Print this page
Sunday, 25 April 2021 00:00

የሄዋን ደብዳቤ (ለአክራሪ ፖለቲከኞች፤ አክቲቪስቶችና ዘረኞች)

Written by  ወንድወሰን ተሾመ
Rate this item
(2 votes)

     አድማስ ትውስታ
              
           ሄዋን እባላለሁ፤ ዛሬ ተክዤ ነው የዋልኩት፡፡ ወጣት ነኝ፤ ወጣትነቴን ግን ብዙ ነገሮች ጎድተውታል---ሃዘን፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ግራ መጋባት ወዘተ፡፡ ሰው ነፍስ ካወቀ ጀምሮ በሃዘንና በስጋት ይኖራል? እኔ የኖርኩት እንደዚያ ነው፡፡ ቀደም ሲል በትምህርት ቤት ውስጥ እና ሌሎች ሰዎች ሲያወሩ በምሰማቸው መጥፎ ወሬዎች እረበሽና አዝን ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በልጅነቴ  አንድ ነገር አጋጠመኝ፡፡ የዛሬ አስር ዓመት አካባቢ ድንገት የግቢያችን በር ተንኳኳ፤ እኔ፣ አባቴ፣ ሁለት ታናናሽ ወንድሞቼና እናቴ ሳሎን ቤት ቁጭ ብለናል፡፡ ሰራተኛችን ራት እያቀራረበች ነበር። የበሩን መንኳኳት የሰማችው የቤት ሰራተኛችን፣ ምግቡን አስቀምጣ ለመክፈት እየሮጠች ሄደች፤ ትጉህ ናት፣ ትዕዛዝ ሳትጠብቅ ነገሮችን በፍጥነት የማድረግ ልምድ አላት፡፡ ልጅነቷን፣ ፍጥነቷን፣ ንቃቷንና አስተዋይነቷን የተረዱት እናትና አባቴ፣ በአቅራቢያ በሚገኝ የመንግስት ትምህርት ቤት ገብታ፣ በቀኑ ክፍለ ጊዜ መማር አለባት ብለው ቀን ቀን ትማራለች፡፡ እናቴ፤ እኔና ወንድሞቼን ለማሳደግ ብላ የቤት እመቤት ሆና ነው የኖረችው፡፡
ይህች ፈጣን ልጅ በር ለመክፈት ሄዳ ከወትሮው በተለየ መልኩ ዘገየች፡፡ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ይሆናል፤ የሰራተኛዋ መዘግየት ያሳሰባት እናቴ፤ “ኽረ ይቺ ልጅ የውሃ ሽታ ሆነች” ስትል እኔ ብድግ ብዬ ወደ ውጪ ሄድኩ፤ ወደ በሩ ስጠጋ  የውጪው በር መዘጋቱ ግራ አጋባኝ፤ የውጪውን በር ከፍቼ ቆምኩ። ሰራተኛችን ከሶስት ሰዎች ጋር ቆማ ታወራለች፡፡ በሩን ገርበብ አድርጌ እንደከፈትኩት፤ “አልማዝ ምን ሆነሽ ነው?” አልኳት፤ በእጇ ምልክት እየሰጠችኝ በአንደበቷ “አንዴ ነይ” አለችኝ። በሩን ገርበብ እንዳደረኩት ወደ አልማዝና አብረዋት ወደ ቆሙት ሰዎች ሄድኩ፤ “ምን ሆና ይሆን? እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው? ምንድነው የሚፈልጉት?” --- የሆነ ፍርሃት ውስጤን ወረረው፤ ግን የአልማዝ  የተረጋጋ የሚመስል አቋም ነገሩ ቀላል እንደሆነ እንዳስብ አደረገኝ፤ “ሰዎቹ የዘመድ ቤት ጠፍቶባቸው ይሆን? ለከተማው እንግዳ ሰዎች ይሆኑ?” የሚሉ ጥያቄዎች በአዕምሮዬ ተመላለሱ፡፡
ግራ ገብቶኛል፤ ልክ አጠገባቸው እንደደረስኩ ከመካከላቸው አንዱ አፌን ግጥም አድርጎ ያዘኝ፤ አንድ ትልቅ ግብዳ እጅ አፌ ላይ ተጭኖ አፈነኝ (ገና’ኮ አስራ ሁለት ዓመቴ ነበር)፤ ሌላው ደግሞ በጆሮዬ አንዳች ማስጠንቀቂያ ነገረኝ፡፡ ሶስተኛው ሰው ለካስ መሳሪያ ታጥቋል፤ ቀስ ብሎ ሄዶ የውጪውን በር ዘጋው። ምን እንደሚፈልጉ ወዲያው ገባኝ፡፡ እኔንም አልማዝንም አይፈልጉንም። ሰዎቹ ወሮበሎች አይደሉም፣ አንዱ ፖሊስ ሲሆን ሁለቱ የደህንነት መስሪያ ቤት ሰራተኞች እንደሆኑ ነግረውናል፡፡ በዚያች ቅፅበት እጅግ በጣም አዘንኩ፤ ውስጤን ፍርሃትና ድንጋጤ ወረረው፤ ሰውነቴ መንቀጥቀጥ ጀመረ፡፡ ድምፅ ብናሰማ በቤተሰቡ ላይ የሚደርሰው ጉዳት የከፋ እንደሆነ ተነገረን፡፡ የሚቀጥለው ሰው እንደኛ አይታገትም፣ ተይዞ ይወሰዳል፤ ሳስበው ዘገነነኝ---ይህ የፍቅር ሰው፣ ቤተሰቡን ለመመገብ ደፋ ቀና የሚል ታታሪ ሰው፣ ለአገሩና ለትውልዱ ህልም ያለው ሰው ዛሬ ማታ ከደጃፉ ላይ በእነዚህ አረመኔ ሰዎች ታፍኖ ይወሰዳል፤ ምን ያደርጉት ይሆን? በጭምጭምታ እንደምንሰማው፤ በእስር ቤት ያሰቃዩት ይሆን? ግን ለምን? በጊዜ ቤቱ ገብቶ ጠዋት በማለዳ ትምህርት ቤት ሄዶ ሲያስተምር የሚውል መምህር፤ ከወረቀትና ከእስክሪፕቶ ውጪ መሳሪያ የሌለው ሰው - አባቴ --- ምን አደረጋቸው?  ይመልሱታል ወይስ ያስሩታል? ወንድሞቼና እናቴ አብረውት ይወጡ ይሆን? --- አባቴ በኔ ተስፋ ያደርግ ነበር ----- የሱን እጣ ፈንታ አሰብኩና ወዲያው ተስፋ ቆረጥኩ፡፡
ይህ ጉዳይ አስር አመት አልፎታል፡፡ ነገሩ ድንገት በመፈጠሩ ህይወቴን ያመሰቃቀለ፤ ተስፋዬን ያጨናገፈ፣ ተስፋ ቢስ ያደረገኝ ጉዳይ ሆኗል፡፡ አባቴ ያጫውተኝ ነበር፣ ያበረታታኝ ነበር፣ ለኔ ልዩ ፍቅር ነበረው። በአጠገቤ ባጣሁት ቁጥር ሃዘኔ ጥልቅ ነው። ለምን? ለምን? ለምን?-- የሚል ጥያቄ በተደጋጋሚ አዕምሮዬ ላይ ያንቃጭላል፡፡ ጉዳዩ አስር ዓመት ቢያልፈውም ዛሬ ብቻዬን ሄጄ የውጪ በር መክፈት ያስፈራኛል፡፡ ትንሽ ጨለምለም ካለ ወደ ውጪ መውጣት ይጨንቀኛል፤ ያ አፌን ያፈነው፣ የሚያስፈራ ማስጠንቀቂያ የሰጠኝ ሰው፣ የውጪውን በር ቀስ ብሎ የዘጋው፣ ያ መሳሪያ የታጠቀው ሰው፤ ደጅ ያሉ ይመስለኛል፣ ነገሩ ትናንት እንደተፈጠረ አዕምሮዬ ውስጥ ይመላለሳል።
ሄኖክ ክፍል ውስጥ ከማዳመጥ ውጪ ጥያቄ ሲመልስም ሆነ ጥያቄ ሲጠይቅ አይቼው አላውቅም። የቡድን ሥራ ተሰጥቶ በሚቀርብበት ጊዜ ስራውን ከሚሰሩት መካከል እንጂ ውጤቱን ከሚያቀርቡት ተማሪዎች መካከል ሆኖ አይቼው አላውቅም፡፡ ብዙ ጊዜ ከማውራት ይልቅ ማዳመጥ ያዘወትራል፤ ጓደኛዬ የሚለው ሰው የለውም፡፡
ሄኖክ ብዙ ጊዜ ከዩኒቨርሲቲ ካፍቴሪያ ምሳውን ወይም ራቱን በልቶ ሲወጣ ብቻውን ቁጭ የሚልባት ቦታ አለችው። ዛሬ ከካፍቴሪያ ራት በልቼ ስወጣ የራሴንም ሆነ የሄኖክን ብቸኝነት መስበር ፈለኩ፤ ውስጤ “አናግሪው - አናግሪው” ብሎ ጎተጎተኝ፤ የሄኖክን የብቸኝነት ሚስጥር ለማወቅ ጓጓሁ፡፡ በተለያየ ጊዜ እንደተረዳሁት፣ ለእኔ ጥሩ አመለካከት ያለው ይመስለኛል፤ ከብዙ ልጆች መካከል አንድ ቀን መፅሐፍ፣ አንድ ቀን ደግሞ እስክሪፕቶ ተውሶ መልሶልኛል፤ ግን ይሄ ብዙ ንግግር አልነበረውም፤ “መፅሀፍሽን አንዴ ታውሺኝ? ትርፍ እስክሪፕቶ አለሽ?” አይነት ንግግር ነው፡፡ ታዲያ ዛሬ ምን ብዬ ንግግር እጀምራለሁ? ከዚህ በፊት ከአንዴም ሁለት ጊዜ የቡድን ሥራ አብረን ሰርተናል፡፡ አራት- አምስት ሆነን  “አንቺ ስሪው፤ አንተ ስራው” እያልን ስንጨቃጨቅ “እኔ እሰረዋለሁ፤ እናንተ ፕሬዘንቴሽኑን ታቀርባላችሁ” ይልና ይገላግለናል፡፡ ዛሬ ለሶስተኛ ጊዜ የቡድን ስራ እሱ ካለበት ቡድን ጋር ደርሶኛል። ለምን ይህንን ጉዳይ በማንሳት ንግግር አልጀምርም? አልኩና ብቻውን ተቀምጦ ወዳለበት ቦታ አመራሁ፤ ሄኖክ አላየኝም፤ ሃሳብ ውስጥ ያለ ይመስለኛል፡፡ ስሙን ጠርቼ ከሃሳቡ አነቃሁትና ባሰብኩት መንገድ ንግግሬን ጀመርኩ፡፡ ስለ ቡድን ስራው ትንሽ ከተነጋገርን በኋላ “ችግር የለም፤ እኔ እሰረዋለሁ፤ እናንተ ፕሬዘንቴሽኑን ታቀርባላችሁ” አለኝና ዝም!
ዛሬ ከሄኖክ አንዳች ነገር መስማት አለብኝ፤ ምን ሆኖ ነው ብቸኛ የሆነው? ለምን አያወራም? ለምን ጓደኛ አያፈራም? የሚሉ ጥያቄዎች በውስጤ ይመላለሱ ጀመር፡፡ ይህንኑ ጥያቄ ደፍሬ ሄኖክን ጠየኩት፤ ቀና ብሎ አይቶኝ ፈገግ አለና አንገቱን አቀርቅሮ ዝም አለ፡፡ ከላይ የጠቀስኩላችሁን የራሴን ታሪክ አካፈልኩት፤ በጣም አዘነ፡፡ በተለይ አባቴ ከዚያች ቀን በኋላ የት እንደደረሰ እንደማላውቅና የአባቴ ናፍቆት እኔና ወንድሞቼን እያሰቃየን እንደኖርን፣ እናቴ ሰው ቤት እንጀራ እየጋገረችና ልብስ እያጠበች እንዳሳደገችን፣ በአባቴ ደብዛ መጥፋት እያዘነች እንደምትኖር እንባዬ በጉንጮቼ ላይ እየወረደ ታሪኬን ሳጫውተው፣ የእሱም አይኖች እንባ አርግዘው አየኋቸው። ሄኖክ አቀፈኝና እንደ ህፃን ልጅ አባበለኝ፤ ከዚያም የራሱን ታሪክ ነገረኝ፡-
“--እኔ የተጎዳሁ ሰው ነኝ፤ተወልጄ ያደኩት ክፍለሃገር ነው፤ አዲስ አበባን ያወኩት ተሰድጄ ነው፤ ክፍለሃገር እያለን አንድ ቀን ማለዳ ሊነጋጋ ሲል ከፍተኛ የጩኸትና የሁካታ ድምፅ ሁላችንንም ከእንቅልፋችን ቀሰቀሰን፤ አባቴ ፈጥኖ ሁላችንም ልብሳችንን በፍጥነት እንድንለብስ እየተራወጠ ከአልጋችን አስነሳን፤ እኔ፣ ሁለት ወንድሞቼና አንድ እህቴ እየተጣደፍን መነሳሳት ጀመርን፤ እናቴና አባቴ ፈንጠር ብለው በሚስጥር ይንሾካሸካሉ፤ ከፍተኛ ድንጋጤ ወድቆባቸዋል፤ የሚይዙትን የሚጨብጡትን አጥተው ሲራወጡ ስናይ እኛም ተረበሽን፤ ያ የሁካታና የጩኸት ድምጽ እየበረታ፣ እየቀረበ መጣ፤ አባቴ ጉዳዩን ለማየት በር ከፍቶ ወጣ፤ እንደገና እየሮጠ ወደ ቤት ተመልሶ “ውጡ! ውጡ!” አለን፤ መረጋጋት አልቻለም፡፡ ወጣን፤ እንደገና “ግቡ! ግቡ! ”አለንና እሱ ውጪ ሆኖ እኛን አስገብቶ በሩን ቆለፈብን፡፡ አባቴና እናቴ ያወቁት ነገር አለ፡፡ እኛ ግን አላወቅንም፡፡ ተወልደን ያደግንበት መንደር እንዲህ በጩኸት ሲናጋ ሰምተን አናውቅም፤ በርካታ ሰዎች ወደ ቤታችን እየተጠጉ መሆኑንና ጩኸትና ዛቻ መበራከቱን ስንረዳ ድንጋጤ ዋጠን፣ ውጪ ያለው አባቴ እያለቀሰ ሰዎቹን በስም እየጠራ ሲለምናቸው ሰማን፤ ጉልበታችን መቆም አቅቶት ሁላችንም ሲሚንቶው ላይ ተዘርረናል፤ ሰውነታችን ይንቀጠቀጣል፡፡
ድንገት አባቴ፤ የእናቴን ስም እየጠቀሰ አካባቢው ላይ በብዛት የሚኖረው ብሔር ዝርያ እንዳላት በመግለጽ ሲለምናቸው ይሰማናል፡፡ እኔ በዚያን ጊዜ አንድ ነገር ትዝ አለኝ፤ ከአንድ ቀን በፊት በቀን ስራ የሚተዳደሩ የሁለት ብሔረሰብ ተወላጆች ተጣልተው ሰፈር ውስጥ ግርግር ነበር፡፡ ለራሴ “አሁን ከተከሰተው ጉዳይ ጋር ምን አገናኘው?” እላለሁ፤ ሰውነቴ እየተንዘፈዘፈ እያለ ታናሽ እህቴ ጮክ ብላ ስትጮህ፣ እናቴ ኡኡታዋን አቀለጠችው፤ “ምን ሊያደርጉን ነው?” የሚለው ጭንቀት ውስጤ እያለ ድንገት በሩ በሃይል ተመታና ሰዎቹ በሩን ሰብረው ገቡ፡፡ አባቴ ተስፋ ሳይቆርጥ እየተከተላቸው ይለምናቸዋል። ሰዎቹ በያዙት ገጀራ አስፈራሩንና፤ “በሉ አሁን ከዚህ አካባቢ በፍጥነት ጥፉ!” የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ሰጡን፡፡ አባቴ “ውጡ! ውጡ!” አለን፤ ሁላችንም እየሮጥን ወጣንና ብሄራችንን ያማከለ መጥፎ ስድቦች እየተሰደብን፣ በተሰበሰበው ህዝብ መካከል ጥሰን መሄድ ጀመርን፤ ጎረቤቶቻችን ግን ሰዎቹን እንዲተዉን ይለምኗቸው ነበር፤ ግን የሚሰማቸው አልተገኘም፡፡ የተወሰነ መንገድ እንደሄድን አልፎ አልፎ ቤቶች በእሳት እየተቃጠሉ ነበር፤ ዞር ብዬ ስመለከት የእኛም ቤት በእሳት ተለኩሶ እየተቃጠለ ነው። ምንም ነገር ሳንይዝ ከዛ ወጥተን በአንድ ቀን  አዲስ አበባ ደርሰን ዘመድ ቤት አደርን። በጉዟችን ማንም ማንንም አላናገረም፤ “ከኋላችን ሰዎች ይከተሉን ይሆን?” የሚል ስጋት ግን በሁላችንም ውስጥ ነበር፤ ቶሎ ቶሎ እየሄድን እንደገና ወደ ኋላ እናይ ነበር፡፡
ከዛ ቀን ጀምሮ ተወልደን ያደግንበት መንደር ሄደን አናውቅም፤ ስለ ቀድሞ ኑሯችንም ደፍረን አናወራም፤ የልጅነት ጓደኞቻችን ይናፍቁናል፤ እኛ ስንወጣ ጓደኞቻችን ጥግ ይዘው ሲያለቅሱ አይቼአለሁ። ወንዙና ሸንተረሩ፣ የከብቶቹ ጩኸት፣ ልጅነቴ አሁንም አዛ መንደር ውስጥ ነው” አለኝና ሄኖክ ረዥም ዝምታ ውስጥ ገባ፡፡
ከልቤ አዘንኩ፤ እንዴት ሄኖክን ላፅናናው እንደምችል አላወኩም፡፡ እኔም ዝም አልኩ፤ ዝም ዝም--- ግን አንድ ጥያቄ አዕምሮዬ ውስጥ ይመላለሳል፡፡ እህቱና ወንድሞቹ፤ እናትና አባቱ በምን ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት? የሚለው ጥያቄ ነው። ወንድሙና እህቶቹ አንደ እሱ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይሆን?  ---- ደፍሬ ጠየኩት። መልሱ አጭር ነበር:- “እህቴ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የአዕምሮ ህመምተኛ ነች፣ ከቤት አትወጣም፤  አንዱ ወንድሜ የለየለት ሱሰኛና ቀማኛ ነው፤ አንዱ ታክሲ ላይ ረዳት ሆኖ ይሰራል፤ እናትና አባቴ አሉ፤ ግን ተስፋ ቆርጠው ነው የሚኖሩት፤ ችግሮች ስላሉብኝ እኔም ቅስሜ የተሰበረና ድብርት ውስጥ ያለሁ ሰው ስለሆንኩ በምክር የሚረዳኝ ሰው እፈልጋለሁ፡፡” ከሄኖክ ጋር ከዚህ በላይ ዝርዝር ማውራት አልፈለኩም፡፡  
እናንተ አክራሪ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶችና ዘረኞች፤ ሥራችሁን እንጂ እናንተን አልጠላችሁም። ከዚህ በፊት ብዙ ግፍ የደረሰባቸውን ሰዎች በሚዲያ ተከታትለናል፤ ዛሬም በየቦታው ስልጣን በያዙ አካላት የሚበደሉ፤ በአክራሪ ብሔርተኞች የሚፈናቀሉ፤ አንዱን ብሔር በሌላው ላይ በሚቀሰቅሱ አክቲቪስቶች ምክንያት የሚጎዱ --- ቅስማቸው የተሰበረ እንደ እኔና እንደ ሄኖክ ጉዳት እየደረሰባቸው ያሉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በገዛ ወገናቸው ተፈናቅለው ማየት ያማል፤ ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው ሩዝና ዘይት በራሽን እየተሰጣቸው (የማያገኙም አሉ) ያለ ትምህርት የሚውሉትን ህፃናትና ወጣቶች፤ ያለ ስራ የሚያሳልፉትን አዋቂዎች ስታስቡ ምን ይሰማችኋል? ስለ ልጆቻቸው ነገ ምንም ማድረግ የማይችሉ እናትና አባቶችን ስታስቡ ምን ትላላችሁ? --- ቤተሰብ አላሳደጋችሁም? ከወንድም ከእህት ጋር አላሳለፋችሁም? ከጎረቤት ጋር ቡና አልጠጣችሁም? በሰፈራችሁ ቦርቃችሁ ከአብሮ አደጎቻችሁ ጋር አላሳለፋችሁም? ከእናንተ መሃል “አኩኩሉ” እያለ ያደገ የለም? ልጆች ወልዳችሁ አልሳማችሁም? የቤተሰብ መፈናቀል አያሳዝናችሁም? እባካችሁ ዘረኝነትን ተዉት፣ ልክ የብሔር ፖለቲካ ማቀንቀን ስትጀምሩ ሌላውን ሰው በብሔሩ ምክንያት ገፍታችሁታል’ኮ፤ ሚዛናዊ ልትሆኑ አትችሉም። ሰውን በሰውነቱ ብቻ አክብሩት፣ በዚህ ምድር የምንኖረው ለአጭር ጊዜ ነው፤ ቀጣዩን ትውልድ ምን ውስጥ ከታችሁት ለመሄድ እንዳሰባችሁ ቆም ብላችሁ አጢኑት --- እኔና ሄኖክ ምናባዊ ነን፤ ግን ብዙ ሆነን በገሃዱ ዓለም እንገኛለን። --- ለካስ ሰዓቱ መሽቷል፤ ደንገዝገዝ ካለ ጨለማ ያስፈራኛል፤ አንዳንዴ በጊዜ ከግቢ ካልወጣሁ ዶርም ከያዙ ጓደኞቼ ጋር እዚሁ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ነው የማድረው --- ሄኖክንም ከድብርቱ ጋር ትቼው ልሄድ ነው --- ምን አደርጋለሁ? ደህና ሁኑ!!  
ከአዘጋጁ፡- ጽሁፉ ከጥቂት ዓመታት በፊት ለንባብ የበቃ ቢሆንም  አድማስ ትውስታ ላይ ዳግም ያወጣነው በሰዎች ላይ የሚደርሰው ብሄር ተኮር ጥቃት እየባሰበት መምጣቱን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው።

Read 3954 times