Saturday, 17 April 2021 11:42

ዳግም ሰቆቃና እልቂት በአጣዬ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(13 votes)

  ከሳምንት በፊት በታጠቁ ኃይሎች ከፍተኛ ጥቃት በተፈጸመበትና በርካቶች  በተገደሉበት  የሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬና አካባቢው፣ ከትናንት በስቲያ ጀምሮ በታጠቁና በተደራጁ ኃይሎች ከፍተኛ ጥቃት እየተፈጸመ መሆኑ ተገለፀ። በጥቃቱ እስከ አሁን ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ዜጎች መገደላቸው የተጠቆመ ሲሆን በከተማዋ የሚገኙ በርካታ መኖሪያ ቤቶች መቃጠላቸውም  ታውቋል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር አቶ ታደሰ ገ/ፃዲቅ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ ሶስተኛ ቀኑን በያዘው በዚህ የታጣቂዎች ጥቃት እስከ አሁን ቁጥራቸው ያልታወቀ የአካባበው ነዋሪዎች ሰዎች ተገድለዋል። እስር ቤት ተዘርፏል፤ እስረኞች ተለቀዋል፣ሆስፒታል ተዘርፏል፤ የጤና ባለሙያዎች ታፍነዋል፤ የግለሰቦች መኖሪያ ቤቶችና ድርጅቶች በእሳት ጋይተዋል፡፡
ጥቃቱ ከዚህ ቀደም በአካባቢው ከተፈፀመውም ሆነ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ከተፈፀሙት መሰል ጥቃቶች የላቀና  ፈፅሞ አይተን የማናውቀው አይነት ነው ያሉት አቶ ታደሰ፤ ሁኔታውን በተደጋጋሚ ለፌደራል መንግስቱ ብናሳውቅም ምንም ምላሽ አላገኘንም ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል በስፍራው ተከስቶ  የነበረውን ችግር ለማረጋጋት ወደ አካባቢው መጥቶ የነበረ የመከላከያ ኃይል ቢኖርም፣ የአሁኑ ጥቃት አድራሾች ከመከላከያ ኃይሉ አቅም በላይ ስለሆኑ ተጨማሪ ሃይል  እንዲላክ ተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብም፣ ምንም ምላሽ አላገኘንም፡፡ የመከላከያ ኃይሉ ደግሞ ሁኔታው ከአቅሜ በላይ ነው ስለአለን ዝም ብለን የህዝቡን ስቃይና ሞት ማየት ብቻ ሆኖብናል ብለዋል- አስተዳደሩ።
ጥቃቱን የሚያደርሱት ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቁ፣ የተደራጁና  በሚገባ የሠለጠኑ ሰዎች ናቸው ያሉት አስተዳዳሪው፤ ሸሽቶ ማምለጥ የቻለ እየሞከረ ነው፤ ያልቻለው ግን በየቤቱ በግፍ እየተገደለ ነው ብለዋል። ሁኔታው ከዚህም እየከፋ ከመሄዱና የሟቹ ቁጥር  ከመጨመሩ በፊት መንግስትና የመከላከያ ኃይል ለህዝቡ ሊደርስለትና ሊታደገው ይገባል- ብለዋል።
በአጣዬና አካባቢው፣ በአንጾኪያ፣ በካራ ቆሬ፣ በአማኑኤልና አካባቢው ጥቃቱ ተባብሶ መቀጠሉን የሚናገሩት አቶ ታደሰ፤ ጥቃቱ  ወደ ተጎራባች አካባቢዎችም እየቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል። መንግስትና መከላከያ እያለቀ ላለው ህዝብ ይድረስለት ሲሉም ተማጽነዋል - አስተዳደሩ፡፡ ጥቃቱን ተከትሎ ከአዲስ አበባ ወደ ደሴ፣ መቀሌ የሚወሰዱ መንገዶች ሙሉ በሙሉ የተዘጉ መሆናቸውንም አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

Read 12876 times