Saturday, 24 April 2021 12:30

በትግራይ ግጭትና በኮቪድ-19 ምክንያት ኢኮኖሚው በእጅጉ ተቀዛቅዟል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

በኮቪድ-19 እና በትግራይ በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት የኢትዮጵያ ዓመታዊ እድገት ከ18 ዓመታት በኋላ ከፍተኛ መቀዛቀዝ እንዳጋጠመው አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) በሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
በተያዘው የፈረንጆቹ 2021 ኢትዮጵያ አማካይ እድገቷ 2 በመቶ እንደሚሆን የተነበየው አይኤምኤፍ፤ ይህም እ.ኤ.አ ከ2003 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ ማሽቆልቆል የታየበት ነው ብሏል፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ  በሃገሪቱ እንቅስቃሴ ላይ ገደብ በማስከተሉ የኢኮኖሚ ድቀትና የገበያ አለመረጋጋት መፈጠሩን፣ በዚህም ግዙፍ የኢኮኖሚ አውታሮች በከፊል ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸውን ተቋሙ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
ከኮቪድ-19 ባሻገር የጎርፍ አደጋ  የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝና በየቦታው የሚከሰቱ ግጭቶች እንዲሁም  የሠብአዊ መብት ጥሰቶች የኢኮኖሚ ድቀትና ማህበራዊ አለመረጋጋት መፍጠራቸው ለኢኮኖሚው መቀዛቀዝ  ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አይ ኤም ኤፍ ጠቁሟል፡፡
በትግራይ ያጋጠመው ያልታሰበው ጦርነት ደግሞ የሃገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት በእጅጉ የገደበ መሆኑን ያመለከተው የተቋሙ ሪፖርት፤ በግጭቱ ቢያንስ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች መፈናቀላቸውና ለተረጂነት መጋለጣቸው፣ ምርት ሙሉ በሙሉ መቆሙና መንግስት አሁንም ግጭቱን ማቆም አለመቻሉ ለኢኮኖሚው ድቀት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ ኢኮኖሚያዊ ቁልቁለት ፈጥና ለማገገም፣ በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን መቻል፤ ዋነኛ መፍትሔ መሆኑንም ተቋሙ ጠቁሟል፡፡ እስከ 2025 ባለው ጊዜም የሃገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ከፍ አለ ከተባለ ከ3.6 በመቶ ላይሻገር እንደሚችል ተተንብይዋል፡፡


Read 10099 times