Print this page
Saturday, 24 April 2021 14:21

ራስህን የራስህ ጓደኛ አድርገው!

Written by  እሸቱ ብሩ ይትባረክ
Rate this item
(1 Vote)

  ብዙዎቻችን የውክቢያ ሕይወት ነው እየገፋን ያለነው፡፡ እንጣደፋለን! እንዋከባለን! ድካማችን ብዙ ዕረፍታችን ጥቂት ነው። እንቸኩላለን! መድረሻችን የት እንደሆነ ግን አናውቀውም፡፡ የኑሯችንን ጎዶሎ ለመሙላት እንሯሯጣለን፡፡ የኑሮ ጣጣ ፈንጣጣው አላላውስ ብሎናል፡፡ የሆዳችንን ጥያቄ ለመመለስ፣ ማጀታችንን ለመሙላት፤ ሳሎናችንን ለማሳመር የማንወጣው ዳገት፤ የማንወርደው ቁልቁለት የለም፡፡ አስቤዛችን እንዳይጎድል እንታትራለን፡፡ የሩጫ ሕይወት! የጥድፊያ ኑሮ! የትርምስ ዓለም! የግፊያ ጊዜ!
አዎ ለራሳችን ጊዜ የለንም፡፡ ለሆዳችን መሮጡ ጥሩ ሆኖ ሳለ የነፍሳችንን ርሃብ ለማስታገስ፣ አዕምሯችንን ለመመገብ አንዲት እርምጃ ግን እየተራመድን አይደለም፡፡ ራሳችንን ያን ያህል አልተገነዘብነውም፡፡ የሆዳችንን ጩኸት እንጂ የሕሊናችንን ድምፀት አንሰማም፡፡ የኑሮ ውድነቱ ትኩረታችንን ጠልፎታል። አስተሳሰባችን ተሰርቋል፤ እኛነታችን በዘመን አመጣሹ የውክቢያ ኑሮ ተነጥቋል። እናውቃለን የምንለውን ማንነታችንን በደንብ አናውቀውም፡፡ ሰውነታችንን በቅጡ አልተረዳነውም፡፡ የምናየውን ዓለም አናስተውልም፤ የምንሰማውን ውስጣዊ ሮሮ አናዳምጥም፡፡ ለራሳችን ትኩረት አልሰጠንም፡፡ ውበታችንን ለመጠበቅ፣ ሳሎናችንን ለማሳመር፤ ኑሯችንን ለመሙላት እንደምንፍጨረጨረው ሁሉ ሰውነታችንን ፈልገን ለማግኘት፣ የሕሊናችንን ውበት ለመጠበቅ፣ ስነ ምግባራችንን ለማሽሞንሞን፣ ውስጣችንን ለማሳመር፣ መንፈሳችንን ለማስዋብ፣ አዕምሯችንን በፍቅር፣ በዕውቀትና በጥበብ ለመሙላት፣ ነፍሳችንን ለማስደሰት ስንፍጨረጨር አንታይም፡፡ ራሳችንን የዘነጋን ከንቱዎች ሆነናል፡፡ በራሳችን ላይ ለጥ ብለን ተኝተናል፡፡ ማን ያነቃን ይሆን?
ወዳጄ ሆይ.... ለራስ የማርያም መንገድ እንደ መስጠት ያለ ብልህነት የለም። ከራስ ደካማ አስተሳሰብና ዓለሙ ካዘጋጀልን የእንቁልልጭ ወጥመድ መውጫ የወንድ በር ማዘጋጀት ያስፈልገናል፡፡ ፈረንጆቹ “Exit door” እንደሚሉት ዓይነት። ከራስ ጋር መነጋገርን የመሰለ ከወጥመድ ማምለጫ መድሐኒት ሌላ ምንም የለም፡፡ ሕይወት እንዳይሰለችህ፣ ኑሮ እንዳይመርህ አዕምሮህን አዲስ ሃሳብ አስተምረው። ከራስ ጋር መነጋገርን አለማምደው፡፡ ሕሊናህን በአዲስ ሃሳብ አሰልጥነው፡፡ ከራስ ጋር ከመደንቆር ይልቅ ከራስ ጋር ለመግባባት ለራስህ ጊዜ ስጠው፡፡


Read 1485 times