Saturday, 17 April 2021 13:01

የማህበረሰብ ችግሮችን የሚፈቱ የስራ ሀሳቦች ላይ ውይይት ተካሄደ

Written by  ናፍቆት ዩሴፍ
Rate this item
(0 votes)


            የማህበረሰብን ችግር የሚፈቱ የስራ ሀሳቦችና ኢንተርፕራይዞች የስራ እድሎችን ለመፍጠርና ችግሮችን ለመፍታት አማራጮች የሚያቀርቡ እንደሆኑ ተገለፀ። ይህ የተገለፀው ከትላንት በስቲያ ረፋድ ላይ ሶሻል ኢንተርፕራይዝ በኢሊሌ ሆቴል ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ነው፡፡ ሶሻል ኢንተርፕራይዞች ለንግድ የተቋቋሙ ድርጅቶች ሲሆኑ መነሻቸው የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ሀሳቦችን በማመንጨትና የሚያተርፉትን ትርፍም መልሰው ለማህበረሰብ አገልግሎት የሚያውሉ ናቸው ተብሏል፡፡
እነዚህ ድርጅቶች የሚመሰረቱት በቡድን ወይም በተናጥል የስራ ሀሳብ  ባላቸው ሰዎች ሲሆን የማህበረሰቡን ችግር ለመፍታት የሚያልሙ በመሆናቸው ለብዙዎች የሚሆኑ ዕድሎችን በቀላሉ የመፍጠር አቅም ያላቸውም እንደሆኑም በውይይቱ ተነስቷል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ እንዲሁም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተወካዮች የተገኙ ሲሆን የመንግስት ተቋማትና ፖሊሲዎች ለሶሻል ኢንተርፕራይዞች ምን የተለዩ ዕድሎችና አማራጮችን ሊያመቻቹ እንደሚገባ ውይይቱ ተደርጎበታል፡፡
የኢፌዲሪ የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን፣ የፖሊሲና ስትራቴጂ አማራጭ ሀሳቦችን በማቅረብ ለስራ ፈጣሪዎች ምቹ ከባቢ  ለመፍጠር ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ እንደሆነ በኮሚሽኑ የአዳዲስ ስራዎችና ፕሮጀክቶች ዳሬክተር ወ/ሮ አለምፀሀይ ደርሶልኝ ገልፀዋል።


Read 19738 times