Saturday, 24 April 2021 12:32

ከብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት በወቅታዊ ሀገራዊና ቀጠናዊ፣ የደህንነትና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ መግለጫ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች፣
ከሦስት ዓመታት በፊት ወደ ለውጥ ጎዳና የገባነው በመንገዱ ላይ ችግሮች አይገጥሙንም በሚል እሳቤ አልነበረም፡፡ ሀገራችን ትከሻ ላይ
የተቆለለውን የበዛ ችግር ከነውስብስብነቱ ተረድተን እንጂ፤ አቅልለን አይተን አልተነሳንም፡፡ ለዘመናት ሲከመር ቆይቶ ወደ ግዙፍ ተራራነት
የተለወጠው ሀገራዊና ቀጠናዊ ችግሮች በቀላሉ መወገድ ቢችሉ ጥሩ ነበር። ነገር ግን ችግሮቹ እንኳን እርስ በእርስ እየተጓተትን ቀርቶ አንድ
ሆነንም በጥቂት ዓመታት ውስጥ ድምጥማጣቸው የሚጠፋ አይደለም፡፡
ይሄንን በሚገባ አውቀን እስከ መጨረሻው ሕቅታ ዋጋ ለመከፈል ቆርጠን ነው የተነሳነው፡፡ ሀገራችን ያሉባት ችግሮች ምንም ያህል እንደ
ምድር አሸዋ ቢበዙ ፈጽሞ ከዜጎቿ አቅም በላይ እንደማይሆኑ ጽኑ እምነት አለን የሚፈቱትም ተነጣጥለን ሳይሆን በአንድነትና በትብብር
እንደሆነ ገና ከጅምሩ አሳውቀናል፡፡ በወቅቱ ያለ ብዙ ፈተና በአንዲት ጀንበር የተለወጠች ሀገር ትኖረናለች ብለው የጠበቁ ሰዎች እንደነበሩ
ግልጽ ነው፡፡ ለውጡ ከአንድ አቅጣጫ ይመጣልም ብለው እንደታዛቢ ዳር ቆመው የሚመለከቱ መኖራቸውም እንዲሁ፡፡
ያኔ የለውጥ ጉዞ በጀመርንበት ወቅት ሁሉም ሰው ከፍ ባለ ሞራልና በፌስታ ተሞልቶ የነበረ ቢሆንም፣ ሁሉም በጀመረበት የመንፈስ ከፍታ
እንደማያጠናቅቅ ግልጽ ነበር። ሀገራችን ለዘመናት ስትናፍቀው የኖረችው የተስፋ አድማስ ላይ ደርሰን ሁላችንም የመንካት አድሉ ይገጥመናል
ብሎ ማሰቡም ሞኝነት ነው፡፡ በየመንገዱ የሚገጥመንን እሾህና ጋሬጣ ሳያቆስለን፣ እባብና ጊንጡ ሳይነድፈን፣ ሀሩርና ቃጠሎው ሳይለበልበን
የምናልማትን የበለጸገች ሀገር መገንባት ብንቸልማ ኖሮ ገና ድሮ በአደረግነው ነበር፡፡
በረሃውን ሳናቋርጥና ባህሩን ሳንሻገር ጉዞው ይጠናቀቃል ብለው ያሰቡ ሰዎች ከመጀመሪያውም ተሞኝተዋል። ከፊታቸው የተዘረጋውን ፈተና
ቀድመው ያላዩ፣ ጉዞው መሐል ላይ ወገባቸው ዝሎ መንቀጥቀጥ ሲጀምር ቢናደዱ፣ መበሳጨት ያለባቸው በሌላ አካል ሳይሆን በተሳሳተ
ግምታቸው ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ይበልጥ ወደ ተስፋ ሰገነታችን እየቀረብን በመጣን ቁጥር ፈተናው እንደሚበረታ መረዳት ይኖርብናል፡፡
በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት ያየናቸው ግጭቶች፣ የሰላም ማጣትና የደህንነት ስጋቶች በለውጥ ጉዞአችን በእጅጉ ከፈተኑን ፈተናዎች ጎራ
የሚመደቡ ናቸው፡፡ መንገድ ያስጀመረንን አንድነት ሊደቁሱ፣ እጅ ለእጅ ያስተሳሰረንን ገመድ ሊበጣጥሱ፣ የጋራ ቤታችንን ሊደረማምሱ
የሚቋምጡ ብርቱ ፈተናዎቻች ጉዞ ከመጀመራችን በፊትም ነበሩ፣ አሁንም አሉ፡፡
ምናልባትም መንገዳችን ላይ ልዩ ልዩ ጋሬጣዎችን እየጣሉ ከጉዞአችን ሊያስቀሩን የሚሹ አካላትን ድብቅ ፍላጎት በአግባቡ ተረድተን
በጥንቃቄና በጥበብ ወደ ግባችን መጓዛችንን እንደማናቆም እስካላሳየናቸው ድረስ በቀሪ ምዕራፎቻችንም ላይ ተከትለውን ይመጣሉ።
የጠላቶቻችን ፍላጎት በጉዞአችን መሐል ወድቀን ግባችንን ሳናሳካ እንድንቀር ነው፡፡ በጋራ ቆመን ያጸናነው ቤታችን ፈራርሶ ወደ ትቢያነት
ሲቀየር ማየት ይሻሉ፡፡ እኛ ደግሞ ለዚያ የተመቸን ሆነንላቸዋል፡፡
አንድ ቤት በሦስት ምከንያቶች ሊፈርስ ይቸላል። በግንባታው ወቅት በገጠሙት ችግሮች፣ ከውስጥ ባሉ ሰዎች እና ከውጭ በሚመጡ
ኃይሎች። እነዚህ ሦስቱ አውቀውትም ይሁን ሳያውቁ የሚተባበሩበት ጊዜ አለ። አንዳንድ ጊዜ በዓላማ፣ አንዳንድ ጊዜ በሂደት፣ አንዳንድ
ጊዜም በውጤት ይተባበራሉ። ከውስጥ ያሉት ሰዎች በውስጥ ጉዳያቸው ሲጣሉ፤ ከውጭ ያሉ ኃይሎች ቤቱን አፍርሰው ቤቱ የተገነባበትን ቦታ
ወይም በቤቱ ውስጥ ያለውን ሀብት መዝረፍ ሲፈልጉ፣ ቤቱ እንዲፈርስ ተባብረው ሊሠሩ ይችላሉ።
ቤቱ ሲገነባ ያጋጠሙት ችግሮች ካሉ ደግሞ ነገሩ “በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ዓይነት ይሆናል።
የተከበራቸሁ ኢትዮጵያውያን፣
ሁላችንም ልንዘነጋው የማይገባን አንድ ሐቅ አለ። ሀገራችን የጋራ ቤታችን ናት፡፡ የሁላችንም ቤቶች በዚያች ትልቅ ቤት ውስጥ የሚገኙ የቤቱ
ከፍሎች ናቸው፡፡ በየከፍሎቻችን ተወሽቀን ያለነው ሁላችንም የጋራ ቤታችንን አጽንጸን በማቆየት ላይ ተመሳሳይ አቅምና አቋም የለንም። ቤትን
ከውጭ የሚመጣ ኃይል ብቻውን አያፈርሰውም። የውስጦቹ ካልተባበሩት በቀር፡፡ የቤቱ ሰዎች የውጭ አፍራሾች በሦስት መንገድ
ዐውቀውም ይሁን ሳያውቁ ሊተባበሯቸው ይችላሉ፡፡ ሆን ብለው፣ ሞኝ ሆነው እና ተኝተው፡፡
ከሚፈርስ ቤት እንጠቀማለን የሚሉ ሞኝ የቤት ሰዎች አሉ፡፤ ከመሥራትና ከመድከም ዋጋ ማግኘት የሚከብዳቸው፤ የቤቱን ፍርስራሽ ሽጠው
ማትረፍ የሚፈልጉ የፍርስራሽ ጌቶች አሉ፡፡ እነዚህ ሆን ብለው ቤቱ እንዲፈረስ ይሠራሉ፡፡ ቤቱ ቶሎ ፈራርሶላቸው ፍራሹን ለመቸብቸብ
ስለሚቸኩሉ፣ ከውጭ ሆነው ቤቱን ከሚነቀንቁት ጋር ተባብረው ያፈርሳሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በምግቡም፣ በልብሱም፣ በሳሎኑም በምኝታ
ቤቱም የሚፈጠርባቸውን ቅሬታ የቤት ማፍረሻ ምክንያት የሚያደርጉ የዋሐን ባለቤቶች ናቸው፡፡
‹የላሞች ጠብ በረቱን ለተኩላ፤ የውሾች ጠብ መንደሩን ለጅብ ይሰጠዋል› እንደሚባለው፣ እነዚህ የቤት ልጆች ከውጭ ያሰፈሰፈውን ጠላት
ባለማወቅ የሚያደርጉት ጠብ፣ ከተራ እሰጣገባ አልፎ ሳያስቡት ቤቱን ያፈርሰዋል። አንዴ ከፈረሰ በኋላ ለውስጦቹ ትርፋቸው ቁጭት
ይሆናል። ከመሆኑ በፊት እንጂ ነገሮች ከተበለሻሹ በኋላ መጸጸትና መቆጨቱ ምንም ትርጉም የለውም፡፡ ሦስተኞቹ ደግሞ ተኝተው ቤት
የሚያፈርሱ ናቸው።፡ የቆሸሸውን ማጽዳት፣ የተሰነጠቀውን መጠገን፣ የጎደለውን ማሟላት፤ የጠመመውን ማቅናት ሲገባቸው እእ ምን አገባኝ›
ብለው ይተኛሉ። አጥሩ ሲፈርስ ሳሎን ሲድረስ ይላሉ፤ ሳሎን ሲፈርስ ምኝታ ቤት እስኪደርስ ይጠብቃሉ፤ ምኝታ ቤቱ ሲፈርስ ጓዳ
ተደብቀው በመተኛታቸው የሚተርፉ ይመስላቸዋል። ሁሉም ግን የጊዜ ጉዳይ ይሆናል፡፡
ዛሬ ታላቋ ቤታችን ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ ላይ ናት፡፡ ሦስቱም ዓይነት ልጆች አሏት፡፡ ከውጭ ጠላቶቿ ጋር ይሁነኝ ብለው በዓላማ ለማፍረስ
የሚሠሩ፤ በዓላማ ባይገጥሙም በውጤት ከውጭ አፍራሾች ጋር የሚሠሩ፤ ቤታቸው ሲቃጠል እያዩ ከመንቃት ይልቅ በሙቀቱ ተከናንበው
የተኙ። ይህ ወቅት ለኢትዮጵያ ከወሳኝ ወቅቶች አንዱ ነው፡፡ በአንድ በኩል ፍትሐዊ፣ ዴሞከራሲያዊና ተአማኒ ምርጫ አድርገን በሕዝብ
ድምጽ የሚጸና መንግሥት ለመመሥረት በሂደት ላይ ነን በሌላ በኩል ደግሞ የሀገራችን ከፍታ አንዱ ማሳያ የሆነውን የሕዳሴውን ግድብ
ሁለተኛውን ዙር ሙሌት ለማከናወን እየተጋን ነው።
ከእነዚህ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ግሥጋሴ ከሚያሠጋቸው የውጭና የውስጥ ጠላቶች ጋር በየአቅጣጫው ግንባር ለግንባር ገጥመናል፡፡ ኢትዮጵያ
እነዚህን ሦስት ፈተናዎች አልፋ ግቦቿን ካሳካች፣ ከዚያ በኋላ ለማንም በቀላሉ እጅ የማትሰጥ የሁላችን መመኪያ ሆና ትወጣለች፡፡ ይህ
እንዳይሳካ ከምንጩ እናደፍርሰው፣ ከእንጎቻው እንሰቅስቀው፣ ከእሸቱ እናጠውልገው› የሚሉ የማሰናከያ ድንጋዮች በየአቅጣጫው
ተነሥተዋል፡፡ ወሳኙ የእነርሱ መነሣት አይደለም፤ የእኛ ምላሽ እንጂ።
ውድ የሀገራችን ሕዝቦች፣
ከለውጡ ጅማሬ አንሥቶ የገዛ ዛፋችንን ከዛፉ በተቆረጠ ጠማማ እንጨት የመቁረጥ አዝማሚያ መኖሩን እየተናገርንም እየታገልንም ነበር።
በተለያየ አቅጣጫ የሚወረወረው ድንጋት በቤታችን ላይ የሚያደርሱትን አደጋ ለመግታት፣ የፖለቲካ አመራሩና የጸጥታ አካሉ መሥዋዕትነት
የተከፈለበት ትግል አካሂዷል። ከጁንታው ጋር የተደረገው ትግል የዚህ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ እነዚህ አካላት ዛሬም አልጠፉም፡፡ የተለያዩ
ብሔሮችን ስሞች ይዘው፣ ሲመች በሰላም ሳይመች በጠመንጃ የላኪዎቻቸውን ዓላማ ለማሳካት እየሠሩ ነው፡፡
የእነዚህን ተልዕኮ ያልተረዱ የዋሖች ደግሞ ሀገር እንድትፈርስ ባይፈልጉም ሀገር እንድትፈርስ ግን እየሠሩ ነው። የቤቱ ጥያቄ የሚመለሰው
መጀመሪያ ቤቱ ሲኖር መሆኑን ዘንግተውታል፡፡ ቤት እያፈረሱ ስለ ቤት ለመወያት ይፈልጋሉ፡፡ ‹ቤቴን እጠብቃለሁ፤ ሙሣቴንም እሟገታለሁ›
የሚሉ አባቶች ልጆች መሆናቸውን ረስተውታል። ስለ ላሟ ወተት የሚኖረው ጥያቄ የሚመለሰው መጀመሪያ ላሟ ስትኖር መሆኑን
ረስተውታል። ከእነዚህ ከሁለቱ ጋር ተደምረው ‹ምን አገባኝ የሚሉ ዜጎችም አሉ፡፡ ምድር ቤቱ ሲቃጠል እሳቱ ሰባተኛ ፎቅ ላይ የሚደርስ
የማይመስላቸው፡፡ ወይ ለመገንባት ወይ ለመመከት አንዳች የማያደርጉ፡፡ እሳቱን ከመከላከል ይልቅ በሙቀቱ ተመቻችተው ያንቀላፉት
ጭምር የሀገራችን ችግሮች ናቸው፡፡
አሁን በአለንበት ጊዜ ሦስት ወሳኝ ዓላማዎቻችንን በጽናት ማሳካት ይኖርብናል። በመጀመሪያ አንድ ወር ያህል ጊዜ የቀረውን ምርጫ ውጤታማ
እናድርገው፡፡ በነቂስ ወጥተን ካርድ እንውሰድ። ሁላችንም ይበጀናል ያልነውን እንምረጥ። የፈለግነውን እንዳንመርጥ እንቅፋት የሚሆንብን
የትኛውም አካል እርሱ የኢትዮጵያ ጠላት ነው፡፡ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን እየተቋቋምን፤ ችግሮችን እያረምን፣ ጉድለቶችን እየሞላን
ምርጫውን ውጤታማ እናድርገው። ይሄንን ምርጫ በድል ተወጣነው የምንለው ሂደቱ የሚጠበቅበትን ደረጃ ለማለፍ ከቻለ ነው፡፡ ለዚህ
ደግሞ መራጩ ሕዝብ፣ ተመራጮች እና የምርጫ ቦርድ ሀገራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ አደራ እንላለን፡፡
ሁለተኛ ከምርጫው ጎን ለጎን ግድባችንን ባቀድነው መንገድና ጊዜ መገንባትና ሁለተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት ማከናወን አለብን፡፡
የትኛውንም ዓይነት ጫና ተቋቁመን፤ የውስጥና የውጭ ፈተናዎቻችንን አልፈን እንሞላዋለን፡፡ ኢትዮጵያን መውደዳችንን የምናሳየው
የኢትዮጵያን ጉዞ በማቀላጠፍ እንጂ በማደናቀፍ አይደለም፡፡ በእሳት ላንቃ ውስጥ እያለፍንም ቢሆን ማድረግ ያለብንን ማድረግ አለብን፡፡
በያዝነው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ግድባችንን ሞልተን ኃይል ማምረት እንጀምራለን በየአቅጣጫው የምናየው የወገኖቻችን አሰቃቂ ግድያ፣
ማፈናቀል፣ ቤትና ንብረት ማውደም፣ ነውጥና ሸፍጥ ሁሉ በሀገር ውስጥ ብቻ የተመረተ አይደለም፡፡
አብዛኛው ጥፋት በውጭ ተምርቶ በሀገር ውስጥ የሚገጣጠም ጥፋት ነው፡፡ ግጭቱንና ጥፋቱን ከውጭ አስመጥተው በሀገር ውስጥ
የሚገጣጥሙት የእፉኝት ልጆች ናቸው። በዚህ ዓመት መጀመሪያ የእፉኝቶችን ዋና መፈልፈያ አፍርሰነዋል። ከዚህ በፊት ፈልፍሎ እዚህና
እዚያ የጣላቸው ግልገሎቹ ግን አሁንም ይቀራሉ፡፡ የትኛውንም ዓይነት የብሔርና የአምነት ስም ቢይዙ፤ ከየትኛው የውጭ ኃይል የሚረዱትን
ገንዘብና መሣሪያ ቢጨብጡ ኢትዮጵያን ይፈትኗት ይሆናል እንጂ አያሸንፋፏትም፡።፡
መጀመሪያ በውስጣችን ያሉትን ባለ ሁለት በላዋዎች እናጸዳለን። ቀን ቀን ለኢትዮጵያ የሚሠሩ የሚመስሉ፤ ሌሊት ሌሊት በኢትዮጵያ ላይ
የሚዶልቱ አሉ። እነርሱ ከውጭ ጠላቶቻችን በላይ ዋነኞቹ ጠላቶቻችን ናቸው፡፡ አጥር ላይ ተቀምጠው፣ አሸናፊውን አይተው፣ ከተመቻቸው
ሊገቡ፣ ካልተመቻቸው ሊሸሹ የሚያስቡ መኖራቸውን ዐውቀናል፡፡ ወቅቱ የምርጫ ነውና መምረጥ አለብን፡፡ ወይ እነርሱን እናጸዳለን ወይ
ኢትዮጵያን አሳልፈን እንሰጣለን። የኛ ምርጫ ኢትዮጵያን ሰእነርሱ ስንል መሠዋት ሳይሆን፤ እነርሱን ለኢትዮጵያ ስንል መሠዋት ነው፡፡
በአጠቃላይ ምርጫውን ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ለማድረግ፤ ግድባችንን በታቀደለት መንገድ ገንብተን ሁለተኛውን ዙር የውኃ
ሙሌት ለማከናወን፤ እንዲሁም ኢትዮጵያን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቿ ታድገን ወደሚገባት ደረጃ ለመውሰድ እንድንቸል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ
በንቃትና በብስለት ከመንግሥት ጎን እንዲቆም ጥሪ እናደርጋለን። ቆም ብለን እናስብ፤ ከሁሉም በፊት ኢትዮጵያን እናስቀድም፡፡ በፌዴራልና
በከልል የምትገኙ የጸጥታ አካላት፣ ተቀናጅታችሁና ተናብባችሁ በመሥራት የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያውያን ሰላምና ደኅንነት እንድታስጠብቁ
እናሳስባለን።
የሚደረጉ ማናቸውም የፖለቲካና የመብት እንቅስቃሴዎች ይደገፋሉ፡፡ የትግላችን ውጤቶች ናቸውና፡፡ እነዚህ የመብትና የፖለቲካ
እንቅስቃሴዎች ግን ኢትዮጵያን እንዲያናውጡ አንፈቅድም፡ ፖለቲካዊ ጨዋታውን ከጨዋታ ሜዳ ውጭ ለማድረግ ለሚፈልጉት ኃይሎች፣
ትእግሥታችን ማለቁን በዚሁ ኢጋጣሚ ልንነግራቸው እንፈልጋለን። ሁሌም እንደምንለው፤ በጽናትም እንድምናምንበት፣ ለኢትዮጵያ ፈተና
ብርቋ፣ ድል ማድረግም ሰበር ዜናዋ አይደለም፡፡ ከዚህ በላይ አልፋ ዛሬ ላይ ደርሳለች። ይሄንን አልፋ ነገ ላይ ትገኛለች፡። ኢትዮጵያ ማሸነፏ
ላይቀር እንዳታሸንፍ ሲታገሉ የኖሩትን ትታዘባቸዋለች፤ በታሪከ ሂደትም ትቀጣቸዋለች፡፡ እርሷ ግን ወጥመዱን በጣጥሳ፣ ሰንኮፉን ነቃቅላ፣
አዚሙን አስወግዳ ያሰበችበት ትደርሳለች።
ኢትዮጵያ እስካሁን የቆየችውም ወደፊትም የምትቆየውም፣ በእኛ በመስዕዋት ልጆቿ ደምና አጥንት ነው። ዛሬ እኛ የምንከፍለው ዋጋ፣ ነገና
ከነገወዲያ ሀገራችንን ወደማይቀለበስ የብልጽግና ከፍታ ላይ እንደሚያደርሳት ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት
ሚያዚያ 16፣ 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ

Read 10815 times