Monday, 26 April 2021 00:00

ነጻ ያልወጣው የነጻው ፕሬስ

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(0 votes)

     እንደ መንደርደሪያ
የአግድሞሽ የቁጥጥርና ሚዛን (check and balance) ሥርዓት፣ የዴሞክራሲያዊ ግንባታ ምሰሶ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህን ጤናማ የሥልጣን ክፍፍል፣ በማይናወጥ መሠረት ላይ በማጽናቱ ረገድ፤ ትልቁን ድርሻ የሚጫወተው ደግሞ ሚዲያ ነው፡፡ የሥነ መንግሥት ንድፈ ሐሳባውያን፣ ዘርፉን «በአራተኛ መንግሥትነት» ይፈርጁታል፡፡
እውቁ አሜሪካዊው የዴሞክራሲ አባት ቶማስ ጀፈርሰን፣ ሚዲያን በተመለከተ ይህን ሐሳብ ሰንዝሯል፤ “ Were it left to me to decide whether we should have a government without newspapers, or newspapers without a government, I should not hesitate a moment to prefer the latter.“
በሕግ አውጪው፣ አስፈጻሚውና ተርጓሚው መካከል ያለው መስተጋብር፣ በተዋረዳዊ ዘይቤ እንዳይቀየድ የአንዱ ቅርንጫፍ ጡንቻ ፈርጥሞ ሌሎች ሎሌ እንዳይሆኑ፤ የሚዲያ ድርሻ የላቀ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ምሕዋሩን የጠበቀ የሥልጣን ክፍፍል በአምባገነናዊ አስተዳደር ውስጥ ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ከላይ ወደ ታች፣ በአውራና ጭፍራ የእዝ ሰንሰለት የተጠረነፈ፤ ምንም የማያፈናፍን የሚዲያ አወቃቀር የሚኖረው በአምባገነን መሪዎች አልያም የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ የበላይነት በነገሠበት የፖለቲካ ሥርዓት ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነት አፋኝ ሥርዓት ውስጥ ዋነኛ ሰለባ የሚሆነው በተለይ የመገናኛ  ብዙኃኑ ነው። በሕዝብ ጫንቃ ላይ፣ የተጫነውን የባርነት ቀንበር ለመስበር በሚደረገው ትግል ውስጥ ሚዲያው የሚኖረው አስተዋጽኦ ስለሚታወቅ፣ የጨቋኞች በትር ይከፋበታል።
ላለፉት ሁለት ዐሥርተ ዓመታት፣ በሀገራችን ተንሰራፍቶ የኖረው መሪር ሐቅ፤ ይህ እንደነበር የአደባባይ ምሥጢር ነው። ሕወሓት/ኢሕአዴግ የዘረጋውን የአፋኝ አገዛዝ ዕድሜ ለማራዘም፤ የሕዝብ ድምጽ ይሆናሉ ብሎ የገመታቸውን ሚዲያዎች፣ በሽብር ክስ ሽፋን ለማሽመድመድ፤ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ከማድረግ ተቆጥቦ አያውቅም፡፡ አብዛኛዎቹ ሀገር ቤት ያሉ እውነተኛ የሕዝብ አጋር የሆኑ ጋዜጠኞች፣ ሰብኣዊ ፍጡር ሊሸከመው የማይችለውን መከራን ለመቀበል ተገድደው ነበር። ከፊሎቹ ደግሞ ትረፉ ሲላቸው ባሕር አቋርጠው፣ የስደት ሰለባ ለመሆን ተገደዋል፡፡
ይህ የአፈና አገዛዝ፣ በአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት በተቀጣጠለ የሕዝብ አመጽ፣ እንዲሁም ከውስጥ በተነሱ የለውጥ ኃይሎች ቅንጅት አማካኝነት ከተገረሰሰ ሁለት ዓመት ቢያልፈውም፣ አሁንም ገና ድንግዝግዙ አልጠራም፡፡ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ከል ለብሶ፣ በምትኩ የዘውጌ ብሔርተኝነት በሚያስበረግግ ደረጃ ፋፍቷል፡፡ ሀገራችን አሁን ያለችበት የሞት ሽረት (critical juncture) ትግል ወደ ኋላ ከተቀለበሰ፤ ዳግመኛ ይህን ዕድል ማግኘት ፈጽሞ የሚታሰብ አይሆንም፡፡ በመሆኑም፣ በዚህ ዝብርቅርቅ የሽግግር ወቅት፣ የሚዲያው ድርሻና ኃላፊነት ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ እንደሚሆን እሙን ነው፡፡
ለመሆኑ ዳዴ የሚለው ሚዲያ ለነጻነቱ መታገል የሚያስችለው ቁመና አለውን?
የሀገራችን የሚዲያ አውታሮች፣ በአብዛኛው ለጋዜጠኝነት የሙያ ሥነምግባር ባይተዋር ናቸው፡፡ መርዶ ነጋሪ ወይም አወዳሽ መሆን ይቀናቸዋል፡፡ ከዚህ በዘለለ፣ በሰለጠነ መንገድ ኂሳዊ ድጋፍ መስጠት ለሚያስችል ተቋማዊ ባህል እንግዳ ናቸው። የዚህ ምክንያት ውስጣዊና ውጫዊ ተብሎ ሊከፈል ይችላል፡፡ የሚዲያዎቹ አደረጃጀት ደካማ መሆን፤ የሙያ ብቃት ያለው የሰው ኃይል እጥረት፤ እንዲሁም የማያወላዳ የፋይናንስ አቅም፤ ውስጣዊ ተግዳሮቶች ተብለው መወሰድ ይችላሉ፡፡ መንግሥት በዘርፉ ላይ በየጊዜው የሚያሳርፈው ረጅም እጅ ከውስጣዊ ፈተናዎች በተጨማሪ ሚዲያውን ወደ ኋላ ሲጎትተው ኖሯል፡፡ በእነዚህ ተገዳዳሪ ነባራዊ ሁኔታዎች የተነሳ፣ ዳዴ የሚለው ፕሬስ ጨርሶ ሊቀነጭር ችሏል፡፡    
የ“አዲስ ፎርቹን” ጋዜጣ ባለቤትና ማኔጂንግ ኤዲተር ታምራት ገብረጊዮርጊስ “Power, media and the Ethiopian public” በሚለው የዳሰሳ ጽሑፍ፣ በአምባገነናዊ ሥርዓት የሚኮረኮመው ሚዲያ የሚላበሰውን ቁመና በግልጽ አስቀምጦታል፡፡ “በፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ውስጥ የሚዲያ ባሕርይ ሥልጣን ላይ ላለው መንግስት ማገልግል ወይም ጽንፈኛ ተቃዋሚ መሆን ነው፤” ይላል። Regrettably, in a landscape where power plays significant role and intervention, the media churns out products that is more of partisan political commentaries than providing dispassionate information, news and analysis.
የታምራት ሐሳብ ውኃ እንደሚቋጥር የምንረዳው፤ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የመንግሥትን ፊት እያዩ ሲዘግቡ የኖሩትን ጋዜጦችና መጽሔቶች ቁመና መለስ ብለን ስንመረምር ነው፡፡ ከመንግሥት ጋር የሚላተሙት የሕትመት ሚዲያዎች በሰበብ አስባቡ ከመድረኩ ገሸሽ እንዲሉ ሲፈረድባቸው አስተውለናል፡፡ አሁንም ፕሬሱ አከርካሪውን ክፉኛ እንደተመታ ነው። የተሽመድመደው ፕሬስ፣ በሁለት እግሩ ለመቆም ገና ወገቡ በቅጡ አላገገመም፡፡
 የለውጡ አመራር የሥልጣን መንበሩን በተቆናጠጠ ማግሥት፣ የእስር ቤት በሮች ተከፍተዋል፤ በሽብርተኝነት ጭምብል የተከሰሱ ጋዜጠኞች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በነጻ ተለቀዋል፤ በአፋኙ ሥርዓት ማዕቀብ ተጥሎባቸው የኖሩት ጋዜጦች፣ መጽሔቶችና ድረገጾች እገዳው ተነስቶላቸዋል፡፡ ይኽ ምናልባት፤ ለሚዲያው እንደ ብሥራት የሚወሰድ በጎ ጅምር ሊሆን ይችላል፡፡ በፕሬሱ በኩል ያለው እድገት ግን ባለህበት እርገጥ ነው፡፡
ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ተቋም (CPJ)፣ በኢትዮጵያ እውን የሆነውን ፖለቲካዊ ሽግግር ዋቢ በማድረግ፣ “የኢትዮጵያ ሚዲያ፣ ቀን ወጥቶለታል፤ በፊት የነበረው ጭቆና  አሁን የለም፤ ነገር ግን፣ ሚዲያው የተገኘውን አንጻራዊ ነጻነትን በመጠቀም፤ የምርመራ ጋዜጠኝነትን (Investigative journalism) ባህል ለማዳበር ሲተጋ አይስተዋልም” ብሎ መዘገቡ የሚታወስ ነው። ተቋሙ፣ ከሁለት ዓመት በፊት ባደረገው የዳሰሳ ጥናት፣ ከአብዛኛው አስተያየት ሰጪዎች የሚነሳው ቅሬታ ተመሳሳይ እንደሆነ አትቷል፡፡ የምሕዳሩ መከፈት፣ ለፕሬሱ ማበብ በራሱ ዋስትና አልሆነም፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ፣ በጥናት ውስጥ የተሳተፉት ባለሙያዎች የሰነዘሩትን ሐሳብ ተንተርሶ፣ በይፋዊ ድረገጹ ላይ የሚከተለውን ነጥብ አቅርቧል፤ “most of those who spoke with CPJ said they felt there was a need for Ethiopian media to grow into professionalism and to act more ethically and responsibly within the newly opened space.”
በአዲሱ የለውጥ አስተዳደር፣ በጻፉትና በተናገሩት መሸማቀቅ፤ ብሎም ወህኒ መወርወር ገታ ቢልም፤በጋዜጠኝነት ሥነምግባር የታነጹ ባለሙያዎችን በዘርፉ ላይ በብዛት እየተመለከትን ግን  አይደለም፡፡
በተቻለ መጠን፤ የሽግግሩን ሂደት በኃላፊነት ስሜት ለመተቸት፤ ስሕተትን በሚጠቁም መልኩ እየነቀሰ ሚናውን ሲወጣ ለመመልከት አልታደልንም። አሁንም፤ ሚዲያው ከቆየው አዙሪት አልተላቀቀም፡፡ ወይ ጭፍን አምላኪ፤ አልያም ጨለምተኛ ከመሆን ዘይቤው አልወጣም፡፡ ሚዲያዎቻችን ፈርጠም ብለው የመንግሥትን ስሑት ገቢር የሚነቅሱበት ሚናቸውን (watch dog role) ለመወጣት ገና መንገዱን አልጀመሩትም።
የማኅበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ሚና  
የማኅበራዊ ትስስር ድረገጾች ተጽእኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበረታ ነው፡፡ ባደጉት ሀገሮች ዲጂታል ሚዲያ አልፎ …ተርፎ ሌሎችን አውታሮች እየተካ መጥቷል። ይህም ሆኖ ግን በሥነምግባርና በሕግ የሚመሩ ሚዲያዎች ቅቡልነት አሁንም አልቀነሰም፡፡ በሀገራችን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ግን ተገላቢጦሽ ነው። ዋና የሚዲያ ምንጭ (Main stream media) የሚባሉት አውታሮች፣ የማኅበራዊ ትሥሥር ድረ ገጾች ተለጣፊ ሆነዋል። የራሳቸውን አጀንዳ በመፍጠር ፈንታ፤ የፌስቡክና ትዊተር የመወያያ ርእስ ጉዳዮች ላይ ብቻ የሙጥኝ ማለትን ይመርጣሉ። የትኩረት አቅጣጫቸው በአብዛኛው፣ ሰሞነኛ ሞቅታ እንጂ፣ ዘላቂ የመፍትሔ አቅጣጫ ማመንጨት አይደለም፡፡
የመንግሥት የቢሮክራሲ ማነቆ
በሕወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን የነበረው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ፈርሶ፣ በምትኩ የፕሬስ ሴክሬታሪያት የተባለ ተቋም በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ሥር ተቋቁማል፡፡ የኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት፣ ከአዲሱ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጋር ሲነጻጸር፣ ተራማጅ ነበር ቢባል ያስኬዳል፡፡
የመንግሥት ተቋማትም ቢሆኑ፣ ለመገናኛ ብዙኃን በራቸው ዝግ ነው። ከዚህ ቀደም በባሰ መልኩ የመረጃ ፍሰቱ ከነጭራሹ ተገትቶ ነበር። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ፣  ከሕትመት ሚዲያ የወጣችው፣ የቦሌ ታይምስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ እንደመሥራቱ መጠን፣ ከመንግሥት ተቋማት መረጃ ለማግኘት ያለውን ፈተና በተግባር ለመታዘብ ችሏል፡፡ ለውጡ ለሚዲያው ይዞት የመጣው በረከት እንደሚጋነነው አይደለም፡፡ እስራት ቀረ እንጂ አሳሪ ቢሮክራሲያዊ ውጣውረዶች ገና ምንም አልተነኩም፡፡
እንደ ማጠቃለያ
የነጻው ፕሬስ አሁንም ፀሐይ አልወጣለትም፡፡ ከ1997 ዓ.ም በፊት የወጡ፣ ለፕሬስ ነጻነት የማይመቹ ሕጎች አሁንም አልተሻሻሉም። በአንቀጽ 29 ላይ የሰፈረውን ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የሚጋፉ አዋጆች ውስጥ የተሰገሰጉ በርካታ ሕጎች መኖራቸውን ባለሙያዎቹ ሲናገሩ ይደመጣል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ሚዲያው ያለፈበት መሰናክል ከግምት በላይ ነው፡፡ በነጻው ፕሬስ ሰማይ ላይ ያጠላው ጽልመት፣ ሁሉንም የዘርፉ አካላት በእኩል ደረጃ ሰለባ የሚያደርግ ነው፡፡ ምንም እንኳን፤ ከሕወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ዘመን ጋር ሲነጻጸር፣ ለዘርፉ ብሥራት የሆኑ አዎንታዊ እርምጃዎች መወሰዳቸው የአደባባይ ምሥጢር ቢሆንም፣ እርምጃው የነጻው ፕሬስ በዴሞክራሲያዊ ግንባታ ሒደት ውስጥ ከሚጫወተው ሚና አኳያ ሲመዘን፤ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
የመንግሥት የቢሮክራሲ ማነቆዎች የነጻው ፕሬስ የሕትመት ውጤቶችን ዕለት በዕለት እያቀጨጩ ይገኛሉ፡፡ በቋፍ ያሉት በጣት የሚቆጠሩ የሕትመት ውጤቶች፣ እንደ ገና ጀንበር ብቅ ብለው ፈጥነው ሲከስሙ እያስተዋልን ነው፡፡ መንግሥትም ለዘርፉ ያሳየውን ዳተኝነት ተከትሎ፣ ይህ ሁኔታ ቢከሰት አይደንቀንም፡፡ በፕሬሱ ላይ የተጫነውን የግብር ሥርዓት መለስ ብሎ በመከለስ፣ እንዲሁም ለሕትመት የሚስፈልጉት ግብአቶች (ለምሳሌ ወረቀት) በአነስተኛ ዋጋ የሚቀርቡበትን አሠራር በማመቻቸት፣ የተጎዳውን ዘርፍ ቢያንስ መደጎም ይቻል ነበር፡፡
ካለፈው ሥርዓት የተወረሱ ማነቆዎች አሁንም ዱካቸው አልጠፋም፤ በገሐድ እያስተዋልናቸው ነው፡፡ በዘርፉ ላይ የተሰማሩት ባለሙያዎችም ቢሆኑ፣ ከሙሾ አውራጅነት ወይም ከአድርባይነት ዘይቤ ተላቀው፣ ለእውነተኛ የጋዜጠኝነት የሙያ ሥነምግባር ተገዢ ለመሆን ከምር መነሳት ይኖርባቸዋል፡፡

Read 8126 times