር።
አንዳርጋቸው የሚገልጽበትን መንገድ ስታዩ የውስጡን ርህራሄ ይዘረግፍላችኋል። ገጽ 68-69 ስለ ለተብርሃን ሲገልጽ፡-
የመመርመሪያ እቃዋን አውጥታ እንዳለፈው አደረገች። እቃዋን በቦርሳዋ ውስጥ መልሳ በፌስታል ይዛ ያመጣችውን እቃ አወጣችልኝ። ´የውስጥ ካናቴራ ይዤልህ መጥቻለሁ´ ብላ ነጫጭ ህንድ የተሰራ የሚል ጽሁፍ ካለበት ማሸጊያ ውስጥ እያወጣች ሰጠችኝ።
“የጥጥ ካናቴራ ናቸው፤ ያሞቁሃል። ካናቴራ ግዢ ብለው በሰጡኝ ገንዘብ ነው የገዛሁት። ይህ ደግሞ በገንዘቤ የገዛሁት ስጦታ ነው።” በማለት አንድ ሰማያዊ የውስጥ ሱሪ ሰጠችኝ። ካናቴራ ከሌለው የውስጥ ሱሪ ሊኖረው አይችልም ብላ ገምታ ሳይሆን አይቀርም። ልቤን ነካችው። በሩ ላይ የቆመው ጠባቂ አንድ ዕለት ባሳየኝ ደግነት ልቤ ተነክቶ ነበር። የዚህች ሀኪም ሩህሩህነት ደግሞ ጭራሹን አንጀቴን አላወሰው።
መፅሐፉ በጣም ብዙ ቀና ነገር፣ ጥንካሬና የዓላማ ጽናትን ያሳያል። የሰው ልጅን በጅምላ መፈረጅም ስህተት መሆኑን ፍንትው አድርጎ ያሳያል። የሰው ልጅ ክፉዎችን ብቻ ሳይሆን  ወርቆችንም መያዙን ጥንቅቅ አድርጎ ያስተምራል።
ከስኮትላንድ መጥቶ አሜሪካዊ ቱጃር የሆነው አንድሪው ካርኒጌ እንደሚለው፤ ወርቅ ስታወጣ ብዙውን ጭቃና አፈር አታስበውም። “ማሰብ ያለብህ ከዚህ አፈር ውስጥ ስለሚገኘው ወርቅ ነው።” ያለውን ያስታውሳል። ሰውም የሰው ቡድንም አፈር ብቻ አይደለም፤ ውስጡ ጥቂት ወርቆች አይጠፉም።
ሌላው መጽሐፉ ውስጥ የደነቀኝና አሁን መሬት ላይ የምናየው ሀቅ ጉዳይ ነው። በተለይ ምዕራባውያኑ የሀገራቸውን ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻር ህሊናቸውን እግራቸው ስር እንደጣሉትና ጭንቅላታቸው ምላስ ብቻ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። በወቅቱ ማረሚያ ቤት እየመጣ የሚጠይቀው የእንግሊዙ አምባሳደር፣ እንደ ህጻን ልጅ የወያኔን ፊት እያነበበ፣ ያላመነበትን ነገር እያወራ ከረሜላ የሚልስ መምሰሉን የምናስተውልባቸው በርካታ ማሳያዎች ሰጥቶናል። በነዚህ አጋጣሚዎች ደግሞ የአንዳርጋቸው የራሱ ድፍረቶች ገርመውኛል። እነዚህ ጨካኝ ሰዎች እጅ ላይ ሆኖ፣ ያንን እንደ ጊንጥ ከኋላ የሸሸጉትን መርዝ ፊት ለፊት እያነሳ ሲያወራ፣ ስቃይ ያበዙብኛል ያለማለቱ እኔም በእጅጉ ጉድ ያሰኘኝ ነገር ነው። ለነገሩ የዚያን ዘመን ሰዎች ለነፍሳቸው የማይሳሱ እንደሆኑ ሺህ ድርሳናት ነግረውናል።
እንዲያውም በተደጋጋሚ እንደተገለጸው፤ የጸሐፊው የልብ ሀዘን የትንንሽ ልጆቹ ጉዳይ ነው። ይሁን እንጂ እነሱም በሌሎች ኢትዮጵያውያን ልጆች ህይወት ማንጸሪያነት በጽናት ጠቅልሎ አስቀመጠው።
እኔ ስለ አንዳርጋቸው መጽሐፍና ሰብዕና ሳስብ የማስተያየው ከዚህ ቀደም በታሪክ እንደምንጠቅሳቸው የሀገራችን ጀግኖች ነው። ኑሯቸውንና ቤታቸውን ትተው ለሀገርና ለድንበር ብለው ቤተሰባቸውን በትነው፣ በየጦሩ ግንባር ከሞቱት አባቶች ጋር ተመሳሳይ ዋጋ ከፍሏል። ነፍሱን አስጨንቋል፤ ተደብድቧል። ይህ ሁሉ ሲሆን አንድም ቦታ የስልጣንና የእንጀራ ጉጉት አናይበትም። ይልቅስ ስለ ሌሎች የራሱንና የቤተሰቡን ህይወት ከፍሏል።
መጽሐፉ ውስጥ አለፍኳቸው ብሎ ካሰፈራቸው የሰቆቃ ጊዜያት፣ የቃሊቲው የባሰ ዘግናኝ ይመስለኛል። ዳዊትና አሰፋ ከተባሉ ሁለት ነፍሰ ገዳዮች ጋር ተዳብሎ ያሳለፈው ጭቅጭቅና ንትርክ በእጅጉ ያምማል።  የሁለቱን ጸብ አስመልክቶ “ምግብ ይጣል፣ አይጣል!” በሚለው ንትርክ በታየው ግብዝነት ወቅት ያሰበው ሃሳብ ብዙ የሚያሳስብ ይመስለኛል። እስቲ ገጽ 162 ላይ ያሰፈረውን እናንብበው፡-
“ከነዚህ ሰዎች ጋር በነጻነት መነጋገር እንደማይቻል ገባኝ። ከሁሉ ያስገረመኝ  ምግብ ትርጉም አጥቶ እንደ ጉድ ከሚጣልባት ከአውሮፓ የመጣሁ ሰውዬ ´ኢትዮጵያ ውስጥ ምግብ እንዴት ይጣላል?´ በሚል ጉዳይ በኢትዮጵያ እስር ቤት ውስጥ ከእስረኛ ጋር መጋጨቴ ነው።
እንግሊዝ ሀገር የመጠቀሚያ ጊዜያቸው አልቋል ተብሎ ከትልልቆቹ ሱፐር ማርኬቶች የሚጣላው ምግብ ለጉድ ነው። ሰዎች እየገዙ ሳይበሉት የሚጥሉት ምግብ ከዚያ ሳይበልጥ አይቀርም።... የሚጣለው ምግብ የአመት ዋጋ ተደምሮ፣ የመላውን ኢትዮጵያ መንግስት  አመታዊ በጀት በሁለት እጥፍ ይበልጥ እንደነበር አስታውሳለሁ ይላል።
አንዳርጋቸው በአጠቃላይ የፍትህ ስርዓቱን ይተቻል። በተለይ መለስ ዜናዊና የቀድሞ የተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤን ተጠያቂ ያደርጋል። ከዚያም ´የፍትህ ስርዐቱ ላይ መቀለጃ ያደረጋቸው ሰዎች´ በሚል አቶ ታምራት ላይኔን ይጠቅሳል።
“ማረሚያ ቤት” የሚለውን ስያሜም አጥብቆ ይተቻል። ለዚህ ማሳያ የሚሆኑ ገጠመኞችንና በእስር ቤት ውስጥ የሚፈጸሙ ድርጊቶችን በመምዘዝ፣ ብዙ ሰዎች ወንጀል ሰርተው እስር ቤት ቢቆዩም በጥፋታቸው የማይጸጸቱ እንደሆኑ እንዲያውም አንዳንዶቹ የእስር ጊዜያቸውን ፈጽመው ከወጡ በኋላ ተመሳሳይ ወንጀል እንደሚፈጽሙ በመጥቀስ አዲሱ ስያሜ ትክክል አለመሆኑን ለማሳመን ይጥራል።
አሰቃቂውንና ምንም አይነት ክህሎት የማይጨመርበትን የእስር ቤት ህይወት የተለያዩ ገጽታዎች  በማዝናናትም በሰቀቀንም ይተርካል። የሃይማኖት አስፈሪነትን፣ የወያኔ መንግስት ሕዝብን ለመከፋፈል እንደሚጠቀምበት፣ እዚያው ካየው ገጠመኝ ጋር እያዛመደ አደጋውን ለመጠቆም ደክሟል።
እስር ቤት ሆኖ የሰማቸውን መዝሙሮችና መንዙማዎች ስንኞቹን አገላብጦ፣ የወደደውን የመሐመድ አወልን ገራሚ መንዙማ ግጥሞች አስፍሯል። አንዳርጋቸው አንድን ነገር በብዙ አቅጣጫ ማየቱን ከመጽሐፉ እንገነዘባለን። ከጎለጎልነው ፖለቲካው... ሃይማኖቱ ... ታሪኩ... ኪነ-ጥበቡ ሁሉ አለበት። ...Read 522 times