Saturday, 17 April 2021 12:06

“አንቀጽ 39፣ ይቅር ወይስ ይኑር?”

Written by  ደስታ መብራቱ
Rate this item
(0 votes)

    "--ሁለተኛው የህገመንግሥታዊ ሥርዓቱ ፈተናዎች ምንጭ በፌደራል ህገመንግሥቱና በክልል ህገመንግሥታት መካከል ሆነ ተብሎ የተራመደው የህግ ይዘት መጣረስና አለመጣጣም ነው። ይህም በአብዛኛው የሚያያዘው በክልሎች ደረጃ ገኖ ከተራመደው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የፖለቲካ አመለካከት ጋር ነው።-"
     
           የዚህ ጽሁፍ መነሻ፣ ‘አንቀጽ 39፣ ይቅር ወይስ ይኑር’ በሚል ርዕስ ላይ የተካሄደ ምሁራዊ ክርክር ነው። ይህንን ክርክር ከጥቂት ቀናት በፊት በበይነ መረብ ከተከታተልኩ በኋላ በእኔ አእምሮ የሚመላለሱ አንዳንድ መሰረታዊ ነጥቦችን ለማካፈል ወደድኩ። በቅድሚያ ግን፣ የሀገሪቱን የወደፊት የፖለቲካ አቅጣጫ ሊወስኑ በሚችሉ እንዲህ አይነት ርዕሶች ላይ ይህንን መሰል ክርክር ላዘጋጁት ወገኖች ከፍተኛ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ። ሃገራችንን ካለችበት የፖለቲካ ምስቅልቅል ለማውጣት እንዲህ አይነት አይነኬ የሚመስሉ ጉዳዮችን ለአደባባይ ውይይት ማብቃት እጅግ አስፈላጊ ነውና፤ ሊበረታታ ይገባዋል። ከዚህ በተጨማሪ፣ በእንደዚህ ዓይነት አወዛጋቢ ርዕስ ላይ አንዱን ወይንም ሌላውን አቋም በመደገፍ ክርክራቸውን ላቀረቡት ሁለቱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አድናቆቴን ለመግለጽ እወዳለሁ። በእኔ ዕምነት፣ ሁለቱም ምሁሮች፣ የተሰጣቸውን አቋም ይመኑበትም አይመኑበትም፣ የመከራከሪያ ነጥቦቻቸውን በሚገባ አቅርበዋል እና ሊመሰገኑ ይገባል።
ወደ ዕለቱ የመከራከሪያ ርዕስ ከመግባቴ በፊት፣ አጨቃጫቂ በሆነው የኢፌዲሪ ህገ መንግሥት ላይ ያለኝን አጠቃላይ ምልከታ ማካፈሉ ተገቢ ይሆናል። በእኔ ዕምነት፣ ባሁኑ ወቅት በሃገሪቱ ያለው ህገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለተደቀኑበት ፈተናዎች መሰረታዊ ምንጮቹ ሁለት ናቸው። የመጀመሪያው፣ የሀገሪቱን ህዝቦች የወደፊት ሁለንተናዊ ደህንነትና እጣ ፈንታ የሚወስኑትን መሰረታዊ ህገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች ካንድ የፖለቲካ ድርጅት ዓላማ ጋር ማደበላለቁ ነው። ይህ በመሆኑም፣ ባሁኑ ሰዓት በስራ ላይ ያለው ህገመንግሥት በርካታ ለህዝቦች ሁለንተናዊ ደህንነት ዋስትና የሚሰጡ አንቀጾች ያሉት ቢሆንም አጨቃጫቂ የሆኑ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ይዘቶችም ተካተውበታል። አንዳንዶች እንደሚናገሩት፣ ይህንን ችግር ለማስወገድ ህገመንግሥቱን ሙሉ ለሙሉ መቀየር የሚለው ሃሳብ ፈረንጆቹ እንደሚሉት ‘የቆሸሸውን ውሃ ለማስወገድ ከታዳጊው ህፃን ጋር አብሮ መድፋት’ ይሆናል። ከዚህ ይልቅ፣ ችግሩን ለማስወገድ ሊወሰድ የሚገባው የመፍትሔ አቅጣጫ፣ የችግር ምንጮች የሆኑትንና  አብዮታዊ ቅኝት ያላቸውን አንቀጾች ለይቶ ማውጣትና በማሻሻያው ሂደት ውስጥ ሌሎች መሰል ፖለቲካዊ ወገናዊነትን የሚያራምዱ አንቀጾች አንዳይካተቱ መከላከል ነው። ይህንን በማድረግም፣ ህገመንግሥቱ ያንድ ወይንም የሌላ የፖለቲካ ድርጅት መጠቀሚያ ከመሆን ይልቅ የህዝቦችን ሁለንተናዊ ደህንነት (Wellbeing) በዘላቂነት የሚያረጋግጥና ለሁሉም የፖለቲካ አመላካከቶች የመተባበሪያና የመወዳደሪያ ማዕቀፍ ሆኖ እንዲያገለግል ማድረግ ይቻላል።
ሁለተኛው የህገመንግሥታዊ ሥርዓቱ ፈተናዎች ምንጭ በፌደራል ህገመንግሥቱና በክልል ህገመንግሥታት መካከል ሆነ ተብሎ የተራመደው የህግ ይዘት መጣረስና አለመጣጣም ነው። ይህም በአብዛኛው የሚያያዘው በክልሎች ደረጃ ገኖ ከተራመደው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የፖለቲካ አመለካከት ጋር ነው። በመሆኑም፣ አብዛኞቹ የክልል ህገመንግሥታት በፌደራል ህገመንግሥቱ  የተከበሩ መሰረታዊ የዲሞክራሲና ሰብዐዊ መብቶችን የሚጥሱ አንቀጾችን አካትተው ይገኛሉ። ለዚህም አንዱ ምሳሌ፣ በየትኛውም ክልል የሚኖሩ ሁሉንም ህዝቦች የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ይልቅ አንድን ክልል ያንድ ወይንም የተወሰኑ ብሔረሰቦች ሃብትና ንብረት አድርጎ መደንገግ ነው። ይህ ሁኔታ፣ በፌደራል ህገመንግሥቱ ውስጥ የተደነገጉትን መሰረታዊ የዲሞክራሲና ሰብዐዊ መብቶች የሚጥስ ከመሆኑም በላይ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት ለተፈጸሙ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ወንጀሎች ዋነኛ ምንጭ ሆኖ ዘልቋል። ለአብዛኞቹ ከባቢያዊ ግጭቶች መባባስም የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህንን ችግር ለማስወገድ ሊወሰድ የሚገባው እርምጃ፣ ሁሉም የክልል መንግሥታት ከፌደራል ህገመንግሥቱ ጋር የሚጋጩ የህግ አንቀጾቻቸውን እንዲመረምሩና እንዲያስተካክሉ አስፈላጊውን ተቋማዊና ሙያዊ ድጋፍ መስጠት ይሆናል። የዚህም መሰረት፣ የፌደራል ህገመንግሥቱ የሃገሪቱ የበላይ ህግ እንደመሆኑ መጠን ከዚህ ህግ ጋር የሚጋጭ ማንኛውም ህግ፣ የክልል ህገመንግስቶችን ጨምሮ፣ ተቀባይነት ሊኖራቸው እንደማይችል መረዳት ነው። እነኚህን ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን ሁለት መሰረታዊ የችግር ምንጮች በማድረቅ በርካታ ህገመንግሥታዊ ውዝግቦቻችን ሊቃለሉ ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ።  
ከላይ ወደተጠቀሰው የመከራከሪያ ርዕስ ስንመለስ፣ የህገመንግሥቱ አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝም ከዚህ በላይ የተጠቀሰው የህገመንግስታዊ ድንጋጌና የፖለቲካ ፕሮግራም መደበላለቅ ችግር ይታይበታል። የዚህ አንቀጽ ዋነኛ መነሻ መሰረት የሆነውን አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ አንድን ብንመለከት፣ “ማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ ያልተገደበ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከመገንጠል ድረስ ይኖረዋል” ይላል። እዚህ ላይ፣ የማንኛውም ህዝብ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ያልተገደበ መብት በዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችም የተከበረ የቡድን መብት በመሆኑ ብዙም የሚያክራክር ሊሆን አይገባውም። ይህ የቡድን መብት በህገመንግሥቱ ውስጥ መካተቱ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላለ የበርካታ ብሔረሰቦች ሃገር ጠቃሚ እንጂ ጎጂ አይሆንም። ከዚህ ጋር ተዳብሎ የገባው ‘እስከ መገንጠል’ የሚለው ሃረግ ግን ከኢህአዴግ የፖለቲካ ፕሮግራም ከመገልበጡ ውጭ ምንም ዓይነት ህገመንግሥታዊ ፋይዳ የሌለው መደበኛ ያልሆነ ህገመንግሥታዊ (extra constitutional) ቅጥያ ነው። ምክንያቱም፣ በሁሉም ሃገሮች ታሪክ እንደታየው የአዳዲስ ሃገሮች ምስረታ የተከሰተው አንድም በሁለት ወገኖች መካከል የተካሄደ ጦርነት ባንደኛው ወገን አሸናፊነት በመጠናቀቁ አለበለዚያም ከተራዘመ ጦርነት በኋላ በተካሄደ ህዝበ ውሳኔ ነው። ከላይ የተጠቀሰውን የህዝቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ያለገደብ የሚያከብር ዲሞክራሲያዊ ህገመንግስት ባለበት ሁኔታ ጦርነት ውስጥ መግባት ሳያስፈልግ የህዝቦች የመብት ጥያቄ የሚስተናገድበት የህዝበ ውሳኔ ሥርዓት ስለሚኖረው የመገንጠሉ ቅጥያን አላስፈላጊ (redundant) ያደርገዋል።
ከዚህም በተጨማሪ፣ የየትኛውንም ሃገር ታሪክ ብንመለከት፣ የመገንጠል መብት በህገመንግሥት ውስጥ በመኖሩ የተገነጠለም ሆነ ይህ ባለመኖሩም መገንጠልን ያስቀረበት ሁኔታ የለም። ይህንን ለመረዳት የቅርቡን ጊዜ የሃገራችንን ታሪክ መመልከቱ በቂ ይሆናል። ሁላችንም እንደምናስታውሰው፣ የኤርትራ ህዝቦች የነፃነት ጥያቄ ከሰላሳ ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ ጦርነቱ በአንደኛው ወገን አሸናፊነት ሲጠናቀቅ መቋጫ ሊያገኝ ችሏል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ኤርትራ ነፃ ሃገር ሆና ልትወጣ ችላለች። የጎረቤታችን የደቡብ ሱዳን ሃገር ሆኖ መፈጠርም ከዚሁ ጋር የሚመሳሰል ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፣ አሁን ባለው ህገመንግሥት ውስጥ የመገንጠል መብት የተጠቀሰ ቢሆንም መገንጠልን ተግባራዊ ለማድረግ ያኮበኮቡ የፖለቲካ ቡድኖች ፍጻሜያቸው ምን እንደሆነ የሚታወቅ ነው። ከጥቂት ዓመት በፊት የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት የዚህን አንቀጽ ተግባራዊነት ለማስጀመር በሚያኮበክብበት ወቅት የተወሰደውን እርምጃ የምናስታውሰው ነው። በተለይም፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት በህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ የተወሰዱ ፖለቲካዊ እርምጃዎችና በመጨረሻም በሃገሪቱ የመከላከያ ኃይል ላይ የተፈጸመው ጥቃት መለስተኛ ግቡ ትግራይን ነፃ ማድረግ እንደነበረ የሚያመላክት በርካታ ማሳያዎች እንደ ነበሩት ይጠቀሳል። የዚህም ውጤት ምን እንደሆነ የሚታወቅ ነው።  
እነኚህ የሃገራችን የቅርብ ጊዜ ሁነቶች በግልጽ የሚያመላክቱት፣ ባንድ ህገመንግሥት ውስጥ የመገንጠል መብት አለመካተት የአዲስ ሃገር ምስረታን የማያስቀር የመሆኑን ያህል ስለተጠቀሰም ብቻ ሃገር እንደምትበታተን አድርጎ ማሰብም ምንም የታሪክ ድጋፍ ያለው አይደለም። ትልቁ ቁምነገር፣ የህዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን ማክበርና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓቱን ማጠናከር ነው። ከዚህ አኳያ፣ አቢዩ ትኩረት መሆን ያለበት ያለውን ህገመንግሥት በጠባብ ፖለቲካዊ ፍላጎት ተነሳሽነት ከተደነቀሩበት የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ህጸጾቹ ማጽዳትና በቀጥተኛ የህዝብ ተሳትፎ ዲሞክራሲያዊነቱን ማጠናከር ቢሆን ይበጃል። እንዲህ ዓይነቱ አካሄድም ለአንቀጽ 39 ብቻ ሳይሆን ለሌሎቹም አጨቃጫቂ ለሆኑ አንቀጾች መፍትሄ በማምጣት ረገድ ጠቃሚ አካሄድ ይሆናል።
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው  ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ስታለንቦሽ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፈሰር ሲሆኑ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትም ያስተምራሉ።


Read 3855 times Last modified on Saturday, 17 April 2021 12:20