Saturday, 17 April 2021 11:36

ግብፅ “ተመድን” በግድቡ ጉዳይ እንዲያደራድር ጠየቀች

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

      በህዳሴው ግድብ ውዝግብ ጉዳይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጣልቃ ገብቶ መፍትሔ እንዲያበጅ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጠየቀ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ ለችግሩ መፍትሔው በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት መነጋገር ነው በሚል አቋሙ ፅንቷል፡፡
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከትናንት በስቲያ ለተባበሩት መንግስታት ዋና ሃላፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ፣ለተባበሩት መንግስታት ም/ቤትና ለጠቅላላ ጉባኤው ፕሬዝዳንት በፃፉት ድብዳቤ፤ “በግድቡ ጉዳይ የመንግስታቱ ድርጅት ያደራድረን” ብለዋል፡፡
የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃገራቸው በግድቡ ጉዳይ ስምምነት ላይ ሳይደረስ  የውሃ ሙሌት እንዳያከናውን ያላትን ፅኑ ፍላጎት ከደብዳቤ መልዕክቱ ባሻገር ከተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጋር ባደረጉት የስልክ ንግግር ማስረዳታቸውን የአረብ ኒውስ ዘገባ ያመለክታል፡፡
የተባበሩት መንግስታትና ተቋሞቹ በግድቡ ድርድር ዙሪያ ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ ነው የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የጠየቁት፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤  በድርድሩ ዙሪያ ከትናንት በስቲያ ሀሙስ በሠጡት መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ድርድሩን ማካሄድ የምትፈልገው በውሃ ሙሌትና የሙሌት አስተዳደር ላይ ብቻ መሆኑን አረጋግጠው የግድቡን ድርድር ጉዳይ ከአፍሪካዊ የድርድር ማዕቀፍ በማውጣት ወደማይመለከታቸው የአረብ ሃገራት ለመውሰድ የሚደረግን ጥረት አንቀበልም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለችግሩ አፍሪካዊ መፍትሔን እንደምታስቀድም ያስገነዘቡት ቃል አቀባዩ፤ ይህም ከብዙ አፍሪካ ሃገራት ድጋፍን ያገኘ አቋም ሆኗል ብለዋል፡፡
አሜሪካ፣የአውሮፓ ህብረት፣የተባበሩት መንግስታት በድርድሩ ላይ ሚና እንዲኖራቸው ግብፅ የያዘችው አቋም ተቀባይነት እንደሌለው የተናገሩት አምባሳደሩ ግብፅና ሱዳን፣ጎረቤት ደቡብ ሱዳን ከድርድር ተሳትፎ እንድትገለል እንደሚፈልጉም ነው ያመለከቱት፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የሱዳን ጠ/ሚኒስቴር አብዳላ ሐምዶክ፤ ከሰሞኑ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውዝግብን ለመፍታት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲደረግ ለግብፅና ለኢትዮጵያ መሪዎች ጥሪ ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡
የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሌላኛው ያልተጠበቀ መግለጫቸው የሁለተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ መሞላት በግብፅ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የለም፤ ችግሩ እንዳይጋጥም አስቀድመን ተዘጋጅተን ነበር ብለዋል፡፡
ያለፈው ዐመት የመጀመሪያ ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌት እምብዛም ጉዳት አላስከተለም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትቱ አስገንዝበዋል፡፡

Read 11456 times