Saturday, 17 April 2021 12:30

ቀውስ ናፋቂው

Written by  ሙሉጌታ መንግስት አያሌው (Ph.D)
Rate this item
(0 votes)

 አድማስ ትውስታ


           ሸክላ ሳህን ተሰባሪ ነው። ትንሽ ቀውስ፤ ስፍራውን ያስለቅቀዋል። ወደ ቀደመ ስፍራው አይመለስም። ከቀውሱ በኋላ እሳት መጫሪያ መሆን ከቻለ ትልቅ ነገር ነው። የተሰባሪ ተቃራኒ የማይሰበር ይመስለናል፤ ነገር ግን አይደለም። የማይሰበር ነገር ማለት፤ በቀውስ ምክንያት ስፍራውን በጊዜያዊነት ቢለቅም፤ ከአፍታ ቆይታ በኋላ ወደ ቀደመ ስፍራው የሚመለስ ነገር ነው።
ፊኒክስ የምትባል በግሪክ ተረት ውስጥ የምትገኝ ወፍ አለች። ፊኒክስ በማንኛውም ሁኔታ ብትሞት ወይም ብትገደል እሳት ፈጥራ ትሞታለች፤ ነገር ግን ከአፍታ ቆይታ በኋላ ከገዛ አካሏ ቅሪት አመድ ውስጥ ነፍስ ዘርታ ትወጣለች። ወደ ቀደመ ቦታዋ ትመለሳለች። እንዲህ አይነት ባህሪ ያለው ነገር፤ ለቀውስ አይበገሬ ይባላል።
ለአብነት የሚሆኑ ማሳያዎችን እያነሳን እንመልከት። ለምሳሌ ሀገራችን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኤኮኖሚ ለመገንባት ስትራቴጂ አውጥታ ትሰራለች። ነገር ግን የአየር ንብረት ለውጥን ብቻችንን ልናስቀረው አንችልም። የአየር ንብረት ለውጡ ስፍራችንን ሊያስለቅቀን፥ ሊሰብረን ይችላል። ይሁን እንጂ ቢያስለቅቀንም፣ ለቀን እንዳንቀር ተሰብረን እንዳንቀር የሚያስችለንን አቅም ለመገንባት እንሰራለን። የማይሰበር፥ ወይም ለቀውስ የማይበገር፣ የተሰባሪ ተቃራኒ ግን አይደለም። መሃል ሰፋሪነት ነው።
የተሰባሪ ተቃራኒ ቀውስ ናፋቂ ነው፤ ልክ እንደ ሃይድራ። ሃይድራ የሚባለው የተረት እባብ፤ ጭንቅላቱን ስትቆርጠው አስር አዳዲስ ጭንቅላቶች ያበቅላል። የተሰባሪነት ተቃራኒ ሃይድራዊነት ነው። ሃይድራዊነት፣ አይሰበሬነት - አይበገሬነት አይደለም። ሃይድራዊነት ቀውስ የሚያብሰው ማንነት ነው። ቀውስ ናፋቂነት ነው። ኢህአዴግ መራሹ መንግስት፤ ቀውስ ናፋቂነትን በበጎ መልኩ አልተጠቀመውም፤ ቃሉን ወይም አባባሉን።
***
የኤርሚያስ ጠቅል አመልጋን ግለ ታሪክ የሚተርከውን “የማይሰበረው” የተሰኘውን መፅሃፍ አነበብኩት። ወደድኩት። አንዳንድ ቦታዎች የማያስፈልጉ «ድራማታይዜሽን» ቢኖሩትም መፅሃፉ ተነባቢ ነው። መፅሃፉን ካነበብኩ በኋላ በውስጤ የቀሩትን ጥቂት ነገሮች ላነሳ ፈለግሁ።

የመጀመሪያው፥ የመፅሐፉ ርእስ “የማይሰበረው” ከሚሆን ይልቅ “ቀውስ ናፋቂው” ቢባል እመርጥ ነበር። ምክንያቱም የኤርምያስ ታሪክ የሚያሳየው ቀውስ ናፋቂነቱን ነውና። በሀገር ውስጥ ኤርሚያስ የሚያደርጋቸው እያንዳንዱ እንቅስቃሴዎች ቀውስ ያጋጥማቸው ነበር። ኤርሚያስ በቀውሶቹ ምክንያት ለጊዜው ስፍራውን ቢለቅም፣ ምላሹ ወደ ቦታው መመለስ ብቻ አልነበረም።
አንድ ሁለት ጊዜ መሬት በሊዝ ለማግኘት ቢጫረትም፣ በሌሎች ተጫራቾች ወይም በገበያው በዝረራ ተሸንፏል። ለሶስተኛ ጊዜ ግን አላሸነፈም፤ ይልቁንም ከማሸነፍ በላይ የሆነ ነገር አደረገ። በሊዝ ተጫርቶ ሊያገኘው ከሚችለው መሬት በላይ የሆነ ሰፊ መሬት ያለው የመንግስት የዘይት ፋብሪካ በጨረታ አሸነፈ። የዘይት ምርቱ በእርዳታ ዘይት በገበያው ውስጥ በስፋትና በቅናሽ በመለቀቁ በቀውስ ቢመታም፤ ምላሹ ከቀውሱ አገግሞ ዘይቱን መሸጥ አልነበረም። ያደረገው ከዘይት ምርቱ ወደ ላቀ የማእድን ውሃ ገበያ ውስጥ መግባት ነበር። የማእድን ውሃው ሽያጭ ቀውስ ሲገጥመው ደግሞ፥ ወደ ተሻለውና የላቀው የታሸገ የተጣራ ውሃ ገበያ ውስጥ ገብቷል። ይህም የታሸገ ውሃ ገበያ ቀውስ ውስጥ ሲገባ፥ ወደ ዘመን ባንክና አክሰስ ካፒታል ሰርቪስ ገባ። እነዚህ ሥራዎች ቀውስ ውስጥ ሲገቡ ወደ አክሰስ ሪል ስቴት። ይሄ ቀውስ ውስጥ ሲገባ ደግሞ፥ ወደ ብረት ማእድን፥ አሊባባና ሌሎች ታላላቅ ስኬቶች ለመሰነቅ ተጋ።

ሁለተኛው፤ በኤርሚያስ እንቅስቃሴ፥ በተለይ ደግሞ በአክሰስ ሪል ስቴት ቀውስ ብዙዎች ተጎድተዋል። ይሄንን እርሱም ያምናል። ነገር ግን የቀውሱ ምክንያት ምንድን ነው? ከምክንያቶቹ ውስጥ አንደኛው የሀገራችን የህዝብ አስተዳደር ተቋማዊ አለመሆኑና የፖሊሲ ድክመቶች ነው።
በየትኛውም ሀገር አክሰስ ሪል ስቴት ለአመታት ይቅርና ለወራትም እንኳን ስራ ፈቶ አይቀርም። የካፒታል ማርኬት በዳበረባቸው ሀገራት፤ አዋጭ ሃሳብ እስካለህ ድረስ በጊዜያዊ የገንዘብ ችግር ምክንያት ብቻ አንድ ድርጅት አይፈርስም። ስራ አይቆምም። ሰራተኛ አይበተንም። ወደ ገንዘብ ገበያው ጎራ በማለት ገንዘብ በርካሽ ዋጋ ትገዛለህ። ስራህን ትቀጥላለህ። የገንዘብ ችግር በተለያየ ምክንያት ይፈጠራል፤ በተለይ «አሴት ኢንተንሲቭ» በሆኑ ስራዎች። ነገር ግን ደህና የካፒታል፥ የገንዘብ ገበያ ችግሩን ሳይባባስ ይፈታዋል። ኤርሚያስ አስተማማኝ የገንዘብ ገበያ በሌለበት ሀገር ነው ስራውን የጀመረው። ያም ቢሆን ወደ ውጭ ሀገራት ገንዘብ ፍለጋ ተግቷል።

ሶስተኛው፥ የህዝብ አስተዳደር ስርአታችን ተቋማዊ አለመሆኑ፥ ሰዋዊ (በግለሰቦች ላይ የተመሰረተ) መሆኑ ነው። ነጋዴዎች የሚያሸንፉት ነፃ በሆነ ውድድር ሳይሆን፥ ሰዋዊ የህዝብ አስተዳደር ስርአታችንን በተለያየ መንገድ በመቆጣጠር ነው። በዚህ ሁኔታ የተሳካለት ሁሉ የውድድር ብልጫ ያገኘው አይሆንም።

አራተኛው፥ መንግስት እየተከተለው ያለው ነጋዴዎቻችንን ወደ ኢንዱስትሪ የመሳብ ስትራቴጂ ጥበብ አልባ ነው። ኢንዱስትሪ ከአገልግሎት፥ ንግድና፥ ሪልስቴት፥ ግብርና አንፃር፤ በብዙ መልኩ የሚከብድ ስራ ነው። ማንም ቢሆን በንግድ ይጀምራል። በንግድ ስትሰለጥን ወደ ግብርናው ትገባለህ። ግብርናው ላይ ስትሰለጥን፥ ኢንዱስትሪው ላይ ለመስልጠን ልምምድ ትጀምራለህ። ገንዘብ ስላለህ ብቻ ዘለህ ኢንዱስትሪ ላይ አትገባም።
ልማታዊ እያልክ ብታሞግሰውም፥ ኪራይ ሰብሳቢ እያልክ ብታሸማቅቀውም፤ የትኛውም ባለሀብት ግብርናው ላይ እና/ወይም ንግዱ ላይ ሳይሰለጥን ኢንዱስትሪው ላይ አይሰለጥንም። በተወሰነ መልኩ መንግስት ይህን ይረዳዋል። ለዛ እኮ ነው፤ ADLI (Agricultural Development Led Industrialization) የሚባለውን ፖሊሲ ያወጀው። ግብርናው ሲያድግ ነው ኢንዱስትሪው የሚያድገው። ልክ ነው። ግብርናውን እንዲያሳድግ እድል ያልተሰጠው የግል ዘርፍ ግን፥ እንዴት ኢንዱስትሪውን ያሳድጋል?

አምስተኛው፥ ልማታዊ መንግስት ራሱን፥ ተፈጥሮውን ሲያስረዳ፥ የመኖር ምክንያቱን ሲተነትን የሚያቀርበው ምክንያት በሀገራችን የካፒታል እጥረት መኖሩን ነው። ልክ ነው። የካፒታል እጥረት አለ። ጥያቄው፤ የካፒታል እጥረት የተፈጠረው ለምንድን ነው? የሚፈታውስ በመንግስትና በውጭ ካፒታል ብቻ ነው?
የካፒታል እጥረት የተፈጠረው፥ የቁጠባ ምጣኔው አነስተኛ የሆነው፥ ባንኮቻችን የግል ቢሆኑም የመንግስት የሚመስሉት በምግባራቸው፥ ኪራይ ሰብሳቢነት በህዝብ አስተዳደር የተንሰራፋው፤ በመንግስት ፖሊሲ ምክንያት ነው። በመንግስት የገንዘብ ፖሊሲ። የተደራጀ፥ ባለብዙ ቅርፅና ቀለም ተዋንያን የተዋቀረ የገንዘብ ገበያ እንዳይፈጠር ፖሊሲው እንቅፋት ሆኗል። የተደራጀ የአክስዮን ገበያ እንዳይኖር፥ የኢንቨስትመንት ባንኪንግ እንዳይኖር፥ የሪቴይን ባንኪንግ ዘርፉ ኢሊጎፖሊ እንዲሆን የሚያደርጉ የመንግስት ፖሊሲዎች የካፒታል እጥረትን ፈጥረዋል። የካፒታል እጥረት ስላለ ተብሎ መንግስት ልማታዊ መሆን አለበት ሲባል፥ የሀገራችን የልማታዊ መንግስት ትርክት እራሱ የፈጠረውን ችግር መሰረት አድርጎ “ስለዚህ ተጨማሪ ሚና፥ ስልጣንና፥ ገንዘብ ይገባኛል” የሚል ይመስላል።
የካፒታል እጥረት፥ የካፒታል ገበያ ጉድለት፤ አክሰስ ሪል ስቴት እንዲወድቅ አድርጓል። ጠንቁ ግን ከአክሰስ ሪል ስቴት በላይ ነው። አስቀድሞ ምርትን በመሸጥ ካፒታል መሰብሰብ፥ ወይም አክሲዮን በመሸጥ ካፒታል መሰብሰብ እድሉ ጠባብ ነው። በተለይ ደግሞ ለአዲስ ተዋናይ። በዚህ ጠባብ እድልም እንኳን ማለፍ ቢቻል፥ በተለይ «አሴት ኢንተንሲቭ» በሆኑ የኢንዱስትሪና ሌሎች ስራዎች፥ የገንዘብ እጥረት ይሰባብርሃል። ስለዚህ ልማታዊ መንግስት፤ የካፒታል/የገንዘብ ገበያውን ማደራጀት ፍሬ፣ በመጠንና በአይነት ብዙ መሆኑን ሊረዳ/ሊገነዘብ ይገባል።
ስድስተኛው፥ አንድ ድርጅት የገንዘብ ችግር ሲያጋጥመው አገግሞ አንደ አዲስ ተደራጅቶ የሚወጣበት ወይም በአግባቡ የሚፈርስበት ስርአት በህግ ተደንግጓል፤ በንግድ ህጉ። የመንግስት ምላሽ ግን ህጉን ቸል በማለት የፖለቲካ ኮሚቴ ማዋቀር ነው። እንዲህ አይነት ችግሮች በፖለቲካ ኮሚቴ አይፈቱም። ችግሩን ያብሱታል እንጂ።

ሰባተኛው፥ አክሰስ ሪል ስቴት ብቸኛው ይህን መሰል ችግር ያጋጠመው ድርጅት አይደለም። የሌሎች ዘርፎችን ትተን በተመሳሳይ ዘርፍ እንኳን ከዚህ በፊት ጃክሮስ የሚባል ድርጅት ወድቆ ነበር። በዚህ ጊዜም መንግስት ጉዳዩ በህግ አግባብ በፍርድ ቤት እንዲታይ ከማድረግ ይልቅ፥ ለቤት ገዢዎች የቀሩትን የድርጅቱን መሬቶችና ተጨማሪ መሬቶች በመስጠት የቤት ባለቤቶች እንዲሆኑ አድርጓል። ይህን ማድረጉ ህጋዊም አይደለም። ተገቢም አይደለም። ለምን አደረገ ቢባል፤ መልሱ ግልፅ አይደለም። ህጋዊ ስርአቶችን ወደ ጎን በማድረግ ለችግሮች የፖለቲካ መፍትሄ መስጠት ከሚያመጣቸው ጠንቆች መካከል፤ ወደፊት ሰዎች በማይገባ መንገድ እንዲተጉ ማድረግ ነው። በሆነ ምክንያት አንድ ድርጅት ቢከስር ወይም ጊዜያዊ የገንዘብ ችግር ቢያጋጥም፥ ገንዘብ ጠያቂዎች (ቤት ገዢዎች) መንግስት ገንዘባቸውን እንዲመልስላቸው ለማድረግ ይተጋሉ። ድርጅቱ እዳውን በአዲስ መልክ አደራጅቶ ከሚወጣ ይልቅ፥ ያለው መሬት ላይ አዳዲስ መሬቶች መንግስት ጨምሮ ለቤት ገዢዎች እንዲያስተላልፍ ለማድረግ ገንዘብ ጠያቂዎች ይተጋሉ። አንድን ህግ ወደ ጎን ስትልና ፖለቲካዊ መፍትሄ ስትሻ፥ ከሚፈጠሩ ብዙ አይነት ጠንቆች መካከል፥ የሚዛቡ ጥቅሞችና ትጋቶች አንደኞቹ ናቸው። ይሄንን ጉዳይ በመፅሃፉ በከፊል አይቻለሁ።
* * *
በመጨረሻም፣ የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ኤርሚያስን መከላከል አይደለም። እርሱ ራሱ የሚያምናቸው ስህተቶች በመፅሃፉ ላይ ይገኛሉ። መፅሃፉን ሳነብ፥ ሚናዬ ዳኝነት አልነበረም። የአንድ ወገንን ታሪክ ሰምቶ ዳኝነት መስጠት ከባድና ተገቢ ያልሆነ ነገር ነው (ምንም እንኳን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያንን ቢያደርግም)። የኔ ሚና፤ “እንዴት ሊሆን ቻለ?” ለሚለው ፍንጭ መፈለግ ነበር። ከዚህ በላይ ያለውን ያየሁትም ከዚህ አኳያ ነው።
የመጨረሻው መጨረሻ፤ ጥሩ መፅሃፍ ነው። ኤርሚያስ በሌሎች ላይ ተነሳሽነትን የሚፈጥር ሰው እንደሆነ ተመልክቻለሁ። ስጋን በመግራት፥ ፍርሃትን፥ ተስፋንና፥ ትዝታን በመመጠን፤ ከአይበገሬነት አልፈህ ቀውስ ናፋቂነትን መገንባት እንደሚቻል ይጠቁማል። ወታደር የሚለማመደው፥ ምሽግ የሚቆፍረው፥ የሚሮጠው፥ የሚደክመው የሚለፋው፤ በሰላም ጊዜ ነው። እንዲህ ማድረጉ፥ በጦርነት ጊዜ ድፍረት፥ ብልሃት፥ አቅም እንዲያገኝ ይሆናል። ለዚህ ነው በደብዳቤዎቹ ላይ ሴኔካ እንዲህ የሚለው፦ (ቃል በቃል አይደለም)
“በወር የተወሰኑ አራት አምስት ተከታታይ ቀናትን ለይና፥ ድህነትን ጓደኛ አድርገው። የሞት ፍርደኛ እንኳን ከሚበላው ያነሰና የቆረቆዘ መናኛ ምግብ ብላ። መናኛ ልብስ ልበስ። እንዲህ ስታደርግ ለራስህ ይሄን ነው የምፈራው በለው። ድህነትን ተለማመድ ሲባል፥ ሃብታሞች ከቁንጣንና ድሎት ፋታ ለማግኘትና ለመደሰት እንደሚያደርጉት አይደለም። ፍፁም ድህነትን ተለማመደው። በአዘቦቱም ቢሆን፥ ምግብ፥ መጠጥና፥ መጠለያን አስመልክቶ፤ ከስጋህ መስጠት ያለብህ “ትንሹን የሚያስፈልገውን እንጂ የምትችለውን መሆን የለበትም”። ከሚያስፈልገው በላይ፥ የምትችለውን ብትሰጠው እንዲደላው እያደረክ ነው። የዛሬ ድሎት፤ ነገ ፍፁም አስፈላጊ ይሆናል። ስጋህ የኑሮህ፥ የህይወትህ አገልጋይ መሆኑ ቀርቶ ተገልጋይ፥ ጌታ ይሆናል።
እነዚህን ሁለቱን ስትለማመድ፥ አንተን የሚችልህ የለም። ፍርሃት አልባ፥ ተስፋን ተደግፎ ሳይሆን በራሱ ቀጥ ብሎ የሚቆም፥ ጠቢብ ትሆናለህ። የነካኽው ሁሉ ወርቅ ይሆናል”

Read 1563 times